Tuesday, March 28, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ዜናመንግሥት ለዳያስፖራው ማኅበረሰብ የድጋፍ ጥሪ ቀረበ

መንግሥት ለዳያስፖራው ማኅበረሰብ የድጋፍ ጥሪ ቀረበ

ቀን:

ከአንድ ሳምንት በፊት ከሕወሓት ኃይሎች ጋር ሦስተኛ ዙር ጦርነት ውስጥ የገባው መንግሥት፣ ለሰብዓዊ ድጋፍና ለአገር ልማት የሚሆን ከውጭ የሚገኙ ወገኖች የገንዘብ ድጋፍ እንዲያደርጉ ጥሪ አቀረበ፡፡

በገንዘብ ሚኒስቴር በኩል ሐሙስ ነሐሴ 26 ቀን 2014 ዓ.ም. ማምሻውን ባወጣው መግለጫ፣ በውጭ አገሮች የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን አገሪቱ ከገባችበት ጦርነት ጋር ተያይዞ የገንዘብ ድጋፍ እንዲያደርጉ በመጠየቅ፣ ሦስት የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የተከፈቱ ዩዩሮ፣ ዶላርና ፓውንድ ሒሳቦችን አካውንቶችን አስታውቋል፡፡

ሚኒስቴሩ ዓርብ ነሐሴ 27 ቀን 2014 ዓ.ም. ባወጣው ተመሳሳይ መግለጫ ተመሳሳይ የባንክ ሒሳቦችን ይፋ በማድረግ፣ በውጭ የሚገኙ ወገኖች ድጋፍ እንዲያደርጉ ሲል ጥሪ አቅርቧል፡፡ በዚህኛው መግለጫ ግን የልማት ሥራዎች እንዳይቆሙ፣ የመልሶ ግንባታ ሥራዎች እንዲፋጠኑና ሰብዓዊ ድጋፉ እንዲዳረስ ነው ድጋፉ እንዲደረግለት የጠየቀው፡፡

‹‹ኢትዮጵያ የወታደሮች ላብ፣ ደምና አጥንት ያፀናት ታላቅ አገር ናት›› በሚል ርዕስ የወጣው ይህ መግለጫ፣ በውጭ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን አገራቸውን በመገናኛ ብዙኃን በመቅረብ ከሐሰተኛ መረጃ መካላከላቸውን፣ ባስፈለገም ጊዜ ሰላማዊ ሠልፎች መውጣታቸውንና በፊትም ገንዘብ መለገሳቸውን ያስታወሳል፡፡

በአሁኑ ጊዜም የኢትዮጵያ የፈተና ጉዞና ድል ወሳኝ ምዕራፍ ላይ እንዳለም በማስታወስና የመከላከያ ሠራዊት አባላትም ጦርነቱን እየመከቱ እንዳሉ በመግለጽ፣ ለተጨማሪ የገንዘብ ድጋፉ የዳያስፖራ አባላትን ጠይቋል፡፡ እንደ መግለጫው ይህ ዘመቻ ለአገሪቱ የሚሰነብትና ለረዥም ጊዜ ፀንቶ የሚቆይ ሰላም የሚያስገኝም እንደሆነ ጠቁሟል፡፡

የኢኮኖሚ ባለሙያው አቶ ዋስይሁ በላይ ገለጻም፣ መንግሥታቶች እንዲህ ዓይነት አስቸጋሪ ሁኔታዎች ሲገጥሟቸው አቅም ማሰባሰብ የተለመዱ ድርጊቶች ናቸው፡፡ አንደኛው የፋይናንስ ምንጭ ከሆነው ከበጀት (ወይም ከክምችት) ቀንሶ የአገር ጦርነት መምራት ሥራ ላይ ማዋል፣ ካልቻለ ወይም ከሌለው፣ ሁለተኛው አማራጭ ሕዝብ ወደ የማስተባር ሥራ ላይ መንግሥታቶች እንደሚሄዱ ነው፡፡ ከዚህ በፊትም በአገሪቱ ላይ በተደረጉት ጦርነቶች የጉልበት ሥራን ጨምሮ ሕዝብን በማስተባበር የተካሄዱ አቅም የማሰባሰብ ሥራዎች የዚህ አካል ናቸው ሲሉ ያስረዳሉ፡፡

