Tuesday, March 28, 2023
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

ዳሽን ባንክ የሥራ ፈጠራ ብድር አቅርቦቱን በማስፋት ከጋምቤላ ክልል ጋር ስምምነት ፈጸመ

- ማስታወቂያ -

ተዛማጅ ፅሁፎች

ዳሸን ባንክ በክልል መንግሥታት ዋስትና ለአነስተኛና ጥቃቅን ተቋማት የብድር አገልግሎት ለማቅረብ የጀመረውን እንቅስቃሴ በመቀጠል ለጋምቤላ ክልል ለሚገኙ ጥቃቅንና አነስተኛ የንግድ ተቋማት ተበዳሪዎች የሚውልና አነስተኛ ወለድ የሚከፈልበት የ25 ሚሊዮን ብር ብድር ለማቅረብ ስምምነት ተፈራረመ፡፡

ባንኩ በጋምቤላ ክልል የንግድ ሥራዎችን ለማስፋፋትና ማኅበረሰብ ተኮር ፕሮጀክቶችን ለመደገፍ ያስችላል ተባለውን የብድር በክልል መንግሥት ዋስትና ለማቅረብ የተስማማ ሲሆን፣ የብድር አቅርቦቱ በክልል በሚገኙ በማክሮ ፋይናንስ ተቋማት በኩል በአነስተኛ ወለድ የሚያቀርብ መሆኑ ታውቋል፡፡ 

ባንኩ ነሐሴ 27 ቀን 2014 ዓ.ም. ከክልሉ መንግሥት ጋር ባደረገው ስምምነት መሠረት ለብድር የሚውለው 25 ሚሊዮን ብር በዋናነት በግብርና፣ በቤቶች ልማትና ለሌሎች አዋጭ ቢዝነሶች ለሚሰማሩና ተበዳሪዎች በአነስተኛ ወለድ የሚሰጥ መሆኑን ከባንኩ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል፡፡ 

በዚህ ስምምነት ዙሪያ ያነጋገርናቸው የዳሸን ባንክ ቺፍ ስትራቴጂና ኢኖቬሽን ኦፊሰር አቶ ሙሌጌታ አለባቸው እንደገለጹት፣ ‹‹ዝቅተኛ የኅብረተሰብ ክፍሎችን ከመድረስ አንፃር ባንኩ እየተጠቀማቸው ካሉ ስትራቴጂዎች ውስጥ አንዱ በክልል መንግሥታት ዋስትና በማክሮ ፋይናንስ ተቋማት ብድር ማቅረብ ነው፤››፡፡ ከክልል መንግሥታት ጋር ለመሥራት በተያዘው ዕቅድ መሠረት ከታች ያሉ የኅብረተሰብ ክፍሎችን የፋይናንስ ተደራሽነት ለማስፋት ጭምር ታስቦ እየተተገበረ መሆኑንም ጠቅሰዋል፡፡ 

በባንኩና በክልሉ መንግሥት መካከል የተደረገውን ስምምነት የጋምቤላ ክልል ፕሬዚዳንት ጽሕፈት ቤትና የካቢኔ ጉዳዮች ኃላፊ ፒተር ሐውቦል የፈረሙ ሲሆን፣ ዳሽን ባንክን በመወከል ደግሞ የባንኩ ቺፍ ስትራቴጂና ኢኖቬሽን ኦፊሰር አቶ ሙሉጌታ አለባቸው ፈርመዋል፡፡  

ይህ የብድር አቅርቦት በባንኩ በኩል መደበኛው የብድር አገልግሎት ለማግኘት ያልቻሉ አነስተኛ ብድር ፈላጊዎችን የሚደግፍ እንደሆነም ተገልጿል፡፡ በተለይም በመደበኛው የባንክ ብድር አገልግሎት ለመጠቀም የሚፈልገውን የብድር ዋስትና ማቅረብ ለማይችሉ ወገኖች እንዲህ ያለው የብድር አቅርቦት ብዙ ጠቀሜታ ይኖረዋል ተብሏል፡፡ ከክልል መንግሥታት ጋር የሚደረስ መሰል ስምምነት አማካይነት ክልሎች የማክሮ ፋይናንስ ተቋማትን በመምረጥ ብድር እንዲቀርብላቸው ለማድረግ ያስችላቸዋል፡፡ ዳሽን ባንክ የሚያቀርበው እንዲህ ያለው ብድር ከሌሎች የብድር ዓይነቶች በተለየ አነስተኛ ወለድ የሚታሰብበት በመሆኑ ተበዳሪዎች በአነስተኛ ወለድ ቢዝነሳቸውን እንዲያንቀሳቅሱ ዕድል የሚሰጥ መሆኑን ከተሰጠው ማብራሪያ መገንዘብ ተችሏል፡፡ 

ይህ አሠራር ተበዳሪዎች ከዳሸን ባንክ ጋር በቀጣይ እንዲሠሩ ዕድል የሚሰጥ መሆኑም ተጠቅሷል፡፡ እንደ አቶ ሙሌጌታ ገለጻ፣ እንዲህ ያለው አሠራር በሌሎች ክልሎችም የሚቀጥል ሲሆን፣ ባንኩ ተመሳሳይ ስምምነቶችን በማስፋፋት የአነስተኛ ተበዳሪዎችን ቁጥር የሚያሳድግ ይሆናል፡፡     

ዳሸን ባንክ በክልል መንግሥታት ዋስትና በማክሮ ፋይናንስ ተቋማት በኩል ለአነስተኛ ተበዳሪዎች የሚውለውን የብድር አቅርቦት ከዚህ ቀደም በተመሳሳይ ከሶማሌ ክልል መንግሥት ጋር ተፈራርሟል፡፡ ከሶማሌ ክልል ጋር አድርጎት በነበረው ስምምነት ከወለድ ነፃና ትርፍ የማከፍልበት ለሥራ ዕድል ፈጣራ የሚውል 50 ሚሊዮን ብር መመደቡን አስታውቆ እንደነበር አይዘነጋም፡፡ እንዲህ ካለው ስምምነት ጎን ለጎን ባንኩ  ማኅበራዊ ኃላፊነትን ለመወጣት ድጋፍ እያደረገ ስለመሆኑም ከባንኩ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል፡፡ 

   

 

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች