Saturday, March 25, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ስፖርትየፌዴሬሽኑን ጠቅላላ ጉባዔ ውሳኔ ውድቅ ያደረገው አስመራጭ ኮሚቴ ምርጫውን ከመታገድ ታደገው

የፌዴሬሽኑን ጠቅላላ ጉባዔ ውሳኔ ውድቅ ያደረገው አስመራጭ ኮሚቴ ምርጫውን ከመታገድ ታደገው

ቀን:

  • የአፋር ክልል ተወካይ ቅሬታቸውን አሰሙ

የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ባለፈው ቅዳሜና እሑድ በአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽን (ኢሲኤ) አዳራሽ ባካሄደው ጠቅላላ ጉባዔ፣ ፈዴሬሽኑን ለቀጣዩ አራት ዓመት የሚያገለግሉ የፕሬዚዳንትና የሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ምርጫ አከናውኗል፡፡ ጉባዔው አቶ ኢሳያስ ጅራ ለሁለተኛ ጊዜ ፌዴሬሽኑን በፕሬዚዳንትነት እንዲያስተዳድሩ በከፍተኛ ድምጽ መርጧቸዋል፡፡

ጉባዔው እሑድ ነሐሴ 22 ቀን 2014 ዓ.ም. በከፍተኛ ውጥረት ካከናወነው ፕሬዚዳንታዊው ምርጫ ቀጥሎ፣ ከአፋርና ከደቡብ ምዕራብ ክልሎች ውጪ፣ ዘጠኝ የሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባላት ምርጫ አከናውኗል፡፡

አቶ ዳኛቸው ንገሩ (ዶ/ር) ከአማራ ክልል ምክትል ፕሬዚዳንት፣ ለሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አቶ ሙራድ አብዲ ከሐረሪ፣ አቶ ሸረፋ ዴሌቾ ከደቡብ፣ አቶ አዲሱ ቃሚሶ ከሲዳማ፣ አቶ ኡጅሉ አዳይ ከጋምቤላ፣ አቶ አሰር ኢብራሒም ከቤንሻጉል፣ ወ/ሮ ሐቢባ ሲራጅ ከአዲስ አበባ፣ ወ/ሮ ፈይዛ ረሽድ ከሶማሌ እና አቶ ብዙአየሁ ጀምበሩ ከድሬዳዋ ናቸው፡፡

አስመራጭ ኮሚቴው በቅርቡ አዲስ ክልል ሆኖ የተዋቀረው ደቡብ ምዕራብና የአፋር ክልል በምርጫው ያልተወከሉበት ምክንያት ለምን እንደሆነ ማብራሪያ ሰጥቷል፡፡ አዲሱ የደቡብ ምዕራብ ክልል በቅርቡ የተቋቋመ በመሆኑና የአፋር ክልልን በሚመለከት ደግሞ ክልሉ ካቀረባቸው ዕጩ ተወዳዳሪዎች መካከል፣ አቶ አሊሚራህ መሐመድ ዓሊ ባለፉት ሦስት ምርጫዎች ላይ ተመርጠው ያገለገሉ በመሆናቸው፣ የፌዴሬሽኑ መተዳደሪያ ደንብ የሚከለክላቸው በመሆኑ እንደሆነ ተናግሯል፡፡

አስመራጭ ኮሚቴው ይህን ውሳኔ ከማሳለፉ አንድ ቀን ቀደም ብሎ ማለትም ነሐሴ 21 ቀን 2014 ዓ.ም. በነበረው የጠቅላላ ጉባዔው የመጀመሪያ ቀን ውሎ፣ አቶ አሊሚራህ መሐመድ ዓሊን የወከላቸው የአፋር ክልል ጉዳዩ በጠቅላላ ጉባዔ እንዲታይ አቅርቦት፣ ጉባዔውም የቀረበለትን ጉዳይ ተመልክቶ ቀደም ሲል በራሱ በጠቅላላ ጉባዔው አማካይነት ይሁንታ አግኝቶ በሥራ ላይ የቆየውን ሕግ ወደ ጎን በማለት፣ ግለሰቡ (አቶ አሊሚራህ) ለአራተኛ ጊዜ መወዳደር እንደሚችሉ በድምፅ ብልጫ ውሳኔ አሳልፎ ነበር፡፡

የጉባዔውን ውሳኔ ተከትሎ አስመራጭ ኮሚቴው፣ ጉዳዩ ለጉባዔው ከመቅረቡ በፊት፣ ለፊፋና ለካፍ ሰዎች በማቅረብ አስተያየት እንዲሰጡበት እንዳደረገ፣ የካፍና የፊፋ ታዛቢዎችም በጉዳዩ ምንም ዓይነት አስተያየት መስጠት እንደማይችሉ፣ ይሁንና ምርጫው በፌዴሬሽኑ መተዳደሪያ ደንብና አስመራጭ ኮሚቴው ባዘጋጀው የምርጫ ሥነ ምግባር ደንብ መሠረት ቢከናወን የሚል ምክረ ሐሳብ መስጠታቸው ለጉባዔው ቢያስረዳም፣ ነገር ግን በውሳኔ ያልተደሰቱት የአፋር ተወካዮች ተቃውሞ ማቅረባቸውን ተከትሎ፣ ጉባዔው ወደ አላስፈላጊ ክርክርና ውጥረት እንዲገባ የሆነበት አጋጣሚ ተፈጥሮ ነበር፡፡

የአንዳንድ ክልል ጉባዔተኞች ምርጫው ውክልናን መነሻ ያደረገ እንደመሆኑና ጉባዔውም ይህን ታሳቢ በማድረግ ‹‹የአፋር ክልል ተወካይ በምርጫው እንዲወዳደሩ ሊፈቀድላቸው ይገባል፣›› በሚል በአስመራጭ ኮሚቴው የተላለፈው ውሳኔ አግባብነት የጎደለው በመሆኑ ውሳኔውን እንዲያነሳ፣ የክልሉ ተወካዮችም በምርጫው መሳተፍ እንደሚገባቸው የሚያመላክቱ አስተያየቶችን ሲሰነዝሩ  ተደምጠዋል፡፡

የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ጠቅላላ ጉባዔ የአገሪቱ እግር ኳስ ትልቁ የሥልጣን አካል ሆኖ ሳለ፣ አስመራጭ ኮሚቴው የአፋር ክልል ተወካዮች በምርጫ እንዳይሳተፉ ሲወስን የሕግ መከራከሪያ መነሻው ምንድነው? የሚሉ አስተያየት ሰጪዎችም አልጠፉም፡፡

በመሆኑም የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ግንቦት 7 ቀን 2014 ዓ.ም. በኢሲኤ የስብሰባ አዳራሽ በጠራው አስቸኳይ ጠቅላላ ጉባዔ፣ ባለፈው እሑድ ሐምሌ 22 ቀን 2014 ዓ.ም. ለተከናወነው የፌዴሬሽኑ ፕሬዚዳንትና የሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ምርጫ አስመራጭ ኮሚቴና ይግባኝ ሰሚ ኮሚቴ መሰየሙ ይታወሳል፡፡

በጠቅላላ ጉባዔው ውክልና የተቀበለው አስመራጭ ኮሚቴውም፣ ኃላፊነት ከተቀበለበት ዕለት ጀምሮ የየክልሉ ዕጩ ተወዳዳሪዎች ለምርጫ ብቁ የሚሆኑበትን ሁኔታ መወሰን ይችል ዘንድ፣ በፌዴሬሽኑ መተዳደሪያ ደንብ አንቀጽ 40 በፊደል ‹‹ሀ›› ተራ ቁጥር ‹‹3›› መሠረት ‹‹ማንኛውም የሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባል በማንኛውም ጊዜ በተለያዩ ወይም በተከታታይ ከሦስት የምርጫ ዘመን በላይ ድጋሚ መመረጥ አይችልም፣›› በሚለውን መመርያ መሠረት፣ የአፋር ክልል ያቀረባቸው አቶ አሊሚራህ መሐመድ ዓሊ ከዕጩ ተወዳዳሪነት ውጪ እንዲሆኑ ማድሩጉን ይገልጻል፡፡

ይሁንና የአፋር ክልል የአስመራጭ ኮሚቴው ውሳኔ ትክክል እንዳልሆነ፣ አቶ አሊሚራህ መሐመድ ዓሊ ዕጩ ተወዳዳሪ ሆነው ለመቅረብ ሕጉ እንደማይከለክላቸው በመጥቀስ፣ የአፋር ክልል እግር ኳስ ፌዴሬሽን ጽሕፈት ቤት ለኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን የሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ዕጩ ተወዳዳሪ ሆነው እንዲቀርቡ ጠይቋል፡፡

ይግባኝ ሰሚ ኮሚቴውም ክልሉ ለኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ጽሕፈት ቤት ያቀረበው አቤቱታ፣ ጉዳዩ በይግባኝ ታይቶ አስመራጭ ኮሚቴው ያሳለፈው ውሳኔ ተገቢ እንደሆነ፣ የዕጩዎች የይግባኝ አቀራረብ ሥርዓት መሠረት የኮሚቴው ውሳኔ የመጨረሻ እንደሆነ፣ አቶ አሊሚራህ መሐመድ ዓሊ ያቀረቡት ይግባኝ፣ በዚህ ውሳኔ በተራ ቁጥር ‹‹5›› ትንታኔ መሠረት ይግባኛቸው ውድቅ መደረጉን አስመራጭ ኮሚቴው ይገልጻል፡፡

አስመራጭ ኮሚቴው ይህ የጉባዔው አካሄድና ውሳኔ ለኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን አደገኛ መሆኑን በመግለጽ፣ ይህ የፌዴሬሽኑ መተዳደሪያ ደንብና የአስመራጭ ኮሚቴው የምርጫ ሥነ ምግባር ደንብ፣ የእንግሊዝኛው ቅጂ በፊፋና በካፍ ታዛቢዎች እጅ እንደሚገኝ ጭምር በዕለቱ ለማስረዳት ሲሞክር ታይቷል፡፡

ይሁንና ከብዙ ክርክርና ውይይት በኋላ አስመራጭ ኮሚቴው እንደ ሥጋት ያቀረባቸው ሐሳቦች፣ በጉባዔው ተቀባይነት እንዲያገኝ ከተደረገ በኋላ፣ የደቡብ ምዕራብ ክልልና የአፋር ክልል ተወካዮች በቀጣይ ማሟያ ምርጫ ተደርጎ በፌዴሬሽኑ ውክልና  እንዲያገኙ በሚል ጉዳዩ ውሳኔ እንዲያገኝ ተደርጓል፡፡ ምርጫው የተደረገው ከዚህ ስምምነት በኋላ እንደነበር ልብ ይሏል፡፡

በዚህ ጉዳይ አስተያየታቸውን ለሪፖርተር የሰጡት የአፋር ክልል ተወካይ አቶ አሊሚራህ መሐመድ ዓሊ፣ ‹‹ከአንድ ዓመት በፊት በአርባ ምንጭ በተደረገው የፌዴሬሽኑ ጠቅላላ ጉባዔ ላይ አንድ ሰው ከሦስት ጊዜ በላይ ዕጩ ሆኖ መቅረብ አይችልም የሚለው ሕግ መውጣቱ ትክክል ነው፡፡ ይሁንና ሕጉ ተግባራዊ መደረግ የሚገባው ከጸደቀበት ቀን ጀምሮ ወደፊት እንጂ ያለፈውን የአገልግሎት ጊዜ ቆጥሮ አይደለም፤›› ብለዋል፡፡

አስመራጭ ኮሚቴው በአንጻሩ እንዲህ ዓይነቱን የውስጥ ጉዳይ በሚስጥር መያዝ ሲገባው ወይም በጋዜጣዊ መግለጫ ላይ ማሳወቅ ሲገባው የሚሉት ቅሬታ አቅራቢው፣ በደፈናው ያለ አግባብ ይፋ ማድረጉ ትክክል እንዳልሆነ፣ ከዚህም ባሻገር ክልሉ በእሳቸው ምትክ ሌላ ሰው መላክ የሚያስችለውን ዕድል እንዳሳጣው ጭምር ተናግረዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ኩባንያ አስተዳደር ለኢትዮጵያ ባንኮች ውጤታማነት

የጠቅላላ ጉባኤ፣ የጥቆማና ምርጫ ኮሚቴ፣ የተቆጣጣሪ ቦርድ፣ የዳይሬክተሮች ቦርድና...

[ክቡር ሚኒስትሩ ከሚያከብሯቸው አንድ የቀድሞ ጉምቱ ፖለቲከኛ ስልክ ተደውሎላቸው እያወሩ ነው]

አንዳንድ ነገሮች ቢያሳስቡኝ ነው ቀጠሮ ሳልይዝ ላወራህ የፈለኩት ክቡር...

የትግራይ ክልል የሽግግር አስተዳደር ምሥረታና የሰላም ስምምነቱ ሒደት

በትግራይ ክልል ጊዜያዊ የሽግግር መንግሥት ለመመሥረት ደፋ ቀና እየተባለ...