Tuesday, March 28, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ማኅበራዊማሻሻል የሚጠይቀው የጤና አገልግሎት ፍትሐዊነት

ማሻሻል የሚጠይቀው የጤና አገልግሎት ፍትሐዊነት

ቀን:

በዓለም አቀፍ ደረጃ እየተተገበሩ ካሉት የምዕተ ዓመቱ የልማት ግቦች መካከል ጤና ሰፋ ያለውን ቦታ ይይዛል፡፡ ለዚህም ምክንያቱ የዘር፣ የሃይማኖት፣ የፆታ፣ የቦታ አቀማመጥና ሌሎች ልዩነቶች ሳይገድበው ፍትሐዊነቱን ባረጋገጠ መንገድ ለኅብረተሰቡ ተደራሽ መሆን ስለሚገባው ነው፡፡

የጤና ፍትሐዊነትን የማረጋገጥ ተግባር የአንድ ወይም የተወሰኑ መንግሥታዊ አካላት ድርሻ ብቻ ሳይሆን ሁሉም የዘርፉ መሥሪያ ቤቶች፣ የባለድርሻና የልማት አጋር አካላትን ትብብር የሚጠይቅ ነው፡፡ በመሆኑም የዘርፉ ባለድርሻዎች የተሳተፉበት የጤና ፍትሐዊነት ስትራቴጂክ ዕቅድ ተዘጋጅቶ ለተግባራዊነቱ ሁሉን አቀፍ እንቅስቃሴ ተጀምሯል፡፡

የጤና ሚኒስትር ሊያ ታደሰ (ዶ/ር) እንደተናገሩት፣ ይኸው የአምስት ዓመት ስትራቴጂክ ዕቅድ ‹‹በተቀናጀ ጥረት የተፋጠነ የጤና ፍትሐዊነት ለጤናማና ፍትሐዊ ማኅበረሰብ ግንባታ›› በሚል መሪ ቃል በተለይ እየተተገበረ ያለው ተመጣጣኝ ልማት በሚሹ አፋር፣ ሶማሌ፣ ጋምቤላና ቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልሎችና የሥራ አፈጻጸም ችግር በሚስተዋልባቸው ሰባት ዞኖች ውስጥ ነው፡፡

ከዓምና ጀምሮ እየተተገበረ ባለው ሥራ፣ 450 ጤና ጣቢያዎች የተገነቡ ሲሆን፣ ከእነዚህም ውስጥ 80 ከመቶ ያህሉ ግንባታ የተከናወነው በጤና ሚኒስቴር ነው፡፡

ከአሥር ዓመት በፊት በጤና ተቋማት የሚወልዱ እናቶች ከአሥር በመቶ በታች እንደነበር፣ በአሁኑ ጊዜ ግን በተቋማቱ የሚወልዱ እናቶች ቁጥር 50 ከመቶ እንደደረሰ፣ ከ80 በመቶ በላይ የሆኑ ሕፃናትም ለልዩ ልዩ በሽታዎች መከላከያ የሚውሉ የተለያዩ ዓይነት ክትባቶችን ማግኘታቸውን ለዚህም ስትራቴጂው አስተዋጽኦ እንዳደረገ ተናግረዋል፡፡

የጤና ጣቢያዎችና የመጀመሪያ ደረጃ ሆስፒታሎችን ግንባታ የማስፋፋትና የማሟላት፣ የአምቡላንስ ድጋፍ የመስጠት፣ የመረጃ ሥርዓትና የሰው ኃይል ሥልጠና ተደራሽ ባልሆኑባቸው አካባቢዎች የማጠናከር፣ ከጤና ተቋማት ግንባታ ጎን ለጎን የጤና ባለሙያዎች በእነዚሁ ክልሎች ተረጋግተው እንዲሠሩ ለማድረግ የሚያስችሉ የመኖሪያ ቤቶች ግንባታ እየተከናወኑ መሆኑንም አስረድተዋል፡፡

እንደ ሊያ (ዶ/ር) ማብራሪያ፣ የጤና ክብካቤ ገቢ ማስገኛና የኅብረተሰብ ጤና መድን ትግበራን በማስፋፋትና የመድሐኒት ግብዓቶችን ድጋፍ በማሟላት ሲሠራ ቆይቷል፡፡ ሆኖም ዕቅዱን በመተግበር ሒደት ላይ ወረርሽኝ፣ ድርቅ፣ ግጭትና መሠረተ ልማቶች አለመሟላት ፈተና ሆነዋል፡፡

