ቴአትር ለሰላም ፌስቲቫል ሊካሄድ መሆኑን የኢትዮጵያ ቴአትር ባለሙያዎች ማኅበር አስታወቀ፡፡ ለሦስተኛ ጊዜ የሚካሄደው የቴአትር ፌስቲቫል ጳጉሜን 2 እና 3 ቀን 2014 ዓ.ም. ‹‹ቴአትር ለሰላም›› በሚል መሪ ቃል በአዲስ አበባ ቴአትርና ባህል አዳራሽ እንደሚካሄድም ማኅበሩ ገልጿል፡፡
ፌስቲቫሉ በተለይም በድኅረ ግጭትና ጦርነት ወቅት ማኅበረሰብን በማስተሳሰርና በማቀራረብ ስለሰላም የሚሰበክበት፣ የወቅቱን የኢትዮጵያ ሁኔታ በማሰብ ሰላምና ተስፋ ርዕሰ ጉዳይ እንደሚሆንበት ማኅበሩ አስታውቋል፡፡
በፌስቲቫሉ ጦርነት ማኅበራዊ መራራቅን፣ ምጣኔ ሀብታዊ፣ አካላዊና ሞራላዊ ቀውስን እንዲሁም የታሪክ ጠባሳን ለተከታዩ ትውልድ ላይ ሚያስከትል መሆኑን፣ የሰው ልጅ ሕይወት በገፍ የሚያልፍበት ኢሰብዓዊ ድርጊት እንደሆነ የሚያንፀባርቁ ሁለት ቴአትሮች ለሕዝብ ዕይታ እንደሚያቀርቡ ተነግሯል፡፡
የሰላም አስፈላጊነትን ጽንሰ ሐሳብና ጭብጥ በቴአትሮቹ ውስጥ እንዴት እንደቀረቡ የሚተነትን ጥናታዊ ጽሑፎች በባለሙያዎች እንደሚቀርቡና ቴአትሩን ከጽሑፍ እስከ መድረክ ያበቁ ባለሙያዎች ከተመልካቾች ጋር በቀጥታ የሚወያዩበት መድረክ መዘጋጀቱንም ማኅበሩ ጠቁሟል፡፡
የተመረጡት ሁለት ቴአትሮች ለሁለት ቀናት በነፃ ለተመልካች እንደሚታዩ፣ ከፌስቲቫሉ በተከታይነት በግጭት ቀጣናዎች የሚገኙ ወጣቶች በቴአትር የግጭት አፈታት ሳይንሳዊ ጥበብ የሚሠለጥኑበት፣ ለችግሮቻቸውና ለሰላም መንገድ ከራሳቸው ባህል፣ ልማድና ትውፊት በመነሳት አገርና ትውልድ የማስቀጠል ሙያዊ ኃላፊነታቸውን የሚወጡበት እንቅስቃሴ እንደሚኖርም ተነግሯል፡፡
የፌስቲቫሉ ዓለማ ቴአትር ለሰው ልጆች አብሮነትና ሰላማዊ ኑሮ መስፈን ያለውን ሚና በተግባር ማሳየት ማኅበራዊ ኃላፊነቱን መወጣት ሲሆን፣ የኪነ ጥበብ ባለሙያዎች፣ የፌደሬሽን ምክር ቤት አፈ ጉባዔ፣ የባህልና ስፖርት ሚኒስትር ደኤታና ሌሎች መንግሥታዊና መንግሥታዊ ያልሆኑ ተቋማት ተወካዮች እንዲሁም ስለ ሰላም የሚሠሩ ተቋማትና ግለሰቦች ይታደሙታል ተብሎ ይጠበቃል፡፡