በኢትዮጵያ በተለያዩ ችግሮች ምክንያት ጎዳና የወጡ ሕፃናትና እናቶችን ማየት የተለመደ ሆኗል፡፡ በመሆኑም መንግሥትና መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች ችግሩን ለመቅረፍ እየሠሩ ይገኛሉ፡፡ መንግሥታዊ ካልሆኑ ድርጅቶች ከሚሠሩት አንዱ ደግሞ ‹‹ሙዳይ የበጎ አድራጎት ድርጅት›› ነው፡፡ ድርጅቱ እናቶችንና ሕፃናት ልጆችን ከጎዳና በማንሳት ለቁም ነገር እያበቃ ይገኛል፡፡ ወ/ሮ ሙዳይ ምትኩ የድርጅቱ መሥራችና ዋና ሥራ አስኪያጅ ናቸው፡፡ የድርጅቱን ሥራ በተመለከተ ተመስገን ተጋፋው አነጋግሯቸዋል፡፡
ሪፖርተር፡- ሙዳይ የበጎ አድራጎት ድርጅት መቼ ተመሠረተ?
ወ/ሮ ሙዳይ፡- ሙዳይ የበጎ አድራጎት ድርጅት ከዛሬ 22 ዓመት በፊት ለአፀደ ሕፃናት ተማሪዎች ትምህርት በመስጠት የተጀመረ ድርጅት ነው፡፡ ድርጅቱን ከአንድ ጓደኛዬ ጋር በመነጋገርና አብሮ በመሥራት ከፍተናል፡፡ በወቅቱም በተለያዩ ችግሮች ምክንያት ትምህርት የማያገኙ ሕፃናት ልጆችን የትምህርት ዕድል እንዲያገኙ በማድረግ እንቅስቃሴ ሊያደርግ ችሏል፡፡ በሰዓቱም ጓደኛዬ የበጎ አድራጎት ድርጅቱን አቁማ ወደ ሌላ ሥራ ገባች፡፡ ጫናውን በመወጣትና ያሉትን ችግሮች በመጋፈጥ ከጊዜ ወደ ጊዜ ድርጅቱን በማስፋትና ጎዳና ላይ የወጡ ሕፃናት ልጆችን ወደ ድርጅቱ በማምጣት አሁንም የተለያዩ አገልግሎቶችን በመስጠት ላይ ነን፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ በሴተኛ አዳሪነት የተሰማሩ እናቶችንም ሆነ ወጣቶችን ወደ ድርጅቱ በማምጣት የሥራ ዕድል እንዲያገኙ ምቹ ሁኔታዎችን መፍጠር ተችሏል፡፡ ለሴተኛ አዳሪዎች የተለያዩ ሥልጠናዎች በመስጠት ወደ ሥራ እንዲገቡ ተደርጓል፡፡ ድርጅቱ ከተመሠረተ ጊዜ ጀምሮ አገልግሎቱን የሚሰጠው በኪራይ ቤት ውስጥ በመሆኑ የተለያዩ ችግሮች ገጥመውናል፡፡ ነገር ግን እነዚህን ችግሮች በማለፍና በተለያየ መስክ ላይ የተሰማሩ እናቶችንና ሴት ልጆችን በሙያቸው የሚሠሯቸውን የእጅ ሥራ ውጤቶችን በመሸጥ ገንዘብ እንዲያገኙ ማድረግ ተችሏል፡፡ ለእነዚህም እናቶች ድርጅቱ ግብዓቶችን በማቅረብ የእጅ ሥራ ውጤታቸውን በቀላሉ እንዲያመርቱ እያደረገ ይገኛል፡፡ ድርጅቱ ሲቋቋም በበቂ ተደራጅቶ የተቋቋመ ባለመሆኑ የተነሳ ሕፃናት ልጆችን በቀን አንድ ጊዜ ብቻ ሲመግብ ቆይቷል፡፡ ይሁን እንጂ በሒደት ድርጅቱ ራሱን ቶሎ በመገንባትና አቅሙን በማሳደግ ሕፃናት ልጆችን በቀን ሦስት ጊዜ እየመገበ ይገኛል፡፡ በአሁኑ ወቅት 150 እናቶችን በራሳቸው እንዲቆሙና ክህሎታቸውን እንዲያሳድጉ ምቹ ሁኔታዎችን ፈጥሯል፡፡ በእነዚህ ዓመታትም 70 የሚሆኑ ልጆችንም በቴክኒክና በሙያ በማስመረቅ ለቁምነገር እንዲበቁና ሥራ እንዲይዙ ማድረግ ችሏል፡፡ በአሁኑ ጊዜ 200 የሚሆኑ ልጆችን በማስመረቅ የሥራ ዕድል እንዲያገኙ ምቹ ሁኔታዎችን እየፈጠረ ይገኛል፡፡ በማዕከሉ ውስጥ 650 ልጆችና 450 እናቶች ይገኛሉ፡፡
ሪፖርተር፡- አገልግሎት አሰጣጣችሁ ምን ይመስላል?
ወ/ሮ ሙዳይ፡- ለሕፃናት ልጆች የትምህርት፣ የመጠለያ፣ የምግብ፣ የአልባሳትና የሕክምና አገልግሎቶችን እየሰጠ ይገኛል፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ ለእናቶች የተለያዩ የሙያ ሥልጠናዎች እንዲወስዱ በማድረግ ድርጅቱንም፣ ራሳቸውንም በሙያቸው እንዲጠቅሙ እያደረገ ይገኛል፡፡ ድርጅቱ አብዛኞቹ እናቶች በሙያቸው በቂ የሆነ ክህሎት እንዲያገኙ በማድረግ ራሳቸው በራሳቸው ቆመው እንዲኖሩ ምቹ ሁኔታዎችን እያመቻቸ ነው፡፡ እናቶች ምግብ በማብሰል በማዕከሉ የሚኖሩ ሕፃናት ልጆችን በአግባቡ እንዲመግቡ እየተደረገ ይገኛል፡፡ ከሁሉም በላይ ደግሞ በድርጅቱ ሥር የሚኖሩ እናቶችም ሆኑ ሕፃናት ልጆች የጤና እክልና ሌሎች ችግሮች ሲገጥሟቸው ድርጅቱ ፈጥኖ በመድረስ አገልግሎቶችን እየሰጠ ይገኛል፡፡
ሪፖርተር፡- ሙዳይ የበጎ አድራጎት ድርጅት ከዚህ በፊት ሊበተን እንደነበር ይታወቃል፡፡ እንዴት ወደ ነበረበት አቋም በፍጥነት መመለስ ቻለ?
ወ/ሮ ሙዳይ፡- እንዳልከው ባለፈው ዓመት ድርጅቱ በተለያዩ ችግሮች ምክንያት ሊበተን ነበር፡፡ በተለይም ከዓመት ዓመት ከቤት ኪራይ መጨመርና ከኑሮ መወደድ ጋር ተያይዞ ድርጅቱን ለመዝጋት ጫፍ ደርሰን ነበር ማለት ይቻላል፡፡ በአሁኑ ወቅት ለቤት ኪራይ ብቻ በወር 185 ሺሕ ብር ወጪ እያደረግን እንገኛለን፡፡ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ ወ/ሮ አዳነች አቤቤ በሐያት አካባቢ 2 ሺሕ ካሬ ሜትር መሬት ቢያስረክቡንም፣ በተለያዩ ችግሮች ምክንያት መሬቱ እጃችን ሳይገባ ቀርቷል፡፡ በዚህም የተነሳ በየወሩ ለከፍተኛ ወጪ እየተዳረግን ነው፡፡ መንግሥት የተሰጠንን መሬት በአፋጣኝ ቢያስረክበን ከአምስት ሺሕ በላይ ሕፃናት ልጆችን የምንረዳ ይሆናል፡፡
ሪፖርተር፡- ድርጅቱ ከተረጂነት መንፈስ ወጥተው ለቁም ነገር የበቁ ሕፃናት ልጆችንም ሆነ እናቶች ማፍራት እንደቻለ ተናግረዋል፡፡ ከድርጅቱ ከወጡ በኋላ ምን ዓይነት ድጋፍ ይደረግላቸዋል?
ወ/ሮ ሙዳይ፡- የድርጅቱ ዋነኛና ትልቁ ዓላማው ተረጂ ወገኖችን ለቁም ነገር በማብቃት በአንድ እግራቸው እንዲቆሙ ማድረግ ነው፡፡ በተለይም በተለያዩ ችግሮች ተተብትበው የሚገኙ ልጆችን ለቁም ነገር ማብቃት በራሱ ትልቅ ስኬት ነው፡፡ ከዚህ በፊት 1,048 የሚሆኑ ሴተኛ አዳሪዎችን የተሻለ ነገር ላይ እንዲደርሱ ማድረግ ችለናል፡፡ እነዚህም ሴተኛ አዳሪዎች ተመልሰው ወደ ድርጅቱ በመምጣት የተለያዩ አገልግሎቶችን እየሰጡ ይገኛሉ፡፡
ሪፖርተር፡- ድርጅቱ ምን ዓይነት ችግር ገጥሞታል?
ወ/ሮ ሙዳይ፡- ድርጅቱ የራሱ የሆነ የቦታ ይዞታ ስለሌለው ለተለያዩ ችግሮች ሊጋለጥ ችሏል፡፡ ድርጅታችን እንጀራ በመሸጥ፣ ባልትና በማቅረብ፣ የአገር ባህል ልብስ በመሸጥ፣ ሻማ በማምረትና በሌሎችም ዘርፎች ላይ እየሠራ በአገር ውስጥ ይሸጣል፡፡ ወደ ውጭ አገር በመላክ ገቢ እያገኘ ይገኛል፡፡ ይህንን ገቢ ሙሉ በሙሉ በሚባል መልኩ ለበጎ አድራጎት ድርጅቱ እየዋለ ነው፡፡
ሪፖርተር፡- ድርጅቱ ከተመሠረተ 22 ዓመታት አስቆጥሯል፡፡ በዚህ ጊዜ ውስጥ መንግሥት ምን ዓይነት ድጋፍ አድርጎላችኋል?
ወ/ሮ ሙዳይ፡- በዚህ ሁሉ ዓመታት ውስጥ መንግሥት ምንም ዓይነት ድጋፍ አላደረገልንም ማለት ይቻላል፡፡ በቅርቡ ግን አዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የተወሰነ ገንዘብ ሰጥቶናል፡፡ ከዚህ ጎን ለጎን በአያት አካባቢ የመሬት ይዞታ እንዲሰጠን ፈቀዶልናል፡፡ የመሬት ይዞታው ከተሰጠን ለቤት ኪራይ የምንከፍለውን ለተለያዩ ተረጂዎች ድጋፍ ማዋል እንችላለን፡፡
ሪፖርተር፡- በቀጣይ ምን ለመሥራት አስባችኋል?
ወ/ሮ ሙዳይ፡- ድርጅቱ በቀጣይ በአዲስ አበባ ከተማ በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ላይ የሚገኙ ወገኖችን ኑሮ ማሻሻልና ቁጥራቸውን መቀነስ ዋናው ዓላማው አድርጎ እየሠራ ይገኛል፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ የተለያዩ ግብዓቶችን በማቅረብ የተለያዩ ሥራዎች ላይ እንዲሰማሩ የሚያደርግ ይሆናል፡፡