የ‹‹ያ ትውልድ›› ተከታታይ ቅጾችና ሌሎች መጽሐፍት ደራሲ በመሆናቸው ብቻ ሳይሆን፣ ዘውዳዊውን ሥርዓት የነቀነቁና ሥር ነቀል የፖለቲካ ለውጥ በኢትዮጵያ እንዲመጣ ያደረጉ የ1960ዎቹ የወጣት ተማሪዎች እንቅስቃሴ ዋና ተሳታፊም ነበሩ፡፡ አንጋፋው ፖለቲከኛ አቶ ክፍሉ ታደሰ የኢትዮጵያ ሕዝብ አብዮታዊ ፓርቲ (ኢሕአፓ) መሥራች፣ የማዕከላዊ ኮሚቴ አባልና ከፍተኛ አመራር ሆነው የሠሩ ሰው በመሆናቸውም ይጠቀሳሉ፡፡ በቅርቡ ነሐሴ 29 ቀን 2014 ዓ.ም. በድምቀት ይከበራል ተብሎ የሚጠበቀውን የኢሕአፓ 50ኛ ዓመት በዓልን ለማክበር ከውጭ አገር በቅርቡ ወደ አገር ቤት ተመልሰዋል፡፡ በተለይ ወጣቶችን በማንቃት፣ በማደራጀትና ለትግል በማሠለፍ ጎልቶ የሚጠቀሰው የኢሕአፓ አባል እንደ መሆናቸው መጠን፣ የአሁኑን ትውልድ ከ‹‹ያ ትውልድ›› ጋር አነፃፅረው ይናገራሉ፡፡ ዮናስ አማረ ከአቶ ክፍሉ ጋር ይህንኑ በትውልዶች መካከል ያለውን የወጣቶች ልዩነት የዳሰሰ ሲሆን፣ ስለኢሠፓ ፓርቲ የምሥረታ ጥያቄና ወቅታዊ የአገሪቱን ቀውሶች የተመለከቱ ጥያቄዎችንም በሰፊው መልስ የሰጡበት ቆይታ እንደሚከተለው ቀርቧል፡፡
ሪፖርተር፡- እርስዎ ወጣቶች ሥር ነቀል ለውጥ ለማምጣት ይታገሉ የነበረበት የዚያ ትውልድ አካል ነዎት፡፡ ያኔ ከነበረው ሁኔታ ተነስተው ዛሬ ያለው ወጣት ጥያቄውን የሚመልስ ሥርዓት ማግኘት ችሏል ይላሉ? የኢትዮጵያ ወጣቶችን ችግር በተጨባጭ የሚፈታ ሥርዓት በኢትዮጵያ ተፈጥሯል ወይ?
አቶ ክፍሉ፡- አሁን ያለው ወጣት ያለበት ችግር ትክክለኛ ትኩረት ያገኘ አይመስለኝም፡፡ ከማኅበረሰቡ አብዛኛው ቁጥር በግምት እስከ 60 በመቶ ወጣት ነው፡፡ ስለዚህ ወጣቱ ትልቅ ቁጥር ያለው የማኅበረሰብ ክፍል ነው ማለት ነው፡፡ አሁን ያለው ወጣት የመጀመሪያ ጥያቄው ሊሆን የሚችለው ደግሞ ሥራ የማግኘት ጥያቄ ነው፡፡ ወጣቱ ምን ያህል እንደተቸገረ ለማወቅ የትም መሄድ አያስፈልግም፡፡ በየመንገዱ፣ በየቀበሌውና በየሠፈሩ ብዙ ወጣት ሥራ አጥቶ ሲንገላታ ማየት በቂ ነው፡፡ የተማረውም ወጣት ቢሆን፡፡ ከዩኒቨርሲቲ፣ ከቴክኒክና ሙያና ከኮሌጆች በየዓመቱ ከሚመረቀው ወጣት ሥራ የሚያገኘው ቁጥር አኃዙ ባይኖረኝም፣ ከ20 እና 25 በመቶ መብለጡን እጠራጠራለሁ፡፡
አሁን ያለው ወጣት ብዙ ችግር ነው ያለበት፡፡ አዲስ አበባ፣ ነቀምት፣ ባህር ዳር፣ ወይም እዚህ ቦታ የምትለው ሳይሆን ችግሩ በመላው ኢትዮጵያ ነው፡፡ በየትም ቢሆን ወጣቱ ተምሮ ሥራ ማግኘት፣ ራስን መለወጥም ሆነ ሕይወትን ማሻሻል ፈተና እንደሆነበት ብዙ ማሳያዎች አሉ፡፡ ይህ አሳሳቢ ችግር በመሆኑ ለነገ የሚባል አይደለም፡፡ ወጣቱ በሱስ ተጠመደ፣ ባከነ ወይም ወደ አልተገባ መንገድ ገባ ይባላል፡፡ በእኔ ዕይታ ግን ወጣቱ ሊፈረድበት አይገባም፡፡ ብዙው ወጣት የሚበላሸው ኑሮው እያስገደደው ነው፡፡
በእኛ ጊዜ የተመረቁ ወጣቶች ሥራ አጡ የሚባልበት ጊዜ ነበር፡፡ አንዳንድ ተመራቂዎች ለተወሰኑ ወራት (ሁለትም ስድስት ወራትም) ሥራ ይቸገሩ ነበር፡፡ ይህን በማየት ያን ጊዜ ሥራ ጠፋ እያልን እናማርር ነበር፡፡ አሁን ካለው ሁኔታ ጋር ግን ስናነፃፅረው የዚያን ዘመኑ ሁኔታ ቅንጦት ነው፡፡ ዛሬ ተመራቂዎች ለጥቂት ወራት አይደለም ለዓመታትም ሥራ ላያገኙ ይችላሉ፡፡
ሪፖርተር፡- ያኔ የወጣቶችን ጥያቄ ሥርዓቱ ቢሰማ ኖሮ አብዮቱ፣ ግጭቱና አሁንም ድረስ የቀጠለው የፖለቲካ ቀውስ ባልነበረ ይባላል፡፡ ከዚያን ጊዜው ጋር በማነፃፀር አሁን ያለው ወጣት የሚደመጥበት ዕድል አለ ይላሉ?
አቶ ክፍሉ፡- መጀመሪያ የሚያዳምጥ ሥርዓት ሲኖር ነው እኮ ወጣቶች ከሌሎች የማኅበረሰብ ክፍል እኩል መደመጥ ችለዋል ወይ ብሎ መገምገም የሚቻለው፡፡ በኢትዮጵያ የመጡ ሥርዓቶች ተጀምሮ እስከሚያልቅ እንዳያዳምጡ ሆነው ነው የተፈጠሩት፡፡ ወጣቱ የሚያዳምጠው ቢያገኝና ቢጠየቅ የሚፈልገውን ነገር ይናገራል፡፡ ወጣቱ ልክ እንደ ማንኛውም ሰው ተምሮና ሠርቶ መለወጥ ነው የሚፈልገው፡፡ ማንኛውም ሰው ያገኘውን ነገር ማግኘት ነው የሚፈልገው፡፡ ወጣቱ ይኼንን ነው የተነፈገው፡፡
በነገራችን ላይ ለወጣቶች ጥያቄ መልስ የሚነፈገው ኢትዮጵያ ቸግሯት ወይም ዕድል አጥታ አይደለም፡፡ በኢትዮጵያ ሰፊ መታረስ የሚችል መሬት አለ፡፡ መሬት ደግሞ በአገራችን ዋነኛው የሀብት ምንጭ ነው፡፡ ወጣቱን በእርሻ ልማት እንዲሰማራ የሚያደርግ ሥርዓት ግን አልተፈጠረም፡፡ እኛ መሬት ለአራሹ ብለን ታግለን ነበር፡፡ ‹የዛሬው ወጣት ዕድል ያስፈልገዋል› በሚል ሐሳብ መሬት ለወጣቱ የሚል ሰፊ ጽሑፍ በቅርቡ በፍትሕ መጽሔት አስነብቤ ነበር፡፡ ከተወሰነ ዕርዳታና ከማቋቋሚያ ገንዘብ ጋር መሬት ቢሰጠው ወጣቱ ራሱን ይችላል፡፡ ትራክተር ወይም ዘመናዊ ማረሻ ቢሰጠውና ቢሰማራ ማልማት ይችላል፡፡
ወጣቱ ራሱን መቻል ብቻ አይደለም ዋናው የካፒታል ምንጭ መሆን ይችላል፡፡ ካፒታል ከተፈጠረ ደግሞ የአገር ኢኮኖሚ የሚንቀሳቀስበት ዕድል ይሰፋል፡፡ ከመሬት ጀምሮ ለወጣቱ የሚሆኑ ብዙ ዕድሎች አሉ፡፡ ቲማቲም በማምረት ዛሬ ቢጀምር ነገ የቲማቲም ድልህ ወደ ማምረት ይገባል፡፡ በበቆሎ ጀምሮ ወደ በቆሎ ዱቄት ማምረት ሊሸጋገር ይችላል፡፡ ወጣቱ መንገድ ያግኝ እንጂ የፈጠራ ጭንቅላት ስላለው በራሱ መንገዶችን ማስፋትና አገር ማሳደግ ይችላል፡፡
ኢሕአዴጎች በማጭበርበር ወደ ሥልጣን ቢመጡም፣ በወጣቱ መስዋዕትነት ነው ለዚያ ሥልጣን የበቁት፡፡ ኢሕአዴጎች ማንም እንደሚያውቀው በ1997 ዓ.ም. ምርጫ ተሸንፈዋል፡፡ እንዲሸነፉ ያደረጋቸው ደግሞ ሆ! ብሎ የመረጠውና ‹‹ድምፄ አይሰረቅም›› ብሎ የምርጫ ውጤቱን ሲከታተል የነበረው ወጣት ነበር፡፡ ከ2009 ዓ.ም. ጀምሮ በነበረው የፖለቲካ ተቃውሞ መሪ የነበረውና ኢሕአዴጎች ሥልጣን እንዲያስረክቡ፣ እንዲሁም የሕወሓት ኃይሎች ጠቅልለው ወደ ትግራይ እንዲገቡ ያደረገው የወጣቱ ኃይል ነበር፡፡ የአሁኑ አስተዳደርም የመጣው በዚሁ የወጣቱ ትግል ነው፡፡
