በፌዴራል መንግሥትና በሕወሓት መካከል ይካሄዳል ተብሎ ሲጠበቅ የነበረው ድርድር አቅጣጫውን ስቶ ጦርነት ሲጀመር፣ ሰብዓዊና ቁሳዊ ውድመት የሚያስከትለውን ጦርነት በእንጭጩ ለመቅጨት አስፈላጊው ሁሉ ርብርብ መደረግ አለበት፡፡ ለአምስት ወራት ያህል የቆየው የተኩስ አቁም ተጥሶ፣ እንደገና ለዕልቂትና ለውድመት የሚዳርግ የጦርነት ድግስ አያስፈልግም ሊባል ይገባል፡፡ በተኩስ አቁሙ ወቅት የነበረው አንፃራዊ ሰላም ተመልሶ ድርድሩ ያለ ምንም ቅድመ ሁኔታ መቀጠል ይኖርበታል፡፡ ከዚህ ቀደም ለማስታወስ እንደተሞከረው ጦርነት ማለት የንፁኃንን ሕይወት ያለ ምክንያት ለዕልቂት መዳረግና አገርን ከማትወጣበት ማጥ ውስጥ መክተት ነው፡፡ ከአንድ ዓመት በላይ በተካሄደው ጦርነት በንፁኃን ላይ የደረሱት ዕልቂት፣ አካላዊና ሥነ ልቦናዊ ጉዳት፣ መፈናቀል፣ መራብና መጠማት፣ የሰብዓዊ መብት ጥሰትና የመሳሰሉት የከፉ ድርጊቶች አይረሱም፡፡ በኢኮኖሚያዊና በማኅበራዊ መስኮች ያጋጠሙ ምስቅልቅሎችና የመሠረተ ልማት ውድመቶችም አይዘነጉም፡፡ አሁንም ለሰላም ዕድል ካልተሰጠ ለሕዝባችንም ሆነ ለአገራችን የከፋ ሁኔታ እንደሚፈጠር መጠራጠር አይገባም፡፡ ከሰላም እንጂ ከጦርነት ምንም ዓይነት መፍትሔ አይገኝም፡፡
ለሰላም የሚከፈለው ዋጋ ተከፍሎ የአውዳሚውን ጦርነት ህልውና ማክተም ሲገባ፣ እንደገና ለሌላ ዙር ዕልቂትና ጥፋት የሚዳርግ አደገኛ ምዕራፍ ውስጥ እየተገባ ነው፡፡ የማንኛውም ጦርነት ማጠናቀቂያ ድርድር በመሆኑ ለዚህ የሚረዳ እንቅስቃሴ በተጀመረ ማግሥት፣ አሁንም እንደገና ንፁኃንን የሚፈጅና የደሃ አገር ጥሪት እሳት ውስጥ የሚከት አውዳሚ ጦርነት ውስጥ መግባት ከጤነኛ አዕምሮ የሚጠበቅ ተግባር አይደለም፡፡ ከጥቅምት 4 ቀን 2013 ዓ.ም. ጀምሮ በትግራይ፣ በአማራና በአፋር ክልሎች በተካሄደው የጥፋት ጦርነት በአገር ላይ የደረሰው ሰቆቃ የሚረሳ አይደለም፡፡ ሕፃናት፣ እናቶች፣ አባቶች፣ አቅመ ደካሞችና ወጣቶች ያለቁበትና ከፍተኛ ጉዳት ያደረሰባቸው ቁስል ሳይጠግ እንደገና የጦርነት ነጋሪት ሲጎሰም ይዘገንናል፡፡ በፌዴራል መንግሥትና በሕወሓት መካከል ሊደረግ የታሰበው ድርድር ለሰላም ተስፋ ይዞ መምጣት ሲገባው፣ አሁንም እዚያው የጥፋት ማዕበል ውስጥ መገኘት ያስከፋል፡፡ በአሁኑ የኢትዮጵያ ነባራዊ ሁኔታ ብቻ ሳይሆን በዓለም አቀፍ ደረጃ ከሚስተዋለው ዘርፈ ብዙ ችግር አኳያ፣ ሰላምን ወደ ጎን ገፍትሮ ጦርነት በመቀስቀስ እንደገና ዕልቂት መደገስ አስከፊ ነው፡፡
ኢትዮጵያን የሰላም፣ የፍትሕና የነፃት አገር ማድረግ የሚቻለው በሰላማዊ የፖለቲካ ትግል እንጂ፣ አሁን እንደሚታየው ጦርነት ቀስቅሶ ሕዝቡን ደም በሚያቃቡ ጀብደኞች ፍላጎት አይደለም፡፡ ከሰላማዊ የፖለቲካ ትግል በማፈንገጥ አገርን የጦርነት አውድማ ማድረግ ከጥፋት በስተቀር ትርፍ የለውም፡፡ ሕዝቡን ከድህነት ማጥ ውስጥ ለማውጣት የሚያስፈልገው ማኅበራዊ ፍትሕ የሰፈነበት ሥርዓት ብቻ ነው፡፡ ይህ ሥርዓት የሚገነባው በሠለጠነ አስተሳሰብ እንጂ ዘመን ባለፈበት አስተሳሰብና በጠመንጃ አምላኪነት አይደለም፡፡ ለአገር የሚበጅ ሥርዓት ዕውን ሊሆን የሚችለው በሕዝብ ይሁንታ እንጂ በጀብደኝነት አይደለም፣ ሆኖም አያውቅም፡፡ ለዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታ በማይመጥን ኋላቀር አስተሳሰብና በጀብደኝነት መንፈስ ለሕዝብ ቆሜያለሁ ማለት ቀልድ ነው፡፡ ለሥልጣን ሲባል ብቻ የጦርነት ነጋሪት እየጎሰሙ በሕዝብ ስም መነገድ የለየለት ቁማርተኝነት ነው፡፡ የሰላማዊ ዜጎችን ሕይወት አደጋ ውስጥ በመክተት ዓላማን ለማሳካት የሚደረግ አደገኛ ሙከራ መቀልበስ አለበት፡፡ ከጦርነት ውድመት እንጂ ልማት አይገኝም፡፡ የሰላም አማራጭን በመተው ጦርነት ላይ መቸከል የለየለት ቁማርተኝነት ነው፡፡
ማንም ቢሆን ልብ ሊለው የሚገባ ዋና ጉዳይ፣ የኢትዮጵያን ህልውና ለምንም ነገር መደራደሪያ ማድረግ እንደማይቻል ነው፡፡ ጠባብ ቡድናዊ ፍላጎትን በማስቀደም ሰላሟን መፈታተን ጠላትነት ነው፡፡ ከውስጥም ሆነ ከውጭ ሆኖ በማሴር ቀውስ መፍጠር የኢትዮጵያውያን መገለጫ አይደለም፡፡ ኢትዮጵዊውያን ፍላጎታቸውን ከኢትዮጵያ ህልውና በታች አድርገው፣ የፈለጉት ጥያቄ በሰላማዊ መንገድ ማቅረብ ይችላሉ፡፡ በኢትዮጵያ ዘርፈ ብዙ ጉዳዮች መሳተፍ የሚችሉትም፣ ብሔራዊ ደኅንነቷንና ጥቅሞቿን ሳይጎዱ ብቻ ነው፡፡ የኢትዮጵያ ሕዝብ በአገሩ ህልውና ላይ የመጣን ማንኛውንም ጥቃትም ሆነ ሴራ ስለማይታገስ፣ ከአጥፊና ከአውዳሚ ድርጊቶች መታቀብ ይገባል፡፡ የኢትዮጵያ ህልውና ሲነካ እጁን አጣጥፎ የሚቀመጥ የለምና፡፡ ኢትዮጵያን ከሥልጣን፣ ከጥቅማ ጥቅም፣ ውሉ ከማይታወቅ በጀብደኝነት ከተሞላ የቡድንተኝነት ስሜት፣ ከክልላዊ ወሰን ጥበትና ስፋት፣ ከማንነትና ከሃይማኖታዊ አጥር፣ ከዓርማዎችና ከምልክቶች ልክፍት፣ እንዲሁም መያዣና መጨበጫ ከሌላቸው ዘመኑን ከማይመጥኑ ዕሳቤዎች በላይ ማክበር ይገባል፡፡ አንድነቷ እንደ ብረት የጠነከረ፣ ዘላቂና አስተማማኝ ሰላም ያላት፣ በኢኮኖሚ የዳበረችና ለሁሉም ሕዝቧ የምትመች ዴሞክራሲያዊት አገር መገንባት የሚቻለው በዚህ ቁመና ላይ መገኘት ሲቻል ብቻ ነው፡፡
