Wednesday, June 19, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

ማኅበራዊየኅብረተሰቡ የጤና ችግር እንደሆነ የቀጠለው የወባ በሽታ

የኅብረተሰቡ የጤና ችግር እንደሆነ የቀጠለው የወባ በሽታ

ቀን:

የወባ በሽታ ከዚህ ቀደም በወረርሽኝ መልክ ተከስቶ በአጭር ጊዜ ውስጥ ብዙ ሰዎችን ለሕመምና ለሞት ዳርጓል፡፡ የወባ በሽታ ትሮፒካል በሚባሉ አካባቢዎች በተለይም በአፍሪካና በተወሰኑ የእስያ አገሮች እንዲሁም በደቡብ አሜሪካ እስካሁን አለ፡፡

ከዚህ ቀደም ሰሜን አሜሪካና አውሮፓ የወባ ችግርን ሲያስተናግዱ የነበረ ቢሆንም፣ በተከናወኑ ሥራዎችና ጠንካራ ርብርብ የወባ በሽታ የኅብረተሰብ የጤና ችግር ከማይሆንበት ደረጃ ላይ አድርሰውታል፡፡

የጤና ሚኒስቴር የበሽታዎች መከላከልና መቆጣጠር ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ወ/ሮ ሕይወት ሰለሞን እንደገለጹት፣ የወባ በሽታ በአሁኑ ጊዜ የሚገኘው ትሮፒካል በሚባሉ አገሮች ብቻ ነው፡፡ በኢትዮጵያ ለተከታታይ ዓመታት በተሠሩ ሥራዎች በጣም ጥሩ የሚባል ወባን መቆጣጠር ሥራ ተከናውኖ ጫናው የመቀነስ አዝማሚያ ቢታይበትም፣ አሁንም ከአንድ ሚሊዮን በላይ ሰዎች በበሽታው ተይዘዋል፡፡

- Advertisement -

የሞት ምጣኔው ከ200 በታች ቢሆንም፣ ሰዎች በወባ ሕይወታቸውን እያጡ ሲሆን፣ በተለይ ዘንድሮ በአየር ንብረት ለውጥ ሳቢያ ወባን ጨምሮ ሌሎች በትንኝ ምክንያት በሚከሰቱ በሽታዎች ሳቢያ የሟቾች ቁጥር እየጨመረ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

ጤና ሚኒስቴር በ2009 ዓ.ም. ወባን ለመቆጣጠርና ለመከላከል የሚያስችል ስትራቴጂ ቀርፆ ለተግባራዊነቱ ሁሉን አቀፍ እንቅስቃሴ ሲያከናውን መቆየቱን፣ በእንቅስቃሴውም ጥሩ ውጤት መመዝገቡን ይህ ሥራ እየተካሄደ ያለው በኢትዮጵያ በ2022 ዓ.ም. ወባ የኅብረተሰቡ የጤና ችግር የማይሆንበት ደረጃ ላይ ለማድረስ በሚል መሆኑንም አክለዋል፡፡

‹‹በወባ በሽታ መከላከልና መቆጣጠር ላይ ያተኮረ ለኅብረተሰቡ ግንዛቤ ማስጨበጫ የተዘጋጁ የቴሌቭዥንና የሬዲዮ ማስታወቂያ የአየር ላይ ሥርዓት ማስጀመሪያ ፕሮግራም ሐምሌ 26 ቀን 2014 ዓ.ም. በተከናወነበት ሥነ ሥርዓት ላይ ዋና ዳይሬክተሯ እንዳብራሩት፣ ወባን ለመከላከል የሚተገበሩ ሥልቶች በጣም ግልጽ መሆን አለባቸው፡፡

የበሽታ አምጪ የሆኑ ትንኞችን መቆጣጠር፣ አክሞ ማዳን፣ በሽታው ከአንድ ሰው ወደ ሌላው እንዳይተላለፍ ማድረግና ለዚህም ፍቱን መድኃኒቶችን መጠቀም፣ የመድኃኒቶችን ፍቱንነት ለማረጋገጥ የሚያስችል በሁለት ዓመት አንዴ የቁጥጥር ሥራ እንደሚከናወን በተጨማሪም የቤት ውስጥ ርጭት ማካሄድና የአልጋ አጎበሮችን ወባማ በሆኑ አካባቢዎች ማሠራጨት ከሥልቶቹ መካከል ተጠቃሽ እንደሆኑ አመልክተዋል፡፡

የአገሪቱ 75 ከመቶ ያህሉ የቆዳ ስፋት ለወባ ሥርጭት ምቹ በመሆኑ በዚህ አካባቢ ያሉ ማኅበረሰቦችን በተጠቀሱት ሥልቶች የመደገፍ፣ ራሳቸውንና ቤተሰቦቻቸውን ከወባ እንዲጠብቁ የማድረግ ሥራ እንዲሁም የጤና ባለሙያዎች ወባ ላይ ክህሎት ኖሯቸው ምርመራውንና ሕክምናውን እንዲያደርጉ የሚያስችላቸውን ተከታታይ የአቅም ግንባታ ሥልጠና መስጠትና የጤና ኤክስቴንሽን ባለሙያዎች ወባን የሚመረምሩበት መሣሪያ እንዲኖራዠው ማስቻል ካሉት ሥልቶች እንደሚገኙበት ተናግረዋል፡፡

የጤና ልማትና ፀረ ወባ ማኅበር ዋና ዳይሬክተር አበረ ምኅረቴ (ዶ/ር)፣ በኢትዮጵያ በዋናነነት ከሚያዝያ እስከ ግንቦት እንዲሁም ከመስከረም እስከ ታኅሳስ ከፍተኛ የወባ ሥርጭት የሚታይባቸው ወቅቶች መሆናቸውን ገልጸው፣ እነዚህ ወቅቶች የምርት ወቅት ከመሆናቸው ጋር ሲታይ ወባ በምርታማነት ላይ የሚያስከትለው ተፅዕኖ ቀላል እንዳልሆነ ለመረዳት እንደማያዳግት አስረድተዋል፡፡

‹‹ጤና አገልግሎቶችን በማቅረብ ረገድ ከፍተኛ ጥረት ተደርጓል፣ ነገር ግን የጤና አገልግሎቶችን በመጠቀም ደረጃ ማኅበረሰባችን ላይ ከፍተኛ ክፍተት ይታያል፤›› ያሉት አበረ (ዶ/ር) ወባን ለመከላከል አጎበር፣ የፀረ ትንኝ ኬሚካል ርጭት፣ የምርመራና የሕክምና እንዲሁም የመድኃኒት አቅርቦት በከፍተኛ ሁኔታ የጨመረ ቢሆንም፣ እነዚህን አገልግሎቶች በመጠቀም በኩል ሰፊ የግንዛቤና የተግባር ክፍተት እንደሚትይ ጠቁመዋል፡፡

በአጎበር ውስጥ አዘውትሮና በትክክል የሚተኛ የኅብረተሰብ ክፍል ዝቅተኛ ሲሆን፣ ትኩሳትና የሕመም ምልክት የሚያሳይ ሰው በዕለቱ ወደ ጤና ተቋም መሄድ ሲገባው ይህ ሲሆን እንደማይታይ፣ አስፈላጊውን የወባ ምርመራ አካሂዶ በሐኪም የታዘዘለትን መድኃኒት በአግባቡ የሚወስደው ሰው ቁጥርም አጥጋቢ አለመሆኑን፣ በየአካባቢው ቁጥጥር ሥራዎች በማካሄድ ወባ ከመከሰቱ በፊት የመከላከሉም ሥራ ዝቅተኛ እንደሆነም ተናግረዋል፡፡

ለሥራ ወደ ወባማ አካባቢዎች ሲንቀሳቀስም ሆነ ወደ ቋሚ መኖሪያ አካባቢው ሲመለስ ጥንቃቄና ምርመራ የሚያደርገው እንዲሁም ሕክምና የሚወስደው ሕዝብ ቁጥር በጣም አናሳ ያሉት አበረ (ዶ/ር)፣ የኅብረተሰቡን ግንዛቤ ለማሻሻል ዘርፈ ብዙ የማስተማር ሥራ በጤና ሚኒስቴርና በተለያዩ አጋር አካላት መሥራት እንደሚገባ አስረድተዋል፡፡

አቅም በፈቀደ መጠን በኅትመትና በኤሌክትሮኒክስ ሚዲያ ተደራሽ ለመሆን በተለያዩ የብዙኃን መገናኛዎች ለመሥራት ማኅበሩ ዕቅድ መያዙን፣ የቅስቀሳ መልዕክቶቹም ቁልፍ የወባ መከላከል ሥልቶች በእያንዳንዱ ግለሰብ፣ ቤተሰብና ማኅበረሰብ መተግበር ብሎም ልምድ መሆን ያለባቸው መሆኑን ጠቁመው፣ ለዚህም የቤተሰብ አባላት ዘወትር በመኝታ ጊዜ አጎበር ውስጥ እንዲተኙ፣ የአልጋ አጎበር ሲቆሽሽ በልብስ ሳሙና በማጠብና ጥላ ቦታ ላይ በማስጣት አድርቀው እንዲጠቀሙ አሳስበዋል፡፡

በማንኛውም ጊዜ የቤተሰብ አባላት የትኩሳት ስሜት ሲኖራቸው በ24 ሰዓት ውስጥ በአቅራቢያ ወደሚገኝ ጤና ተቋም መውሰድ፣ የፀረ ወባ መድኃኒት በሕክምና ባለሙያ በታዘዘው መሠረት ሳይቋረጥ ሙሉ በሙሉ መጠቀምና የፀረ ወባ ትንኝ ኬሚካል ለሚረጩት ባለሙያዎች አስፈላጊውን ትብብር ማድረግ አስፈላጊ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

የፀረ ወባ ትንኝ ኬሚካል የተረጨውን ግድግዳ ለስድስት ወራት በጭቃም ሆነ አዛባ መለቅለቅ ወይም በጋዜጣና በወረቀት መለጠፍ ተገቢ አለመሆኑን ገልጸዋል፡፡ በመኖሪያ አካባቢ የሚገኙ ውኃ የሚይዙና ጥቅም የማይሰጡ ቁሳቁሶችንና ረግረጋማ ቦታዎችን በየሳምንቱ ማፅዳት፣ ማፍሰስና መድፈን እንደሚያስፈልግ ተናግረዋል፡፡

ጤና ልማትና ፀረ ወባ ማኅበር ከ24 ዓመታት በፊት የወባ በሽታ በሕዝቡ ላይ ያስከተለውን እጅግ አስከፊ ሕመም፣ ስቃይና የበርካቶችን ሞት ለመቀልበስ የበኩሉን አስተዋጽኦ ለማበርከት የተቋቋሙና በወባ መከላከልና ቁጥጥር ሥራ በማገዝ ረገድ ጉልህ ሚና እየተወጫተ የሚገኝ ማኅበር መሆኑንም ጠቁመዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የንብረት ማስመለስ ረቂቅ አዋጅና የሚስተጋቡ ሥጋቶች

ከሰሞኑ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የቀረበው የንብረት ማስመለስ ረቂቅ...

የመጨረሻ የተባለው የንግድ ምክር ቤቱ ምርጫና የሚኒስቴሩ ውሳኔ

በአገር አቀፍ ደረጃ ደረጃ የንግድ ኅብረተሰቡን በመወከል የሚጠቀሰው የኢትዮጵያ...

ሚስጥሩ!

ጉዞ ከካዛንቺስ ወደ ስድስት ኪሎ፡፡ የጥንቶቹ አራዶች መናኸሪያ ወዘናዋ...