በሻሎም አ.
ለምን እንደሆነ ባይገባኝም በአገራችን ያለው የትራንስፖርት ዘርፍ ከመሻሻል ይልቅ እያደር ወደ ኋላ የመሄዱ አሳዛኝ እውነታ፣ በትራንስፖርት ባለንብረቶች ላይ አሉታዊ ጫና ማሳደሩ፣ ተማክሮ ሠሪና አስተዋይ ያጣ አስመራሪ ዘርፍ የመሆኑ ትራጄዲ ሁሌም ያሳዝነኛል፡፡ ይህን ስል በአሁኑ ጊዜ በተወሰነ ደረጃ ያለውን መሻሻል ዓይኔን ግንባር ያድርገው አላየሁም አለማለቴ ይመዝገብልኝ፡፡
በአንድ ወቅት በዘርፉ በተሰማራ ስመ ጥር በሆነ ግዙፍ ድርጅት ውስጥ እሠራ ስለነበር የቀድሞዎቹን ሁለት መንግሥታት የአሠራር ፖሊሲዎች፣ ደንብና መመርያዎች አፈጻጸም ለመገንዘብ ዕድል አግኝቻለሁ፡፡ አነሰም በዛ በነበረው የአገሪቱ የሎጂስቲክስ ኢንዱስትሪ በአሁኑ ዘመን ካለው የትራንስፖርት አመራርና አስተዳደር ጋር ሊወዳደር በማይችል መጠን ሥርዓት ያለውና አሠራሩ የተሻለ ነበር፡፡ ከረዥም ዓመት አገልግሎት በኋላ በፈቃዴ ዘርፉን ትቼው ብወጣም፣ ዛሬም ያለሁበት የሥራ መስክ ከዚህ ዘርፍ ጋር የሚያገናኝ በመሆኑ ችግሮቹና ተግዳሮቶቹ በቀጥታ ባይመለከቱኝም፣ ከቅርብ ርቀት ሐሳብና አዕምሮዬን መጎንተላቸው ግን አልቀረም፡፡
እንዲያውም በተለምዶ የትራንስፖርት ዘርፍ ሥራ ፈታኝና አስመራሪ በመሆኑ፣ አንዳንድ አሽከርካሪዎችንና ባለንብረቶችን ‹‹የአባትና የእናት እርግማን ሳይኖርባችሁ አይቀርም›› ይሏቸዋል፡፡ በባህር ማዶም (በጣሊያን) አንድን ሰው መርገም ሲፈልጉ «…የትራንስፖርት ድርጅት ኃላፊ ያድርግህ›› ይባላል ሲሉ አንድ ከፍተኛ ባለሥልጣን በመድረክ ሲናገሩ መስማቴን አስታውሳለሁ፡፡
ከደርግ ዘመን ጀምሮ ዘርፉን በሚኒስትርነት ደረጃ የሚመሩት የፖለቲካ ባለሥልጣናት በመሆናቸውና ዘርፉም በባለሙያ ባለመመራቱ ችግሩ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየገዘፈ መጥቶ፣ አሁንም በዘመነ ብልፅግና በነሐሴ ወር 2014 ዓ.ም. በወጣው አዋጅ ቁጥር 1274 ምንም ዓይነት የማሸጋገሪያ (መውጫ) ስትራቴጂ ሳይቀየስ መመርያና ደንብ ባልወጣቡት ሁኔታ፣ ወደ ንግድ ተቋም ተደራጁ በሚል ስም የአገር ባለውለታ ማኅበራትን ግብዓተ መሬት ለመፈጸም ግፊቱ በመጣደፍ ላይ ነው፡፡ አስለቃሽ ዕድርተኛውን ደረቱን እየመታ ለማስለቀስ የለቅሶ ስንኝ በመደርደር በጣዕመ ዜማ ‹‹ምነው በአፈሩ…›› ላይ ለማሰኘት ተዘጋጅታ የምትጠብቅ ይመስላል፡፡
በመሠረቱ የትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ ሚኒስቴር አዋጅ 1274/2014 ሲያረቅም ሆነ ለማስፈጸም በሚያወጣው መመርያ ማኅበራት ወደ መዋቅራዊ ለውጥ ሊሸጋገሩ የሚችሉበትን ጊዜ፣ የአደረጃጀት አግባብና ሁኔታ ያገናዘበ እንዲሆን የባለድርሻ አካላትን የሐሳብ ግብዓት በሚያዘጋጀው መመርያ ማዕቀፍ በማካተት፣ የሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱን ሕግና የአሠራር መርህ ቅቡልና ተፈጻሚ እንዲሆን በማድረግ ረገድ የማይተካ ሚና ቢኖረውም ይህ ግን ሲደረግ አልታየም፡፡ ምንም እንኳ በሚኒስቴሩ መሥሪያ ቤቱ ውስጥ ባለሙያዎች ቢገኙም፣ የመወሰን ሥልጣን ስሌላቸው ባደራጇቸው የትራንስፖርት ማኅበራት ላይ የሚፈጥሩት የግዳጅ ጫና በቀላሉ የሚገለጽ እንዳልነበረና እንደሆነም በገሃድ ይታወቃል፡፡ ማኅበራት በአደረጃጀታቸው ከነበረው የተሻለና ትርፋማም እንዲሆኑ ማዘመን አስፈላጊ እንደሆነ በእጅጉ ይታመናል፡፡ ማኅበራት ከነበሩበት ዝቅተኛ የንግድ ሳይሆን የሲቪክ ማኅበር አደረጃጀት ወጥተው በሠለጠነ ባለሙያ የሚመሩ፣ እንደ ዜጋ የሚጠበቅባቸውን የግብር ግዴታ የሚወጡና አትራፊ እንዲሆኑ በአክሲዮን፣ በኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማኅበር ወይም በንግድ ሕጉ መሠረት በተዘረዘሩት የአደረጃጀት አማራጮች መለወጥ አስፈላጊና ወቅታዊም ነው፡፡ በበኩሌ ለዚህ ሥምረት ከመንግሥት ጎን እሠለፋለሁ፡፡
ችግሩ ግን በበቂ ጊዜ ተገቢ ግንዛቤ እንዳይኖረው የተደረገውን ትራንስፖርተር ስለአደረጃጀት ሽግግሩ ምንም መረጃና የሥነ ልቦና ዝግጅት ሳያደርግ የተሸከርካሪ ባለንብረት ንብረቱን አስገምቶ በሚቋቋም አክስዮን በቀጥታ እንዲያስገባ ባይነገርም፣ በውስጠ ወይራነት በሚገለጹ ቋንቋ መነገሩ ምን ያህል ግራ አጋቢ እንደሚሆንና በተስፋ አስቆራጭ መንፈስ እንደሚያውክ ማንም ጤነኛ አዕምሮ ካለው አደራጅ ልቦና የሚሰወር አይደለም፡፡ ስለዚህ የመደራጀት ጊዜ ያስፈልጋል፡፡ ጊዜ የመስጠትና ሁኔታዎችን የማጤን ኃላፊነት ያለው ደግሞ በመንግሥት እጅ ላይ ነው፡፡
ከዚህ ዱብ ዕዳ ከሚመስል ገፊ የአደረጃጀት ለውጥ አፈጻጸም ጀርባ መሥሪያ ቤቱ ይህንን ግልጽነት የጎደለው አካሄድ ለምን መረጠ ሲሉ በርካታ አሉታዊና አዎንታዊ መላ ምቶች፣ አሉባልታዎችና ተጨባጭነት ባይኖራቸውም በመልካምም በመጥፎም በሞቅታ የሚደመጡ ወሬዎች ይዘዋወራሉ፡፡ እነዚህም መንግሥት ከትራንስፖርት ዘርፍ ማግኘት የሚፈልገውን ገቢ በፈለገው መጠን እንዲሰበስብ ለማመቻቸት፣ የነዳጅ ቁጥጥር ለማከናወን፣ የተሽከርካሪዎችን የጉዞ እንቅስቃሴ በጂፒኤስ ለመከታተልና ሥምሪታቸውን ለመቆጣጠር፣ የኮንትሮባንድና ሕገወጥ የጭነት ዝውውሮችን እንቅስቃሴ ለመከታተል፣ ከወደብ የሚነሳውን ጭነት በዘመናዊ አሠራር ለማቀላጠፍና፣ የትራንስፖርት ዘርፉን ለማዘመንና ለማሳለጥ፣ በአገሪቱ ያለውን የጭነት ታሪፍ ለመቆጣጠርና ለውጭ ኢንቨስተሮችን ጥያቄ ምላሽ ለማዘጋጀት፣ የዓለምን የመንገድ ትራንስፖርት ደረጃ በሚመጥን የኮሜሳ አባል አገሮችን መመዘኛ ለማሟላት፣ በቀጣናው በአቻነት ለመቀላቀልና ኢንቨስተሮችን ለመጋበዝ፣ የአገር ውስጥ ባለሀብቶችንም ወደ ምሥራቅ አፍሪካ አገሮች እንዲዘልቁ ለማመቻቸት፣ ለአገር የለፉ በርካታ ማኅበራትን ወደ ጎን ገፍቶ ጥቂት ቀረቤታ የፈጠሩ የአገር ውስጥ ባለሀብቶችን በርካታ ተሽከርካሪ እንዲያስገቡ የባንክ ብድርና ፋስሊቲ ለማመቻቸት፣ የክልል መንግሥታት የራሳቸውን የትራንስፖርት ዘርፍ በማቋቋም ተሽከርካሪዎችን ከውጭ እንዲያስገቡ፣ ከግሉ ዘርፍ ይልቅ ለመንግሥታዊ የልማት ድርጅቶች ተሽከርካሪ ወደ አገር በማስገባት በትራንስፖርት ዘርፍ በሰፊው እንዲሰማሩ ለማድረግ፣ በዕርዳታ ሥራ የተሰማሩትን ድርጅቶች ተሽከርካሪ ወደ አገር ውስጥ እንዲያስገቡ፣ በዚህም ዘርፉን በፈለገው መጠን መቆጣጠር እንዲያስችለው እንደሆነ በሰፊው ይነገራል፡፡
ከተያዘው አካሄድ ይልቅ ግን ትራንስፖርተሩን እንደ አጋርና ወሳኝ ባለድርሻ አካል በግልጽ መድረክ ለማወያየት ቢቻልስ? አወያይቶም ከሆነ በተደጋጋሚ ከአብዛኞች ጋር ለምን ውይይቱ አልተካሄደም? ይህ ዜጋን ከባለቤትነት የሚያርቅ ሰወርዋራ አካሄድ ሰዎች በመንግሥት ላይ ያላቸውን እምነት በማምከን በጥርጣሬና በጎሪጥ እንዲመለከቱ አያስገድድም?
ከዚህ እውነታ ስንነሳ በትራንስፖርት ዘርፉ በማኅበር የተደራጁ የፈሳሽ፣ የደረቅ ጭነትና የሕዝብ ማመላለሻ ማኅበራት ለአገራቸው ያበረከቱትን አስተዋጽኦ መንግሥት በወጉና በትክክል ያልተረዳና ቢገነዘብም ዕውቅና ለመስጠት ያልፈለገ ያስመስለዋል፡፡ ለዚህ ማረጋገጫው አንድ የትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ ሚኒስቴር ጽሕፈት ቤት የሕግ አማካሪ የሆኑ ግለሰብ፣ የአገራችን ከፍተኛው የሥልጣን አካል በሆነው በተወካዮች ምክር ቤት የውይይት መድረክ ላይ መንግሥት በአዋጅ/በሕግ ያደራጃቸውን የትራንስፖርት ማኅበራት፣ ‹‹ማኅበራቱ ሠራተኞችም ሆነ ጽሕፈት ቤት የላቸውም… ወዘተ›› በማለት በሚያነውሩ ክብረ ነክ ቃላት በድፍረት ሲናገሩ አንድም የአደራጁ አካል ባለሥልጣን ሃይ አለማለቱን በትዝብትና ቁጭት ተመልክተናል፡፡ ይህ ዘርፍ ለዘመናት አገራችን ለገጠማት የጦርነትም ሆነ የድርቅ ቀውስ ፈጥኖ በመድረስ፣ ተስፋ ለጣለችባቸው የግብርና ክፍለ ኢኮኖሚ፣ የኢንዱስትሪና የኃይል ከፍተኛ የልማት ፕሮጀክቶች ግብዓት በማቅረብ የደም ሥር ሆኖ አላገለገለም? ግን ለምን ውለታው ተረሳ? ዛሬ አገራችን ከገባችበት የኢኮኖሚና የፖለቲካ ውጥረትና ቀውስ አንፃርስ ዘርፉን በዚህ ሁኔታ ማወክና ማጎሳቆል ተመራጭ ነው? እኔ ተቃዋሚም ይባሉ ተፎካካሪ ፓርቲዎች ሚናና ፍላጎት ምን እንደሆነ አልገባ ካለኝ የቆየሁ ቢሆንም እንዲህ ዓይነት ግጥጥና ፍጥጥ ያለ የመከራ ዘመን ለመጋፈጥ ጫፍ ላይ ስንደርስና ችግሩ ከፊት እየተጋረጠብን እየተመለከቱ ዝምታቸው አይገባኝም፡፡ ‹‹…አላልናችሁም ብልፅግና አይጠቅማችሁም ብለን እኛን ብትመርጡ ኖሮ ይህ አይገጥማችሁም ነበር›› ለማለት ከሆነ ተሳስተዋል፡፡ እነሱ የሚንቀሳቀሱት ሥልጣን ለማግኘት፣ መንግሥትን ለማጥላላት በመሆኑ ትኩረታቸውን ፖለቲካ ብቻ ላይ ማድረጋቸው ያስተዝዝበናል፡፡ አሁን ነበር ለሕዝብ ያላቸው አክብሮት መለኪያው ግን አመለጣቸው፡፡ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤትና የሚኒስትሮች ምክር ቤት፣ እንዲሁም ቋሚ ኮሚቴውን ትክክል አይደላችሁም ብዬ ለመተቸትና ክብር ለመንካት አልችልም፡፡ ተገቢም አይመስለኝም፡፡ ይሁን እንጂ ይህንን አዋጅ ለማፅደቅ የትኛውን እውነት አገኝተውበት ይሆን ያፀደቁት ብዬ ለመጠየቅ ግን እገደዳለሁ፡፡
በአዋጅ ቁጥር 1274/2014 ቀደም ሲል ማኅበራትን ያደራጀው አዋጅ 468/1997 የፈረሰ መሆኑን ሲደነገግ፣ ዋናው የአዋጁ መልዕክት ማኅበራት ፈርሰው ወደ ንግድ አደረጃጀት ይግቡ የሚል መንፈስ አለበት፡፡ ይህ ተገቢና ሁሉንም የሚያግባባ ነው፡፡ ከሆነም በ1243/2013 የንግድ ሕግ በምዕራፍ አራት አንቀፅ 42 መሠረት ማኅበራት ወደ ነጋዴ ወኪልነት፣ በምዕራፍ አምስት አንቀጽ 54 መሠረት ወደ ሕጋዊ ደላላነት፣ በምዕራፍ ስድስት አንቀጽ 58 መሠረት ወደ ኮሚሽን ወኪልነት፣ በምዕራፍ ስድስት በአንቀጽ 60 መሠረት ወደ አክሲዮን ደላላነት፣ በምዕራፍ ስድስት አንቀጽ 247 የገንዘብ አክሲዮንነት መለወጥ እንደሚችሉ ሕጉ ቢደነግግም፣ የትራንስፖርትና ሎጂስቲክ ሚኒስቴር ይህን የሚቀበለው አይመስልም፡፡ የንግድ ሕግ 1243/2013 ላይ በምዕራፍ ስድስት አንቀጽ 257 ባለው የዓይነት አክሲዮን ብቻ ማኅበራት እንዲደራጁ በእጅ አዙር ጫና ለማሳደር ይዳዳዋል፡፡ ሌሎች የንግድ ሕግ ላይ ያሉትን አማራጭ አደረጃጀቶች ተቀብሎ ካልፈጸመ ደግሞ፣ የአገሪቱን ሕግ የጣስው ራሱ የሚኒስቴሩ ጽሕፈት ቤት ይሆናል ማለት ነው፡፡ ማኅበራት ደግሞ ማኅበራት ብቻ መሆን ነው የምንፈልገው ቢሉ አያዋጣም፣ ሰሚም አያገኙም፡፡ ባይሆን ጊዜ መጠየቅ መብታቸው ይሆናል፡፡
ከትራንስፖርተሮች አምባ በደማቁ የሚወራው የተሽከርካሪው ባለንብረት ወደ አክሲዮን ወይም ኃላፊነቱ የተወሰነ ማኅበር እንዲለወጥ ካስፈለገ፣ በንግድ ሕግ በአንቀጽ 257 መሠረት የንብረትነት ማረጋገጫውን ሊብሬ በሚቋቋመው አክሲዮን ስም አስለውጦ፣ ተሽከርካሪውን በገንዘብ አስገምቶ፣ ለአክሲዮኑ በማስረከብ በዓመት የሚሰጠውን ትርፍ እንዲጠብቅ ይገደዳል በሚል በፍራቻ ስሜት መቆራመዳቸውን ነው፡፡ ይህ ደግሞ ካቻምናም፣ አምናም፣ ዘንድሮም አንድ ባለንብረት ገቢው ከእጅ ወደ አፍ ሆኖበት ከመቸገሩ በላይ ማኅበራዊ ሕይወቱን ለመግፋትና ኑሮውን ለመለወጥ ባልቻለበት ሁኔታ፣ በአክሲዮን ትርፍ ዓመት ጠብቅ ማለት ምን ያህል ቀና ትርጉም እንደሚኖረው አዋቂው አምላክ ብቻ ይሆናል፡፡ ወደ ዓይነት አክሲዮን እንዲለወጥ 1274/2014 አዋጅ ጫና አይፈጥርም፡፡
ስለዚህም የትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ ሚኒስቴር ጽሕፈት ቤትን አንድ የተሽከርካሪ ባለንብረት ሄዶ እንዴት ሊብሬዬን በአክሲዮን ስም ንብረቴን እለውጣለሁ ብሎ ቢጠይቅ፣ የለም እኔ አላልኩም ባይሆን የአክሲዮን አደረጃጀት በሚጠይቀው ሕግ መሠረት ተደራጅታችሁ በአክሲዮን ስም ተሸከርካሪ አቅርቡ ነው ያልኩት እንደሚለው ጥርጥር አይኖርም፡፡ የአክሲዮን ወይም ኃላፊነቱ የተወሰነ ማኅበር ለማቋቋም የብቃት ማረጋገጫ የሚሰጠው የትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ ሚኒስቴር ጽሕፈት ቤት ግን፣ አክሲዮኑን ለመቋቋም የተፈቀደውን የተሸከርካሪ ቁጥር በአክሲዮኑ ስም ሊብሬ ማቅረብ ተቀዳሚ መሥፈርት ስላደረገው ይህንን አዋጅ ለመተርጎም ህልም ሆኖ ይቀራል ተብሎ ጥርጣሬ ውስጥ ይጥለናል፡፡ ከዚህም በሻገር ምናልባት ማኅበራት ተሳክቶላቸው አክሲዮን ለመመሥረት ቢፈቀድላቸው ደግሞ የሥራ ማስኪያጅ የፋይናንስ አቅም የላቸውም፣ ሊኖራቸውም አይችልም፡፡ የተደራጁት በዓይነት ስለሆነ የተሸከርካሪዎች ማቆሚያ ሥፍራ፣ የተሸከርካሪ የጥገና ቦታና የተሸከርካሪ ማጠቢያ ቦታ ስለሌላቸው ተግባራዊ ማድረግ አይቻላቸውም፡፡ ይህን የአዋጁን ዓላማ በተግባር ለመተርጎም ደግሞ መንግሥት ለዚህ ሁሉ አክሲዮንና ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማኅበር ጽሕፈት ቤቶች ቦታ ለመስጠት አቅም አለው ተብሎ አይታሰብም፡፡ ይህ ካልሆነ ደግሞ የአክሲዮኖችን ተሽርካሪዎች የት ቦታ አቁሞ ማስተናገድ ይቻል ይሆን?
ችግሩ ግን ከላይ የተገለጸው አዋጅ ሲወጣ ባለሙያዎችና ባለድርሻ አካላት በበቂ ጊዜ በይፋ ሊመክሩበት፣ ሊነጋገሩበት፣ ሊከራከሩበትና የጋራ አቋም ሊወስዱበት ይገባ እንደነበረ ድምፄን ከፍ አድርጌ መሞገት እወዳለሁ፡፡ ምንም እንኳ አገሪቱ ከምትከተለው የንግድ ሕግ አንፃር ይህ አዋጅ የማይከለክላቸው አማራጭ መብቶች አለመስተዋላቸው እንዳለ ሆኖ፣ በመንግሥት በኩል ሲታይ በተወሰነ ገጽታው መልካምነት አለው፡፡ ግን አስፈጻሚው አካል ብቻ ሳይሆን ተግባሪውም ሊያብላላውና ሊገነዘበው፣ አስቀድሞም ሊረዳው መብት አለው፡፡ ይህ ጉዳይ ይበልጥ አኅጉራዊ ይዘት እንዲኖረው የሚያደርገውና ማናቸውንም ባለሥልጣናት እንቅልፍ የሚነሳው የትራንስፖርቱ ዘርፍ ኃላፊዎችና የባለንብረት የቦርድ ሥራ አመራሮች በየቀኑ የሚጮሁት፣ ሠራተኛው ማኅበሩ እንዳይፈርስበት ለአምላኩ ምህላ የሚቆምበት ይህ ስስና ወሳኝ የአገር ኢኮኖሚ የጀርባ አጥነት የሆነውን የትራንስፖርት ዘርፍ መንካት የወቅቱ አሳሳቢ ጉዳይ ስለሆነ ነው፡፡ በነገራችን ላይ በአገራችን ከብሔር ግጭት ቀጥሎ ሕዝብ ዕንባውን አፍስሶ ለአምላኩ የሚያሳቅልበት አንዱ የትራንስፖርት ችግር ለመሆኑ በመሃላ መግለጽ ይቻላል፡፡ ይህንን አለማመን ባይቻልም ጉዳዩ የሚመለከተው አካል በአዲስ አበባ ነዋሪዎች ብቻ ሥቃዩን በታዛቢነት ለመመልከት ከፈለገ መጋበዝ ይችላል፡፡
ዛሬ በሰሜን አገራችን በትግራይ ክልል በኩል ያለው ችግር ገና ባልተፈታበት፣ በምሥራቅና በምዕራብ ወለጋ ያለው ፀረ ሰላም ኃይል ባልከሰመበት፣ በቤንሻንጉል ጉሙዝና በጋምቤላ ያለው ያለየለት የብሔር ጥላቻ ባሻው ሰዓት በሚገነፍልበት፣ በሱዳን ድንበር በኩል ያለው ግጭት ገና ሥርዓት ባልያዘበት፣ አሸባሪ ኃይሎች ብሔር ተኮር የዘር ማጥፋት በየቀኑ በሚፈጽሙበት፣ የሕወሓት ቡድን፣ የሸኔ ታጣቂ፣ የአልሻባብ ሽብርተኞች በተቀናጀ ሁኔታ በአገር ህልውና ላይ ጥቃት ለማድረስ ባልተኙበት፣ በሶማሊያ በኩል ያለው የአልሸባብ እንቅስቃሴ ለመግታት እጅ ለእጅ ተያያዘን ልንቆም በሚገባን ወቅት፣ በተለያዩ አካባቢዎች የክልል መብት ይሰጠን የሚሉ መንግሥትን ባስጨነቁበት፤ በአፋር ክልል ከኢሳ ጎሳ ጋር ያለው ግጭት ወጣ ገባ በሚልበት፣ የምዕራባውያንና የአሜሪካ መንግሥታት ለኢትዮጵያ መንግሥት ያላቸው ጤናማ ያልሆነ አመለካከት በጥርጣሬ በሚስተዋልበት፣ የአገሪቱ ሕዝብ በኑሮ ውድነት ተስፋ በቆረጠበት፣ የብሔር ፖለቲከኞች ሕዝቡን በመከፋፈል በመንግሥት ላይ በየቀኑ ጫና ለመፍጠር ተቀናጅተው በሚሹለከለኩበት፣ የከተማ ወጣት በአደንዛዥ ዕፅና በመጤ ባህል ራሱን እንዲስትና ጠያቂ የልማት ትውልድ እንዳይሆን በሥውርና በግልጽ በሚሠራበት፣ የተማረ የሰው ኃይል ወደ ተለያዩ አገሮች መፍለስና የሠለጠነ የባለሙያ የሰው ኃይል ዕጦት እንዲኖር በሚሴርበት፣ በርካታ የልማት አውታሮች በተለያዩ ምክንያቶች በጅምር በሚቀሩበት፣ በውጭ ምንዛሪ እጥረት ምክንያት ለተሽከርካሪ የሚሆኑ መለዋወጫ ዕቃዎች ዋጋ በየጊዜው እየናረ በሚሄድበት፣ በየዋና ከተማው የሚታየውን የሕዝብ ፍልሰት መቆጣጠር ባልተቻለበትና በየጊዜው እየናረ በመሄድ የማኅበራዊ ቀውስ በምንናጥበት ወቅት፣ የክልል መንግሥታት በትራንስፖርት ዘርፉ ላይ ያላቸው መብትና የሥልጣን ገደብ የፌዴራሉ መንግሥት ከሚያወጣው መመርያና አዋጅ ያልተጣጣመ ሆኖ በሚንቀሳቀሱበት ፈታኝና አስጨናቂ ወቅት ሌላ ተደራራቢ የሥጋትና የሽብር ምንጭ ሊሆን የሚችል አካሄድ መከተልና በትራንስፖርት ዘርፉ የእሾህ አጥር ማድረግ ተገቢ ነው?
የትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ ሚኒስቴር አሁን በሚከተለው ያልተመከረበትና ያልተዘከረበት የአደረጃጀት ለውጥ የተነሳ፣ ለጊዜውም ቢሆን የትራንስፖርት ማኅበራት ለአገር የሚሰጡት ኤኮኖሚዊ ጥቅም ይቀዛቀዛል፣ ከዚሁ ጋር ተያይዞ የተጀመሩ በርካታ የልማት አውታሮች ለማስቀጠል በአቅርቦት ምክንያት የአፈጻጸም መዘግየት ይገጥማቸዋል፣ በጥሬ ዕቃ እጥረት ምክንያት ኢንዱስትሪዎች ፋብሪካዎች ሥራቸውን ለማቆም ይገደዳሉ፣ የኤክስፖርት ጭነቶች በወቅቱ ለመላክ ባለመቻሉ የውጭ ምንዛሪ አገሪቱ ታጣለች፣ በአገሪቱ በማናቸውም የዕቃ ግዥ ላይ ከፍተኛ የሆነ የዋጋ ንረት ይከሰታል፣ ወጪና ገቢ ዕቃዎች ባለመኖራቸው የኑሮ ውድነት በከፍተኛ ሁኔታ ይባባሳል፣ የትራንስፖርት ማኅበር ሠራተኞች ይበተናሉ፣ የትራንስፖርት ማኅበራት ጽሕፈት ቤቶች ይፈርሳሉ፣ አሽከርካሪዎችና ረዳት አሽከርካሪዎች ከሥራ ይሰናበታሉ፣ በርካታ ባለንብረቶች ተሸካርካሪያቸው በመቆሙ ለችግር ይደረጋሉ፣ ከወደብ መነሳት የሚገባው የአገር ንብረት ባለመነሳቱ ለከፍተኛ የውጭ ምንዛሪ ክፍያ እንዳረጋለን፣ የተሽከርካሪ ባለንብረቶች ግለሰቦች ቢሆኑም መብታቸው ካልተከበረ ኑሮአቸውና ህልውናቸው አደጋ ውስጥ ሲወድቅ ደግሞ ዝም ማለት ስለማይቻላቸው ሕገ መንግሥታዊ መብታቸውን በመጠቀም ሰላማዊ ሠልፍ የማድረግ፣ የሥራ ማቆም አድማ በሰላማዊ መንገድ ወደ ማድረግ አስገዳጅ ሁኔታ ይገፋሉ፡፡
አዋጁ የዘጠኝ ወራት ዕድሜ ለማኅበራት እየሰጠ የትራንስፖርትና የሎጂስቲክስ ሚኒስቴር ጽሕፈት ቤት ደግሞ ማኅበራትን ለማፍረስ የተቻኮለ እስከሚመሰል በመስከርም ወር ጠቅላላ ጉባዔ ጥሩ፣ ንብረታችሁን አስመዝግቡ ይላል፡፡ ለተለያዩ መንግሥታዊ ድርጅቶች የማኅበራት ህልውና በመጪው ሚያዝያ 2015 ዓ.ም. ስለሚያከትም በማናቸውም ጨረታ በማኅበር ስም እንዳይጫረቱ በማለት፣ ከወዲሁ የሚያሳዝን ዕርምጃ እየወሰደ ነው፡፡ ለመሆኑ ምን ተፈልጎ ይሆን? መንግሥትስ የማኅበራትን የመፍረስና የመዋከብ ታሪክ ሰምቶ አሜን ብሎ ይሆን? ይህ ጉዳይ አግባብ አይመስለኝም፡፡ መንግሥትም ሁኔታው በቅርቡ የራስ ምታት ስለሚሆንበትና አላስፈላጊ ዕርምጃ ውስጥ ስለሚገባ ከወዲሁ ደጋግሞ ማሰብ ያስፈልገዋል፡፡ ስለዚህ ባለድርሻዎችን ማማከርና የዘርፉን ‹‹እሳት ሳይቃጠል በቅጠል›› ማለት ተገቢ ይመስለኛል፡፡ እኔ አረረም መረረም ድግሴን ተወጣሁት፡፡ መጪው አዲስ ዓመት የሰላም፣ የብልፅግና፣ የአንድነትና ያለ መፍረስ ይሁንልን!
ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እንገልጻለን፡፡