Tuesday, March 28, 2023
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

ደመወዝን ጨምሮ ክፍያቸውን በቴሌ ብር ያደረጉ ተቋማት ከ2.2 ቢሊዮን ብር ክፍያ ፈጽመዋል ተባለ

- ማስታወቂያ -

ተዛማጅ ፅሁፎች

ከ23 ሚሊዮን በላይ ደንበኞች እየተገለገሉበት ነው በተባለው የቴሌ ብር የሞባይል አገልግሎት፣ 30 የሚደርሱ ተቋማት ደመወዝን ጨምሮ ሌሎች ከ2.27 ቢሊዮን ብር የበለጠ ትላልቅ ክፍያዎችን መፈጸማቸው ተገለጸ፡፡

በቴሌ ብር ከሲም ካርድ፣ ከድምፅ፣ የመልዕክትና ዳታ አገልግሎቶች በተጨማሪ፣ የፋይናንስ አገልግሎቶች (ገንዘብ ማስገባት፣ ጥሬ ገንዘብ ወደ ኤሌክትሮኒክ ክፍያ መቀየር፣ የሃዋላ ዝውውር፣ የአየር ሰዓትና የአገልግሎት ክፍያዎች መፈጸም) መጀመሩ የሚታወስ ሲሆን፣ ከዚህ ባሻገር ድርጅቶች ትላልቅ ክፍያዎቻቸውን (በልክ ፔይመንት) እየፈጸሙበት እንደሚገኙ ኢትዮ ቴሌኮም አስታውቋል፡፡

በሞባይል የገንዘብ ዝውውር 1.1 ሚሊዮን ዶላር የሚደርስ የሃዋላ ገንዘብ እንደተዘዋወረና የሞባይል ገንዘብ ዝውውር፣ ደመወዝ፣ አበልና ሌሎች ትላልቅ ክፍያዎች መከፈል ከተጀመረበት ጊዜ አንስቶ 30 የሚሆኑ ተቋማት 2.27 ቢሊዮን ብር የሚደርስ ክፍያዎችን መፈጸማቸው ተጠቅሷል፡፡ ከዚህ ባሻገር ኢትዩ ቴሌኮምም 17 ሺሕ ለሚደርሱት ሠራተኞቹ አስፈላጊውን ክፍያ ራሱ ባበጀው አማራጭ እየከፈለ እንደሚገኝ ተገልጿል፡፡

ዓለም አቀፍ የሞባይል ሃዋላ ዝውውርን ጨምሮ የአነስተኛ ብድርና ቁጠባ አገልግሎት እየቀረበበት በሚገኘው የቴሌ ብር አገልግሎት 59 የሚሆኑ የጤና፣ የትራንስፖርት፣ አገልግሎት ሰጪ መንግሥታዊና መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች ከኢትዮ ቴሌኮም ጋር ስምምነት አድርገዋል ተብሏል፡፡

በቀጣይም የንግድና ቀጣናዊ ትስስር፣ የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ፣ የገቢዎች ሚኒስቴርና ሌሎች የክልልና የከተማ አስተዳደር መሥሪያ ቤቶች ላይ የሚደረጉ የጥሬ ገንዘብ ክፍያዎችን በቴሌ ብር እንዲከፈሉ ሥራዎች እየተሠሩ መሆኑን በኢትዮ ቴሌኮም የሞባይል መኒ ዲፓርትመንት ኃላፊው አቶ ብሩክ አድሃና ተናግረዋል፡፡

ቴሌ ብር በቅርቡ ካስተዋወቃቸው አገልግሎቶች አንዱ በሆነው ‹‹መዳረሻ›› የሚል ስያሜ ባለው አማራጭ ተቋማት ለሠራተኞቻቸው ደመወዝ መክፈል የሚችሉ ሲሆን፣  ይህን ያደረጉ ተቋማት ሠራተኞች የደመወዛቸውን 30 በመቶ ብድር የሚያገኙበት ሁኔታ ስለመመቻቸቱ ተገልጿል፡፡

በሌላ በኩል ኢትዮ ቴሌኮም ከሰነዶች ማረጋገጫና ምዝገባ አገልግሎት ጋር የአገልግሎት ክፍያዎችን በቴሌብር ለመፈጸም የሚያስችል ስምምነት ነሐሴ 26 ቀን 2014 ዓ.ም. ተፈራርሟል።

የሰነዶች ማረጋገጫና ምዝገባ አገልግሎት እስካሁን ይሰጥ የነበረውን የጥሬ ገንዘብ አገልግሎት በቴሌ ብር አማካይነት በማድረግ ደንበኛው ሰነዶችን በድረገፅ በመሙላት አገልግሎቱን የሚያገኝበት አዲስ አገልግሎት ስለመሆኑ ተመላክቷል፡፡ ይፋ በተደረገው አዲስ አገልግሎት  ተገልጋዮች ኤጀንሲው የሚሰጣቸውን 27 አገልግሎቶች ክፍያ በቴሌብር መፈጸም የሚያስችል ነው ተብሏል።

የሰነዶች ማረጋገጫና ምዝገባ አገልግሎት በዚህ ወቅት 15 ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤቶች፣ 27 ልዩ ልዩ አገልግሎቶች እንዲሁም ከሰባት ሺሕ በላይ ደንበኞች በቀን የሚያስተናግድ ሲሆን፣ በቀን በአማካይ ከ6.5 ሚሊዮን ብር በላይ የአገልግሎት ክፍያ እንደሚፈጸም ታውቋል፡፡

ተገልጋዮች በተቋሙ አገልግሎት ካገኙ በኋላ በሚላክላቸው ወይም በሚሰጣቸው የክፍያ ማዘዣ ቁጥር በመጠቀም የመኪና ሽያጭ ውል፣ የስጦታ፣ የውክልና፣ የብድር፣ የማኅበር ምሥረታና ቃለ ጉባዔ የመሳሰሉ የአገልግሎት ክፍያዎችን በቀላሉ በቴሌብር መተግበሪያ ወይም በአጭር ቁጥር የመልዕክት አገልግሎት መፈጸም ይችላሉ ተብሏል፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች