Saturday, March 25, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -

የተመረጡ ፅሑፎች

ሰበበኞች!

ሰላም! ሰላም! እንደምን ከረማችሁ ወዳጆቼ፡፡ ሰላም ስንሻ የጦርነት ግብዣ ይዞልን ከሚቀርብ ነገረኛ ጋር የተያያዝነው ትግል መቼ እንደሚያበቃ እንጃ፡፡ በዚያን ሰሞን ለአዲስ ዓመት መቃረቢያ የምሥራች ይሆን ዘንድ በግ አርጄ ከጎረቤቶቼ ጋር ስንደሰት ቤቴ የሠርግ አዳራሽ መስሎ ሰነበተ። ለአንድ ለሁለት ቀንም ቢሆን ‘ሰለብሪቲ’ ሆንኩ። ስንት ዓመት ተሸውጄ ኖሯል እያልኩ በውስጤ ጎረቤቶቼን ‘ብሉ ጠጡ’ ስል እኔ አንድ ጎድን ሳይደርሰኝ ድስቱ ባዶ ሆነ። ተመሥገን ነው ለነገሩ። ዋናው ኪስ ነው። ዳሩ ቻይና ቦርቀቅ ቦርቀቅ ያለ ኪስ እየሰፋችልን የዘንድሮ ኪስ ቶሎ አይሞላም። ‘ከቻይና ሱሪ ነው ከእኛ የኢኮኖሚ ዕድገት ነው ችግሩ?’ ብዬ እንዳልጠይቅ ማንን አምኜ። ዘንድሮ እንኳን ‘ሲሪየስ’ ነገር የታመመ ለመጠየቅም መታወቂያ እያዩ ሆኗል አሉ። አያድርስ ነው። አዛውንቱ ባሻዬ፣ ‹‹ከመሸ መወለድ ትርፉ ይኼ ነው…›› እያሉ ይቆዝማሉ። እሳቸው ደግሞ ሰሞኑን የስምንተኛው ሺሕን ነገር ሲያነሱ ሲጥሉ መዋል አብዝተዋል። እኔም ይኼንን ሁኔታቸውን እየታዘብኩ ‘እውነትም ባሻዬ ሲመሽ ተወልደዋል’ እላለሁ በሐሳቤ፡፡ ማንም ከመሬት እየተነሳ በድንገት ሚሊዮንና ቢሊዮን ረብጣ ሲቆጥር፣ እሳቸው ስምንተኛው ሺሕ ላይ ‘ስታክ’ ማድረጋቸው ግራ ያጋባኛል። እንዴት ነው ግን እንግሊዝኛዬ? መሻሻል ይታይብኛል አይደል? በተለይ ሰሞኑን ምን እንደታየኝ አላውቅም ‘ቮካብላሪ’ ጥናት ላይ በርትቻለሁ። በዚህ አያያዜ የቻይኖቹን ማንዳሪን ከጨመርኩበት ተስፋ አለኝ፡፡ ተስፋ መልካም ነው!

እንዲያው ሌላው ቢቀር ባሻዬን አንድ የውጭ አገር ጋዜጠኛ አግኝቷቸው፣ ‘እስኪ ስለስምንተኛው ሺሕ ያጫውቱን’ ብሎ መጠየቁ አይቀርምና ልዘጋጅ ብዬ እኮ ነው። መቼም ባሻዬ ከእኔ ወዲያ ምሁሩን ልጃቸውንም ቢሆን አምነው ለአስተርጓሚነት አይመርጡም። ትርጉምና አተረጓጎም ነዋ ዓለምን የበጠበጣት። ለነገሩ በአስተርጓሚም መናገራቸው እሳቸው ሆነው ነው። ይኼው አታዩም አስተርጓሚዎች ማን እንደ እኛ እያሉና ባልዋልንበት ዋሉ እያሉ ሲያስቁብን። በቀደም ዕለት ምድረ ተላላኪ የፈረንጅ ደላላ አንዴ ወልዲያ፣ ሌላ ጊዜ ላሊበላ ተያዙ እያሉ ሲያምሱን ከረሙ፡፡ የእኛዎቹ ወሬ ለቃቃሚዎች ደግሞ እነሱን እየተከተሉ ግራ ሲጋቡ ታዘብን፡፡ ለነገሩ ዘንድሮ ምድረ ወሬኛ በበላበት ነው የሚጮኸው፡፡ ታዲያላችሁ ስለዘመኑ ጥቀርሻ፣ ስለዚህ በጥቅም ስለመቧደን፣ በብሔር ስለመከፋፈል፣ በሃይማኖት ወገንተኝነት ስለመፋቀር (ወይ ፍቅር?) የምናገረውን በእንግሊዝኛ አጥንቼ ሳበቃ ስምንተኛው ሺሕ ላይ ስደርስ በእንግሊዝኛ ምን እንደሚባል የሚነግረኝ ሰው ጠፋ። እናንተ ታውቁ ይሆን? ቄሱም ዝም መጽሐፉም ዝምʼ ሆነ እኮ!

  ለአዲስ ዓመት መቃረቢያ ብዬ ባረድኩት አንድ በግ ዝናዬ ከእትዬ ስርጉት እስከ ባሻዬ ቤት መናኘቱን ዓይቶ አንድ ወዳጄ፣ ‹‹ይኼን ያህል የእኛ ሰው የበግ አምሮት ካለው ለምንድነው ታዲያ የዘመኑ ድንገተኛና ፈጣን ልማታዊ ባለሀብቶች ሥጋ ቤትና ውስኪ ቤት ከሚተራመሱ የበግ ዕርባታ ኢንቨስትመንት ጀምረው በዓል ሲመጣ ለሰፊው ሕዝብ በቅናሽ የማያቀርቡት?›› አለኝ። ‹‹ዝም ብሎ ለሕዝብ ማዘን አለ እንዴ? ያውም በግ በቅናሽ ዋጋ? የእኛ ብዙዎቹ ባለሀብቶችማ በስንት መከራ ቡና፣ ቆዳና ወርቅ ሸጠን የምናገኘውን ዶላር እየተቀራመቱ አሉሚኒየምና መስተዋት እየገዙበት አስጠሊታ ሕንፃ ይገንቡበት፡፡ የአምቦ ድንጋይ ተጠቅመው ውብ ሕንፃዎች መገንባት እየቻሉ በተሰረቀ ዲዛይን አስቀያሚ ሕንፃ እየገነቡ በሙቀት ይፍጁን እንጂ፣ ጭራሽ ኢንቨስትመንት ውስጥ ገብተው ሊሠሩ ነው ብለህ አታስቀኝ…›› እያለ አንዱ ሲስቅ ሳልፈልግ የግዴን ፈገግ ለማለት ተገደድኩ። እኔ ምለው ግን ሰው እንዲህ ምሬት ውስጥ ነው ማለት ነው? አጀብ ማለት አሁን ነው!

አዛውንቱ ባሻዬ ደግሞ ሌላ ርዕስ በውስጠ ወይራ ይዘው ብቅ ሲሉ እንዲህ ነበር ያሉት፡፡ ‹‹…አንድም የትምክህት አንድም የድሮ ዘመን ናፋቂ ሰው አስተሳሰብ ይመስላል። ሁሉም ዘመን እንደ ልኩ እንደ ዑደቱ የሚታረዱ በጎች አሉት። በድሮና በዘንድሮ በጎችና አራጆች መሀል ያለው ልዩነት ምን መሰለህ አንበርብር? ድሮ በጎች የሕዝብ ናቸው። የአገር ናቸው። አገር ዜጋዋን በዋጋ ግዛኝ አትልም ነበር። ስለዚህ ከዓመት ዓመት በተቀመጥክበት፣ ሁለት ሦስት የእንጀራ ገመድ ሳይኖርህ በግ ቀርቶ በሬ ታርዳለህ። አሁን ግን የለውጥ ባቡር አለ። ባቡሩ ላይ ሳትሳፈር እንዲሁ በዋዛ የመስዋዕቱን በግ የሚያዘጋጅልህ ማንም የለም። የድሮ በግ ተውሰህ እንኳ ብታርደው እንደ ጌታው ነበር የሚቆጥርህ። ዘንድሮ እንደምታየው በካቦም አስረኸው ንቀቱ ንቀት አይደለም…›› ሲሉኝ ሳቄ ትን ብሎኝ ልሞት ነበር። እሳቸው ይህንን አስተያየት ሲሰጡ ያዳመጠ ደላላ ወዳጄ፣ ‹‹አንበርብር እኚህ ሰው ፈላስፋ ወይስ የፖለቲካ ተንታኝ ናቸው…›› እያለ በጥያቄ ምልክት ሲያየኝ፣ ‹‹ዝም ብለህ ስማ ከፍልስፍናም ሆነ ከፖለቲካ ጋር አይያያዝም…›› ብዬ ለማስተባበል ስሞክር፣ ‹‹ተው እንጂ አንበርብር፣ ፍልስፍናም ፖለቲካም ካልሆነ ቅኔ ከመሆን ግን አያልፍም…›› ብሎኝ እብስ አለ፡፡ ያሰኛል!

