Sunday, March 26, 2023

ጦርነቱ ወዴት እያመራ ነው?

- Advertisement -spot_img

በብዛት የተነበቡ

የአውሮፓ ኅብረትና የአሜሪካ ልዩ ልዑካን መቀሌ ደርሰው መመለሳቸው ሕወሓትና ፌዴራል መንግሥት በድርድር ጠረጴዛ ዙሪያ የመቀመጣቸውን ጉዳይ ወደ እርግጠኝነት ያቀረበው ይመስል ነበር፡፡ ከወር በፊት በድርድሩ ዙሪያ ይሰሙ በነበሩ መረጃዎች ድርድሩ ከቦታና ከቀኑ ውጪ ብዙ ጉዳዮች የተገባደዱ አስመስለው ነበር፡፡ ሆኖም በጥቂት ሳምንታት ነገሮች ተገለባበጡ፡፡ በአንዴ ከድርድሩ ይልቅ ጦርነቱ አይቀሬ መሆኑን የሚያመለክቱ መረጃዎች መሰማት ጀመሩ፡፡

የብሔራዊ የደኅንነት ምክር ቤት የቅርብ ጊዜ መግለጫ በተለይ የትግራይ ክልል የፀጥታ ሁኔታ፣ ‹‹ከፀጥታ ኃይሎች አቅም በታች ነው›› ማለቱ ጦርነቱ ዳግም የሚጀመርበትን ዕድል ያጠበበ ነበር፡፡ ባለፉት ሁለት ሳምንታት ግን ይህ ሁኔታ ፍፁም ሲቀየር ነው የታየው፡፡ መንግሥት ሕወሓት የተኩስ አቁም ስምምነቱን አፍርሶ ሦስተኛ ዙር ጦርነት መክፈቱን አስታወቀ፡፡ በሁለት ዓመታት ለሦስተኛ ዙር ያገረሸው ጦርነቱ አሁንም አድማሱን ሊያሠፉ እንደሚችል መረጃዎች ያመለክታሉ፡፡

‹‹ከፀጥታ ኃይሎች አቅም በላይ አይደለም›› የተባለው ሕወሓት ወደ አማራና አፋር ክልሎች መግባቱ የተነገረ ሲሆን፣ ሕዝባዊ ኃይሎች ወረራውን እንዲመክቱ ዳግም የክተት ጥሪ እየተላለፈላቸውም ነው፡፡

‹ሊጀመር ተቃርቧል› ሲባልለት የቆየው የሰላም ሐሳብ ብዙም አይነሳም፡፡ ከዚህ ይልቅ ውጊያው ያየለ እየመሰለ ነው፡፡ ይህ ቦታ ተለቀቀ፣ በዚያ በኩል ወራሪ ኃይል ተሸነፈ፣ ወዘተ የሚሉ የዓውደ ውጊያ ያልተጣሩ ወሬዎች በርክተዋል፡፡ ከዚህ ባስ ሲልም ውጊያው እየተካሄደባቸው ያሉ የሰሜን ወሎና የአፋር አካባቢ ነዋሪዎች ለዳግም መፈናቀልና እንግልት መዳረጋቸው ሲነገር ይሰማል፡፡

በዚህ መካከል ግን ዳግም ጦርነቱ መቋጫው ምን ይሆናል? የሚለው ብዙዎችን እያሳሰበ ነው የሚገኘው፡፡ ጦርነቱ ወዴት እያዘገመ ይገኛል ከሚለው ጎን ለጎን፣ ‹‹ለምን በዚህ ወቅትና ሁኔታ ተጀመረ?›› የሚለውም እያጠያየቀ ነው፡፡

ይህንን በተመለከተ ማብራሪያ የሚሰጡት የኢትዮጵያ ሕዝብ አብዮታዊ ፓርቲ (ኢሕአፓ) ተቀዳሚ ምክትል ሊቀመንበር መጋቢ ብሉይ አብርሃም ሃይማኖት፣ ሕወሓት ከዚህ ጦርነት የሚፈልጋቸው ነገሮች እንዳሉ ይናገራሉ፡፡ ‹‹ሕወሓት ጦርነቱን በዚህ ወቅት የከፈተው ቢችል እንዳለፈው እስከ ደብረ ብርሃን የተወሰኑ ቦታዎችን ይዞ የራሱን የአሸናፊነት ሥነ ልቦና ከፍ ለማድረግ፣ መንግሥት ላይ ጫና ለማሳደርና ድርድሩን በሚፈልገው መንገድ ለመጠምዘዝ ይፈልጋል፤›› ብለዋል፡፡

የሕወሓት ፍላጎት ግን በዚህ የተገደበ ብቻ አለመሆኑን ያከሉት መጋቢ ብሉይ አብረሃም፣ የሕወሓት ፍላጎት ከዚህም የሚሻገር መሆኑን ነው ያመለከቱት፡፡ ‹‹በዋናነት የወልቃይት አካባቢን በመውረር ከሱዳን ጋር የሚያገናኘውን ድንበር በማስከፈት፣ የውጭ ኃይሎችን በመጋበዝ ኢትዮጵያን በፈለገው መንገድ ለመዘወር ያለመ ነው፤›› ሲሉ ይገልጻሉ፡፡

የሕወሓት ቃል አቀባይ አቶ ጌታቸው ረዳ ከትናንት በስቲያ በሰጡት መግለጫ፣ የቡድናቸው ፍላጎት ምን እንደሆነ ሲገልጹ ተደምጠዋል፡፡ ‹‹አብዛኛው ኃይላችን ምዕራብ ትግራይ ነው የሠፈረው፡፡ በድንገት የተኩስ አቁሙ ፈርሶ ዕርምጃ ውስጥ እንገባለን ካልን ሌላ ፍላጎት የለንም፡፡ ቆቦ፣ ኮምቦልቻ ምናምን ምን ይሠራልናል? ባህር ዳር፣ ወዘተ የሚል ውስጥ መግባት አንፈልግም፡፡ ትግራይን ነፃ የማውጣት ሥራ ላይ ነን፡፡ ስለዚህ መሆን ካለበት በአብዛኛው ኃይላችን ምዕራብ ነው፡፡ ይህንን አጋጣሚ ተጠቅመው ሜካናይዝድ ዩኒት ያለው ሦስት ዕዝ አሠልፈው አጠቁ፡፡ ለሁለት ቀናት ተከላከልን፣ ፀረ ማጥቃት በሦስተኛው ቀን አደረግን፡፡ ከዚህ በላይ ዝርዝሩን አልገልጽም፤›› ሲሉ ስለወታደራዊው አሠላለፋቸው ማብራሪያ ሰጥተዋል፡፡

አንጋፋው ፖለቲከኛ አቶ ኤፍሬም ማዴቦ፣ ‹‹አሁን አሁን ጦርነቱ እየቀጠለ ያለው በሕወሓት ፍላጎት ነው የሚለውን ማመን ትቻለሁ፡፡ ሕወሓት የሦስተኛ ወገን ኃይሎችን ፍላጎት ለማስፈጸም ሲል ነው ጦርነቱን ዳግም የቀጠለው፤›› በማለት ነው የሚናገሩት፡፡   

ኢትዮጵያ የምትገኝበት ጂኦ ፖለቲካዊ አጣብቂኝና ያለፈችበት የገዘፈ ታሪክ ሁሉ ብዙ ጠላቶች በጋራ እንዲሠለፉባት ማድረጉን የጠቀሱት አቶ ኤፍሬም፣ ‹‹ሕወሓት የእነዚህ ጠላቶች መጋለቢያ ፈረስ እንጂ፣ በራሱ ፍላጎት አይደለም ጦርነቱን የቀጠለው፤›› ሲሉ አብራርተዋል፡፡  

ኢትዮጵያን በዓለም አቀፉ ፍርደ ገምድል የማዕቀብና የጣልቃ ገብነት ጦርነት ከተከፈተባቸው ከእነ ቻይናና ሩሲያ ጋር ያመሳሰሉት አቶ ኤፍሬም፣ ‹‹ኢትዮጵያ ለብዙ ሺሕ ዓመታት ጠብቃ ያቆየችውን ታሪክ፣ ትርክት፣ ነፃነት፣ መሬት፣ አገርና ሉዓላዊነትን ዛሬም አላስነካም ብላ መታገሏ ጠላት አብዝቶባታል፡፡ ሕወሓት በኢትዮጵያ ላይ ያሻቸውን ተፅዕኖ ለማሳረፍ ለሚፈልጉ ኃይሎች ተባባሪ ነበር፡፡፡ ለዚህ ነው ወደ ሥልጣን ለማምጣት የሚያግዙት፡፡ ከምዕራባውያን ኃይሎች በተጨማሪ የግብፆች ፍላጎትም አለ፡፡ የእስራኤሎች ፍላጎትና ሌሎችም የተሠለፉበት ብዙ ውስብስብ ቢሆኖች (Scenarios) ባሉበት ቀጣና ዕንብርት ላይ ነው ኢትዮጵያ የምትገኘው፤›› ሲሉም ሰፊ ማብራሪያ ሰጥተዋል፡፡ 

በህዳሴው ግድብ ግንባታ መዘዝ ብዙ የውጭ ጫና ኢትዮጵያ ሲያርፍባት መቆየቱን ያስታወሱት አቶ ኤፍሬም፣ ‹‹የኢሳያስ፣ የዓብይና የፎርማጆ በጋራ መቆም ቀጣናውን ያስተባብራል፡፡ የቀጣናው በጋራ መቆም ማለት ደግሞ ወደ አራትና አምስት ሺሕ ኪሎ ሜትር የባህር መስመርን መቆጣጠር ማለት ነው፤›› ሲሉ ያስረዳሉ፡፡ ቀጣናውን በመከፋፈልም ሆነ ለውጭ ኃይሎች ተፅዕኖ የተመቸ በማድረግ ብዙ ሚና ሲጫወት የቆየው ሕወሓት ዳግም ወደ ሥልጣን እንዲመለስ የሚፈልጉ ብዙ የውጭ ኃይሎች፣ ከዚህ ጦርነት ጀርባ መሠለፋቸውን ነው አቶ ኤፍሬም የገለጹት፡፡  

የሕወሓት ቃል አቀባይ አቶ ጌታቸው፣ በደቡብ ግንባር ጦርነቱን እንደማይፈልጉ ቢናገሩም፣ በቆቦና በአፋር መስመሮች የሕወሓት ኃይሎች ጥቃት መቀጠሉን የአካባቢው ምንጮች ይናገራሉ፡፡ የሕወሓት ኃይሎች ዳግም ወረራ ከእነዚህ የግንባር ቀጣናዎች አልፎ ያሉ አካባቢዎችን እያሠጋ መሆኑንም የተለያዩ መረጃዎች ያመለክታሉ፡፡ ባለፈው ሳምንት የመከላከያ ኃይል ከነበረበት ቦታ አንድ ኢንች ገፍቶ አለመግባቱን የጦር ኃይሎች ጠቅላይ ኤታ ማዦር ሹም ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ ጦርነቱ በጀመረ ማግሥት መናገራቸው አይዘነጋም፡፡ ሆኖም ጦርነቱ ቀናት ባስቆጠረ ቁጥር የመንግሥት ወገን ጦር በምዕራብ በኩል አልፎ ወደ ትግራይ መግባቱንና በሽራሮ በኩል ጥቃት መክፈቱን መረጃዎች እየጠቆሙ ነው፡፡ ይህን ደግሞ የሕወሓቱ ጌታቸው በመግለጫቸው አረጋግጠዋል፡፡

የሰሞኑን ጦርነት በሚመለከት በሁለቱም ተፋላሚ ወገኖች በመንግሥትም ሆነ በሕወሓት በኩል ተገደው የገቡበት እንጂ፣ ቀዳሚ ምርጫቸው የሰላም አማራጭ መሆኑን ደጋግመው ሲናገሩ ተደምጠዋል፡፡ አንደኛው ሌላውን አጠቃኝ ከሚለው ውንጀላ በዘለለ፣ እንደገና ወደ ጦርነቱ ለመግባት ምርጫ ያሳጣቸውን አስገዳጅ ምክንያት በግልጽ አልተነገረም፡፡

