Tuesday, March 28, 2023

በአርጆ ዲዴሳ ስኳር ፋብሪካ ላይ ታጣቂዎች ጥቃት መፈጸማቸው ተገለጸ

- Advertisement -spot_img

በብዛት የተነበቡ

የገንዘብ ሚኒስቴር ለግል ባለሀብቶች በጨረታ ለመሸጥ የፍላጎት መግለጫ ካወጣባቸው ስምንት የስኳር ፋብሪካዎች ውስጥ አንዱ በሆነው አርጆ ዲዴሳ፣ በታጣቂዎች ጥቃት እንደተፈጸመበት ተገለጸ፡፡

ታጣቂዎቹ ማክሰኞ ነሐሴ 24 ቀን 2014 ዓ.ም. ባደረሱት ጥቃት የፋብሪካውን ተሽከርካሪዎች እንዳቃጠሉና ጥቃቱን ከፈጸሙ በኋላ ከአካባቢው መውጣታቸውን፣ የኢትዮጵያ ስኳር ኢንዱስትሪ ግሩፕ አስታውቋል፡፡ የግሩፑ የሕዝብ ግንኙነትና ተሳትፎ ክፍል ዋና ኃላፊ አቶ ረታ ዘለቀ፣ በተሽከርካሪዎች ላይ የደረሰውን ትክክለኛ ጉዳት ለማጣራት ጥናት እየተደረገ መሆኑን ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡

‹‹እስካሁን ፋብሪካው ላይ የደረሰ ጉዳት ስለመኖሩ የደረሰ መረጃ የለም›› ያሉት አቶ ረታ፣ አንድ ሠራተኛ ላይ ከደረሰ ድብደባ በስተቀር በሰው ላይ የደረሰ ጉዳት አለመኖሩን ተናግረዋል፡፡ በግቢው ውስጥ የሸንኮራ ማሳ ማሽነሪዎች፣ ትራክተሮችና የፋብሪካው ተሽከርካሪዎች መኖራቸውን ጠቅሰው፣ ‹‹በየትኞቹ ላይ ምን ያህል ጉዳት ደርሷል የሚለው እየተጣራ ነው፤›› ብለዋል፡፡

እንደ ዋና ኃላፊው ገለጻ፣ በፋብሪካው ላይ የደረሰው ጥቃት በሰሜን ኢትዮጵያ በድጋሚ ካገረሸው ጦርነት ጋር የሚያያዝ ሲሆን፣ ታጣቂዎቹ በጦርነቱ ምክንያት አካባቢው ላይ የተፈጠረውን ክፍተት ተጠቅመዋል፡፡

‹‹ኦነግ ሸኔ ተብሎ በዚያ ደረጃ የሚጠቀስ አይደለም፣ ግርግር ተጠቅመው ታጣቂዎች ሊገቡ ይችላሉ፣ ወለጋ አካባቢ ስለሆነ ግን እንደዚያ [ኦነግ] ተብሎ ነው የሚታወቀው፤›› በማለት አስረድተዋል፡፡

በክረምት ወራት ላይ ሁሉም የስኳር ፋብሪካዎች የስኳር ምርት አቁመው ሙሉ ማሽነሪ ጥገና ላይ እንደሚሰማሩ የገለጹ አቶ ረታ፣ ጥቃቱ ሲደርስ የፋብሪካው ሠራተኞች በማሽነሪ ጥገና ላይ እንደነበሩ ገልጸዋል፡፡ ፋበሪካውን ወደ የሚያስተዳድረው የስኳር ኢንዱስትሪ ግሩፕ ሪፖርት የደረሰው ረዕቡ ነሐሴ 25 ቀን 2014 ዓ.ም. መሆኑን ጠቅሰው፣ ጥቃቱ የደረሰበትን ሰዓት ለመናገር እንደሚቸገሩ ተናግረዋል፡፡

