Wednesday, November 29, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ዜናየአካባቢ ምርጫ በቀበሌ ምክር ቤቶች እንደማይደረግ ምርጫ ቦርድ አስታወቀ

የአካባቢ ምርጫ በቀበሌ ምክር ቤቶች እንደማይደረግ ምርጫ ቦርድ አስታወቀ

ቀን:

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ክልሎች የሕግ ማሻሻያ አድርገው የቀበሌ ምክር ቤቶች ያላቸውን የመቀመጫ ብዛት ሳያስተካካሉ፣ በ2015 ዓ.ም. ለማድረግ ያቀደውን የአካባቢ ምርጫ በቀበሌ ደረጃ እንደማያደርግ አስታወቀ፡፡

አሁን ባለው የዞን፣ ወረዳ፣ የከተማ አስተዳደርና የቀበሌ ምክር ቤቶች አወቃቀር መሠረት የሁሉም ምክር ቤቶች አጠቃላይ የመቀመጫ ብዛት 3.6 ሚሊዮን እንደሆነ፣ ቦርዱ የአካባቢ ምርጫን አስመልክቶ ባስጠናው ጥናት ላይ ተጠቅሷል፡፡ ቦርዱ ለ3.6 ሚሊዮን መቀመጫ የሚወዳደሩ ዕጩዎችን የሚያስተናግድ የአካባቢ ምርጫን ማድረግ “ከአቅሙ በላይ” እንደሆነ ያስታወቀ ሲሆን፣ በተጀመረው በጀት ዓመትም ምርጫውን የሚያካሂደው ከቀበሌ በላይ ባሉ ምክር ቤቶች እንደሆነ ገልጿል፡፡

ምርጫ ቦርድ ይህንን ያስታወቀው ነሐሴ 28 ቀን 2014 ዓ.ም. የአካባቢ ምርጫን አስመልክቶ ስላስጠናው ጥናት ከፖለቲካ ፓርቲዎች ጋር ባደረገው ውይይት ነው፡፡ ቦርዱ የፌዴራሊዝም መምህር በሆኑት ዘመላክ አየለ (ዶ/ር) እና ክርስቶፍ ቫንደር (ዶ/ር) በተባሉ አጥኚዎች ያስጠናው ጥናት፣ የአካባቢ ምርጫ በኢትዮጵያ ያለውን የሕግ ማዕቀፍ፣ ቀደምት አፈጻጸሞችና አሁን በሚደረገው የአካባቢ ምርጫ ያሉ ዕድልና ሥጋቶችን የዳሰሰ ነው፡፡ አጥኚዎቹ በጥናቱ ማጠቃለያ ላይ የአካባቢ ምርጫን በተሳካ ሁኔታ ለመተግበር ያስችላሉ ያሏቸውን ምክረ ሐሳቦች አስቀምጠዋል፡፡

ከእነዚህ ምክረ ሐሳቦች ውስጥ አንዱ፣ ‹‹የምክር ቤቶች መቀመጫ ብዛትን ለአስተዳደር በሚያመች መንገድ መቀነስ አስፈላጊ ነው፤›› የሚለው ይገኝበታል፡፡ አጥኚዎቹ ይህንን ምክረ ሐሳብ ያቀረቡት አሁን ባለው የአካባቢ ምክር ቤቶች መቀመጫ ብዛት፣ የአካባቢ ምርጫ ማድረግ “እጅግ ከባድ” ሥራ መሆኑን በመጥቀስ ነው፡፡

ከአጥኚዎቹ መካከል አንዱ የሆኑት ዘመላክ (ዶ/ር) በመድረኩ ላይ እንዳስረዱት፣ የኢሕአዴግ መንግሥት ወደ ሥልጣን ከመጣ ጊዜ አንስቶ አራት ጊዜ የአካባቢ ምርጫዎች ተደርገዋል፡፡ እስከ 2000 ዓ.ም. ድረስ የሁሉም የአካባቢ ምክር ቤቶች መቀመጫ ብዛት 600 ሺሕ ነበር ብለዋል፡፡

‹‹እ.ኤ.አ. በ2008 በተለይ በቀበሌ የነበረውን የምክር ቤት መቀመጫ ብዛት በጣም ጨመሩት፡፡ የቀበሌ ምክር ቤት መቀመጫን ብዛት ወደ 200 እና 300 ሲያስገቡት፣ 600 ሺሕ የነበረው የመቀመጫዎች ብዛት በአንድ ጊዜ ወደ 3.6 ሚሊዮን አደገ፤›› በማለት አስረድተዋል፡፡

ለምክር ቤቶቹ መቀመጫ ቁጥር ማደግ በመንግሥት በኩል ቀርቦ የነበረው ምክንያት፣ ‹‹የሕዝቦችን የመወከል ዕድል ለማብዛት የምክር ቤቶቹን መቀመጫ ቁጥር ማብዛት ይገባል›› የሚል እንደነበር አጥኚው አስታውሰዋል፡፡ የፖለቲካ ፓርቲዎች ግን ገዥው ፓርቲ ተቃዋሚዎች በምክር ቤቶቹ መቀመጫ በብዛት ዕጩዎችን ማቅረብ እንደማይችሉ በመገንዘብ፣ የምክር ቤቶቹን መቀመጫ ለመያዝ ያስተላለፈው ውሳኔ መሆኑ ይናገራሉ፡፡ ይህ ሐሳብ በመድረኩ ላይ ከተገኙ የፖለቲካ ፓርቲዎችም ተነስቷል፡፡

ከእነዚህ ፓርቲዎች ውስጥ አንዱ የኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትሕ (ኢዜማ) ሲሆን፣ የፓርቲው ሊቀመንበር ጫኔ ከበደ፣ (ዶ/ር) ‹‹እንደ ከዚህ ቀደሙ 100 እና 200 ዕጩ አቅርቡ የምንባል ከሆነ ባንሳተፍ ይሻላል፤›› ሲሉ የፓርቲያቸውን አቋም አስረድተዋል፡፡

የምክር ቤቶቹን መቀመጫ ብዛት አስመልክቶ ምላሽ የሰጡት የምርጫ ቦርድ ዋና ሰብሳቢ ወ/ሪት ብርቱካን ሚደቅሳ፣ የአካባቢ ምርጫ በተመለከተ የምክር ቤቶችን ቁጥር ለምርጫ አስተዳደር በሚያመች መንገድ የማስተካከል ሥራ “ግልጽ ሆኖ የመጣ” መሆኑን ተናግረዋል፡፡

ወ/ሪት ብርቱካን፣ ‹‹ለዝግጅት ብለን እንዳየነው እንኳን፣ የቀበሌ ምክር ቤቶችን እንዳሉ ወስደን የአካባቢ ምርጫን ማድረግ እንደ ምርጫ ቦርድ ከምንችለው በላይ ነው፤›› በማለት ቦርዱ የመቀመጫዎቹን ቁጥር መቀነስ ሐሳብን እንደሚደግፈው ገልጸዋል፡፡

ቦርዱ ያስጠናው ጥናት ሲጠቃለል ምክረ ሐሳቦችን ለክልሎች እንደሚሰጥ የጠቀሱት ዋና ሰብሳቢዋ፣ ክልሎች በዚህ መሠረት ማስተካከያ ያደርጋሉ የሚል ተስፋ መኖሩን አስረድተዋል፡፡ ክልሎቹ በተለይም በቀበሌ ደረጃ ያሉ ምክር ቤቶችን መቀመጫ ብዛት በተመለከተ የሕግ ማሻሻያው ላይ “የበለጠ ጊዜ እንዲወስዱ” በማለት፣ በሚቀጥለው ዓመት የሚካሄደውን የአካባቢ ምርጫ ከቀበሌ በላይ ባሉ ምክር ቤቶች ለማከናወን ማቀዱን አስታውቀዋል፡፡

የቀበሌ ምክር ቤቶች ምርጫ የመቀመጫዎቹ ብዛት ከተሻሻለ በኋላ እንደሚደረግ የገለጹት ወ/ሪት ብርቱካን፣ ‹‹[የአካባቢ ምርጫ በሚደረግበት ጊዜ] ካሻሻሉት በጣም ጥሩ አብረን ምርጫውን እናደርጋለን፣ አለበለዚያ ግን ቀልድ ነው፤›› ሲሉ አስረግጠው ተናግረዋል፡፡

ምርጫ ቦርድ ከአሥር ዓመት ለሚበልጥ ጊዜ ያልተደረገውን የአካባቢ ምርጫ በተጀመረው የ2015 በጀት ዓመት በአብዛኞቹ ክልሎች የማድረግ ዕቅድ ይዟል፡፡ ቦርዱ የአካባቢ ምርጫውን በተመሳሳይ ዕቅድ የማካሄድ ዕቅድ እንደሌለው ያስታወቀ ሲሆን፣ የአካባቢዎቹን የፀጥታና ሌሎች አስቻይ ሁኔታዎች እየገመገመ ለየክልሎቹ የጊዜ ሰሌዳ እንደሚያዘጋጅ ገልጿል፡፡

ለአምስተኛ ጊዜ ይደረጋል ተብሎ በሚጠበቀው የአካባቢ ምርጫ 44.4 ሚሊዮን መራጮች ይሳተፋሉ የሚል ግምት አለ፡፡

ቦርዱ ይህንን ምርጫ ለማድረግ በተያዘው በጀት ዓመት 6.94 ቢሊዮን ብር እንደሚያስፈልገው አስታውቆ፣ 6.02 ቢሊዮን ብር መንግሥት እንዲበጅትለት ጠይቆ ነበር፡፡ የ2015 ዓ.ም. በጀት ሲፀድቅ ቦርዱ የተፈቀደለት 212 ሚሊዮን ብር ሲሆን፣ የአካባቢ ምርጫ ሊያደርግ ያቀደበትን ቀንና መርሐ ግብሩን ሲያሳውቅ ለምርጫው የሚያስፈልገው ቀሪ በጀት እንደሚለቀቅለት ገንዘብ ሚኒስቴር አስታውቆ ነበር፡፡ ሚኒስቴሩ ለአካባቢ ምርጫ የሚሆነውን በጀት ለምርጫ ቦርድ ሊሰጥ ያሰበው፣ በበጀት ዓመቱ ለመጠባበቂያነት ከያዘው 24 ቢሊዮን ብር ላይ መሆኑን ማስታወቁ ይታወሳል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የመቃወም ነፃነት ውዝግብ በኢትዮጵያ

ስሟ እንዳይገለጽ የጠየቀችው በአዲስ አበባ ከተማ በተለምዶ የሾላ አካባቢ...

የሲሚንቶን እጥረትና ችግር ታሪክ ለማድረግ የተጀመረው አጓጊ ጥረት

በኢትዮጵያ በገበያ ውስጥ ለዓመታት ከፍተኛ ተግዳሮት በመሆን ከሚጠቀሱ ምርቶች...

የብሔር ፖለቲካው ጡዘት የእርስ በርስ ግጭት እንዳያባብስ ጥንቃቄ ይደረግ

በያሲን ባህሩ በሪፖርተር የኅዳር 9 ቀን 2016 ዓ.ም. ዕትም “እኔ...