‹‹ጦርነት ትልቅ የፋይናንስ አቅም ስለሚጠይቅ ተዘጋጀም አልተዘጋጀም በመንግሥት አቅም ብቻ የሚሆን አይደለም፤›› በማለት ባለሙያው ይናገራሉ፡፡

ባለፈው ዓርብ ነሐሴ 27 ቀን 2014 ዓ.ም. የመከላከያ ሚኒስትሩ አብርሃም በላይ (ዶ/ር) በሰጡት መግለጫ፣ መንግሥት ያለምንም ቅድመ ሁኔታ በማንኛውም አጀንዳ ላይ ለመወያየት ዝግጁነቱን እየገለጸ ባለበት ጊዜ፣ የሕወሓት ኃይሎች ጦርነቱን እንዳስጀመሩት አሳውቀዋል፡፡

ይህ ድንገተኛ የውይይት ሐሳቦች እየተሰሙ ባለቡት ጊዜ የተቀሰቀሰው ጦርነት፣ መንግሥት ከዚህ በፊት የወደሙትን መልሶ የመገንባት ውጥን ላይ ባለበት ሰዓት ነው፡፡ ይህ መልሶ የመገንባት ውጥን ከሰብዓዊ ድጋፉ ጋር ተደምሮ ከፍተኛ ወጪ በሚያስፈልገው ጊዜ ጦርነቱ መቀስቀሱን ተናግረዋል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድን (ዶ/ር) ጨምሮ በርካታ የመንግሥት ኃላፊዎች ከዚህ በፊት ሲናገሩ እንደተሰማው፣ ከሕወሓት ኃይሎች ጋር በተደረጉት ጦርነቶች፣ የመንግሥት ወጪ በጣም እንደጨመረ ነው፡፡ መንግሥት በዚህ ዓመት የመደበው የ786.6 ቢሊዮን ብር አጠቃላይ የአገሪቱ በጀት ውስጥ በ84 ቢሊዮን ብር በጀትም ጦርነቱ እንደማይቀጥልና መንግሥት ካቀዳቸው ውጥኖች ሌላ ወጪ እንደማይኖርበት ታሳቢ በማድረግ ነው፡፡

የክልል ድጎማዎችን ሳይጨምር በዚህ ዓመት ከፀደቀው የፌደራል የመደበኛና የካፒታል ወጪ በጀት 563.2 ቢሊዮን ብር (14.9 በመቶ) የመከላከያ በጀት ሁለተኛውና ከፍተኛው ነው፡፡ አንደኛው በ125.9 ቢሊዮን ብር (23.3 በመቶ) የዕዳ ክፍያ ነው፡፡ ለፍትህና ደኅንነት የተመደበው በጀት 17 ቢሊዮን ብር ወይም የመደበኛና የካፒታል ወጪን ሦስት በመቶ የሚሆነውን ነው፡፡ ለአደጋ መከላከል ደግሞ 13 ቢሊዮን ብር ነበር የተመደበለት፡፡

እንደ ኢኮኖሚ ባለሙያ አቶ ዋስይሁን ገለጻ፣ ይህ መንግሥት ቀድሞ መድቦት የነበረው የፍትሕና ደኅንነቱ የ17 ቢሊዮን ብርና የአደጋ መከላከሉ 13 ቢሊዮን ብር አገሪቱ ውስጥ ቀድሞውኑ እንደ ኦሮሚያ ክልልና ቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል እየተፈጠሩ ካሉት ትግሮች አንፃር፣ ለትልቅ አቅም አያዘጋጅም፡፡ ለመከላከያም ጭምር እየተመደበ ያለው ዓመታዊ በጀት እንዲህ ዓይነት ጦርነቶች ሲከሰቱ በቂ ሊሆን እንደማይችል ነው ባለሙያው የገለጹት፡፡