ከባሻዬ ቅኔ ወደ እኔ የቀን ውሎ ስንሸጋገር ደግሞ ጭርታን እናገኛለን። ʻለጭርታ ለጭርታ ለምን ታሻግረናለህ? ቅኔው ላይ ጠበቅ አድርገህ አውጋንʼ የምትሉኝ ካላችሁ በውስጥ መስመር አነጋግሩኝ። ዘንድሮ እንኳን በውጭ ውስጥ ለውስጥም መስኮት ከፍተን ሐሜቱን አልቻልነውም። ያልተናገርነውን ተናገሩ፣ ያላልነውን አሉ፣ ያልነውን አላሉም የሚሉን በዝተዋል። በጣም የማዝነው ሁሉም ስለሐሳብ ብዝኃነትና ልዩነት እያወራ ቆይቶ ሐሳባችሁ አልጥም ሲለው፣ ‹‹መቼ ነው የመለመሉሽ?›› ብሎ ያሽሟጥጣል። እውነቴን እኮ ነው። ምሁሩ የባሻዬ ልጅ ሁሌም እንደሚያጫውተኝ ʻዴሞክራሲʼ የሚለው ቃል ምንጩ ከግሪክ ነው። ‹‹ከግሪክ ሥልጣኔ በፊት ደግሞ ኩሽ ኢትዮጲስ ጽፈት የጀመረች አገር ነች። በግሪክ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት በሐሳብ የተሸነፈው ቡድን አገር ውስጥ እንዲቀመጥ አይፈቀድለትም ነበር…›› ሲለኝ ገርሞኝ አፌን ከፍቼ ነበር የማዳምጠው። በሐሳብ የተሸነፈው ወይ ይሰደዳል ወይ ይወገራል ማለቱ ነው። እኛ አገር ደግሞ ተገልብጦ በሐሳብ የተሸነፈ ኃይል ጦርነት ቀስቅሶ ደም ለማፍሰስ ይራወጣል፡፡ ድንቅ ይላል!

አንዴ ይኼን ‘ፖዝ’ አድርጉና ቅኔ ቤት እንሂድ። እንዲህ የምንወዳትና የምንኮራባት አገራችን የቅኔ አድባር ናት። ቅኔ የብዙኃን፣ ቅቤ የጥቂቶች መሆኑንም ልብ በሉ። በቅኔ ቤት ደግሞ ሰላ ሰላ ያለ ሒስና ትችት እንኳን ሥጋ ለባሽ አማልዕክቱም አይቀርላቸውም። የስም አወጣጥና አወራረስ ላይ ካልሆነ በእኔ አስተያየት በተለየ አብዮታዊ የመናገርና የማሰብ ባህል፣ ከአቴና በፊት እዚህ እኛ አገር ቅኔ ቤቶች ነበረ ባይ ነኝ። ደላላ ብሆንም የተቻለኝን ያህል ታሪክ አጣራለሁ። አንዳንዶቻችን ለምን እንደሆነ አላውቅም በደረቁ ያለ ዜማ ‘የኋላው ከሌለ የለም የፊቱ’ ሲባል ቀዝቃዛ ነን። ሁልጊዜ ቁም ነገር በሆይ ሆይታ ተሞልቶ እንዴት ይዘለቃል? ታሪካዊት አገር ቅብጥርስ ምንትስ እያልን ገና ለገና በፖለቲከኞች አፍ ‘ሐሳብ ለሐሳብ መደማመጥ ለምን ተሳነን…’ ብለን ብስክስክ ስንል ግራ ይገባኛል። ወይ ባህር አልተሻገርን ወይ ታሪክ አላሻገርን መላው ጠፍቶ ቁጭ ብለናል፡፡ አንዳንዴ እኮ እንደ ብሉይ ዘመን ሰዎች አሻጋሪ ከላይ ካልታዘዘልን በስተቀር እንደተፈጠርን ያለን ሰዎች በዝተናል፡፡ ቁጥር ብቻ!