አገር ችግር ሲያጋጥማት ዜጎች የመጀመሪያ ተግባራቸው ለመፍትሔ የሚረዱ ሐሳቦችን ማመንጨት ነው፡፡ በዕውቀት ላይ የተመሠረቱ የመፍትሔ ሐሳቦች ከተለያዩ አቅጣጫዎች እንዲመጡ ደግሞ መድረክ ያስፈልጋል፡፡ ለምሳሌ አገራዊ የምክክር መድረኩ የሚረዳው፣ ገንቢ ሐሳቦች ቀርበው የተሻለውን አማካይ ሐሳብ ሥራ ላይ በማዋል ችግርን ለመፍታት ነው፡፡ እያንዳንዱ ችግር መንስዔ ስላለው የሚያስከትለው ውጤትም በዚህ ላይ ይመሠረታል፡፡ መንስዔና ውጤትን በመተንተን ምክንያታዊ የሆኑ ሐሳቦች ለማፍለቅ መነጋገር ያስፈልጋል፡፡ ከዚህ ቀደም የሰዎች አስተሳሰብ እንዲዘምንና ሐሳብን መለዋወጥ ባህል እንዲሆን ባለመሠራቱ፣ አንድ ችግር ሲያጋጥም ተነጋግሮ መፍትሔ ለማፍለቅ ከመትጋት ይልቅ ዱላ መምዘዝ የተለመደ ነው፡፡ ጠንካራ የዴሞክራሲና የሙያ ተቋማት በሌሉበትና ብዙዎቹ መንግሥታዊ ተቋማት ልፍስፍስ በሆኑባት ኢትዮጵያ፣ አስተሳሰብን ለማዘመን ቀርቶ መለስተኛ የሚባሉ ቅራኔዎችን ለማርገብ ፈቃደኝነት የለም፡፡ በዚህም ምክንያት ግጭትን ወይም ጦርነትን ሙጥኝ በማለት ዓላማን ለማስፈጸም ጥድፊያው ይበረታል፡፡ ይህ ለዘመኑ የማይመጥን አስተሳሰብ አገር ለማፍረስ እንጂ ለማልማት አይጠቅምም፡፡
ከዚህ ቀደም የዕልቂት ምክንያት የነበረው አውዳሚ ጦርነት ሁለት ዓመታት ሊሞሉ ጥቂት ጊዜ ነው የቀሩት፡፡ በዚህ ጊዜ ውስጥ በሺዎች የሚቆጠሩ ኢትዮጵያዊያን ሞተዋል፣ በሚሊዮኖች የሚቆጠሩት ደግሞ ከአካላዊና ከሥነ ልቦናዊ ጉዳት በተጨማሪ ተፈናቅለው ሜዳ ላይ ወድቀዋል፣ ግምቱ እጅግ በጣም ከፍተኛ የሆነ የአገር ሀብት ወድሟል፡፡ የወጣቶች አገር የሆነችው ኢትዮጵያ በተፈጥሮ የተለገሰቻቸው ፀጋዎች ለምተው እጅግ አስመራሪ ከሆነው ድህነት መገላገል ሲገባት፣ ወጣቶቿ ግራና ቀኝ ተሠልፈው አውዳሚ ጦርነት ውስጥ ሆነው እየተፋጁ ነው፡፡ ሰላም እንዲሰፍን ቀንና ሌሊት በሚለመንባት አገር ውስጥ በተራዘመ ጦርነት መረጋጋት ጠፍቷል፡፡ ጦርነቱን በፍጥነት በመጨረስ ሰላም ለማስፈን ከፍ ያለ ፍላጎት ቢኖርም፣ ከጦርነት ውስጥ ለመውጣት የሚረዳ መፍትሔ ማቅረብ አልተቻለም፡፡ አሜሪካን ጨምሮ ምዕራባውያንና ሌሎች ኃይሎች ጥቅማቸውን እያሰቡ ራሳቸውን ለጣልቃ ገብነት ከማመቻቸት ውጪ፣ ይህ ነው የሚባል የረባ መፍትሔ ይዘው መቅረብ አልቻሉም፡፡ ይልቁንም ለጣልቃ ገብነት እንዲመቻቸው በማሰብ ‹‹የዕብድ ገላጋይ›› ለመሆን ነው የሚቅበዘበዙት፡፡ ኢትዮጵያውያን ይህንን አደገኛ ሁኔታ በመገንዘብ በአንድነት ለመቆምና ሰላም ለማስፈን የሚረዱ ምክረ ሐሳቦች ላይ ያተኩሩ፡፡ ከጦርነት መቼም ቢሆን መፍትሔ አይገኝም!