ዳግም የተቀሰቀሰው ግጭት እንዲረጋጋ እና የተጀመረው የሰላም ሂደት እንዲቀጥል ተጠየቀ ይህን የጠየቀው የኢትዮጵያ ሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ምክር ቤት ነው፡፡
የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ምክር ቤቱ በሰሜኑ የኢትዮጵያ ክፍል መልሶ ያገረሸው የትጥቅ ግጭት በእጅጉ እንደሚያሳስበዉ አስታዉቋል፡፡
ከዚህ በፊት የተፈጠረው የትጥቅ ግጭት ተነግሮ የማያልቅ የሰው ልጅ ስቃይ እና ከፍተኛ መሰረተ ልማቶች መውደም ምክንያት መሆኑንም ምክር ቤቱ ገልጿል፡፡
በመሆኑም አሁን ዳግም የተቀሰቀሰው የትጥቅ ግጭት እንዲረጋጋና ግጭቱ እንዳይባባስ አስፈላጊው ሁሉ እንዲደረግ ምክር ቤቱ አጥብቆ ያሳስባል ሲል ለመገናኛ ብዙሃን በላከው መግለጫው አስታዉቋል።
በተጨማሪም አስቸኳይ የሰብዓዊ ተኩስ አቁሙ መከበር ለሰብአዊ ዕርዳታ አቅርቦት ቀጣይነት እና ለሰላም ሂደቱ ስኬታማነት ወሳኝ እንደሆነ እንደሚያምን ተናግሯል።
ምክርቤቱ አለመግባባቶች በፖለቲካዊ ውይይት መፈታት እንዳለባቸው በጥብቅ እንደሚያምንና ለዚህም የሰላም ማስፈን ሂደቱ በአስቸኳይ እንዲቀጥልና ሀገሪቱን ከተጨርማሪ ጥፋት ለመታደግ የሰላም ሂደቱ በቅን ልቦና እንዲካሄድ ጠይቋል።