ወጣቱ ስድብ አይገባውም፡፡ ወጣቱ በደንብ መያዝ አለበት፡፡ ወጣቱ እንዲህ ሆነ የሚባለው ወዶ አይደለም፡፡ ተስፋ የሚቆርጠው ብዙ ችግሮች ተደራርበውበት ነው፡፡ ካላወቅንበትና በአግባቡ ካልያዝነው ወጣቱ ጊዜ ጠብቆ ሊፈነዳ የሚችል ፈንጂ ነው፡፡ አክራሪ ብሔርተኛ ኃይሎች ሊያፈነዱት ይችላሉ፡፡ ሌሎች ኃይሎች ሊያፈነዱት ይችላሉ፡፡ ስለዚህ በኢትዮጵያ የወጣቱን ችግር ማድመጥና መፍታት አማራጭ የሌለው ተግባር ነው፡፡
ሪፖርተር፡- የእናንተ ትውልድ ወጣት ለለውጥ ተራማጅና የገዘፉ ሐሳቦችን የሚያነሳ የነቃ ወጣት ነበር ይባላል፡፡ ከመሬት ለአራሹ ጀምሮ የወጣበትን ማኅበረሰብ መሠረታዊ ጥያቄዎች ማንሳቱ ይጠቀስለታል፡፡ ከዚህ አልፎም ደቡብ አፍሪካ፣ ቬትናም፣ ዚምባብዌ ነፃነት ይምጣ የሚሉ ዓለም አቀፍ የሆኑ ጉዳዮችን ያነሳ ነበር ይባላል፡፡ አሁን ያለው ወጣት ያን ዓይነት የፖለቲካ ስሜት አያንፀባረቅም ይባላል፡፡ ከፖለቲካ ኃይሎች ጋር ተጣብቆ ፍላጎቱን ለማስፈጸም መጣር፣ በአቋራጭ የመበልፀግና ሌላም ወደ ግለኝነት ያጋደለ ዝንባሌ በአሁኑ ወጣት ላይ ይታያል ተብሎ ይተቻል፡፡ ይህን ቢያነፃፅሩልን?
አቶ ክፍሉ፡- ይህ ጥያቄ በጥንቃቄ መታየት አለበት፡፡ ወጣቱ አርዓያ የሚሆነው፣ የሚያደራጀውና የሚመራው ካገኘ አሁንም ቢሆን ትልልቅ ለውጦችን መፍጠር ይችላል ነው የምለው፡፡ በ1997 ዓ.ም. ምርጫ የሚመራው አካል ስላገኘ ነው ሆ ብሎ ወጥቶ ምርጫ የመረጠው፡፡ ምርጫ እንዳይጭበረበር የተከላከለውና ድምፄ አይዘረፍም ብሎ ነው የታገለው፡፡ ኢሕአዴግ ‹‹አደገኛ ቦዘኔ›› ብሎ ስለፈረጀው ተናዶ ነው ወጣቱ ያን ያደረገው ቢባልም፣ በጊዜው ግን ወጣቱን የሚያደራጁና የሚመሩ እንደ ቅንጅት ያሉ ጠንካራ ተቃዋሚዎች ተፈጥረው ነበር፡፡
በ2010 ዓ.ም. በመጣው ለውጥም ቢሆን አንዳንዶች እኛ አስተባበርነው ወይም መራነው ብለው ቢናገሩም፣ ወጣቱ ግን በራሱ መንገድ ነበር ሥርዓቱን የታገለውና ከሥልጣኑ ነቅንቆ ያወረደው፡፡ ሦስተኛው አጋጣሚ ደግሞ ከትግራይ ጦርነት ጋር ተያይዞ ወጣቱ የፈጸመው ገድል ነው፡፡ ለዚህች አገር የደረሰላት ወጣቱ ነው፡፡ የፈለግከውን ስም ስጠው፣ በፈለገ መንገድ ፈርጀው ነገር ግን ወጣቱ ለአገሩ ቀላል የማይባል አስተዋጽኦ እያደረገ ነው፡፡ አዎን ችግር አለበት፣ ሥራ ማጣት በራሱ ለወጣቱ ትልቅ ችግር ነው፡፡ ነገር ግን አገር ለማዳን ውትድርና ግባ ወይም ዝመት ሲባል ስንቶች ወጣቶች ሆ ብለው መከላከያ፣ ልዩ ኃይልና ፋኖ ሲሆኑ አላየንም ወይ?
የአሁኑ ወጣት ከያኔው የተለየ ወጣት አይደለም፡፡ በዚያን ጊዜ በተለይ በ1964 ዓ.ም. አካባቢ ‹‹ቻይና ግሩፕ›› እየተባለ ሴቶችን ማስቸገርና ሌላ አልባሌ ምግባር በአንዳንዶች ዘንድ ይንፀባረቅ ነበር፡፡ ሆኖም ወጣቱ ብዙም ሳይዘገይ አቅጣጫ ሊሰጡ፣ ሊያደራጁና ሊያስታግሉ የሚችሉ ጠንካራ መሪዎችን አገኘ፡፡ ወጣቱ መሪዎቹን እንኳን አያውቅም፡፡ ነገር ግን በሳምንት አንዴ በምትበተን አነስተኛ በራሪ ወረቀት አማካይነት የፖለቲካ ንቃት እንዲያገኝ ውጤታማ ሥራ መሠራት ተቻለ፡፡ የወደፊት ተስፋው ብሩህ እንደሆነ፣ መታገል፣ መለወጥና በቀጥታ መሳተፍ እንዳለበት ወጣቱ ተቀሰቀሰ፡፡ ሰፊ ውይይት በመፍጠር የወጣቱ ጥያቄ ጎልቶ እንዲሰማ ማድረግ የሚችሉ አመራሮች ነበሩ፡፡ በ1997 ዓ.ም. በተመሳሳይ ወጣቱን የሚነቀንቅ አመራር ተፈጥሮ ነበር፡፡ አሁን ያለው ወጣትም አመራር ቢያገኝና የወደፊት ብሩህ ተስፋ የሚያሳየው ኃይል ቢያገኝ ለውጥ መፍጠር እንደሚችል በግሌ ትልቅ ተስፋ አለኝ፡፡ የአሁኑ ትውልድም ከሌሎች የተለየ አይደለም፡፡
ሪፖርተር፡- በኢትዮጵያ የፖለቲካ ታሪክ ወጣቱ ይታገላል፣ ለሥልጣን መንገድ ይጠርጋል፡፡ ሆኖም እሱ በታገለው ሌሎች ያደቡ ኃይሎች ናቸው ሥልጣኑን የሚጨብጡት፡፡ የእናንተ ትውልድ ንጉሡን ታግሎ ደርግ ቦታውን እንደያዘ ሁሉ፣ አሁን ሥልጣን የያዘው ኃይልም በወጣቱ መንገድ ጠራጊነት የመጣ ነው፡፡ ወጣቱ ለምን ከሥልጣን ይገፋል? ለምን ይፈራል? ወይም አጀንዳውን ይነጠቃል?
አቶ ክፍሉ፡- ያኔ የነበሩ ወጣቶች እስከሚችሉት ድረስ ታግለዋል፡፡ እጅ ሰጥተው ሳይሆን ገሸሽ ያሉት ሥልጣን የያዘው ኃይል ስለገደላቸውና ስላሳደዳቸው ነው፡፡ የሚሰደደውም አገር ጥሎ ወጣ፡፡ የሞተውም ሞተ፡፡ በረሃ የገባውም ገባ፡፡ አንገታቸውን ደፍተው አይደለም፣ እስከሚችሉት ታግለዋል፡፡ ‹‹ያ ትውልድ›› ከአሁኑ ጋር የሚነፃፀር አይደለም፡፡ አሁን ያለው ወጣት መሪ የለውም፡፡ ወጣቱ ከተነሳ ሊያስቆመው የሚችል የለም፡፡ ወጣቱ የሚያየው አርዓያ ይፈልጋል፡፡ በእኛ ዘመን ወጣቱ ሀቀኝነትን፣ ለእውነት መቆምንና ጥንካሬን ከታታላቆቹ ያያል፡፡ አሁን ያለው ወጣት በየቀበሌውና በየቦታው ዘረፋና ሙስና ሲፈጸም እያየ ያድጋል፡፡ ይህንን እያየ ያደገ ወጣት ታዲያ ቀና መንገድን መከተል እንዴት ይችላል?
ሪፖርተር፡- በኢትዮጵያ በእናንተ ዘመን ያቆጠቆጠው የዴሞክራሲ ትግል ወዴት ተጓዘ? ትግሉ በዘመናት ዑደት ዛሬ የደረሰበትን ሒደት ቢያስረዱን?
አቶ ክፍሉ፡- በዚያን ጊዜ የነበረው ትውልድ ካነሳቸው ጥያቄዎች አንዱ፣ ‹‹ኢትዮጵያ ኅብረ ብሔራዊ እኩልነት የተከበረባት አገር ትሁን›› የሚለው በዋናነት ይገኝበታል፡፡ ደርግ ግን ጥያቄዎቹን በሙሉ አፍኖ በጉልበት መልስ እሰጣለሁ የሚልበት ጊዜ ነበር፡፡ በዚህ ወቅት ሦስት የፖለቲካ ኃይሎች በዋናነት በኢትዮጵያ ነበሩ፡፡
አንደኛው እንደ መኢሶንና ኢሕአፓ ያሉ ኅብረ ብሔራዊ ኃይሎች ሲሆኑ፣ ሁለተኛው ደርግ ራሱ፣ ሦስተኞቹ ደግሞ ብሔርተኛ ኃይሎች ነበሩ፡፡ ደርግ በመጀመሪያ ኅብረ ብሔራዊ ኃይሎችን ጨፈጨፋቸው፡፡ በዚህ የተነሳ ብሔርተኞችና ደርግ ብቻቸውን ቀሩ፡፡ ብሔርተኛ ኃይሎቹ ደግሞ ከውጭ ኃይሎች በተለይ እንደ አሜሪካና እንግሊዝ ባሉ ምዕራባውያን ኃይሎች ከፍተኛ ድጋፍ በማግኘታቸው እየጠነከሩ ሄዱ፡፡ መጀመሪያ ከሶቪየት ኅብረት ጋር የተጣበቀው ደርግ የሚያገኘው ድጋፍ እየቀነሰና እየተዳከመ ሄደ፡፡ በዚህ የተነሳ ብሔርተኛ ኃይሎች የበላይነት ያዙ፡፡
ብሔርተኛ ኃይሎች የበላይ እንዲሆኑ መንገድ የጠረገላቸው ደርግ ራሱ ነው፡፡ ኅብረ ብሔራዊ ኃይሎችን አስቀድሞ በመምታቱ ብሔርተኛ ኃይሎች ከሥልጣን ለማስወገድ መንገዱ ተመቻቸላቸው፡፡ ብሔርተኛ ኃይሎች ደርግን አሸንፈው ሥልጣን ያዙ፡፡ ኅብረ ብሔራዊ ኃይሎች ወደ ጎን ተባሉ፡፡ በአገራቸው እየኖሩ ኢትዮጵያዊ ፖለቲካን እንኳ ማራመድ ተከለከሉ፡፡ እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ ኅብረ ብሔራዊ ኃይሎች በአገራቸው እንኳን የመኖር ዕድል አልነበራቸውም፡፡
ሪፖርተር፡- ወጣቱ የራሱን አጀንዳ በራሱ ቀርፆና ራሱን በራሱ ወክሎ ጥያቄዎቹን ለማስመለስ በራሱ በፖለቲካ አደባባዮች በቀጥታ የሚሳተፍበት ዕድል መመቻቸት የለበትም ወይ?
አቶ ክፍሉ፡- ወጣቱ ቢያንስ አቅጣጫ ሊያሳየው የሚችል የራሱ ጠንካራ የፖለቲካ ድርጅት ያስፈልገዋል፡፡ አሁን እንደዚያ ዓይነት ድርጅት አለ ወይ ለሚለው እኔን ያጠራጥረኛል፡፡ ሁለተኛው ደግሞ ወጣቱ መሠረታዊ ፍላጎቶቹን የሚሞላበት ምቹ ሁኔታ የማግኘት ጥያቄ አለበት፡፡ ለመኖርና ሕይወቱን ለማቆየት የሚችልበት መንገድ መመቻቸት አለበት፡፡ ለእሱ የሚያስብለትና የሚጨነቅለት ወገን ያስፈልገዋል፡፡ ይህ ሲሆን ነው ወጣቱ በፖለቲካው ንቁ ተሳትፎ ለማድረግ የሚችለው፡፡
ሪፖርተር፡- ኢሠፓ ፓርቲን ዳግም ለመመሥረት ጥረት ተጀምሯል፡፡ ይህን ጉዳይ ሲሰሙ ምን ተሰማዎት?
አቶ ክፍሉ፡- ለምርጫ ቦርድ ጥያቄ ማቅረባቸውን ሰምቻለሁ፣ ምን እንደደረሰ አላውቅም፡፡ ደርግ ከወደቀ በኋላ ታስረው የነበሩ ብዙ የደርግ ባለሥልጣናት ምሕረት ተብሎ መለቀቃቸው ይታወቃል፡፡ ኢሠፓን የማቋቋሙ ጥያቄ የሕግ ጉዳይ ነውና በቀጥታ ምርጫ ቦርድን ነው የሚመለከተው፡፡ ሰዎቹ በግሌ እንደ ማንኛውም ሰው የመደራጀት መብታቸው ሊከበር ይገባል ነው የምለው፡፡ ወንጀል የሠሩ ካሉ በሕጉ መሠረት ሊጠየቁ ይችላሉ፡፡ ከዚያ ውጪ ኢሠፓን በተመለከተ መረዳት የሚኖርብን በደርግ የግድያ ዘመን ሳይሆን ዘግይቶ የተመሠረተ ድርጅት ነው፡፡ በግድያው ከፍተኛ ተሳትፎ የነበረው ኃይል ኢሠፓን የመሠረተው ኃይል ነው ማለት አይቻልም፡፡ ወደ 1971 ዓ.ም. አካባቢ እኮ ቀይ ሽብርና ግድያው በአብዛኛው አልቋል ማለት ይቻላል፡፡ ኢሠፓ የተመሠረተው ደግሞ ከዚያ ጊዜ ሁለትና ሦስት ዓመታት ዘግይቶ ነው፡፡ በኢሠፓ ውስጥ የነበሩ ሰዎች በኢኮኖሚና በፖለቲካ ተጠቅመው ሊሆን ይችላል፡፡ ነገር ግን የኢሠፓ አባላት ነበሩ በጭፍጨፋው የተካፈሉት ብሎ መደምደም አይቻልም፡፡ ዋና ዋናዎቹ እነ መንግሥቱ ኃይለ ማሪያምና ሌሎችም በመንግሥቱ ሥርዓት ቁንጮ የነበሩ ሰዎች በኢሠፓ ውስጥ ነበሩ፡፡ ነገር ግን የጊዜውን ግድያ ከኢሠፓ ጋር ማገናኘት አይቻልም፡፡ ኢሠፓን ለመመሥረት ዳግም መጠየቁ የሕግ ጉዳይ ነው የሚሆነው፣ ውጤቱ ሲነገር እንሰማለን፡፡
ሪፖርተር፡- ኢትዮጵያን ዛሬም የሚፈትናት የ1960ዎቹ ፖለቲካ ውርስ ነው ይባላል፡፡ መፈራረጅ፣ የከረረ አቋም መያዝና ችግሮችን በመግባባት ሳይሆን በኃይል ለመፍታት መሞከር ካለፈው ትውልድ የተወረሰ የአሁኗ የኢትዮጵያ ችግር ነው ይባላል፡፡ ይህንን እንዴት ይቀበሉታል? እንዲሁም ለዚህ ችግር ማደግ ኢሕአፓም ቢሆን አንዱ ተጠያቂ ነው ማለት አይቻልም ወይ?
አቶ ክፍሉ፡- በዚያን ጊዜ ኢሕአፓን ጨምሮ እንደ አንድ ትውልድ ወጣቱ ያነሳቸው ጥያቄዎች ምንድናቸው ብሎ መጠየቅ ያስፈልጋል፡፡ አንደኛ፣ ‹‹ሕዝባዊ መንግሥት ይመሥረት›› የሚል ነው ጥያቄው፡፡ ሁለተኛ የመምረጥ፣ የመደራጀት፣ የመቃወም፣ የመሰብሰብና የመሳሰሉ ዴሞክራሲያዊ መብቶች ይከበሩ ነው የተባለው፡፡ ሌላውና መሠረታዊ ጥያቄ ደግሞ መሬት ሳይኖረው የሚለፋውና ጭሰኛ ሆኖ የሚኖረው አርሶ አደሩ መሬት ይኑረው (መሬት ለአራሹ) የሚል ጥያቄ ነው የተነሳው፡፡ ሌላው በኢትዮጵያ ውስጥ ቆየው የእኩልነት መዛባት ጉልህ ጥያቄ ነበር፡፡ ኢትዮጵያ እንደ አገር ስትመሠረት በእኩልነት ላይ የተመሠረተ ሥርዓት አልተፈጠረም፡፡ ከአፄ ቴዎድሮስ ጀምሮ አፄ ዮሐንስና አፄ ምኒልክ ኢትዮጵያን አንድ ለማድረግ በተነሱበት ጊዜ ብዙ ጦርነቶች ተካሂደዋል፡፡ እነዚያ ጦርነቶች ደግሞ ብዙ ወገኖችን ተጎጂ አድርገዋል፡፡ አንዳንዶች በባርነትም ተሸጠዋል፣ መብታቸው ተገፏል፡፡ ይህ ደግሞ በኢትዮጵያ ብቻ የተፈጠረ ሳይሆን በብዙ አገሮች የታየ ችግር ነበር፡፡ አሜሪካኖችም አሜሪካንን ሲመሠርቱ ከአንዳንድ መጻሕፍት እንዳነበብኩት ወደ 75 ሚሊዮን ነባር ሕዝቦች (ቀይ ህንዶች) ተጨፍጭፈዋል፡፡ በአሜሪካ ጥቁሮች እስከ 1964 ዓ.ም. መምረጥም ሆነ መመረጥ አይችሉም ነበር፡፡ ነጭ ሴቶች እስከ 1922 ዓ.ም. ድረስ መምረጥ አይችሉም ነበር፡፡ ይህንን መሰል ለውጥ በአሜሪካ የመጣው ብዙ ትግል ታልፎ ነው፡፡ በደቡብ አፍሪካም ቢኬድ አስከፊ የጭቆና ታሪክ አለ፡፡
በዴሞክራሲ የተገነባ አገር የለም፡፡ በብዙ አገሮች ዴሞክራሲ የኋለኛው ዘመን ታሪክ ነው፡፡ ኢትዮጵያም ብትሆን ከዚህ የተለየ ታሪክ የላትም፡፡ በ1960 ዓ.ም. የመጣው የእኛ ትውልድ ከታሪክ ጋር የተያያዙ ጥያቄዎች ሊመለሱ ይገባል ብሎ ለመጀመሪያ ጊዜ ጥያቄ ያነሳ ትውልድ ነው፡፡ የሃይማኖት እኩልነት፣ የማንነት እኩልነትና ሌሎች እኩልነቶች መመለስ አለባቸው ብሎ ተነሳ፡፡ እነዚህ ጥያቄዎች ግን ተንከባለው እስካሁን ድረስ መጥተዋል፡፡ ሆኖም መፍትሔ ማግኘት አልቻሉም፡፡ ለዚህ ዋና ምክንያት የሆነው ደግሞ ደርግ ኅብረ ብሔራዊ ኃይሎችን በመጥረጉ ብሔርተኞች አሸናፊ ሆነው አገሪቱን በመያዛቸው ነው፡፡ ብሔርተኛ ድርጅቶች ዋና ግባቸው የራሳቸውን ጎጥ ከፍ ማድረግ እንጂ እኩልነት ባለመሆኑ፣ ያን መሠረታዊ ጥያቄ ሆን ብለው እንዳይመለስ አድርገውታል፡፡ ብሔርተኞች በደልን ተመርኩዘው ራሳቸውን ነፃ ለማውጣት ብቻ ነው የሚሠሩት፡፡
የኢትዮጵያ አንድነት ተጠብቆ እኩልነት ይረጋገጥ ይሉ የነበሩ ኅብረ ብሔራዊ ኃይሎች ከጨዋታ ውጪ በመደረጋቸው የእኩልነት ጥያቄ ተዳፍኗል፡፡ ደርግ ግን ሁላችንንም በኃይል በመደምሰስ በጦርነት መፍትሔ አመጣለሁ ብሎ በመነሳቱ በሁላችንም ላይ ቀይ ሽብር አወጀብን፡፡ እኩልነት ማስፈን ለኢትዮጵያ ወሳኝ ጥያቄ ነው ብለን ተነሳን፡፡ በፕሮግራማችንም እኩልነት ብለን መንቀሳቀስ ጀመርን፡፡ ጥያቄው ንጉሡ ከሥልጣን እንዲወድቁ ምክንያት መሆኑን በማሳየት ቀሰቀስን፡፡ ሕዝቡን ለማንቃት ታገልን፡፡ ነገር ግን ደርግ በቀይ ሽብር ዘመቻ ጨፈጨፈን፡፡
ያ ትውልድ ከተከሰሰ ባነሳቸው ጥያቄዎች ነው መከሰስ ያለበት፡፡ እኛ ያቀረብናቸውን ጥያቄዎች ለማስፈጸም ብዙ ወጣቶች ለጥይት ደረታቸውን ሰጥተው ታግለዋል፡፡ ብዙ ወጣቶች በመቀጠፋቸው እኔ በግሌ አዝኛለሁ፡፡ በተለይ ወላጆቻቸው ያሳዝናሉ፡፡ እኔ በግሌ በመጽሐፌም ይቅርታ ጠይቄያለሁ፡፡ ይህን ምናደርገው ግን ያነሳናቸው ጥያቄዎች ስህተት ናቸው በሚል አይደለም፡፡
እኛ ያነሳናቸውን ጥያቄዎች እኮ ይኼው ሳይመለሱ ተንከባለው የአሁኑ ዘመን ትውልድም እያነሳቸው ነው፡፡ የዚህ ዘመን ትውልድ ጥያቄዎቹ ስህተት ናቸው አይልም፡፡ እኛም በጊዜው ያነሳናቸው ጥያቄዎች ከዚህ የተለዩ አይደሉም፡፡ ወጣቶቹ እነዚህን ጥያቄዎች የእኔ ብለውና አምነውባቸው ነው ሕይወታቸውን ሰጥተው ሲያስተጋቧቸው የነበሩት፡፡ የአሁኑ ትውልድ ያን ትውልድ ቀድሞ የታገለልኝ ብሎ ማመሥገን ነው ያለበት፡፡ ደርግ ለእኩልነት የሚታገሉ ኅብረ ብሔራዊ ኃይሎችን በማጥፋት ብሔርተኛ ኃይሎች ጠንክረው ለሥልጣን እንዲበቁ አድርጓል፡፡ ብሔርተኞች ደግሞ ለራሳቸው የበላይነት ነው የሚታገሉት፡፡ እነሱ ሥልጣን ከያዙ ወዲህ በአማራ ላይ የደረሰውን መከራ አሳምረን የምናውቀው ነው፡፡ ዛሬ ድረስ ለተወራረሰው ችግር ደርግ የፈጠረው ችግር መዘለል የለበትም፡፡
ሪፖርተር፡- ኢትዮጵያ ታሪካዊ ጠላት አላት ይባላል፡፡ ኢትዮጵያ በባንዳና በአገር ወዳድ ኃይሎች መካከል ፍልሚያ ሲካሄድባት የኖረች አገር ናትም ይባላል፡፡ የኢትዮጵያ ጠላት ማነው? ከጠላት ጋር ተመሳጥሮ ኢትዮጵያን አሳልፎ የሰጣትስ ማን ነው?