‹‹መጠላለፍ ሆኗል የእኔና አንቺ ነገር፣ ወተት በተገፋ አሬራና ነገር›› ያለው ገበሬ መቼም የቻለውን ችሎ ነው። ውድ ባለቤቴ ማንጠግቦሽ በቀደም ዕለት፣ ‹‹ሥራ ላይ ቀዝቀዝ ብለህ ወሬ አብዝተሃል…›› አለችኝ። ልክ መርጬ የማወራ ይመስል። አይገርማችሁም? እና ይህችም ቁም ነገር ሆና ተኮራረፍን። ከፍትፍቷ ፊቷ እያልኩ ደጅ እውላለሁ። ሥራው ቀዝቅዟል። መስከረም ሊገባ ሲጣደፍ የጦርነት ወሬ ሲነሳ ሁሉም ነገር ቀዝቅዟል። ካፌውና ወሬው ብቻ ደርቶ ያጋጥመኛል። ስለሰላም፣ ፍትሕ፣ ነፃነት፣ እኩልነትና አብሮ መኖር ጠያቂው ብዛት ሪፖርት ሳዳምጥ ተቀምጬ እቀራለሁ። የአገራችን ሰው ደግሞ እንደምታውቁት ባይጻፍለትም አንድ አባባል አምጥቷል። ‘ሰው በምግብ ብቻ አይኖርም፣ በወሬም ጭምር እንጂ’ ማን ነበር ‘ከኩንታል ወሬ አንዲት ግራም ተግባር ትከብዳለች’ ያለው? ነገሩን ማለቴ ነው። የሆነስ ሆነና ወሬ ላይ ተጥደን ስለበጋ ስንዴው ልማትና ስለታላቁ ግድባችን እመርታዊ ዕድገት የምንተነትነው በምን መረጃ ነው ብትሉኝ መልሴ ምንም ነው፡፡ በቃ ምንም!

ይህን ለራሴ ነግሬው ለብቻዬ ፈገግ ስል መገናኛ አካበቢ ኮረብታው ላይ ዘመናዊ ቪላ ቤት የማጋዛው ደንበኛዬ ደወለ። የምንገናኝበትን ሥፍራ ወስነን ስልኩ ተዘጋ። ይኼ ደንበኛዬ የአቮካዶ እርሻ አለው። አዘውትሮ፣ ‹‹አገሬን በአቮካዶ ምርት ራሷን የቻለች በማድረግ የውጭ ምንዛሪ አስገኛለሁ…›› ሲል ምድረ ወሬኛ ሰምቶ ይስቃል። በጎ ራዕይና ሕልም እንደ ቅዠት በሚታይበት አገር አዳሜ ሳቁን ሲጨርስ በተለመደው ሐሜት ይለበልበዋል። እንዲህ ዓይነት ሰዎች ከመቼውም ጊዜ በላይ ቁጥራቸው መጨመሩ የሚያሳስባቸው አዛውንቱ ባሻዬ ጆሯቸው ውስጥ ጥጥ ወትፈው፣ ሕመማቸውን ማዳመጥ መርጠው ተቀምጠዋል። የባሻዬ ፅናት ራሴን እንድፈትሽ ያደርገኝና ያሳፍረኛል። አንዳንዱ እኮ መብቱን፣ ሰላሙን፣ ልማቱን ቀርቶ የገዛ ሕመሙን በተመለከተ በአግባቡ ማዳመጥ ተስኖታል። አያዋጣም ተው ሲባሉ የሚብስባቸው፣ ያላሰቡትን ጀምረው ሰው ያላሰበውን የሚያሳስቡ፣ ለያዥ ለገናዥ ያስቸገሩና መጥፊያቸውን ብቻ ሲያስሱ የሚኖሩትን በበኩሌ ለመቁጠር ታክቶኛል። አንዱ በቀደም ዕለት ከባለ ሱቅ ጋር ይጨቃጨቃል፡፡ ምን ሆነው ይሆን ብዬ ጠጋ ብዬ ሳዳምጥ፣ ሰውዬው ባለሱቁን የሚጠይቀው ወያኔ የሚያሰራጨውን የዩቲዩብ ዜና በስልኩ ከፍቶ እንዲያሳየው ነው፡፡ ነገሩ አስገርሞኝ፣ ‹‹ምን የሚሉት ጥያቄ ይሆን…›› እያልኩ ሰውዬው ላይ ሳፈጥበት፣ ‹‹የመረጃ ጥማት ነው…›› እያለ ከአጠገባችን ተፈትልኮ ሄደ፡፡ ጎበዝ ይህንን ገልጃጃ ምን ይሉታል!    

