ዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ላይ የሚኖሩ የዜጎች ቁጥር ከቀን ወደ ቀን እየጨመረ መጥቷል፡፡ የኑሮ ውድነቱ ከቀን ወደ ቀን መጨመሩና ያልተገታ መሆኑ ደግሞ በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ የሚኖሩትን ብቻ ሳይሆን፣ መካከለኛ ላይ ያሉትንም ቢሆን ፈትኗል፡፡ ደህና ኑሮ አላቸው፣ ሀብታም ናቸው የሚባሉትም ቢሆኑ ሲያማርሩ ይሰማል፡፡
መሠረታዊ ምግብ ነክና ምግብ ነክ ያልሆኑ የፍጆታ ዕቃዎች ዋጋ መጨመር የአብዛኛውን ነዋሪ የዕለት ኑሮ መገዳደሩንም ከከተማ እስከ ክልል በተለያዩ ጊዜያት በተደረጉ የውይይት መድረኮች ከነዋሪዎች ሲገለጽ እንደነበር ይታወሳል፡፡
መነሻው በርካታ መሆኑ የሚነገርለት የኑሮ ውድነት፣ በተለይም በሰሜኑ የኢትዮጵያ ክፍል ያለው ጦርነት እንዲሁም የዩክሬንና የሩሲያ ጦርነት ኢኮኖሚያዊ፣ ማኅበራዊና ፖለቲካዊ ቀውሶችን አስከትሏል፡፡
የበዓል ወቅት ደግሞ የኑሮ ውድነትን ከሚያባብሱ መካከል የሚጠቀስ ሲሆን፣ የ2015 ዓ.ም. ዘመን መለወጫም በብዙ ችግሮችና ውጥንቅጦች ውስጥ ሆኖ እንዲያልፍ የሚስገድዱ ሁኔታዎች ከወዲሁ ይታያሉ፡፡ ከእነዚህ ውስጥ በገበያዎች የሚጠራው ዋጋ ከፍተኛ አንዱ ማሳያ ነው፡፡
ኢትዮጵያውያን አዲስ ዓመትን ለመቀበል ብዙ ሸመታዎች ያከናውናሉ፡፡ ከምግብና ከመጠጡ ባለፈ ወቅቱ ትምህርት ቤት የሚከፈትበት መሆኑ ወጪን ያበዛል፣ ወላጆችንና አሳዳጊዎችንም ያስጨንቃል፡፡ የዘንድሮ የልጆች የትምህርት ቤት ወጪ ሲታሰብ ደግሞ፣ ከኑሮ ጋር አንገት ለአንገት የሚተናነቁበት ወቅት መሆኑን ያሳያል፡፡
ወ/ሮ ዓለምነሽ አንድነት የካ ክፍለ ከተማ ወረዳ 5 ነዋሪ ሲሆኑ፣ ሾላ ገበያ ሲገበያዩ አግኝተናቸዋል፡፡ የአራት ዓመት ልጅ እንዳላቸው የሚናሩት ወ/ሮ ዓለምነሽ፣ ለ2015 ዓ.ም. ልጃቸው ትምህርት ቤት መመዝገቡን ይናገራሉ፡፡
ለ2015 ዓ.ም. የትምህርት ዘመን ለልጃቸው የትምህርት ቁሳቁስ ብቻ ብዙ ገንዘብ እንዳወጡ ይናገራሉ፡፡ ዩኒፎርም፣ ምሳ ዕቃ፣ ደብተርና ሌሎችም ግብዓቶች ዋጋ መጨመሩንም ለሪፖርተር ተናግረዋል፡፡
‹‹እኔ እንዴትም ብዬ ለልጄ ለትምህርት የሚሆነውን መግዛት ችያለሁ፤›› የሚሉት ወ/ሮ ዓለምነሽ፣ ከሁለት በላይ ልጆች ያሏቸው ወላጆች ከመሠረታዊ የምግብ ፍጆታዎች መጨመር ጋር ተደምሮ ኑሮው ከባድ ይሆንባቸዋል ብለዋል፡፡
በየካ ክፍለ ከተማ የሚኘው ትልቁ ሾላ ገበያ መሠረታዊ የምግብ ፍጆታን ጨምሮ በርካታ ቁሳቁሶች የሚኝበት የገበያ ሥፍራ ነው፡፡ ይሁን እንጂ ከጊዜ ወደ ጊዜ የሰዎች (የዜጎች) ገቢ ሳይጨምር፣ የነገሮች ወጋ በመናሩ የገበያው ሁኔታ መቀዛቀዙን አንዳንድ ያነጋገርናቸው የሾላ ገበያ ነጋዴዎች ይናገራሉ፡፡
ከዚህ ቀደም ሦስትና ከዚያ በላይ ቁሶችን የሚሸምቱበት ገንዘብ፣ ዛሬ ላይ አንድ ቁስ እንኳን በላይ ለመግዛት አያስችልም፡፡
ትምህርትና የኑሮ ውድነት
መንግሥት ትምህርት ቤት የሚያስተምሩ ወላጆች የተማሪዎች በትምህርት ግብዓት ወጪ ዕፎይ ቢሉም፣ ከግማሽ በላይ ዜጎች ልጆቻቸውን የግል ትምህርት ቤት የሚያስተምሩ መሆናቸው የችግሩ ዋነኛ ተጋላጭ ያደርጋቸዋል፡፡
በሾላ ገበያ የ2015 ዓ.ም. የተማሪዎች ቁሳቁስ ሽያጭ ዩኒፎርም፣ ደብተር፣ ስክሪብቶ፣ ቦርሳና መሰል ግብዓቶች ዋጋቸው አይቀመሴ መሆኑን ሪፖርተር በቦታው ተገኝቶ አረጋግጧል፡፡
ለምሳሌ የጀማሪዎች የዩኒፎርም ዋጋ ሹራብ ከ500 ብር ጀምሮ የሚሸጥ ሲሆን፣ ሰደርያ ወይም እጅጌ የሌለው ሹራብ ደግሞ እንደ ዓይነቱ ከ500 ብር በታች እንደሆነና ዋጋው እንደሚቀንስ ተመልክተናል፡፡
ለጀማሪ ተማሪዎች የዩኒፎርም አነስተኛ ዋጋው ሹራብ 500፣ ሸሚዝ 400፣ ሱሪ (ቀሚስ) 400 ብር እየተሸጠ እንደሚገኝ የሾላ ገበያ ነጋዴ አቶ ብርኃኑ ታደለ ነግረውናል፡፡
አቶ ብርኃኑ እንዳስረዱት፣ የዩኒፎርም ገበያው ከዓምና ጋር ሲነፃፀር የዋጋ ጭማሪ አሳይቷል፡፡ ምክንያቱም ለዩኒፎርም የሚሆኑ ጨርቃ ጨርቅ ዋጋቸው በመጨመሩ ነው፡፡ ነጋዴውም የባለሙያዎች፣ የትራንስፖርትና የሌሎች ግብዓቶች ዋጋ ሲታከልበት ዋጋው ከፍ ማለቱን አስርድተዋል፡፡
ዓምና ለጀማሪ ተማሪ የሹራብ ዋጋ ከ250 ብር ጀምሮ መሸጡን ያስረዱት አቶ ብርኃኑ፣ የተለያዩ ግብዓቶች ዋጋ ከፍ ማለቱ ለዘንድሮ ገበያ መወደድ ምክንያት መሆኑን ገልጸዋል፡፡
በሾላ ገበያ ለአንድ ተማሪ ሙሉ ዩኒፎርም እስከ 1500 ብር ድረስ እየተሸጠ ሲሆን፣ የዋጋው ልዩነት ደግሞ የጨርቅ፣ ልዩነትና በተማሪዎች ዕድሜ የሚወሰን መሆኑን ገልጸዋል፡፡
በአዲስ ክፍለ ከተማ በሚገኘው የኢትዮጵያ ትልቁ የመገበያያ ቦታ መርካቶ፣ ሚሊተሪ ተራ በሚባለው ሥፍራ የተማሪዎች ዩኒፎርም ይሸጣል፡፡
በሥፍራው በሚገኙ የገበያ አዳራሾች የተማሪዎች ዩኒፎርም ሹራብ፣ ሸሚዝና ሱሪ/ቀሚስ የሚሸጥ ሲሆን፣ የሸሚዝ ዋጋ 300፣ የሹራብ 400 ቀሚስ (ሱሪ) 400 ብር እየተሸጠ ይገኛል፡፡ በእነዚህ የገበያ አዳራሾች ይበልጥ አዋጭ የሚያደርገው በብዛት (በጅምላ) የሚገዙትን መሆኑን በንግድ ሥራ የተሰማሩት አቶ ይድረስ ተካልኝ ነግረውናል፡፡ የአንድ ትምህርት ቤት ወላጆች በጋራ መጥተው ቢሸምቱ ዋጋው ሊቀንስላቸው እንደሚችል አቶ ይድረስ ጠቁመዋል፡፡
የዋጋ ልዩነቱ በተማሪዎች የትምህርት ደረጃና በሰውነታቸው ልክ የሚወሰን ሲሆን፣ የትምህርት ደረጃቸው ከፍ ሲል ዋጋው በዚያው መጠን ይጨምራል ብለዋል፡፡
የዩኒፎርም ዋጋ ከዓምና ጋር ሲነፃፀር መጨመሩን የገለጹት አቶ ይድረስ፣ የሁሉም ነገሮች ዋጋ መናር ለዩንፎርም ዋጋ መጨመሩ ምክንያት መሆኑን አንስተዋል፡፡
የቦርሳና የደብተር ገበያ
በሾላ ገበያ አንደኛ ደረጃ የራዲካል ባለሁለት ሽፋን 50 ገጽ ደብተር አንዱ በ71 ብር፣ የደርዘን ዋጋ ደግሞ 857 ብር እየተሸጠ ይገኛል፡፡
ራዲካል 2ኛ ደረጃ ባለ ሽፋን ደብተር ደግሞ በ58 ብር እየተሸጠ መሆኑን፣ የደርዘን ዋጋው 696 ብር እንደሆነ ከሱቅ ደጃፍ ሆነው ሲሸጡ ያገኘናቸው ነጋዴ ይናገራሉ፡፡
የእነዚህ የመማሪያ ግብዓት በተለይም የደብተር ደርዘን ዋጋ ዓምና በ371 ብር እንደነበር፣ በዘንድሮው ገበያ ደግሞ የ481 ብር ጭማሪ ማሳየቱን ገልጸዋል፡፡ የዋጋው ልዩነት፣ በደብተር ዓይነቶችና ደረጃቸው እንደሚለያይ፣ ቅናሽ የሚባለው በደርዘን 500 ብር መሆኑን አክለዋል፡፡ የደብተር ዋጋ በከፍተኛ ሁኔታ የመጨመር ምክንያት የወረቀት ዋጋ መጨመር መሆኑንም አስረድተዋል፡፡
ለልጆች ትምህርት ቤት ከሚያስፈልጉ ግብዓቶች መካከል ቦርሳ ተጠቃሽ ሲሆን፣ በሾላ ገበያ አንድ ቦርሳ ከ800 ብር እስከ 1500 እየተሸጠ መሆኑን ተመልክተናል፡፡
የመርካቶ ገበያ ደግሞ ከሾላ ገበያ አንፃር ቅናሽ ያለው ሲሆን፣ ከ500 ብር እስከ 1000 ብር እየተሸጠ መሆኑን ሪፖርተር በቦታው ተገኝቶ ተመልክቷል፡፡
በዚህ ጉዳይ ላይ ያነጋገርናቸው አንድ ወላጅ እንደተናገሩት፣ ለመጀመርያ ጊዜ ትምህርት ቤት ለሚገባ ልጅ የሚያስፈልገው ወጪ ከባድ ነው፡፡
ለጀማሪ ተማሪ ለዩኒፎርም፣ ለደብተር፣ ለምሳ ዕቃና ሌሎችም ግብዓቶች ከአምስት ሺሕ ያላነሰ ወጪ ማውጣታቸውን ተናግረዋል፡፡
የትምህርት ቤት ክፍያን ሳይጨመር ተማሪዎችን የመማሪያ ግብዓቶች ለማሟላት መቸገራቸውን ወላጆች ገልጸዋል፡፡ ከአንድ በላይ ልጆች በላይ ላላቸው ወላጆች ከኑሮ ውድነት ጋር ተደምሮ አስቸጋሪ ሊሆንባቸው እንደሚችል ነግረውናል፡፡
ለልጆቻቸው ደብተርና ሌሎችም ግብዓቶች ለመግዛት በሾላ ገበያ ሲዘዋወሩ ያገኘናቸው አቶ በላይ ሙላት እንደተናገሩት፣ ለሦስት ልጆቻቸው የትምህርት ቁሳቁስ ብቻ ከአሥር ሺሕ ብር በለይ አውጥተዋል፡፡
የትምህርት ቤት ክፍያቸውን ሳይጨምር መሆኑን የገለጹት አቶ በላይ፣ ሌሎች የሚያስፈልጉ ነገሮችን ለመግዛት እንደከበዳቸው ገልጸዋል፡፡
ከዚህ ቀደም ለአዲስ ዓመት ወይም ለዘመን መለወጫ ከትምህርት ቤት ግብዓቶች በተጨማሪ ልብስና ጫማ ለልጆቻቸው እንደሚገዙ፣ ዘንድሮ ግን ይህን ማድረግ እንደማይችሉ አስረድተዋል፡፡
በሾላ ገበያ የስክርቢቶ ዋጋ በነጠላ ከ16 ጀምሮ፣ በጅምላ ደግሞ ከ800 ብር እስከ 1000 ብር፣ የምሳ ዕቃ ከ1200 ብር እስከ 1800 ብር እየተሸጠ መሆኑን ተገንዝበናል፡፡ አንዱ እሽግ እስክሪብቶ 50 ፍሬ የሚይዝ ሲሆን፣ በነጠላ ዋጋው እንደ ስያሜያቸው እንደሚለያይ አይተናል፡፡
ዓምና የተማሪዎች የውኃ መያዣ 250 ብር ድረስ የገዙ ወላጆች ለ2015 ዓ.ም. ትምህርት ዘመን 500 ብር መግዛታቸውን ተናግረዋል፡፡
የኑሮ ወድነት ተከሰተ የሚባለው የዜጎች የመግዛት አቅም ከጊዜ ወጊዜ እየተዳከመ ሲመጣ መሆኑ ይታወቃል።
በኢትዮጵያ በዋጋ ግሽበቱ ዝቅተኛ ገቢ ያላቸውና ጊዜያዊ ወይም የዕለት ሥራ ላይ ኑሯቸውን መሠረት ያደረጉ ዜጎች ላይ ይበረታል፡፡
በዝቅተኛ ገቢ የሚተዳደሩ የማኅበረሰብ ከፍሎች በአሁኑ ጊዜ የኑሮ ውድነት በጣም ተጎጂ መሆናቸውን፣ በኢትዮጵያ ከግማሽ በላይ የሚሆነው የማኅበረሰብ ክፍል በኢ-መደበኛ ወይም በቀን ሥራ የሚተዳደሩ መሆናቸው ችግሩ የጎላ ያደርገዋል፡፡
ምግብ ነክና ምግብ ነክ ያልሆኑ መሠረታዊ ሸቀጦች ዋጋ ከዕለት ዕለት ዋጋ መጨመሩ በገበያ ማዕከላትና በመደብሮች ያለው ዋጋ ምስክር ነው፡፡
በተጠናቀቀው በጀት ዓመት የተመዘገበው አማካይ የምግብ ዋጋ ግሽበት 40.2 በመቶ ሆኖ የተመዘገበ ሲሆን፣ በሌላ በኩል ምግብ ነክ ያልሆኑ ቁሶች የነበራቸው የዋጋ ግሽበትም 25 ከመቶ እንደነበር የኢትዮጵያ ስታስቲክስ ኤጀንሲ ማስታወቁ ይታወሳል፡፡
በኢትዮጵያ ለችርቻሮ ዋጋ ጥናት የሚያግዙ 119 የተመረጡ የገበያ ቦታዎች መሠረት ተደርጎ የሚቀርበው የሸማቾች ዋጋ መመዘኛ ኢንዴክስ የሐምሌ 2014 ዓ.ም. ሪፖርት እንደሚያሳየው፣ አጠቃላይ የዋጋ ግሽበቱም ሆነ ምግብ ነክና ምግብ ነክ ያልሆነው የግሽበት ሁኔታ አሁንም በ30ዎቹ በመቶ ውስጥ ይገኛል፡፡
የዋጋ ግሽበት በዚህ ጊዜ በኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን ባደጉ አገሮች ጭምር ፈተና እየሆነ መምጣቱን ያስታወቀው የስታትስቲክስ አገልግሎት፣ ‹‹ካለው ዓለም አቀፍና አገር አቀፍ የኢኮኖሚ ሁኔታና ሌሎች ፈታኝ ሁኔታዎች አንፃር በሐምሌ 2014 ዓ.ም. የታየው የዋጋ ግሽበት መልካም የሚባል ነው፤›› በማለት ገልጾታል፡፡
በሐምሌ ወር የምግብ ኢንዴክስ ክፍሎች መጠነኛ መረጋጋት ማሳየታቸውን የሚሳየው የአገልግሎቱ ሪፖርት፣ በአንፃሩ ምግብ ያልሆኑ የኢንዴክስ ክፍሎች ላይ የሚስተዋለው ጭማሪ አሁንም እያሻቀበ እንደሚገኝ ያመላክታል፡፡
ምግብ ነክ ያልሆኑ ቁሳቁሶች የዋጋ ግሽበት ካለፈው ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነፃፀር ከፍ እንዲል ካደረጉትና ዋና ምክንያቶች ተብለው ከተጠቀሱት ውስጥ በአልኮልና በትምባሆ፣ በልብስና ጫማ፣ የቤት መሥሪያ ዕቃዎች ተብለው በሚመደቡት የቤት ኪራይ፣ ሲሚንቶ፣ የቤት ክዳን ቆርቆሮ፣ የቤት ዕቃዎች፣ ነዳጅ፣ ሕክምናና ጌጣ ጌጦች የተመዘገበው የዋጋ ንረት ይጠቀሳል፡፡
በጠቅላላው የሐምሌ ወር አጠቃላይ የዋጋ ግሽበት መጠን 33.5 በመቶ የምግብ ዋጋ ግሽበት 35.1 በመቶ እንዲሁም ምግብ ነክ ያልሆኑ የዋጋ ግሽበት 30.4 በመቶ ሆነው መመዝገባቸውን የማዕከላዊ ስታትስቲክስ አገልግሎት ሪፖርት ያሳያል፡፡