‹‹ጦርነቱን የከፈተው ሕወሓት ነው፤›› የሚሉት የኢሕአፓ ሊቀመንበር መጋቢ ብሉይ ግን፣ ይህ ዳግም ከመሠረታዊ የጦረኝነት ባህሪው እንደሚመነጭ ጠቁመዋል፡፡ ‹‹አንዳንዶች የተስፋ መቁረጥ መፍጨርጨር ቢሉትም እኔ ግን እንደዚያ አላየውም፡፡ ሕወሓት ዳግም ወረራውን የቀጠለው የራሱን ህልውናም ለመታደግ ሲል ነው፡፡ ከዚህ ቀደም በጦርነት ፍላጎቱን ማሳካት አልቻለም፡፡ ቅድመ ሁኔታዎች መደርደር በመምረጡ በሰላም ተደራድሮ ችግሩን መፍታትም አልቻለም፡፡ በዚህ የተነሳ እጁ ላይ የቀረው የትግራይ ሕዝብን ማሳመኛ ብቸኛ ዘዴ ጦርነቱን ዳግም መቀጠል ነው፤›› ሲሉ ሕወሓት ግጭቱን ለምን እንደመረጠ አስረድተዋል፡፡

‹‹ሕወሓት ውስጣዊ ጫናውን ለመቀነስ ጦርነቱን ቀጥሎታል፤›› የሚሉት መጋቢ ብሉይ፣ ‹‹ከተቻለም ወልቃይትና ሑመራን አስለቅቆ ከሱዳንና ከግብፅ ጋር ግንኙቱን ለማጠናከር ይህንን ጦርነት ይሻል፤›› ብለዋል፡፡

ሕወሓት በአሁኑ ወቅት ጦርነት ማወጅ የፈለገበትን ምክንያት ያብራሩት ፖለቲከኛው፣ ‹‹በብልፅግና ጥበብ የጎደለውና ደካማ አመራር የተነሳ የአገር አንድነት ላልቷል፡፡ የአገሪቱ ኢኮኖሚ ተዳክሟል፣ እንዲሁም ጥላቻና መቃቃር ሠፍኗል ብሎ ባመነበት ጊዜ ነው ጦርነቱን የከፈተው፤›› ብለዋል፡፡

አቶ ኤፍሬም በበኩላቸው፣ ‹‹ባለፉት አምስት የጦርነት ቀናት ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ተዘረፈ ካሉት የነዳጅ ጉዳይ ውጪ ሕወሓትን ወደ ሰላም እንዲመጣ ሲጠይቁ አልታዩም፡፡ በኢትዮጵያ መንግሥት ላይ በሚያደርጉት ልክ ወረራ እየፈጸመም ሕወሓትን ሲጫኑ አናይም፤›› በማለት ነው የውጭ ኃይሎች ግፊት ታክሎበት ሕወሓት ጦርነቱን መቀጠሉን ያሰመሩበት፡፡

ጦርነቱ ወዴት እያመራ ነው? | Ethiopian Reporter | ሪፖርተር

የሕወሓት መሠረታዊ ባህሪ ሁሉንም ነገር በጉልበት የመፍታት ፍላጎት መሆኑን የተናገሩት አቶ ኤፍሬም፣ ‹‹በአፍሪካ ትልቅ ጦር ያሠለፈውን የደርግ ኃይል አሸንፈናልና የሚችለን የለም፤›› በሚል ትዕቢት የተወጠሩ ናቸው ብለዋቸዋል፡፡ በሌላ በኩል ኢትዮጵያውያን በጋራ ተሠልፈው ራሳቸውን መከላከል እንዳይችሉ በዘርና በፖለቲካ ከፋፍለናቸዋል የሚል ድምዳሜ ሕወሓቶች እንዳላቸው የጠቀሱት አቶ ኤፍሬም፣ ‹‹ከሁሉ በላይ ግን በድርድርና በሰላም ችግራችንን መፍታት ተሸናፊ ያደርገናል ብለው ስለሚያምኑ ነው ጦርነቱን የገፉበት፤›› ብለዋል፡፡

ባለፉት ጥቂት ቀናት የሕወሓት ኃይሎች ‹‹ሰላም እንፈልጋለን›› የሚል ሐሳብ ሲያነሱ ተሰምተዋል፡፡ የኢትዮጵያ መንግሥትም በበኩሉ ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ሕወሓትን ከጦርነት መንገዱ እንዲመልሰው ሲጠይቅ ነበር፡፡ ይሁን እንጂ ይህ ብቻውን ሁለቱን ወገኖች ወደ ሰላም ጠረጴዛ እንዲመጡ መንገድ የሚጠርግ ነው ብለው የሚያምኑ ጥቂቶች ናቸው፡፡

ከመሃል አገር ፖለቲካ ከተገፋ ረዥም ጊዜ የሆነው የሕወሓት ኃይል፣ ‹‹ትግራይን ነፃ ለማውጣት›› ለሚለው ማሳመኛው ብቻ ሳይሆን በኢትዮጵያ ፖለቲካ ላይ አሁንም ቢሆን ጠንካራ ሚናና ተፅዕኖ አለኝ ብሎ ራሱን ለማሳየት ጦርነቱን ይፈልገዋል የሚሉ በርካቶች ናቸው፡፡

በሌላም በኩል ከውጭ ኃይሎች ጋር የተበጠሰውን ግንኙነቱን ዳግም ለመቀጠል፣ እንዲሁም ራሱን በማደርጀትና ቢቻል በውጭ ኃይሎች ድጋፍ ወደ አራት ኪሎ ሥልጣን ለመምጣት የጦርነት መንገዱን እንዲመርጥ እንደሚያደርገው የሚገምቱ ብዙ ናቸው፡፡

‹‹የእኛ ድርጅት ኢሕአፓ በአሲምባ በረሃ ገና በእንጭጩ የሕወሓትን ማንነት አውቆታል፡፡ ሕወሓት መካድ፣ መካካድና ጦርነትና አድብቶ በሴራ ማጥፋት ባህሉ የሆነ ድርጅት ነው፡፡ ዛሬ ሰላም እፈልጋለሁ ቢልም ጦርነትን መኖሪያው ያደረገ በመሆኑ በራሱ በትግራይ ሕዝብ ላለመበላት ሲል ጦርነቱን አይተውም፤›› ሲሉ መጋቢ ብሉይ አብረሃም ይናገራሉ፡፡ ይህ ኃይል የልማትና የዕድገት ሳይሆን የአገር ጠላት መሆኑን የጠቀሱት ፖለቲከኛው፣ መላው አገር ተረባርቦ ሊመክተው ይገባል ብለዋል፡፡

አቶ ኤፍሬም በበኩላቸው፣ ‹‹ሕወሓቶችን አሁንም እንደ የጡት አባቱ የሚመለከተታቸው ብሔርተኛና የፖለቲካ ኃይል በኢትዮጵያ መብዛቱ የልብ ልብ ሰጥቷቸዋል፤›› ይላሉ፡፡ የውጭ ዕርዳታ ይገኛል ብለው በማመን የአሁኑን ጦርነት መክፈታቸውን የጠቀሱት አቶ ኤፍሬም፣ ‹‹በአንድነት የሚዋጋ የኢትዮጵያ ኃይል አለ ብለው ቢገምቱ ኖሮ፣ ለሁለት ቀናት ውጊያ ግንባር አይቆሙም ነበር፤›› ብለዋል፡፡

‹‹የሰላም እጅ አንዴ ከተዘረጋ አይታጠፍም፡፡ ነገር ግን ሰላምን የምታስብ ከሆንክ ሁሌም ለጦርነት ተዘጋጅ፤›› የሚሉ መሠረታዊ መርሆዎች በኢትዮጵም እንደሚሠሩ ያመለከቱት አቶ ኤፍሬም፣ ሕወሐትን በአንድነት መመከትም ሆነ ለሰላም ዝግጁ መሆን የኢትዮጵያ ብቸኛ ምርጫዎች መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ትኩስ ጽሑፎች

ተዛማጅ ጽሑፎች

- Advertisement -
- Advertisement -