በሉ እንሰነባበት። ደንበኛዬን ያንን ኮረብታ ላይ ያለ የመገናኛ ቪላ ካጋዛሁት በኋላ በሚገባ ጋብዞኝ ተለያየን። ያው ዘንድሮ ሰው ሲጋብዝም ሆነ ሲጋበዝ አዩኝ አላዩኝ እየተባለ ሆኗል። እናም ደንበኛዬና እኔም የምንጫወተው ስለዚሁ ጉዳይ ነበር። ‹‹ጉድ እኮ ነው አንበርብር። ጭራሽ ስለምንሰማው ሙዚቃ፣ ስለምናየው ፊልም፣ ስለምንለብሰው ልብስ ቀለም፣ ውኃ ስለምንጠጣበት ብርጭቆ ቅርፅ ሊነግሩን የሚፈልጉ መጥተውልሃል። ወሬ እየፈተሉ፣ ወሬ እያያዳወሩ፣ ወሬ እየሸመኑ ሲለብሱ ውርደታቸውን ክብር አድርጎ የሚያሳያቸው መስታወታቸው እንዲሰበር ብቻ ነው ምኞቴ…›› ሲለኝ እንደ መተከዝ አልኩ። ለካ የእኛ ችግራችን ለራሳችን መመልከቻ ብለን ከሠራነው መስታወታችን ነው ማለት ብፈልግም፣ ራሴን መታዘብ ስጀምር ግን የሠራት መስታወት ሳይሆን እኔው የራሴ ችግር ፈጣሪ መሆኔ ተከሰተልኝ። ‹‹ጥያቄው መስታወቴ ማንን ነው የሚያሳየኝ? መልሱ ደግሞ እኔ የሠራሁትን ከንቱ ፍጡር አልኩ፡፡ እንደ ማኅበረሰብ ጣታችንን ሌላ ላይ ከመቀሰራችን በፊት ራሳችንን እንመልከት ማለት መለመድ አለበት፡፡ ሰላምን ገፍተን ለምን ጦርነት እንፈልጋለን፣ ከዚያ ለምን ይሆን መልካም ነገሮችን ትተን ክፉ ነገሮች ላይ የምናተኩረው፣ ከሰላማዊ መረጃዎች ይልቅ ለምን የተሳሳቱ የግጭት ወሬዎች ጆሮአችንን ያስቀስሩናል፣ ወዘተ ብንል መልሱ ቀላል ነው፡፡ ከእውነታው እየሸሸን ምክንያት ፍለጋ ውስጥ እንደበቃለን…›› የሚለኝ ደግሞ ምሁሩ የባሻዬ ልጅ ነው፡፡ ሰበበኞች በዝተናል ማለት ነው፡፡ መልካም ሰንበት!

Latest Posts

- Advertisement -

ወቅታዊ ፅሑፎች

ትኩስ ዜናዎች ለማግኘት