ታጣቂዎቹ ጥቃቱን ካደረሱ በኋላ ለምን ያህል ጊዜ በፋብሪካው ቅጥር ጊቢ ውስጥ እንደቆዩ ያልተገለጸ ሲሆን፣ የፋብሪካው ሠራተኞች ግን ወደ ፋብሪካው ተመልሰው የጥገና ሥራውን እያከናወኑ መሆናቸውን ኃላፊው አስታውቀዋል፡፡

አርጆ ዲዴሳ 16 ሺሕ ሔክታር የእርሻ መሬት የያዘ ሲሆን፣ በኦሮሚያ ክልል ምሥራቅ ወለጋ ቡኖ፣ በደሌና የጅማ ዞኖች መካከል የዲዴሳ ወንዝን ተከትሎ በዲዴሳ ሸለቆ ውስጥ የሚገኝ ነው፡፡ ከአዲስ አበባ በ395 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ ይገኛል፡፡

ፋብሪካው በ2001 ዓ.ም. አልሀበሽ በተባለ የፓኪስታን የግል ኩባንያ የተቋቋመ ሲሆን፣ ኩባንያው ከሦስት ዓመት በኋላ የግንባታ ሥራው ሳይጠናቀቅ ለቀድሞው የስኳር ኮርፖሬሽን ተሸጧል፡፡

በ2007 ዓ.ም. ሥራ የጀመረው አርጆ ዲዴሳ፣ በዓመት 100 ሺሕ ቶን ስኳርና 39 ሺሕ ሞላሰስ የማምረት አቅም አለው፡፡ ፋብሪካው ካለው ለእርሻ የሚሆን 16 ሺሕ ሔክታር መሬት ውስጥ አሁን የሸንኮራ አገዳ እያመረተ ያለው 3‚700 ሔክታር በሚሆነው መሬት ላይ ነው፡፡

እስከ ሐምሌ 30 ቀን 2014 ዓ.ም. ባለው መረጃ፣ ፋብሪካው 954 ቋሚና 14 ጊዜያዊ ሠራተኞች አሉት፡፡ በፋበሪካው ቅጥር ውስጥ 124 መኖሪያ ቤቶች አለ፡፡

የገንዘብ ሚኒስቴር ከሁለት ሳምንት በፊት ነሐሴ 13 ቀን 2014 ዓ.ም. አርጆ ዲዴሳን ጨምሮ በስኳር ኢንዱስትሪ ግሩፕ ሥር ያሉ ስምንት ፋብሪካዎችን ለመሸጥ መወሰኑን ገልጾ፣ ባለሀብቶች የፍላጎት መግለጫ (Expression of Interest) እንዲያስገቡ ዓለም አቀፍ ጥሪ አቅርቧል፡፡

ኦሞ ኩራዝ አንድ፣ ኦሞ ኩራዝ ሁለት፣ ኦሞ ኩራዝ ሦስት፣ ኦሞ ኩራዝ አምስት፣ ከሰም፣ ጣና በለስና ተንዳሆ ጨረታ የወጣባቸው ቀሪዎቹ የስኳር ፋብሪካዎች ናቸው፡፡

በኦሮሚያ ክልል የሚገኙት አርጆ ዲዴሳና ለጨረታ ያልቀረበው ፊንጫአ ስኳር ፋብሪካ፣ በአካባቢው በሚንቀሳቀሰው “ኦነግ ሸኔ” ምክንያት የፀጥታ ሥጋት ያለባቸው አካባቢዎች ናቸው፡፡ በሆሮ ጉዱሩ ወለጋ ዞን ዓባይ ጮመን ወረዳ ውስጥ የሚገኘው ፊንጫአ የካቲት ወር 2014 ዓ.ም. በአካባቢው ላይ በተፈጠረ የፀጥታ ሥጋት ምክንያት ሥራ አቁሞ እንደነበር መገለጹ ይታወሳል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ትኩስ ጽሑፎች

ተዛማጅ ጽሑፎች

- Advertisement -
- Advertisement -