ሕፃናት ከለጋ ዕድሜያቸው ጀምሮ የመልካም ሥነ ምግባር ባለቤት ሆነው የመስጠት ልምድን በቀላሉ እንዲረዱ የሚያስችል ፌስቲቫል ሊካሄድ መሆኑን ‹‹ተያይዘን ኢትዮጵያ የበጎ አድራጎት ድርጅት›› አስታወቀ፡፡
ድርጅቱ ‹‹የሚሰጥ ዘር›› በሚል ስያሜ ያዘጋጀው ዓመታዊ ፌስቲቫልም ከነሐሴ 25 እስከ 29 ቀን 2014 ዓ.ም. ድረስ በአዳማ ከተማ የሚካሄድ ሲሆን፣ ሕፃናት ልጆች ለመልካም ሰብዕና ግንባታ ጠቃሚ ዕውቀትን እየተዝናኑ የሚቀስሙበት፣ ታዋቂ ከሆኑ የልጆች ፕሮራሞች ጋር የሚገናኙበት እንዲሁም የበጎ አድራጎት ተግባር የሚያከናወኑበት መሆኑን ተቋሙ በሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ አስታውቋል፡፡
የተያይዘን ኢትዮጵያ የበጎ አድራጎት ድርጅት ዋና ሥራ አስኪያጅ አቶ ምሥጋናው ታደሰ እንደገለጹት፣ ሕፃናት ልጆች በተሻለ የሰብዕና ማንነት እንዲታነፁና ያላቸውን ለሰው ልጅ ማካፈል እንዳለባቸው እንዲያውቁ ለማድረግ ተቋሙ ‹‹የሚሰጥ ዘር›› የሚል ፕሮጀክት ነድፎ ሲሠራ ቆይቷል፡፡
‹‹የሚሰጥ ዘር›› የተሰኘው ፕሮጀክት አዳማ ውስጥ በሚገኙ አምስት ትምህርት ቤቶች ተግባራዊ መደረጉን የገለጹት ዋና ሥራ አስኪያጁ፣ ፕሮጀክቱ ከተፀነሰበት ጊዜ ጀምሮ የሕፃናት ልጆችን የመስጠት መንፈስ የማንቃት ሥራ ሲሠራ እንደነበር አስረድተዋል፡፡
በአዳማ ለተከታታይ አምስት ቀናት በሚካሄደው ፌስቲቫል ላይ ሕፃናት ልጆች፣ ወላጆች፣ አርቲስቶችና ሌሎች ተጋባዥ እንግዶች የሚሳተፉ መሆኑንና ሕፃናት ልጆችም ደብተር፣ እስክሪብቶ፣ የጠበባቸውን ልብስ፣ ጫማና ሌሎች ግብዓቶችን ይዘው መጥተው በጎ ተግባር የሚፈጽሙበት እንደሆነ አክለዋል፡፡
‹‹የሚሰጥ ዘር›› ፕሮጀክት መዝጊያ የከተማ አቀፍ የልጆች፣ የወላጆችና የትምህርት አመራሮች የሚሳተፉበት ፌስቲቫል ላይ የሚሰበሰቡ የትምህርት ግብዓቶችና ሌሎች ስጦታዎች ለተቸገሩ ሕፃናት የሚውል መሆኑን ጠቁመዋል፡፡
በትምህርት ቤቶች ላይ ሲከናወን የነበረውን ፕሮጀክት ዕውን ለማድረግ የቀድሞ የትምህርት ሚኒስትር ጌታሁን መኩሪያ (ኢንጂነር) አስተዋጽኦ የጎላ መሆኑን አቶ ምሥጋናው ተናግረዋል፡፡
በአምስቱ ትምህርት ቤቶች ውስጥ ተግባራዊ ሲደረግ በነበረው ፕሮጀክት ተቋሙ የራሱን አሠራር በመዘርጋትና ሕፃናት ልጆች በሳምንት አንድ ጊዜ ስጦታ እንዲሰጣጡ በማድረግ የመስጠት ልምድን እንዲያካብቱ መደረጋቸውን ገልጸዋል፡፡
ሕፃናት ልጆች በሳምንት አንድ ጊዜ ስጦታ በሚሰጣጡበት ወቅት አንዱ ለአንዱ የሚሰጠው ስጦታ ብሔርን፣ ዘርንና ሃይማኖትን የሚያንፀባርቁ ስጦታዎችን እንዳይሰጣጡ ለማድረግ ወላጆችና መምህራን ሲከታተሉ እንደነበር ዋና ሥራ አስኪያጁ አብራርተዋል፡፡
ሕፃናት ልጆች የመስጠትን ሐሳብ በቀላሉ እንዲያውቁ በተተገበረው ፕሮጀክት የተማሪዎችን የትምህርት ጊዜ በማይሻማ መልኩ እንደነበር፣ ሆኖም በቀጣይ እንደ ሌሎች የትምህርት ክፍለ ጊዜዎች እንድ ክፍለ ጊዜ ኖሮት እንዲተገበር ተቋሙ ትምህርት ሚኒስቴርን የሚጠይቅ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
‹‹የሚሰጥ ዘር›› ፕሮጀክት መሬት ወርዶ ተግባራዊ እንዲሆን ትምህርት ሚኒስቴር በእሱ ሥር ባሉ ሙያተኞች ጥናት ማድረጉን የተናገሩት ዋና ሥራ አስኪያጁ፣ ጥናቱ ከተደረገ በኋላ ለኦሮሚያ ትምህርት ቢሮ ደብዳቤ በመላክ አዳማ ከተማ ላይ በሚገኙ አምስት ትምህርት ቤቶች ፕሮጀክቱ ዕውን መሆኑን አክለዋል፡፡
በቀጣይ በተለያዩ ክልሎች ላይ ለመሥራት ቅድመ ዝግጅት መደረጉን፣ በፌስቲቫሉ መጨረሻ ነሐሴ 29 ቀን 2014 ዓ.ም. ከ27 በላይ የሚሆኑ አርቲቶች፣ ሕፃናት ልጆች፣ ወላጆች፣ መምህራንና ሌሎች ሰዎች የሚሳተፉበት ሩጫ የሚካሄድ መሆኑን አስረድተዋል፡፡
‹‹የሚሰጥ ዘር›› ፕሮጀክት በተለያዩ ክልሎች ውስጥ ተግባራዊ ለማድረግና ሥራው ቀጣይነት እንዲኖረው ለማስቻል የትምህርት ሚኒስትሩን ብርሃኑ ነጋ (ፕሮፌሰር) በደብዳቤ መጠየቃቸውንና ምላሽ እየተጠባበቁ መሆኑን አብራርተዋል፡፡