ከችግሮቹ ለመላቀቅ በተካሄደው ጥረት አልፎ አልፎ መሻሻሎችና በአፋር፣ በሶማሌ፣ በኦሮሚያ፣ በደቡብ ብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ክልሎች በሚገኙና ከተወሰኑ አርብቶ አደር ቦታዎች በስተቀር ጤና ተደራሽነት ላይ ሰፊ ለውጥ መምጣቱን ተናግረዋል፡፡

የጤና ፍትሐዊነትን ከማረጋገጥ አኳያ አሁንም በክልሎች፣ በዞኖች፣ በወረዳዎችና በጤና ተቋማት መካከል ልዩነቶች መታየታቸውን፣ ልዩነቶችን ለማጥበብ ሁሉም ባለድርሻ አካላት በእያንዳንዱ ተግባራት ውስጥ ፍትሐዊነትን እንዲያሰፍንና ኢፍትሐዊነትን እንዲያጠብ ጥሪ አቅርበዋል፡፡

የቆላማና መስኖ ልማት ሚኒስትር አይሻ መሐመድ (ኢንጂነር)፣ በአርብቶ አደሩ አካባቢ ብዙ ነገሮች ፍትሐዊ እንዳልሆኑ ይህም ወደ ኋላ መቅረትንና ልዩነቶችንም እያሰፋ እንዳመጣ ተናግረዋል፡፡

በአርብቶ አደርና ዝቅተኛ አፈጻጸም ባላቸው ዞኖች፣ በጤናው ዘርፍ የሚነሱ ኢ-ፍትሐዊነት በሌሎችም ዘርፎች ይነሳሉ ያሉት ሚኒስትሯ፣ በጤናው ዘርፍ ኢ-ፍትሐዊነት መኖር የሚያስከትለው ጉዳት ከፍተኛ መሆኑን፣ ይህንን ችግር በዘላቂነት ለመፍታት በልዩ ድጋፍ አማካይነት ዘርፈ ብዙ ሥራዎች መሠራታቸውን ጠቁመዋል፡፡

በአራቱም ክልሎችና በአርብቶ አደር አካባቢዎች እንዲሁም ዝቅተኛ አፈጻጸም ባላቸው ዞኖች ባለፉት ዓመታት በጤናው ዘርፍ የተመዘገቡ ውጤቶች በሌሎችም ዘርፎች ለመድገም ሚኒስቴራቸው እንደሚሠራም አክለዋል፡፡

ብሔራዊ የጤና ፍትሐዊነት በሁሉም ዘርፍ በሁሉም አካባቢዎች ያሉ ኢ-ፍትሐዊነት ለማጥበብ በተለይም የጤና አገልግሎት ሽፋንና ጥራቱን ለማሻሻል የሚያግዝ ስትራቴጂ ነው፡፡

የጤና ፍትሐዊነት ስትራቴጂክ ዕቅድን በአርብቶ አደሩ የልማት ፖሊሲ ውስጥ አካትቶ በመንቀሳቀስ ውጤታማ ማድረግ እንደሚቻልም ሰሞኑን ጤና ሚኒስቴር ከአጋሮቹ ጋር በስትራቴጂክ ዕቅዱ ተፈጻሚነት ዙሪያ በመከረበት ወቅት ተገልጿል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ለፋይናንስ ዘርፉ ብቃት ያለው የሰው ኃይል የማፍራት የቤት ሥራን የማቃለል ጅማሮ

የአገሪቱ የፋይናንስ ዘርፍ እያደገ ለመሆኑ ከሚቀርቡ ማስረጃዎች ውስጥ  የግል...

የምድር ባቡርን የሚያነቃቃው የመንግሥት ውሳኔ

በኢትዮጵያ ወደብ አልባነት ላይ የተደመረውን የሎጀስቲክስ ችግር ለመፍታት ግዙፍ...

የፓርላማ አባላት ስለሰላም ስምምነቱ አፈጻጸም ግልጽ መረጃ የለንም አሉ

‹‹ሕወሓትን ለፍረጃ አብቅተውት የነበሩ ጉዳዮች በአብዛኛው መልክ ይዘዋል›› ሬድዋን...