ከነሐሴ 26 ቀን ጀምሮ የተማሪዎች የትምህርት ግብዓት በቅኛሽ ዋጋ የሚሸጥበት ኤግዚቢሽንና ባዛር በጊዮግ ሆቴል ቅጥር ግቢ እንደሚካሄድ የሬዲዮና የቴሌቪዥን ማስታወቂያዎች ሲነገሩ ሰንብተዋል፡፡ ይህንንም ተከትሎ ወላጆች ቅናሽ ዋጋ እናገኛለን ብለው ኤግዚቢሽኑ በተከፈተበት ዕለት በሥፍራው ተገኝተዋል፡፡ ሪፖርተር በቦታው ተገኝቶ እንደታዘበው፣ በሥፍራው በዕለቱ ከነበሩ 20 ያህል ድንኳኖች ከአምስት ያልዘለሉት ብቻ የተማሪዎች ቁሳቁስ የያዙ ሲሆን፣ ዋጋውም ከገበያ ዋጋ ይበልጥ እንደሆነ እንጂ የቀነሰ አልነበረም፡፡ የመግቢያ 100 ብር ከፍለው የገቡ ሸማቾች በሥፍራው በማስታወቂያ የተነገረውን ያህል ባለማግኘታቸው ሲያማርሩ እንደነበርም ታዝበናል፡፡ ኤግዚቢሽኑ በተከፈተበት ነሐሴ 26 ቀን 2014 ዓ.ም. ራዲካል ደብተር በደርዘን 900 ብር፣ ሲነርላይን በደርዘን 650 ብር እንዲሁም በአገር ውስጥ የተመረተ ደብተር 500 እና 600 መቶ ብር በደርዘን እየተሸጠ ነው፡፡ የተማሪ ቦርሳ ከ650 ብር (ለጀማሪ) እስከ 950 ብር እንደሚሸጡ፣ የተማሪ ምሳ ዕቃ ደግሞ ይህንንም ያህል እንዳልነበረ ለመታዘብ ችለናል፡፡ በሥፍራው የነበሩ ወላጆችም በሁኔታው ሲበሳጩ አይተናል፡፡
- ፎቶ በመስፍን ሰሎሞን