Tuesday, March 28, 2023
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

የአማራ ክልል የጫት ፍጆታን ለመግታት በኪሎ የሚታሰብ ቀረጥ ጣለ

- ማስታወቂያ -

ተዛማጅ ፅሁፎች

የአማራ ክልል ‹‹በፍጥነት እያደገ ያለውን የጫፍ ፍጆታ›› ለመግታት ያግዛል ያለውን ቀረጥ፣ ወደ ገበያ በሚቀርብና በሚጓጓዝ የጫት ምርት ላይ ጣለ፡፡

የክልሉ የገንዘብ ቢሮ አውጥቶት፣ ካለፈው ሳምንት ጀምሮ ተግባራዊ መሆን የጀመረው ከጫት ምርት ላይ ቀረጥ መሰብሰቢያ መመርያ፣ ከአንድ ኪሎ ጫት 30 ብር ቀረጥ እንዲሰበሰብ ያዛል፡፡

በጫት ላይ የተጣለው ይኼ ቀረጥ፣ በጫት ንግድ ሥራ ላይ የተሰማሩ ግብር ከፋዮች ጫቱን ለተጠቃሚዎቻቸው ሲሸጡ ለመንግሥት ከሚያስገቡት የንግድ ትርፍ፣ ተጨማሪ እሴትና ተርን ኦቨር ታክሶች በተጨማሪ ነው፡፡

የክልሉ መንግሥት በ2003 ዓ.ም. የጫት ምርት ቀረጥ ለማስከፈል ያወጣው አዋጅ ከአሥር ዓመት በላይ ቢሆነውም፣ እስካሁን ድረስ አዋጁን ማስፈጸሚያ መመርያ አለመውጣቱ ለአዲሱ መመርያ መዘጋጀት በምክንያትነት ተጠቅሷል፡፡

ከዚህ በተጨማ የኅብረሰተቡን ደኅንነት መጠበቅና እያደገ የመጣውን የጫት ፍጆታ መግታት የቀረጡ ዓላማ መሆኑን በመመርያው ተመልክቷል፡፡ በመመርያው መግቢያ ላይ፣ ‹‹በክልሉ ውስጥ የጫት ፍጆታ በከፍተኛ ፍጥነት እያደገ በመሄዱ፣ ይህንን ሁኔታ ለመለወጥ የሚያግዝ የጫት ምርት ቀረጥ ክፍያ ማስቀመጥ አስፈላጊ ሆኖ መገኘቱ›› ተብሎ ሠፍሯል፡፡

የክልሉ መንግሥት ከጫት ምርት ላይ ቀረጥ ለመሰብሰብ ካቀደባቸው ሥፍራዎች የመገበያያ ቦታዎች ይጠቀሳሉ፡፡ ለዚህም ሲባል የክልሉ ከተሞችና ወረዳዎች የጫት ምርት ተመርቶ ግብይት የሚፈጸምባቸውን ቦታዎች ለይተው የማሳወቅ ኃላፊነት ተጥሎባቸዋል፡፡

በተጨማሪም ነጋዴዎች የጫት ምርት በእንስሳትም ሆነ በተሽከርካሪ ጭነው ሲያጓጉዙ በተገኙበት ቦታ በኪሎ 30 ብር ቀረጥ ለመክፈል እንደሚገደዱ መመርያው አስቀምጧል፡፡ እነዚህ ነጋዴዎች የተቀረጡበትን ጫት ይዘው በማግሥቱ ሌላ ከተማ እያጓጓዙ ከተገኙም በድጋሚ ቀረጥ ይከፍላሉ፡፡

የኢትዮጵያ ስታትስቲክስ አገልግሎት የ2012 ዓ.ም. መረጃ እንደሚያሳየው፣ በአማራ ክልል ውስጥ የሚገኙ ከ235 ሺሕ በላይ አርሶ አደሮች በዓመቱ 10,886 ሔክታር መሬት ላይ ጫት አምርተዋል፡፡ በዚህም ከ68 ሺሕ ኩንታል በላይ የጫት ምርት አግኝተዋል፡፡ በዚህ ምርት መሠረት አሁን የተጣለው ቀረጥ ሲሰላ የክልሉ መንግሥት ከ204 ሚሊዮን ብር በላይ ገቢ ከቀረጥ ብቻ ማግኘት ይችላል፡፡

የክልሉ ገንዘብ ቢሮ በመመርያው ላይ ማጭበርበሮችን ለመከላከል ሲባል የተቀረጡ ነጋዴዎች የሚሰጣቸው ደረሰኝ ላይ ቀረጡ ተፈጻሚ የሆነበትን ሰዓት ደረሰኙ ላይ በመጻፍ ምልክት እንዲያደርጉ አዟል፡፡ ቀረጡ ተፈጻሚ የሆነበት ሰዓት የተጻፈበት ይኼ ደረሰኝ ቀረጥ በከፈለበት ከተማ ወይም ወረዳ ላይ የሚያገለግለው፣ ከተቆረጠበት ጊዜ ጀምሮ ለሁለት ሰዓት ብቻ እንደሆነም በመመርያው ላይ ተገልጿል፡፡

ኢትዮጵያ ወደ ውጭ ልካ ከፍተኛ የውጭ ምንዛሪ ከምታገኝባቸው ምርቶች ውስጥ አንዱ የሆነው ጫት በተጠናቀቀው የበጀት ዓመት 392 ሚሊዮን ዶላር አስገኝቷል፡፡ ይኼ ገቢ ከጫት 402 ሚሊዮን ዶላር ገቢ ከተገኘበት ከቀደመው በጀት ዓመት ጋር ሲነፃፀር በ2.5 በመቶ ያንሳል፡፡

የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር ከጫት ምርት የሚገኘውን ገቢ ለመጨመር እየሠራ መሆኑን በተደጋጋሚ እየገለጸ ሲሆን፣ ግንቦት 2014 ዓ.ም. ላይ 830 የጫት ላኪ ድርጅቶች ላይ ከጊዜያዊ የንግድ ፈቃድ ዕገዳ አንስቶ እስከ መሰረዝ የደረሰ ዕርምጃ ወስዶ ነበር፡፡

የኮንትሮባንድ ንግድ ጫት ወደ ውጭ ተልኮ የሚገኘውን ገቢ እያስቀረ እንደሆነ የሚገልጸው ሚኒስቴሩ፣ አሁን በተጀመረው የ2015 በጀት ዓመት በሐምሌ ወር ብቻ 30.9 ሚሊዮን ብር የሚያወጣ ጫት በኮንትሮባንድ ከአገር ሊወጣ ሲል መያዙን አስታውቋል፡፡

የአማራ ክልል በበኩሉ ለጫት ምርት የሚሰጠውን ትኩረት እየቀነሰ ነው፡፡ ሪፖርተር ያነጋገራቸው የክልሉ የንግድና ግብይት ቢሮና የግብርና ቢሮ ኃላፊዎች በቢሮአቸው የጫት ምርት ምርትና ግብይትን እንደማይከታተሉና የተጠናቀረ መረጃ እንደሌላቸው ገልጸዋል፡፡

የክልሉ የግብርና ቢሮ የሰብል ምርት ዳይሬክተር አቶ አለባቸው አሊጋዝ፣ በክልሉ የሚገኙ የጫት እርሻዎችን ‹‹እየነቀሉ›› በሌሎች የሰብል ምርቶች የመተካት ሥራ እየተከናወነ መሆኑን ገልጸው፣ በዚህም የተነሳ ቢሮአቸው የጫት ምርትን እንደማይከታተል አስረድተዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች