ሕወሓት ‹አገር የመበተን› ዕቅዱ ለመጨረሻ ጊዜ በዚህ የጦርነት ምዕራፍ መዘጋት የሚችልበት ጫፍ ላይ ደርሷል ሲሉ የጠቅላይ ሚኒስትሩ የደኅንነት አማካሪ ሬድዋን ሁሴን (አምባሳደር) ገለጹ፡፡
የደኅንነት አማካሪው ከሰሜን ኢትዮጵያ ጦርነት ጋር በተገናኘ ለሰላም እጁን ዘርገቶ የሚመጣ ካለ መንግሥት ለማስተናግድ ዝግጁ መሆኑን፣ ነገር ግን ለሌሎች አካላት መሣሪያ ሆኖ የመሚመጣን አካል ለመመከት ዝግጁ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ በመሆኑም በተጀመረው ሦስተኛው ጦርነት ላይ አገሪቱ ለጥቃት ተጋላጭ እንዳትሆን በአስተማማኝ መልኩ፣ መልክ የማስያዝ ሥራ እየተሠራ ነው ብለዋል፡፡
በጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት ፕሬስ ሴክሬታሪያት ‹‹አዲስ ወግ›› በሚል የሚዘጋጀው የውይይት መድረክ የ2014 ዓ.ም. የመጨረሻ ክፍል ‹‹ፈተና፣ ድልና ተስፋ›› በሚል በርካታ ተሳታፊዎች በተገኙበት ነሐሴ 30 ቀን 2014 ዓ.ም. በጠቅላይ ሚኒስትር ጸሕፈት ቤት ተካሂዷል፡፡
በውይይቱ ንግግር ያደረጉት የደኅንነት አማካሪው በፀጥታ ኃይልና በደኅንነት መዋቅሩ ውስጥ የነበሩ ብርበራዎችና መረጃን ጠቅልሎ የመውሰድ፣ የማጥፋትና ወግና የማስቀርት ተግባራት ተስተካክለው ተቋማቱ አገርን መከላከል በሚያስችል በቂ ቁመና ላይ እንደሚገኙ ተናግረዋል፡፡
በደኅንነት መዋቅር ውስጥ መሠረታዊ ለውጥ መካሄዱን የጠቀሱት ሬድዋን (አምባሳደር) ከዚህ ቀደም የአገር መከላከያ ኃይልን ጨምሮ ወደ አንድ ፓርቲና ሥርዓት ያጋደሉ እንደነበር በመጠቆም አሁን ላይ የአገርን ሉዓላዊነትና የሕዝብን ደኅንነት የመጠበቅ ቃል ኪዳንና እምነት እንዲይዝና ኢትዮጵያን አንዲመስል ተደርጎ ከሥርዓት ጋር የማይቀየር ተሻጋሪ ተቋም መገንባቱን አስረድተዋል፡፡
በተመሳሳይ የብሔራዊ ደኅንነት ተቋም ከዚህ ቀደም ተቋሙን በሚመሩት ኃላፊዎችና ሥርዓቱን በሚመሩት መካከል ከነበረ የዕርስ በርስ መጠላለፍ ድባብ ወጥቶ፣ መሠረታዊ የተቋሙን መፈጠር ምክንያት የዜጎችን ደኅንነት የማረጋገጥ፣ የመጠበቅ፣ የማገልገልና በአገሪቱ መሠረታዊ ጉዳዮች ውስጥ ከውስጥም ሆነ ከውጭም የሚደረጉ ሴራዎችን መቃኘትና ማክሸፍ፣ ዜጎች የእኔ የሚሉት ተቋም እንዲሆንና ለዜጎች ክፍት ሆኖ የሚያውቁት፣ ቅሬታ የሚያቀርቡበትና የሚያግዙት እንዲሁም ዘመኑን የሚመስል ሆኖ እንደተገነባ ተናግረዋል፡፡
በፖሊስ በኩል የፖሊስን መሠረታዊ አስተሳሰብ ለመለወጥ የተደረገ የዶክትሪን ማሻሻያ ስለመካሄዱና በዚህም ሕዝብን የማገልገልና ወንጀልን የመከላከል እንዲሁም ለሰዎች ተስፋና አለኝታ እንዲሆን ተደርጎ መቀረጹን የገለጹት አማካሪው አሁን ላይ ተገንብቶ ያለቀና የተሟሸ ተቋም አለ ማለት የማይቻል በመሆኑ በቀጣይ በየደረጃው ያለውን ሁኔታ የማጥራት ሥራ አንደሚያስፈልግ አመላክተዋል፡፡
በሌላ በኩል የተጠናቀቀው በጀት ዓመት የማክሮ ኢኮኖሚ ሁኔታን አስመልተው ማብራሪያ የሰጡት የፕላንና ልማት ሚኒስትር ፍጹም አሰፋ (ዶ/ር) በ2014 ዓ.ም. በሁሉም ባንኮች 427 ቢሊዮን ብር 300 ሺሕ ለማይሞሉ ዜጎች ብድር መሰጠቱን ተናግረዋል፡፡
የባንኮች አጠቃላይ ተቀማጭ ገንዘብ 1.8 ትሪሊዮን ብር መድረሱን የገለጹት ሚኒስትሯ በዚሁ በጀት ዓመት ባንኮች ካበደሩት ገንዘብ መካከል 276 ቢሊዮን ብር ተመላሽ መደረጉን አስታውቀዋል፡፡
በተጠናቀቀው የ2014 ዓ.ም. በጀት ዓመት ከሸቀጦች የውጭ ንግድ 4.1 ቢሊዮን ዶላር፣ በውጭ ከሚኖሩ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን እንዲሁም ሌሎች ድርጅቶች የተላከ ገንዘብ 7.8 ቢሊዮን፣ ወደ ውጭ የተላከ አገልግሎት 6.3 ቢሊዮን ዶላር፣ የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንት 3.3 ቢሊዮን ዶላር በአጠቃላይ 22 ቢሊዮን ዶላር የውጭ ምንዛሪ መገኘቱን ተናግረዋል፡፡
በዓመቱ 360 ቢሊዮን ብር የአገር ውስጥ ገቢ ለመሰብሰብ ታቅዶ 336 ቢሊዮን ብር ገቢ እንደተሰበሰበና ይህም በፋይናንስ ዘርፍ አፈጻጸሙ ‹‹በጣም አጅግ ጥሩ አፈጻጸም›› የታየበት ነው ያሉት ሚኒስትሯ፣ ይህም አፈጻጸም ኢኮኖሚው ጤናማ እንደሆነ ማሳያ ነው ብለዋል፡፡
በ2014 ዓ.ም. በሁሉም የሥራ ዕድል ዘርፎች 2.3 ሚሊዮን የሥራ ዕድል መፈጠሩን የገለጹት ፍጹም (ዶ/ር)፣ የግብርና ዘርፉ በሚገባው ልክ ያልታገዘና በፖሊሲ ተገቢውን ትኩረት ያልተሰጠው ቢሆንም የተሻለ አፈጻጸም እንደታየበት አስረድተዋል፡፡
ለአብነት እንኳ በ2014 ዓ.ም. በበጋ ስንዴ ከ600 ሔክታር ለምቶ 26 ሚሊዮን ኩንታል እንደተመረተና በቀጣይ ዓመት የበጋ እርሻ አንድ ሚሊዮን ሔክታር መሬት በማረስ 40 ሚሊዮን ስንዴ ለመሰብሰብ መታቀዱንና ከዚህ ውስጥ አሥር ሚሊዮን ኩንታል ወደ ውጪ ለመላክ እንደታሰበ ተናግረዋል፡፡