በተጠናቀቀው የበጀት ዓመት አጋማሽ ላይ መንግሥት አስቀድሞ መድቦት ከነበረው የ561 ቢሊዮን ብር ዓመታዊ በጀት በተጨማሪ 122 ቢሊዮን ብር ተጨማሪ በጀት አፅድቆ እንደነበር የሚታወስ ነው፡፡ ተካሂዶ በነበረው ጦርነት ምክንያትም መከላከያን ለማጠናከር ከተጨማሪው የ122 ቢሊዮን ብር ተጨማሪ በጀት ውስጥ በአብዛኛው (90 ቢሊዮን ብር) የሚሆነው ለመከላከያ ነበር የተለቀቀው፡፡

ይህ ጦርነት የሚቀጥል ከሆነ የበጀት ዓመቱ ሲጀምር በጀቱ ሲፀድቅ የተፈጠረውን የ309 ቢሊዮን ብር በጀት ጉድለት እንደሚያባብሰው ተፈርቷል፡፡ ባለፈው ዓመት አጋማሽ ላይ ተጨምሮ የነበረው የ122 ቢሊዮን ብር ተጨማሪ በጀት በጊዜው ተፈጠሮ የነበረውን የ144 ቢሊዮን ብር የበጀት ጉድለት አባብሶት እንደነበር ዕሙን ነው፡፡

የጦርነቱ አስከፊነትና ከገንዘብ ጋር ያለውን ቁርኝት የኢኮኖሚ ባለሙያው አቶ ዋስይሁን ሲገልጹ፣ በአሁኑ ጊዜ የውጭ ምንዛሪ አስፈላጊነት እጅግ በጣም እንደሚያድግም ነው፡፡ የመሣሪያ ግዥ፣ የነዳጅ ወጪ፣ ስንዴና ሌሎች ለሰብዓዊ ዕርዳታ የሚወጡ ወጪዎችና የመድኃኒት ዓይነት ወጪዎችን ጨምሮ ለበርካታ ነገሮች የውጭ ምንዛሪን ጦርነቱ እጅጉን እንደሚጎዳ ገልጸዋል፡፡

ለዚህም መንግሥት በውጭ የሚኖሩ ወገኖችን መጠየቁ ሌላ አማራጭ ስለማይኖረውና ብዙ አቅም ስላለቸውም እንደሚሆን ባለሙያው ተናግረዋል፡፡ እንደ ህንድ፣ ፓኪስታንና ናይጄሪያን ጨምሮ በርካታ ሌሎች አገሮችም በውጭ በሚኖሩ ዜጎቻቸው እጅጉን እንደሚጠቀሙ ተናግረዋል፡፡

‹‹በሌላ ዓለም ያሉ የአንድ አገር ዜጎች ከአገር ውስጥ በተሻለ ከፍተኛ የውጭ ምንዛሪና የፋይናንስ አቅም ይኖራቸዋል፤›› ሲሉ አክለዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ለፋይናንስ ዘርፉ ብቃት ያለው የሰው ኃይል የማፍራት የቤት ሥራን የማቃለል ጅማሮ

የአገሪቱ የፋይናንስ ዘርፍ እያደገ ለመሆኑ ከሚቀርቡ ማስረጃዎች ውስጥ  የግል...

የምድር ባቡርን የሚያነቃቃው የመንግሥት ውሳኔ

በኢትዮጵያ ወደብ አልባነት ላይ የተደመረውን የሎጀስቲክስ ችግር ለመፍታት ግዙፍ...

የፓርላማ አባላት ስለሰላም ስምምነቱ አፈጻጸም ግልጽ መረጃ የለንም አሉ

‹‹ሕወሓትን ለፍረጃ አብቅተውት የነበሩ ጉዳዮች በአብዛኛው መልክ ይዘዋል›› ሬድዋን...