አቶ ክፍሉ፡- ጠላታችንም ወዳጃችንም ዓባይ ወንዝ ነው፡፡ አሁን ዓባይን የኤሌክትሪክ ኃይል ለማመንጨት እየተጠቀምንበት ሲሆን፣ ወደፊት ደግሞ ዓሳና ሌላም ልማት ልንጠቀምበት እንችል ይሆናል፡፡ ነገር ግን በዓባይ ምክንያት ለረዥም ዘመን ስንጎዳ ኖረናል፡፡ እንግሊዝ በተለይ የዓባይ ውኃን ለረዥም ጊዜ ለራሷ ለመጠቀም ስትሞክር ኖራለች፡፡ ከአሜሪካና ከህንድ ታግዝ የነበረውን ጥጥ በማጣቷ እንግሊዝ ግብፅን በቅኝ ግዛት ለመያዝና በዓባይ ውኃ የሚበቅል ጥጥን ለመጠቀም ጥረት ጀመረች፡፡ ለዚህ ደግሞ የዓባይን ምንጭ መቆጣጠር አስፈላጊ ነው ብላ አመነች፡፡ በግብፅም ይሁን በሱዳኖች የሚደርስብን ጫና በከፊል እንግሊዞች የፈጠሩት ነው፡፡ እንግሊዝ ከዚህ በተጨማሪም በሶማሊያ በነበራት ቅኝ ግዛት ወደ ኢትዮጵያ ድንበር የሚሻገር ጊዜውን ጠብቆ ሚፈነዳ ቦምብ ቀብራ ነው የወጣችው፡፡ የኬንያ፣ የኢትዮጵያ፣ የጂቡቲና የሶማሊያ ሶማሌን በማዋሀድ ታላቅ አገር የመፍጠር ሐሳብን ለሶማሊያ ብሔርተኞች ያቀበለችው እንግሊዝ ናት፡፡ በእንግሊዞች በተተከለ መርዝ የተነሳ ብዙ ግጭትና ጦርነት ሲገጥመን ኖረናል፡፡
ሪፖርተር፡- አሁን ከተገባበት ቀውስ እንዴት መውጣት ይቻላል? ሦስተኛው ዙር ጦርነት ሰሞኑን ተጀምሯል፡፡ በየአካባቢውም ግጭት አለ፡፡ የኢትዮጵያ ሰላም እንዴት ይመለሳል?
አቶ ክፍሉ፡- ጦርነቱ ካሳጣን ውድ የሰው ሕይወት በዘለለ እጅግ ከፍተኛ ችግር አድርሶብናል፡፡ ጦርነቱ ለማንም አይበጅም፡፡ የዕቃዎች መጥፋት፣ የዋጋ ውድነት፣ የኑሮ መቃወስ ሁሉ ቀላል አይደለም፡፡ ነገር ግን የሕወሓት ኃይል በጦርነት አሸንፋለሁ ብሎ ያመነ ይመስላል፡፡ ሆኖም በእኔ ግምት የትግራይ ሕዝብ ነው ከማንም በከፋ ሁኔታ እየተጎዳ ያለው፡፡ አሁን ባለው ጦርነት ተገደን የገባንበት ቢሆንም፣ ነገር ግን ማንኛውም ዓይነት የሰላም አማራጭ ከተገኘ እሱን ለመጠቀም መሞከር አለበት፡፡ ለሰላም ብዙ ነገር መከፈል አለበት፡፡ ኢትዮጵያ ደቃለች፡፡ ለሰላም ሲባል ጉልበትን መጠቀም ይኖርብህ ይሆናል፡፡ ሆኖም ትንሽም ብትሆን የሰላም ቀዳዳ ከተገኘ በሚገባ ዕድሉን መጠቀም ያስፈልጋል፡፡