Tuesday, March 28, 2023
- Advertisment -
- Advertisment -

ለኢትዮጵያ የሚያዋጣው ሰላም ብቻ ነው!

የሰላም ዋጋው የሚታወቀው መልካው ተናግቶ ዕልቂትና ውድመት አገር ምድሩን ሲናኘው ነው፡፡ ኢትዮጵያ ከታሪኳ ክፍል አብዛኛውን ገጽ የሚሸፍነው ጦርነት ነው፡፡ ከጥንት እስካሁን ለኢትዮጵያውያን ሰላም ቅንጦት እስኪመስል ድረስ፣ ለበርካታ ዓመታት በጦርነት ውስጥ ማለፍ አዲስ ነገር ሆኖ አያውቅም፡፡ በዚህ ዘመን እንኳን ቀደም ያሉትን ትተን ሁለት ዓመታት ባልሞላ ጊዜ ውስጥ፣ ሦስተኛ ዙር ጦርነት ተቀስቅሶ ተጨማሪ ዕልቂትና ውድመት እየተደገሰ ነው፡፡ ለሰላም የሚደረገው የድርድር ሒደት ሳይጀመር ጦርነት በአቋራጭ ሲከሰት፣ የኢትዮጵያ ታሪካዊ ጠላቶች እሳቱን ለማራገብ አድፍጠው መዘጋጀታቸው የታወቀ ነው፡፡ በቀይ ባህር አካባቢ የጦር ሠፈራቸውን የመሠረቱ ኃያላንና የኢትዮጵያን መተራመስ የሚጠባበቁ ያደፈጡ ኃይሎች፣ ከጥቅማቸው አኳያ የአሁኑን ዙር ጦርነት እንደ ቴአትር ከመመልከት እንደማይቦዝኑ ማስተዋል ይገባል፡፡ ይህ አደገኛ አውዳሚ ጦርነት አድማሱን ሳያሰፋ በአጭሩ ካልተቀጨ፣ ከዚህ ቀደም ከደረሰው ዕልቂትና ውድመት የባሰ ሊያጋጥም ይችላል፡፡ በመሆኑም ኢትዮጵያ ከዚህ ጦርነት ውስጥ በፍጥነት የምትወጣባቸው መላዎች ይፈለጉ፡፡ ለኢትዮጵያ ከሰላም ውጪ ምንም የሚያዋጣ አማራጭ እንደሌለ ይታወቅ፡፡

በኢትዮጵያ ምድር ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ የጦርነት ምዕራፍ ተዘግቶ ሰላም እንዲሰፍን፣ ኢትዮጵያውያን በሙሉ ከዳር እስከ ዳር በአንድነት መንቀሳቀስ ይጠበቅባቸዋል፡፡ ሰላም በአንድ ወገን ፍላጎት ብቻ ስለማይሰፍን ከሰላማዊ መንገድ ያፈነገጡ መገደድ አለባቸው፡፡ በአንድ እጅ ጠመንጃ በሌላ እጅ ነጭ እርግብ ይዞ መንቀሳቀስ አይቻልም፡፡ በሰሜን ኢትዮጵያ የተቀሰቀሰው ጦርነት አድማሱን ሳያሰፋ ሰላም እንዲሰፍን ከተፈለገ፣ የሰላሙን መንገድ አልሻም ብሎ የኃይል መንገድ የመረጠው ተገዶ ጭምር ለድርድር መቀመጥ ይኖርበታል፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ ልዩነትን ማቀራረብ ወይም ቅራኔን ማርገብ የሚቻለው በክብ ጠረጴዛ ዙሪያ እንጂ፣ የምፈልገውን አስፈጽማለሁ በሚል ጀብደኝነት እንዳልሆነ መታመን አለበት፡፡ አሁንም በፌዴራል መንግሥትና በሕወሓት መካከል ይደረጋል ተብሎ የሚጠበቀው ድርድር እንዲካሄድ፣ የተጀመረው ጦርነት በፍጥነት መቆም ይኖርበታል፡፡ ከሰላማዊ ድርድር በማፈንገጥ ሕዝብን ለዕልቂት፣ አገርን ደግሞ ለውድመት የሚዳርግ አደገኛ ጦርነት ማካሄድ ተቀባይነት የለውም፡፡ አሁንም በተደጋጋሚ ማሳሰብ የሚያስፈልገው ከሰላማዊ ድርድር በላይ ምንም ነገር ጠቀሜታ እንደሌለው ነው፡፡ የኢትዮጵያ ሕዝብ ጦርነት የሰለቸው በመሆኑ ለሰላም ዕድሉ ይሰጥ፡፡

በአንድ አፍ ስለሰላም እየዘመሩ በሌላ አፍ ጦርነትን የሚደግፉ የፖለቲካ ተዋንያንም ሆኑ አክቲቪስቶች፣ ጦርነቱ ተባብሶ እንዲቀጥል የሚያደርጉ ፕሮፓጋንዳዎችን ከማሠራጨት ይቆጠቡ፡፡ በተጨማሪም ሐሰተኛ ወሬዎችን እየፈበረኩ በግራና በቀኝ የሚረጩ ራስ ወዳዶች አደብ ይግዙ፡፡ ሰላማዊ ዜጎችን ለዕልቂትና ለስደት የሚዳርገውን ጦርነት ከማስተጋባት ይልቅ፣ ለንፁኃን ተስፋ ይዞ የሚመጣውን ሰላም ይስበኩ፡፡ በተለይ ባህር ማዶ ሆነው የማይደርስባቸውን ጦርነት ምስኪኑ የኢትዮጵያ ሕዝብ ላይ የሚያውጁ ሰዎች፣ ድርጊታቸው ወደፊት በሕግም ሆነ በታሪክ የሚያስጠይቅ እንደሆነ ይገንዘቡ፡፡ ከሰላማዊ ድርድሩ በማፈንገጥ ጦርነቱን ያቀጣጠለው አካል ደጋፊዎችም ሆኑ ከበስተጀርባው የሚያጋግሉ በሙሉ፣ ከዚህ ጦርነት ትርፍ እናገኛለን ብለው አስበው ከሆነ ተስፋ ይቁረጡ፡፡ ይህ ጦርነት ለሰላም የነበረውን ተስፋ አጥፍቶ የበለጠ ሰቆቃ የሚያስከትል እንደሆነ ይወቁ፡፡ ኢትዮጵያውያን በሙሉ ተጠቃሚ መሆን የሚችሉት ከሰላም እንጂ ከጦርነት አይደለም፡፡ ጦርነት በሰሜን ኢትዮጵያ አካባቢዎች ያስገኘው ዕልቂት፣ ውድመት፣ ስደት፣ ረሃብና ተስፋ ቢስነትን ነው፡፡ አሁን የተጀመረው ጦርነት በፍጥነት ቆሞ የድርድሩ ሒደት እንዲቀጥል ርብርብ ይደረግ፡፡

ኢትዮጵያ ችግር ውስጥ በምትገባበት ጊዜ ሊታደጓት ከየጎራው የሚጠራሩ ልጆቿ፣ ጦርነቱን በጨዋነት አጠናቃ ወደ ሰላማዊ ምዕራፍ ማሸጋገር ይጠበቅባቸዋል፡፡ ይህ ሽግግር ስክነትና ብስለት ይፈልጋል፡፡ ከቂምና በቀል በመፅዳት ኢትዮጵያዊ ጨዋነትን በማሳየት፣ ዳግም በኢትዮጵያ ምድር አውዳሚው ጦርነት እንዳይከሰት ክፍተቶችን መድፈን ተገቢ ነው፡፡ በሕግና በሥርዓት የማይመራ ጦርነት ንፁኃንን በመግደል፣ በማፈናቀል፣ በመዝረፍ፣ በመድፈርና ለጆሮ የሚሰቀጥጡ ድርጊቶች እንደሚፈጸሙበት በአማራና በአፋር ክልሎች በሚገባ ታይቷል፡፡ በሰብዓዊ ፍጡራን ላይ ከተፈጸሙ ወንጀሎች ጀምሮ በዘር ማጥፋት የሚያስጠይቁ አደገኛ ድርጊቶች ተስተውለዋል፡፡ እነዚህ ለሕግና ለታሪክ ሰነድነት ከመጥቀም አልፈው፣ ለማስተማሪያ ጭምር የሚውሉ እንደሚሆኑ መገንዘብ ይገባል፡፡ ኢትዮጵያውያን እንዲህ ዓይነት ነውረኛ ጭካኔዎች በአገራቸው ውስጥ ዳግም እንዳይከሰቱ ከማድረግ በተጨማሪ፣ ነገ በሕግም ሆነ በታሪክ ከሚያስጠይቁ ወንጀሎች ራሳቸውን ከወዲሁ መግታት ይጠበቅባቸዋል፡፡ መንግሥትም ቢሆን ባለበት ኃላፊነት መሠረት የጦርነቱን ፍፃሜ በማሳመር፣ ወደፊት ሊከናወኑ የሚገባቸው አገር ገንቢ ተግባራት ላይ እንዲተኮር መሥራት ይጠበቅበታል፡፡ ኢትዮጵያ የሚጠቅማት ዘለቄታዊ ሰላምና ዕድገት ነው፡፡

የዚህች አገርና የእዚህ ጨዋና አስተዋይ ሕዝብ ዋስትና በአንድነት መቆም መቻል ነው፡፡ ይህ አንድነት የተለያዩ ማንነቶችን፣ ባህሎችን፣ ቋንቋዎችን፣ እምነቶችንና የመሳሰሉ ልዩነቶችን የሚያከብር ሲሆን ደግሞ የኢትዮጵያ ሕዝብ ለአገሩ ክብርና ዘለዓለማዊነት በጋራ ይቆማል፡፡ ይህ ከትውልድ ወደ ትውልድ ሲሸጋገር የኖረ የአገር ፍቅር ስሜት ይበልጥ አብቦ ዴሞክራሲያዊት ኢትዮጵያ ትገነባ ዘንድ ቅንነትና በጎ ፈቃድ ያስፈልጋል፡፡ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት የሚገነባው በአምባገነንነት አስተሳሰብ ስላልሆነ፣ ለዴሞክራሲያዊ እሴቶች መገዛት ተገቢ ነው፡፡ ያረጁና ያፈጁ ለአገር የማይጠቅሙ አስተሳሰቦችና ድርጊቶች ለዚህ ዘመን ትውልድ ስለማይመጥኑ አሽቀንጥሮ መጣል ይገባል፡፡ በብሔርተኝነት ካባ ውስጥ የአገርን ህልውና የሚንዱ ተግባራትም ሆኑ፣ ማናቸውም ፀረ ኢትዮጵያ ድርጊቶች ፋይዳ የላቸውም፡፡ ከዚህ ይልቅ በሕዝብ ፈቃድና ፍላጎት ላይ ለተመሠረተ የፖለቲካ ግንኙነት መገዛት ይገባል፡፡ የኢትዮጵያ ሕዝብ ከዳር እስከ ዳር የሚፈልገው ሰላም፣ ዴሞክራሲና ዕድገት ነው፡፡ በእኩልነት ተከባብሮና ተፋቅሮ መኖር ነው፡፡ ከጋራ እሴቶቹ የሚመነጩትም በአንድነት መቆም፣ የጋራ ግብና ራዕይ ይዞ ከትውልድ ወደ ትውልድ መቀባበል ነው፡፡ በዚህ መንፈስ የዓመታት ስህተቶችን ማረምና አዲስ ምዕራፍ መጀመር የወቅቱ ጥሪ ነው፡፡

የኢትዮጵያ ምድር ከአሁን በኋላ የተትረፈረፈ ምግብ የሚመረትበት መሆን ይኖርበታል እንጂ፣ መድፍና ታንክ የሚያጓሩበት እንዲሆን መፈቀድ የለበትም፡፡ አገራቸውን በልማት የሚያኮሩ አርበኞች የሚከበሩበት እንጂ፣ አገር ለማፍረስ የሚያሴሩና ሕዝብ የሚያስጨንቁ መሰሪዎች የሚንጎማለሉበት መሆን አይገባውም፡፡ ሁሉንም በእኩል ዓይን የሚያይ ሥርዓት እንዲፈጠር እንጂ፣ ከፋፋዮችና አጥፊዎች የሚፈነጩበት ሥርዓት እንዳይኖር መታገል ይገባል፡፡ የኢትዮጵያ ወጣቶች ጥራት ያለው ትምህርት አግኝተው የዘመኑን ቴክኖሎጂ በሚገባ እንዲጠቀሙበት ለማድረግ መሥራት ያስፈልጋል፡፡ በአሁኑ ወቅት ኢትዮጵያ ጦርነት ውስጥ ነው ያለችው፡፡ ይህንን አውዳሚ ጦርነት ለማስቆም የሁሉንም ኢትዮጵያውያን ርብርብ ይጠይቃል፡፡ ለዚህ ስኬት ደግሞ ብሔራዊ ምክክር አስፈላጊ ነው፡፡ የአገር ጉዳይ ያገባናል የሚሉ ወገኖች በሰላማዊና በሕጋዊ መንገድ ተቀራርበው መነጋገር ይጠበቅባቸዋል፡፡ ጠመንጃ አንግቶ መነጋገር አይቻልም፡፡ ጠመንጃ ከኢትዮጵያ ፖለቲካ ውስጥ መውጣት አለበት፡፡ ጦርነቱ ሲጠናቀቅ ኢትዮጵያ ዳግም ወደ ጦርነት እንዳትመለስ ተደርጎ መሆን ይኖርበታል፡፡ የኢትዮጵያ የፖለቲካ ኃይሎችም ሆኑ ሌሎች የአገር ጉዳይ የሚመለከታቸው ወገኖች፣ ኢትዮጵያ ከግጭት የፀዳች አገር እንድትሆን ቁርጠኝነታቸውን በተግባር ያሳዩ፡፡ ለኢትዮጵያ የሚያዋጣው ሰላም ብቻ ነው!

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

የኦሮሞን ሕዝብ ታሪክ አልባ በማድረግ ታሪክ አይሠራም

በኢተፋ ቀጀላ​​  ከዛሬ ሃምሳ ዓመት ወዲህ ከተፈጠሩት የኦሮሞ ድርጅቶች መካከል ከኢጭአት በስተቀር፣...

የፓርላማ አባላት ስለሰላም ስምምነቱ አፈጻጸም ግልጽ መረጃ የለንም አሉ

‹‹ሕወሓትን ለፍረጃ አብቅተውት የነበሩ ጉዳዮች በአብዛኛው መልክ ይዘዋል›› ሬድዋን...

ጉራጌን በክላስተር ለመጨፍለቅ የሚደረገውን ጥረት እንደሚቃወም ጎጎት ፓርቲ አስታወቀ

ለጉራጌ ሕዝብ ሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶች መከበር እንደሚታገል የሚናገረው አዲሱ...

‹‹ኢኮኖሚው ላይ የሚታዩ ውጫዊ ጫናዎችን ለመቀልበስ የፖሊሲ ሪፎርሞች ያስፈልጋሉ›› ዓለም ባንክ

በዓለም ደረጃ ከተፈጠረው የኢኮኖሚ አለመረጋጋት ጋር በተገናኘ፣ በኢትዮጵያ ውጫዊ...
- Advertisment -

ትኩስ ፅሁፎች

ለፋይናንስ ዘርፉ ብቃት ያለው የሰው ኃይል የማፍራት የቤት ሥራን የማቃለል ጅማሮ

የአገሪቱ የፋይናንስ ዘርፍ እያደገ ለመሆኑ ከሚቀርቡ ማስረጃዎች ውስጥ  የግል...

የምድር ባቡርን የሚያነቃቃው የመንግሥት ውሳኔ

በኢትዮጵያ ወደብ አልባነት ላይ የተደመረውን የሎጀስቲክስ ችግር ለመፍታት ግዙፍ...

የፓርላማ አባላት ስለሰላም ስምምነቱ አፈጻጸም ግልጽ መረጃ የለንም አሉ

‹‹ሕወሓትን ለፍረጃ አብቅተውት የነበሩ ጉዳዮች በአብዛኛው መልክ ይዘዋል›› ሬድዋን...

ብሔራዊ ባንክ የፖሊሲ ማሻሻያዎችን ይፋ ሊያደርግ ነው

የፋይናንስ ዘርፉን ለማረጋጋት የሚረዳ ሪፎርም ማጠናቀቁን የገለጸው የኢትዮጵያ ብሔራዊ...
spot_img

ተዛማጅ ፅሁፎች

ግልጽነትና ተጠያቂነት የጎደለው አሠራር ለአገር አይበጅም!

ሰሞኑን የአሜሪካና የኢትዮጵያ መንግሥታት በሰሜን ኢትዮጵያ ጦርነት ተፈጽመዋል በተባሉ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶችና የጦር ወንጀሎች መግለጫ ላይ አልተግባቡም፡፡ አለመግባባታቸው የሚጠበቅ በመሆኑ ሊደንቅ አይገባም፡፡ ነገር ግን...

የምግብ ችግር ድህነቱን ይበልጥ እያባባሰው ነው!

በአገር ውስጥና በውጭ የተለያዩ ተቋማት የሚወጡ መረጃዎች እንደሚያሳዩት፣ በአሁኑ ጊዜ በኢትዮጵያ ከ22 ሚሊዮን በላይ ዜጎች አስቸኳይ የምግብ ዕርዳታ ያስፈልጋቸዋል፡፡ እነዚህ ወገኖች በሰሜን ኢትዮጵያ ጦርነት፣...

መብትና ነፃነትን የሚጋፉ ድርጊቶች ይወገዱ!

ኢትዮጵያውያን በየትኛውም የአገሪቱ ክፍል የመዘዋወር፣ የመኖር፣ የመሥራትና ሀብት የማፍራት ሕጋዊ መብት አላቸው፡፡ ይህ መብት በግልጽ የተደነገገው በሥራ ላይ ባለው ሕገ መንግሥት ሲሆን፣ አሁንም ሕገ...