Tuesday, March 28, 2023

የኢትዮጵያ ወጣቶች ከትናንት እስከ ዛሬ

- Advertisement -spot_img

በብዛት የተነበቡ

እ.ኤ.አ. ግንቦት 2013 በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት አፍሪካ ሪኒዋል ድረ ገጽ ላይ ኪንግስሌ ኢግቦር ያስነበቡት ጽሑፍ፣ ኢትዮጵያን ጨምሮ የአፍሪካ አገሮች የተጋፈጡትን ችግር በሚገባ ያሳያል፡፡ ‹‹Africans Youth a [Ticking Time Bomb›› or an Opportunity?›› ወይም ‹የአፍሪካ ወጣት ጊዜ ጠብቆ የሚፈነዳ ቦምብ ወይስ ዕድል?› በሚል ርዕስ የተነበበው ይህ ዘገባ፣ አኅጉሪቱ እየጨመረ በመጣው የወጣቶች ቁጥር እንዴት እንደምትፈተን በሚገባ ያመለክታል፡፡

ከዓለም አሥር ፈጣን የኢኮኖሚ ዕድገት አስመዝጋቢ አገሮች ውስጥ ስድስቱ ከሰሃራ በታች ባሉ የአፍሪካ አገሮች የሚገኙ ናቸው፡፡ ነገር ግን በአፍሪካ ካለው የሥራ አጥ ቁጥር ውስጥ 60 በመቶው ወጣት ነው ይላሉ ኪንግስሌ ኢግቦር በሐተታቸው፡፡ ጸሐፊው በሴኔጋል የተፈጠረውን ሁኔታ ማሳያ የሚያደርጉት የወጣቶች የሥራ አጥ ቁጥር በአኅጉሩ መጨመር ምን ዓይነት የፖለቲካ አደጋ እንደሚጋብዝ ሊያሳዩ ይሞክራሉ፡፡

በሴኔጋል እ.ኤ.አ. በ2021 የፖለቲካ ተቀናቃኝ ኃይሎች አንዳቸው በሌላው ላይ ተቃውሞ ሲነሱ፣ ወጣቶችን በማደራጀት ማሠለፍ ጀመሩ ይላል ዘገባው፡፡ የዓለም ባንክ ከዚህ የፖለቲካ ቀውስ ጥቂት ቀደም ብሎ በሴኔጋል ባደረገው የዳሰሳ ጥናት፣ 40 በመቶ የሚሆኑ የዚያች አገር ወጣቶች ሥራ በማጣት ተስፋ ቆርጠው ወደ ተቃውሞና አመፅ መቀላቀላቸውን አረጋግጦ ነበር ይላል ዘገባው፡፡

በአፍሪካ 70 በመቶ የሚሆኑ ወጣቶች በቀን ከሁለት ዶላር በታች በሆነ ገቢ አስከፊ ሕይወትን እንደሚመሩ ያመለከተው ዘገባው፣ ይህ የኑሮ ሁኔታ ተስፋ እያስቆረጣቸው ወደ ቀውስ ሕይወት የሚከታቸው ወጣቶች በርካታ መሆናቸውን ይጠቁማል፡፡

ኢትዮጵያን ጨምሮ የአፍሪካ አገሮች የማደግም ሆነ የመጥፋት ዕድላቸው በወጣቱ ሕዝባቸው ላይ የተመሠረተ ነው ይባላል፡፡ ወጣቱ ትኩስ የሥራ ኃይል ተገቢና አሠሪ ፖሊሲዎችን ቀርፆ የሚያሰማራው ካገኘ፣ ዋነኛው የአገር ኢኮኖሚ አንቀሳቃሽ ሞተር የሚሆንበት ዕድል ሰፊ ነው፡፡ በተቃራኒው ግን ከፖለቲካ ተሳትፎ ወጣቱን በማግለል ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ዕድሎችን የሚዘጉበት ከሆነም፣ ወጣቱ ባልተፈለገ አቅጣጫ በማምራት ለአገር ውድመት ምክንያት እንደሚሆን በርካቶች ይገምታሉ፡፡

ኢትዮጵያን ጨምሮ የአፍሪካ አገሮች ለወጣቱ ሰፊ ሕዝባቸው አንቀሳቃሽ ፖሊሲና ምቹ ሁኔታ በመቅረፅ ረገድ፣ ብዙ ጉድለት እንዳለባቸው የሚናገሩ ብዙ ናቸው፡፡

አንጋፋው የፖለቲካ ሰው አቶ ክፍሉ ታደሰ፣ ‹‹በኢትዮጵያ በአንዳንድ መረጃዎች 60 በመቶ ይሆናል ተብሎ የሚገመተው ወጣቱ ትውልድ ተገቢው ትኩረት አልተሰጠውም፤›› ሲሉ ይናገራሉ፡፡ የ‹‹ያ ትውልድ›› ተከታታይ ቅጽ መጽሐፎች ደራሲ፣ እንዲሁም ወጣቶችን በሰፊው በማደራጀት ስሙ የሚጠራው የኢትዮጵያ ሕዝብ አብዮታዊ ፓርቲ (ኢሕአፓ) መሥራችና አመራር የነበሩት አቶ ክፍሉ፣ የአሁኑ ትውልድ ወጣት እጅግ ብዙ ፈተናዎች ያሉበት መሆኑን ነው የሚናገሩት፡፡ በተለይም ከችግሮቹ ትልቁ የሆነው ‹‹የወጣቱ የሥራ ዕጦት ተገቢው ትኩረት አልተሰጠውም፤›› በማለት ያስረዳሉ፡፡

‹‹ወጣቱ ምን ያህል እንደተቸገረ ለማወቅ ብዙ መጓዝ አይጠይቅም፡፡ በየመንገዱ፣ በየቀበሌውና በየአካባቢያችን የምናየው ነው፡፡ በየዓመቱ ከዩኒቨርሲቲዎች፣ ከኮሌጆችና ከቴክኒክና ሙያ ትምህርት ቤቶች ብዙ ወጣቶች መመረቃቸውን እንሰማለን፡፡ ነገር ግን ከእነዚህ ውስጥ ምን ያህሉ ሥራ እንደሚያገኙ አይታወቅም፡፡ የአገራችንን ወጣቶች ችግር መፍታትና መርዳት ለነገ የሚባል ጉዳይ አይደለም፤›› ሲሉ ነው አቶ ክፍሉ የሚናገሩት፡፡

‹‹ወጣቱ ተበላሽቷል፣ ለአጉል ነገርና ለሱስ ተጋላጭ ሆኗል ብሎ መፈረጅ ተገቢ አይደለም፤›› ሲሉ የሚያክሉት አቶ ክፍሉ፣ በኑሮ አስገዳጅነትና በተስፋ ማጣት ለመጥፎ ነገሮች ተጋላጭ እንደሚሆን አብራርተዋል፡፡ ኢትዮጵያን ጨምሮ በሌሎች የአፍሪካ አገሮች ብዙ ወጣቶች ዕድል በማጣታቸው፣ ሕይወታቸው ወደ መጥፎ መንገድ እንደሚገባ ጥናቶች ይጠቁማሉ ሲሉ ያክላሉ፡፡

እ.ኤ.አ. በ2015 እና በ2018 ‹Jobs for Youth in Africa› በሚል ርዕስ የአፍሪካ ልማት ባንክ ባወጣቸው ሪፖርቶች ይህንኑ የሚደግፉ መረጃዎች ይሰጣሉ፡፡ ከዓለም ብዙ ወጣት ሕዝብ ካላቸው 40 አገሮች ውስጥ 36 የሚሆኑት በአፍሪካ ይኖራሉ ይላል ሪፖርቱ፡፡ ከአፍሪካ 1.2 ቢሊዮን ሕዝብ ውስጥ ደግሞ 420 ሚሊዮን የሚሆኑት ከ15 እስከ 35 የዕድሜ ክልል ውስጥ ያሉ ወጣቶች ናቸው ይላል፡፡ በየዓመቱ በአፍሪካ ከ10 እስከ 12 ሚሊዮን የሚሆኑ ወጣቶች ወደ ሥራ ገበያው እንደሚቀላቀሉ የሚጠቅሰው የአፍሪካ ልማት ባንክ ሪፖርት፣ ከእነዚህ ውስጥ ሦስት ሚሊዮን ብቻ ሥራ ለማግኘት እንደሚበቁ ነው የሚያብራራው፡፡

አሁን ከ420 ሚሊዮን የአፍሪካ ወጣቶች ውስጥ አንድ ሦስተኛ የሚሆኑት ሥራ አጥ ናቸው የሚለው የአፍሪካ ልማት ባንክ እ.ኤ.አ. 2025 ሪፖርት ደግሞ፣ ይህ ቁጥር እያደገ በመሄድ ወደ 263 ሚሊዮን ወጣቶች የኑሮ መሠረት (ሥራ) የሌላቸው እንደሚሆኑ ይተነብያል፡፡ ‹‹የወጣቶች ጥያቄ ጊዜ ጠብቆ የሚፈነዳ ቦምብ ነው›› በአፍሪካ የሚል ጽሑፍ ያስነበቡት ኪንግስሌ ኢግቦርም ቢሆንም፣ ከአፍሪካ ሥራ አጦች ውስጥ 60 በመቶ ወጣቶች መሆናቸውን ይናገራሉ፡፡ የወጣቶች ሥራ አጥነት ደግሞ በየዓመቱ በ30 ከመቶ እያደገ የሚሄድ ችግር ነው ይሉታል፡፡

የኢሕአፓው አንጋፋ ፖለቲከኛ አቶ ክፍሉ ታደሰ የተማሪዎች የፖለቲካ እንቅስቃሴ በኢትዮጵያ ጎልቶ መነሳት በጀመረበት በ‹ያ ትውልድ›› ዘመን፣ ሥራ አጥነት አንዱ ማኅበራዊ ችግር መሆን የጀመረበት ወቅት እንደነበረ ያስታውሳሉ፡፡

‹‹በዚያ ጊዜ የሚመረቁ አንዳንድ ወጣቶች ለሁለትና ለሦስት ወራት ሥራ ለማግኘት ይቸገሩ ነበር፡፡ በጊዜው በኢትዮጵያ ከፍተኛ የሥራ አጥነት ችግር አለ ተብሎ ይነገር ነበር፡፡ ይህ ሁኔታ አሁን ካለው አገራዊ ሁኔታ ጋር ሲነፃፀር ቅንጦት ነበር ማለት እችላለሁ፡፡ የአሁን ዘመን ወጣት አይደለም ሁለትና ሦስት ወራት በሁለት ዓመትም ሥራ ለማግኘት ሲቸገር እያየን ነው፤›› በማለት፣ የወጣቶች ችግር ባለፉት 50 ዓመታት በኢትዮጵያ እየከፋ መምጣቱን አቶ ክፍሉ የሚናገሩት፡፡

እንደ ኢትዮጵያ ባሉ የአፍሪካ አገሮች ወጣቶች የኑሮ መሠረት (ሥራ) በማጣታቸው ለፍልሰት ሕይወት እንደሚዳረጉ ይነገራል፡፡ የሞ ኢብራሂም ፋውንዴሽን በ2020 ባወጣው ሪፖርት የተማሩ የአፍሪካ ወጣቶች ሥራ በማጣት ወደ በለፀጉ አገሮች እንደሚኮበልሉ ይገልጻል፡፡ እ.ኤ.አ. በ2015 በአሜሪካ ከተቀጠሩ ሐኪሞች ውስጥ 86 በመቶዎቹ እንደ ግብፅ፣ ጋና፣ ናይጄሪያና ደቡብ አፍሪካ ካሉ አገሮች ለሥራ ፍለጋ የኮበለሉ ናቸው የሚለው ሪፖርቱ፣ በዚህ የተነሳ አፍሪካ ለተማረ የሰው ኃይል ፍልሰት (Brain Drain) ተጋላጭ መሆኗን ያትታል፡፡ በአፍሪካ እ.ኤ.አ. በ2030፣ 30 ሚሊዮን ወጣት ሥራ ፈላጊ ይኖራል ይባላል፡፡ ወጣቱን ሥራ ለማስያዝ ደግሞ በዓመት 18 ሚሊዮን የሥራ ዕድል መፍጠር ያስፈልጋል ይላል ሪፖርቱ፡፡ አሁን ግን በየዓመቱ በአፍሪካ የሚፈጠረው የሥራ ዕድል ከሦስት ሚሊዮን በላይ እንዳልሆነ የሚናገረው የሞ ኢብራሂም ፋውንዴሽን፣ እ.ኤ.አ. በ2017 በአፍሪካ ከሚንቀሳቀሱ ፅንፈኛ የትጥቅ ቡድኖች አባላት መካከል 53 በመቶዎቹ ሥራ አጥተው ተስፋ በመቁጥረ የተቀላቀሉ ወጣቶች መሆናቸውን ያትታል፡፡

‹‹የአፍሪካ ወጣቶች ዕድል በማጣት ሥራ ፍለጋ ወደ በለፀጉ አገሮች ይሰደዳሉ፡፡ ካልሆነም የትጥቅ ቡድኖችን በመቀላቀል በጦርነት ይማገዳሉ፡፡ የሚለው ሪፖርቱ›› 60 በመቶ የአኅጉሩ ወጣቶች መንግሥታቶቻቸው የእነሱን ችግር ለመፍታት በቂ ጥረት እያደረጉ ነው ብለው እንደማያምኑም ያመለክታል፡፡

ይህን መረጃ የሚደግፍ አስተያየት የሚሰጡት የኢሕአፓው ፖለቲከኛ አቶ ክፍሉ፣ ‹‹የወጣቱን ችግር የሚያዳምጥ ሥርዓት በኢትዮጵያ ኖሮ አያውቅም፤›› ሲሉ ይናገራሉ፡፡ ‹‹በኢትዮጵያ የሕዝብ ችግር የሚያዳምጥ የፖለቲካ ሥርዓት ተፈጥሮ አያውቅም፡፡ ወጣቱ ቢጠየቅ የሚፈልገውን ይናገራል፡፡ አብዛኛው ወጣት ተምሮ ወይ ሥራ አግኝቶ ኑሮውን መለወጥ እንደሚፈልግ ይናገራል፡፡ ወጣቱ ማንም ያገኘውን ዕድል ማግኘት ነው የሚፈልገው፤›› በማለትም ይገልጻሉ፡፡

በኢትዮጵያ የወጣቶችን ሕይወት ለመለወጥ የሚያስችሉ እጅግ በርካታ ዕድሎች መኖራቸውን የሚናገሩት አቶ ክፍሉ፣ ‹‹ኢትዮጵያ ታርሶ ሊለማ የሚችል ሰፊ መሬት አላት፤›› ሲሉ ይናገራሉ፡፡ ያኔ እሳቸውና የዕድሜ አቻዎቻቸው ‹መሬት ለአራሹ› በሚል መፈክር ለፖለቲካ ለውጥ ሲታገሉ መቆየታቸውን ያስታወሱት አቶ ክፍሉ፣ ይህ እንቅስቃሴ በአሁኑ ትውልድ በሥራ ፈጠራ እንዲደገም በማሰብ ‹መሬት ለወጣቱ› የሚል አነሳሽ የሆነ ጽሑፍ በቅርቡ በፍትሕ መጽሔት እንዳስነበቡ ተናግረዋል፡፡

ወጣቱ ትውልድ በኢትዮጵያ የአዲስ ሐሳብና የለውጥ መንስዔ እንደሆነ ተደጋግሞ ይነገራል፡፡ የአሜሪካ ዓለም አቀፍ የልማት ዕርዳታ ድርጅት (USAID)፣ የወጣቶች ልማት በኢትዮጵያ በሚል እ.ኤ.አ. በ2017 ያወጣው ሪፖርት ብዙ አመልካች አኃዞችን ያስቀምጣል፡፡ ከ105 ሚሊዮን የኢትዮጵያ ሕዝብ ውስጥ 40.5 በመቶ ዕድሜው ከ15 እስከ 30 የሚሆን ወጣት ነው፡፡ ነገር ግን አብዛኛው የኢትዮጵያ ወጣት የአንደኛ ደረጃ ተማሪ ቤትን እንኳ የመጨረስ ዕድል እንደሌለው የድርጀቱ ሪፖርት ይገልጻል፡፡ የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ተሳትፎ ከ30 በመቶ በታች ነው የሚለው ሪፖርቱ፣ እ.ኤ.አ. በ2017 የቴክኒክና ሙያ (TVET) ተሳትፎ ከቀደመው ዓመት በ14 ከመቶ የቀነሰ ሆኖ እንደተገኘ ያትታል፡፡ ሪፖርቱ ሲያክልም በኢትዮጵያ 27 በመቶ ያህል ወጣቶች ሥራ አጥቶ ከመቀመጥ በሚል ብቻ ውጤታማ ባልሆኑበት የሙያ ዘርፍ ለመሥራት ይገደዳሉ በማለት ያስረዳል፡፡

ይህ ሁሉ ሪፖርት የኢትዮጵያ ወጣቶች ልክ እንደ ሌሎች ታዳጊ አገሮች የተጋፈጧቸው ችግሮች ቀላል አለመሆናቸውን አመላካች መሆናቸውን ብዙዎች ይናገራሉ፡፡ ይህ ሁሉ መሠረታዊ ችግር ባለበት ሁኔታ ደግሞ የኮሮና ወረርሽኝ ተፅዕኖ፣ እንዲሁም ግጭትና ጦርነት በአገሪቱ ያስከተሉት ቀውስ የወጣቶችን ችግሮች የበለጠ እንዳወሳሰቧቸው ነው በርካቶች የሚናገሩት፡፡

አሁን የሚታየው የወጣቶች ችግርና ሸክም ከዓምናውም ሆነ ከሌላው ጊዜ የባሰ እንደሆነ ብዙዎች ይናገራሉ፡፡ ጥራት ያለው ትምህርት ካለማግኘት በተጨማሪ ራስን ለማሻሻልና ለመለወጥ ያሉ ዕድሎች መጥበባቸው ዋናው ችግር ይባላል፡፡ ከሕዝብ ቁጥር ጭማሪ ጋር ተያይዞ ጠንካራ ፉክክርን በሚጠይቅ የሥራ ገበያ ላይ ተወዳድሮ ሥራ ማግኘትና ሕይወትን ማስተካከልም፣ እንዲሁ ቀዳሚ ከሆኑ እንቅፋቶች መካከል ይጠቀሳሉ፡፡ ፅንፈኝነትና አክራሪ ብሔርተኝነት በተጫነው ፖለቲካ ግራና ቀኝ እየተላጋ ሕይወትን ለመግፋት የሚገደደው የኢትዮጵያ ወጣት፣ በቢሮክራሲና የመልካም አስተዳደር ችግሮች በራሱ ታግሎ ዕድሎችን ለመፍጠር እንደሚፈተንም ይነገራል፡፡ ይህንን የወጣቱን የኑሮ ሸክም የሚያቀሉ ፖሊሲዎችና ስትራቴጂዎችን ከማበጀት በተጨማሪ፣ ከግጭትና ከሰላም ዕጦት ችግር የወጣቱን ሕይወት የመታደግ ከባድ ሸክም አሁን አገር የሚመራው መንግሥት እንደተጫነበት የሚናገሩ በርካቶች ናቸው፡፡

ልክ እንደ ደርግና ኢሕአዴግ መንግሥት ሁሉ በወጣቶች ከባድ ተጋድሎና የደም መስዕዋትነት ወደ ሥልጣን የመጣው የጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) አስተዳደር፣ ወጣቶችን በተመለከተ ትርጉም ባለው መንገድ ተጠቃሚ የሚያደርግና ሕይወት ቀያሪ ፖሊሲዎችና የፖለቲካ ፕሮግራሞች ቀርፆ መተግበር እንደሚጠበቅበት ብዙዎች ይናገራሉ፡፡ አሁን ያለው አስተዳደር ወጣቶችን በተመለከተ የሚጠበቅበትን አድርጓል የሚለው ጉዳይ ግን ብዙዎችን እንደማያሳምናቸው ያስረዳሉ፡፡

የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ በአንድ ወቅት የሰበሰቧቸውን ወጣቶች ‹‹ጫት አትቃሙ›› የሚል ምክር መክረው እንዳሰናበቷቸው ሁሉ፣ ሰሞኑን ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ (ዶ/ር) የሰበሰቧቸውን ወጣቶች ‹‹ጫት አትቃሙ›› የሚል ምክር ሲለግሷቸው ታይተዋል፡፡ ‹‹የእኛ ዘመን ወጣት ሚና›› በሚል ርዕስ ዓብይ (ዶ/ር) ከመላው ኢትዮጵያ ከተውጣጡ ወጣቶች ጋር ያደረጉት ሰሞነኛ ውይይት፣ ልክ እንደ ከዚህ ቀደሞቹ መሪ ወጣቶችን የመከሩበት፣ ወጣቶች በምላሹ አድናቆትና በጎ አስተያየቶችን ለመሪዎች ሲያጎርፉ የታየበት በጭብጨባና በፉጨት የደመቀ ስብሰባ ነበር፡፡

የቀድሞ ዘመን የኢትዮጵያ ወጣት መፈናፈኛ በሌለበትና ፍፁም አምባገነናዊ ሥርዓት በሰፈነበት በዚያ አስከፊ ዘመን መብቱና ጥቅሙን ለመጠየቅ ከባድ መስዕዋትነት እስከመክፈል ይሄድ እንደነበር በማስታወስ፣ የአሁኑ ዘመን ወጣት ግን ከመሪዎች ጋር ተሞጋግሶ ይለያያል ሲሉ ጉዳዩን የተቹ በርካቶች ናቸው፡፡ የመሪዎችን የሕይወት ተሞክሮና ምክር መስማት መጥፎ ባይሆንም፣ ይሁን እንጂ ወጣቱ ትውልድ የመንግሥትን ልዩ ትኩረትና ምላሽ የሚፈልጉ ውስብስብ ችግሮች እንዳሉበት የጠቀሱ አንዳንድ ተቺዎች፣ የዓብይ (ዶ/ር) አስተዳደር እነዚህን ችግሮች በመቅረፍ ላይ እንዲተጋ ያሳስባሉ፡፡

የቀደመው ትውልድ ከራሱ ሕይወት ባለፈ ‹‹መሬት ለአራሹ›› ብሎ ለወጣበት ማኅበረሰብ መብት ይሟገት እንደነበር ይጠቀሳል፡፡ የቀደመው ትውልድ ከኢትዮጵያና ከራሱ አልፎ ለደቡብ አፍሪካ፣ ለዚምባቡዌ ወይም ለቬትናም ነፃነት ጭምር ድምፁን እስከ ማሰማት የደረሰ ነበርም ይባላል፡፡ ይህን እንደ ማነፃፀሪያ በማቅረብም የአሁኑ ትውልድ የራሱን ፍላጎቶችና አጀንዳዎች ትቶ መንግሥትን ወይም ሌላ የፖለቲካ ኃይል በመጠጋት ሕይወቱን ለመቀየር መሞከሩ፣ ትውልዱ የፖለቲከኞች ተመፅዋች እየሆነ መምጣቱን ያሳያል በማለት አንዳንዶች ሲተቹ ታይተዋል፡፡

ይህን በሚመለከት በእሳቸው ዘመን ከነበረው የወጣቱ ትግል ጋር በማነፃፀር እንዲመልሱ የተጠየቁት የኢሕአፓ መሥራቹ አቶ ክፍሉ፣ ‹‹የአሁኑ ትውልድ ምን ያድርግ?›› ሲሉ ነው ጥያቄ የሚያነሱት፡፡

የአሁን ዘመንን ወጣት ከቀደመው እያነፃፀሩ ትውልድ መከነ እያሉ መርገሙ አንዳችም ጠቀሜታ እንደሌለው አቶ ክፍሉ ያሰምሩበታል፡፡ ‹‹ወጣቱ በቀደደው የትግል መስመር ደርግ ወደ ሥልጣን እንደ መጣው ሁሉ፣ ኢሕአዴጎች አጭበርብረውም ቢሆን ለሥልጣን የበቁት ወጣቱን አታግለው ነው፡፡ የአሁኑ ትውልድም በተለያዩ አጋጣሚዎች የራሱን ታሪክ ሲጽፍ ዓይቻለሁ፡፡ በ1997 ዓ.ም. ምርጫ ወጣቱ ሆ ብሎ ወጥቶ በመምረጥና ድምፁ እንዳይጭበረበር በመታገል የደገፈውን ፓርቲ ለሥልጣን ለማብቃት ጥሯል፡፡ ድምፁ በኢሕአዴግ ቢዘረፍም ወጣቱ በ1997 ዓ.ም. ለዴሞክራሲ ያደረገው የትግል ታሪክ የማይረሳው ነው፡፡ የዓብይ አህመድ (ዶ/ር) አስተዳደር ወደ ሥልጣን እንዲመጣ ወጣቱ ያደረገው ትግልና የከፈለው መስዕዋትነት ቀላል አልነበረም፤›› በማለት አቶ ክፍሉ ይናገራሉ፡፡ ወጣቱ ጥያቄዎቹ የማይሰሙበትና ችግሮቹ የማይፈቱበት መሠረታዊ ምክንያት እንዳሉ ያመለከቱት አቶ ክፍሉ፣ ‹‹ብዙ ጊዜ የወጣቱ አጀንዳ ይጠለፋል ሲሉ አስቀምጠውታል፡፡ ወጣቱ አደራጅቶ የሚያታግለውና አርዓያ የሚሆነው ካገኘ ዛሬም ቢሆን ጠንካራና ለውጥ ፈጣሪ ኃይል መሆኑን እንደሚያምኑ፣ አንጋፋው ፖለቲከኛ ካለፉበት ተሞክሮ በመሳነት አስረድተዋል፡፡

ከሰሞኑ አገር የሚመራው ብልፅግና ፓርቲ መሪ ዓብይ (ዶ/ር) ወጣቶችን ሰብስበው እንዳነጋገሩት ሁሉ፣ የኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትሕ (ኢዜማ) የወጣቶች መምሪያም እሑድ ነሐሴ 15 ቀን 2014 ዓ.ም. የራሱን የወጣቶች ስብሰባ ሲያካሂድ ታይቷል፡፡ ከስብሰባው ጋር በቀጥታ የተገናኘም ባይሆን የወጣቶችን የፖለቲካ ተሳትፎ በሚመለከት በኢትዮጵያ ያለውን ምቹ ዕድል ወይም እንቅፋት እንዲያስረዱ የተጠየቁት የፓርቲው ሥራ አስፈጻሚ አባልና የወጣቶች መምርያ ኃላፊ ገነት አራጌ፣ ‹‹የወጣቶች የፖለቲካ ተሳትፎ ከሌላው የማኅበረሰብ ክፍል የፖለቲካ ተሳትፎ ተለይቶ የሚታይ አይደለም፡፡ አሁን ያለው የፖለቲካ ዓውድ ለወጣቱም ሆነ ለሌላው ማኅበረሰብ አመቺ የተሳትፎ ዕድል የፈጠረ አይደለም፡፡ ነገር ግን የኢትዮጵያ ወጣቶች በታሪክም ካየን የፖለቲካ ምኅዳሩ እንዲለወጥ ብዙ ሲታገሉ ኖረዋል፡፡ ከአፄ ኃይለ ሥላሴ ጀምሮ፣ መንግሥቱ ኃይለ ማርያም፣ መለስ ዜናዊም ሆነ ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) ወደ መሪነት የመጡት በወጣትነታቸው ዘመን ነበር፡፡ የመጡበት የፖለቲካ ሁኔታ ግን ውጣ ውረድ ያለበትና ጠንካራ ተቋማት የሌሉበት ነው፤›› ብለዋል፡፡

ይህ ዘመን የተሻገረ ችግር አሁን ባለው መንግሥት ላይ እንደሚንፀባረቅ ያስረዱት ገነት፣ ከሰሞኑ መንግሥት ያደረገው የወጣቶች ስብሰባም ትርጉም የለሽ እንደሆነባቸው ተናግረዋል፡፡ ‹‹ወጣት የማይመስሉ ሰዎች ሲካፈሉ ያየንበት፣ የወጣቱ ጥያቄ ያልተነሳበት፣ እንዲሁም የብሔር ፖለቲካ ውክልና የሚንፀባረቅበት ስብሰባ ይመስላል፤›› ሲሉም የመንግሥትና የወጣቶች ስብሰባ ተችተውታል፡፡

እሳቸው አባል የሆኑበት የኢዜማ ፓርቲ ‹‹በራሱ በወጣቱ የተቀረፁ ፖሊሲና ፕሮግራሞች አሉት፤›› ሲሉ የተናገሩት ገነት፣ በኢትዮጵያ የወጣቶችን ችግር ለመቅረፍና ወጣቶችን የበለጠ አሳታፊ ለማድረግ ሁሉንም አካታች የሆነ የፖለቲካ አካሄድ እንደሚያስፈልግ አሳስበዋል፡፡

‹‹ወጣቱ አንዳንዴ በስሜት የመሄድ ወይም ባለማስተዋል የመጓዝ ችግር አለበት፤›› የሚሉት የኢዜማ የወጣቶች መምርያ ኃላፊ፣ ‹‹በዕድሜና በልምድ የበሰሉ ሰዎችን ከወጣቱ ጋር በማቀናጀት መሥራት ለዚህ መፍትሔ ነው፤›› ሲሉ ገልጸዋል፡፡

በብዙ የፖለቲካ መድረኮች ወጣቶች በአደረጃጀት ወይም በውክልና ሲሳተፉ ይታያል፡፡ በቅርቡ የብሔራዊ ምክክር ኮሚሽን ስትራቴጂክ ዕቅዱን ሲያስገመግም፣ ‹‹ወጣቶች ራሳችንን ችለንና የራሳችንን አጀንዳ ይዘን የምንቀርብበት መድረክ ቢመቻች›› የሚል ጥያቄ ማቅረባቸው ጎልቶ ተነስቶ ነበር፡፡ አሁን ከዚህ ይልቅ እንደ ቀደሙ አስተዳደሮች ሁሉ በተለያዩ አደረጃጀቶችና ክንፎች የወጣቱን ድምፅ የማስተጋባት ዝንባሌ እንደሚታይ፣ ይህ ደግሞ መንግሥት የወጣቱን ነባራዊ ችግሮች ለማድመጥና ለመፍታት ዕድል አይሰጠውም የሚል ሥጋት እንደሚፈጥር የሚያሳስቡም ብዙ ናቸው፡፡

spot_img
- Advertisement -

ትኩስ ጽሑፎች

ተዛማጅ ጽሑፎች

- Advertisement -
- Advertisement -