Tuesday, March 28, 2023
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

ለሽያጭ የቀረቡት ስምንቱ ስኳር ፋብሪካዎች ከዕዳ ነፃ ሆነው ለግል ባለሀብቶች ይተላለፋሉ ተባለ

- ማስታወቂያ -

ተዛማጅ ፅሁፎች

የገንዘብ ሚኒስቴር ለሽያጭ ያቀረባቸው ሰምንት ግዙፍ የመንግሥት ፋብሪካዎች በመንግሥት ዋስትና ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክና ከውጭ መንግሥታት ተበድረው ያልመለሱት ከፍተኛ ዕዳ ቢኖርም፣ ከዕዳው ነፃ ሆነው በሚወጣው ዓለም አቀፍ ጨረታ ተወዳድረው ለሚያሸንፉ ባለሀብቶች እንደሚተላለፉ ተገለጸ። 

የገንዘብ ሚኒስቴር ነሐሴ 13 ቀን 2014 ዓ.ም. ባወጣው መግለጫ የግሉ ዘርፍ በኢኮኖሚው ውስጥ የሚያደርገውን ተሳትፎ ለማሳደግ መንግሥት የተለያዩ ማበረታቻዎችንና ማሻሻያዎችን እያደረገ መሆኑን ጠቅሷል። እየተደረጉ ከሚገኙት ጥረቶች መካከል አንዱ የግሉ ዘርፍ በስኳር ኢንዱስትሪው ውስጥ የሚያደርገውን ተሳትፎ መደገፍና ለዚህ የሚረዱ ማሻሻያዎች ማድረግ እንደሆነም አስታውቋል።

ከዚህ አንጻርም በመንግሥት ባለቤትነት ሥር የሚገኙ ስኳር ፋብሪካዎችን ለአገር ውስጥና ዓለም አቀፍ ባለሀብቶች እንዲተላለፉ በመንግሥት መወሰኑን ጠቅሶ፣ ፋብሪካዎቹን በጨረታ ለማስተላለፍ በሚወጣው ጨረታ ለመሳተፍ የሚሹ ባለሀብቶች የፍላጎት መግለጫ (Expression of Interest) እንዲያስገቡ ዓለም አቀፍ ጥሪ አውጥቷል።

በሽያጭ እንዲተላለፉ የተወሰነባቸው በመንግሥት ባለቤትነት ሥር የሚገኙት ስኳር ፋብሪካዎች ስምንት ሲሆኑ እነዚህም፣ ኦሞ ኩራዝ 1፣ ኦሞ ኩራዝ 2፣ ኦሞ ኩራዝ 3፣ ኦሞ ኩራዝ 5፣ አርጆ ደዴሳ፣ ከሰም፣ ጣና በለስና ተንዳሆ የስኳር ፋብሪካዎች ናቸው።

ገንዘብ ሚኒስቴር የፍላጎት መግለጫ ማስታወቂያውን ተከትሎ ባወጣው ዝርዝር መረጃ ደግሞ በአሁኑ ወቅት በመንግሥት ባለቤትን የሚተዳደሩ ስኳር ፋብሪካዎች ብዛት 12 እንደሆነና እነዚህም በድምሩ 450,000 ሜትሪክ ቶን ስኳር በዓመት እያመረቱ እንደሚገኙ አስታውቋል። 

እ.ኤ.አ. በ2021/2022 የኢትዮጵያ የስኳር ፍላጎት በነፍስ ወከፍ 11 ኪሎ ግራም ሲገመት በዚህም መሠረት አጠቃላይ የአገሪቱ ዓመታዊ አጠቃላይ የስኳር ፍጆታው 1.3 ሚሊዮን ቶን እንደሆነ አስታውቋል። ይህ የስኳስ ፍላጎት በነፍስ ወከፍ እስከ 2029/30 ድረስ በየዓመቹ አንድ በመቶ ያድጋል ተብሎ የሚጠበቅ ሲሆን፣ በዚህም መሠረት በትንሹ የኢትዮጵያ አጠቃላይ ዓመታዊ የስኳር ፍላጎት 1.7 ሚሊዮን ቶን እንደሚሆን አመልክቷል።

በአገሪቱ የሚገኙት ፋብሪካዎች የአገር ውስጥ ፍላጎትን እየሸፈኑ ባለመሆኑ የኢትዮጵያ መንግሥት የአገሪቱን ዓመታዊ የስኳር ፍላጎት ለማሟላት ከውጭ ግዥ እንደሚፈጽም ይገልጻል። 

ለአብነት ያህልም እ.ኤ.አ. በ2020 የአገር ውስጥ የስኳር ፍላጎትን ለማሟላት መንግሥት 153 ሚሊየን ዶላር ወጪ በማድረግ ከውጭ የስኳር ግዥ ፈጽሞ ለገበያ ማቅረቡን ገልጿል። እ.ኤ.አ. ሰኔ 2022 ዓመትም 100,000 ሜትሪክ ቶን የስኳር ግዥ እንደፈጸመም መረጃው ያመለክታል። ለመንግሥት የስኳር የሚሸምትባቸው ዋናዎቹ አገሮችም ህንድ፣ ብራዚል፣ የተባበሩት ዓረብ ኤምሬትስ፣ ብራዚልና ደቡብ አፍሪካ መሆናቸውን መረጃው ያመለክታል።

በመሆኑም የውጭ ኩባንያዎች በኢትዮጵያ የስኳር ኢንደስትሪ ውስጥ ቢገቡ ቢያንስ የኢትዮጵያን ዓመታዊ የስኳር ፍጆታ ጉድለት ማሟላት የሚችሉበት ገበያ የትም ሳይሄዱ በእጃቸው አንደሚያገኙ አስታውቋል።

ነገር ግን የኢትዮጵያ ጎረቤት በሆኑት የምሥራቅ አፍሪካ አገሮች እንዲሁም በአውሮፓ ምቹ ገበያዎች መኖራቸውንም አብዛኞቹም የኢትዮጵያን ስኳር የሚፈልጉ እንደሆነ ጠቁሟል። 

ለአብነት ያህልም እ.ኤ.አ. በ2021 የኬንያ፣ የሶማሊያ፣ የደቡብ ሱዳን፣ የሱዳን እና የጅቡቲ ገበያዎች 3.1 ሚሊዮን ቶን የስኳር ምረት አቅርቦት ጉድለት እንደነበረባቸው የገንዘብ ሚኒስቴር መረጃ ያመለክታል። 

በተጨማሪም የአውሮፓ ህብረት እና የባህረ ሰላጤው ሀገራት እንደ ቅደም ተከተላቸው 2.24 ሚሊዮን ቶንና 6.12 ሚሊዮን ቶን የምርት ጉድለት እንደነበረባቸው ጠቅሷል።

በመሆኑም የኢትዮጵያ መንግሥት ሊሸጣቸው ያሰባቸውን ስምንት ስኳር ፋብሪካዎች የሚገዙ የውጭም ሆነ የአገር ውስጥ የግል ባለህብቶች በዓመት 11.46 ሚሊዮን ቶን ስኳር ማቅረብ የሚችሉበት የተዘጋጀ ገበያ እንደሚጠብቃቸው አስተዋውቋል።

ለሽያጭ የቀረቡት ስምንቱ ስኳር ፋብሪካዎች ከዕዳ ነፃ ሆነው ለግል ባለሀብቶች ይተላለፋሉ ተባለ | Ethiopian Reporter | ሪፖርተር

በመሆኑም ፍላጎቱ ያላቸው ባለሀብቶች የኢትዮጵያ የስኳር ኢንተርፕራይዞችን በተናልም ሆነ በሽርክና መግዛት የሚችሉበት እንድል እንደተመቻቸ አስታውቋል።

ለሽያጭ የቀረቡት አባዛኞቹ ስኳር ፋብሪካዎች አዲስ የተገነቡ መሆናቸውን የሚጠቅሰው ይኸው መረጃ፣ ሁሉም ፋብሪካዎች በቂ ውኃና ምርጥ የአገዳ ልማት ሁኔታ ያላቸው መሆናቸውንም ጠቁሟል።

ፋብሪካዎች በጥቅሉ በመቶ ሺዎች ሄክታር የመሬት ይዞታ ያለቸው ሲሆን በጨረታ ተወዳድረው ፋብሪካዎቹ ባለቤት የሚሆኑ የግል ኩባንያዎች ለሚረከቡት የመሬት ይዞታ ለረዥም ዓመታት የሊዝ ኮንትራትና ክፍያ እንደሚፈጽሙም አስታውቋል።

ይሁን እንጂ ፋብሪካዎቹ ያለባቸው የአገር ውስጥም ሆነ የውጭ አገር ዕዳ ነፃ ሆኖ ለገዥዎች እንደሚተላለፉ የገንዘብ ሚኒስቴር መረጃ ይግልጻል። 

ይህ መረጃ ፋብሪካዎቹ ያለባቸውን የእዳ መጠን እንዲሁም እንዴት ከእዳ ነፃ ሆነው ሊተላለፉ እንደሚችሉ ባያመላክትም ፣ ሪፖርተር የተመለከተው ሌላ የመንግሥት ሰነድ የፋብሪካዎቹ እዳ የመንግሥት ልማት ድርጅቶችን ዕዳና ሀብት ለማስተዳደር ለተቋመው ኮርፖሬሽን (Liability and Asset Management Corporation) እንደሚተላለፍ ይጠቁማል።

መንግሥት በመጀመሪያ ይዞት የነበረው ዕቅድ በእጁ የሚገኙትን 13ቱንም ስኳር ፋብሪካዎች (በትግራይ ክልል የሚገኘውን ወልቃይት ስኳር ፋብሪካ ጨምሮ) ለመሸጥ የነበረ ሲሆን ይህንንም ወደ ተግባር ለመቀየር የሁሉም ፋብሪካዎች አጠቃላይ ሀብትና ንብረት በገለልተኛ የኦዲት ኩባንያ እንዲገመት አድርጓል።

ይህንን የሀብትና ንብረት ግመታ እንዲያከናውንም ቡከር ቴት የተባለ የእንግሊዝ ኩባንያ ተቀጥሮ የግመታ ሥራውን ከዓመት በፊት አጠናቆ ሪፖርቱንም ለመንግሥት እንዳቀረበ ሪፖርተር ያገኘው የሰነድ መረጃ ያመለክታል።

ኩባንያው ባካሄደው የግመታ ሥራ የ13ቱ ስኳር ፋብሪካዎች አጠቃላይ ሀብትና ንብረት እ.ኤ.አ. እስከ 2019 ድረስ 88 ቢሊዮን ብር እንደሆነ ተገምቷል። 

ይሁን አንጂ በተመሳሳይ ወቅት የነበረው የስኳር ፋብሪካዎቹ አጠቃላይ የሀገር ውስጥ ዕዳ ወለድን ሳይጨምር ብቻውን 81.6 ቢሊዮን ብር የነበረ ሲሆን፣ በዚሁ ተመሳሳይ ወቅት የፋብሪካዎቹ አጠቃላይ የውጭ ዕዳ መጠን ወለድን ሳይጨምር 2.1 ቢሊዮን ዶላር ነበር። 

በመሆኑም የ13ቱ ስኳር ፋብሪካዎች አጠቃላይ የሀገር ውስጥ እና የውጭ ዕዳ ወለድን ሳይጨምር ነገር ግን በአሁኑ ወቅት ባለው የውጭ ምንዛሬ ተመን ስሌት 190 ቢሊዮን ብር በላይ ይሆናል። ይሁን እንጂ ይህ ግመታ ከተከናወነ በኋላ መንግሥት ተጨማሪ ወጪዎችን በስኳር ፋብሪካዎች ላይ በማውጣት የምርት ማሻሻያ ሽራዎችን እንዲሁም የተመረጡ ፋብሪካዎችን የግንባታ ደረጃ የማሻሻል ጥረቶችን ያደረገ በመሆኑ የቀደመው የሀብት መጠን ላይ ለውጥ እንደሚያመጣ መረዳት ይቻላል።

ሪፖርተር ያነጋገራቸው እንድ ለጉዳዩ ቅርብ የሆኑ ከፍተኛ የመንግሥት ኃላፊ ‹‹መንግሥት እነዚህን ፋብሪካዎች ለመሸጥ የወሰነው ዕዳውን ይመልስልኛል ብሎ ሳይሆን ባሉበት ሁኔታ ተሽጠው የአገር ውስጥ የስኳር ምርት ፍላጎትን በማሟላት እንዲሁም በምሥራቅ አፍሪካና በአውሮፓ ያለውን ሰፊ ገበያ የመያዝ ዕድልን ታሳቢ በማድረግ ነው፤›› ገልጸዋል።

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች