- የግምጃ ቤት ሰነድ ሽያጭ 163 በመቶ አድጓል
በ2013 በጀት ዓመት መጨረሻ አንድ ትሪሊዮን 176 ቢሊዮን ብር የነበረው የመንግሥት የአገር ውስጥ አጠቃላይ የብድር ክምችት፣ በተጠናቀቀው የበጀት ዓመት አንድ ትሪሊዮን 530 ቢሊዮን ብር መድረሱን የገንዘብ ሚኒስቴር ያወጣው ሪፖርት አመለከተ፡፡
ይህ መንግሥት በ2014 በጀት ዓመት የተበደረው 354 ቢሊዮን ብር የአገር ውስጥ ብድር፣ በአንድ ዓመት ውስጥ የተመዘገበ ከፍተኛው መጠን ሲሆን፣ በ2013 ዓ.ም. መንግሥት ከአገር ውስጥ ተበድሮ የነበረው 257 ቢሊዮን ብር በሁለተኛ ደረጃ ከፍተኛ ሆኖ ተመዝግቧል፡፡
በተያያዘም የመንግሥት የግምጃ ቤት ሰነድ ሽያጭ ዕዳ ክምችት በ2013 በጀት ዓመት መዳረሻ ላይ ተመዝግቦ ከነበረው 163 በመቶ በማደግ፣ 317.6 ቢሊዮን ብር ዋጋ ያለው የግምጃ ቤት ሰነድ ክምችት በተጠናቀው የ2014 በጀት ዓመት መመዝገቡ በሪፖርቱ ተጠቅሷል፡፡ ከአጠቃላይ የግምጃ ቤት ሰነድ ክምችት ውስጥ ለባንኮች የተሸጠላቸው 196 ቢሊዮን ብር ዋጋ ያለው መሆኑን፣ ባንክ ላልሆኑ ተቋማት ደግሞ 121 ቢሊዮን ብር ዋጋ ያለው ሰነድ መሸጡ ተመላክቷል፡፡
በዚህ ዓመት መንግሥት ከብሔራዊ ባንክ በቀጥታ የተበደረው 76 ቢሊዮን ብር መሆኑን፣ ይህም አጠቃላይ የመንግሥትን የብሔራዊ ባንክ ብድር ክምችት ወደ 159 ቢሊዮን ማድረሱ ታውቋል፡፡
የአገር ውስጥ ብድር መብዛት እንደ ምክንያት ሊሆን የሚችለው የውጭ ብድር አቅርቦት በበቂ ሁኔታ አለመኖርና የመንግሥት የውጭ ብድር ጫናን ለማቅለል እንደሚሆን፣ አንድ ስማቸው እንዳይጠቀስ የፈለጉ የኢኮኖሚ አማካሪ ባለሙያ ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡ እንደ ባለሙያው ገለጻ፣ የመንግሥት ፍላጎት እየተፈጠረ ባለው የበጀት እጥረት ምክንያት ከዚህም ሊበልጥ እንደሚችል ነው፡፡
እስከ ተጠናቀቀው በጀት ዓመት መጨረሻ ድረስ መንግሥት ያለበት አጠቃላይ የውጭ ብድር ዕዳ 27.9 ቢሊዮን ዶላር ሲሆን፣ ይህም በ2013 በጀት ዓመት መጠናቀቂያ ድረስ ከተመዘገበው የ29.5 ቢሊዮን ዶላር አኳያ ከ1.5 ቢሊዮን ዶላር በላይ ቅናሽ አሳይቷል፡፡
በበጀት ዓመቱ መጠናቀቂያ ላይ ከተመዘገበው አጠቃላይ የውጭ ዕዳ፣ የፌደራል መንግሥት ዕዳ 19 ቢሊዮን ዶላር ሲሆን፣ የመንግሥት የልማት ድርጅቶች ዕዳ ግን 8.8 ቢሊዮን ዶላር ነው፡፡ ከ2013 በጀት ዓመት አንፃር የታየው ቅናሽም በመንሥት የልማት ድርጅቶች ላይ ያለው የውጭ ብድር ሲሆን፣ የፌዴራል መንግሥት በግማሽ ቢሊዮን ዶላር አድጎ ነበር፡፡ የፌደራል መንግሥት ዕዳ አገሪቱ ካለባት የአጠቃላይ የውጭ ብድር ውስጥ 68 በመቶውን ድርሻ ይይዛል፡፡
እንደ ገንዘብ ሚኒስቴር ሪፖርት በተጠናቀቀው በጀት ዓመት 290 ሚሊዮን ዶላር መጠን ያላቸው ሦስት የብድር ውሎች ተፈጽመው የነበረ ሲሆን፣ ከእነዚህም አብዛኛው (279.5 ሚሊዮን ዶላር) ብድር የኢትዮጵያ አየር መንገድ የወሰደው ነው፡፡
በአገር ውስጥም ሆነ በውጭ መንግሥት ያለበት አጠቃላይ የብድር ክምችት 57.3 ቢሊዮን ዶላር ሆኖ የበጀት ዓመቱ ተጠናቋል፡፡ ይህም የአገሪቱን ጥቅል አገራዊ ምርት 50 በመቶ እንደሆነና የውጭ ብድር ብቻውን ደግሞ 24.5 በመቶ መድረሱ በሪፖርቱ ተጠቅሷል፡፡
እንደ ኢኮኖሚ ባለሙያው ገለጻ፣ መንግሥት የውጭ ብድሮችን ማቅለሉ ጥሩ ሆኖ ሳለ፣ ለአገር ውስጥ ብድሮች ግን፣ በተለይም ከብሔራዊ ባንክ የሚወስደው ብድር ላይ ከፍተኛ ችግር ሊያስከትል ይችላል፡፡ ‹‹ብሔራዊ ባንክ ከየትም አምጥቶ ሳይሆን አትሞ ነው ብሩን የሚሰጠው፡፡ ይህ ደግሞ የዋጋ ግሽበትን ያባብሳል፤›› ብለዋል፡፡
የኢኮኖሚ ባለሙያው በተያዘው በጀት ዓመት የተፈጠረውን የ309 ቢሊዮን ብር በጀት ጉድለት በማስታወስ፣ የበጀት ዓመቱ ሲጠናቀቅ የአገር ውስጥ ብድር በተለይ ከብሔራዊ ባንክ የሚወስደው ሊያድግ እንደሚችል አክለዋል፡፡