የምዕራብ ኦሞ ዞን በተፈጥሮ ገፀ በረከት የተላበሰ ከመሆኑ ባሻገር፣ የብዙ ባህል ባለቤት ነው፡፡ ከዚህ ውስጥ ልክ እንደ ሰሜን ኢትዮጵያ አካባቢዎች ደም መላሽነትን ለማስቀረት የሚደረገው ዕርቅ ይገኝበታል፡፡ ይህ የገዳይ ቤተሰብ ለሟች ቤተሰብ የሚሰጠው ‹‹አሻ›› (ካሳ) ይባላል፡፡ የ‹‹አሻ›› ሥርዓት የቀንድ ከብቶችና ገንዘብ መስጠት የሚችሉ ቤተሰቦች የሚካካሱበት ሥርዓት ነው፡፡
የአሻ ሥርዓትን ለመፈጸም በብሔረሰቡ ዘንድ የሚጠየቀው የከብቶችና የገንዘብ መጠን እየጨመረ መምጣቱን የደቡብ ኦሞ ዞን ኮሙዩኒኬሽን ጉዳይ መምሪያ ኃላፊ ወ/ሮ ኅብረት ታደመ ተናግረዋል፡፡
በአካባቢው ለሟች ቤተሰብ አሻ ወይም ከሳ መክፈል ያቃታቸው የገዳይ ቤተሰቦችን ከቤት ንብረቶቻቸው የማፈናቀል መሰል ያልተገቡ ድርጊቶች መበራከታቸውን አስረድተዋል፡፡
በአሻ ሥርዓት የሚጠየቀው የካሳ መጠን ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ በመሆኑም ወደ ግጭትና ያልተገባ ድርጊት መቀየሩን ወ/ሮ ኅብረት ለሪፖርተር ተናግረዋል፡፡ የአሻ ሥርዓት ከሚከናወንባቸውና አሁን አሁን ለግጭት ምክንያት ከሆኑባቸው በምዕራብ ኦሞ ዞን ከሚገኙ ብሔረሰቦች መካከል መኧን አንዱ ነው፡፡
በዞኑ ሰባት ወረዳዎችና ሦስት ከተማ አስተዳደሮች የሚገኙ ሲሆን፣ የሜኤን ብሔረሰብ በአምስት ወረዳዎችና በሁለቱ ከተማ አስተዳደሮች ውስጥ ይገኛል፡፡ ብሔረሰቡ የበርካታ ባህልና ትውፊት ባለቤት መሆኑን የዞኑ ኮሙዩኒኬሽን ጉዳይ መምርያ ያስረዳሉ፡፡
ከእነዚህም የባህልና የትውፊት ሥርዓት ‹‹አሻ›› (ካሳ) እና ጥሎሽ ይገኙበታል፡፡ በብሔረሰቡ እነዚህ ባህሎችና እሴቶች ከጊዜ ወደ ጊዜ ከጠቃሚነታቸው ይልቅ ጎጂነታቸው ገዝፎ የአካባቢው የፀጥታ ሥጋት እስከመሆን ደርሰዋል፡፡
ወ/ሮ ኅብረት እንዳስረዱት፣ ለችግሩ መፍትሔ ለመስጠት በተለያዩ ጊዜያት ውይይት ተደርጓል፡፡ ነገር ግን በውይይቱ የጋራ ስምምነት ቢደረስም፣ ተፈጻሚነቱ ላይ ችግር ታይቷል፡፡ የ‹‹አሻ›› (ካሳ) እና የጥሎሽ የክፍያ ቁጥሩ ወጥ አለመሆኑ ሌላ ችግር በማምጣቱም፣ ብሔረሰቡ በሚገኝበት አካባቢዎች ወጥ አሠራርና ትግበራ ባለመኖሩ ዞኑ ሕጋዊ ረቂቅ ደንብ ማዘጋጀቱን ጠቁመዋል፡፡
የአሻ (ካሳ) እና ጥሎሽ ሥርዓትን አቅም ባፈቀደ መጠን ለማድረግ የወጣው ረቂቅ ደንብ ላይ ሁለቱ ከተማ አስተዳደሮች፣ የምክር ቤት አፈ ጉባዔዎች፣ የፍትሕ አካላት፣ የፓርቲ አመራሮችና ሌሎች አካላት በተገኙበት ውይይት መደረጉን አስረድተዋል፡፡
በብሔረሰቡ ጠቃሚ እሴቶችንና ልምዶችን ማስቀጠል የግድ መሆኑን ያስረዱት ወ/ሮ ኅብረት፣ ነገር ግን የአከፋፈል ሥርዓቱ ወጥ ባለመሆኑ ኢኮኖሚያዊና ማኅበራዊ ቀውስ ከመፍጠሩ በተጨማሪ፣ ዘላቂ ሰላም ለማስፈን ትልቅ እንቅፋት መሆኑን ገልጸዋል፡፡
የረቂቅ ደንቡ ዓላማ
በብሔረሰቡ በተለይም አሻ፣ በጥሎሽና በለቅሶ ጊዜ የሚደረገውን የመሣሪያ ተኩስ ሥርዓት የሕግ ማዕቀፍ ውስጥ በማስገባት የሚፈጠሩ ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ችግሮችን መቅረፍ አንዱ ዓላማ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
የጋራ እሴትና ባህሉን የሚሸረሽሩ ችግሮችን ለመቅረፍ የሕግ ማዕቀፍ ማበጀት አስፈላጊ ሆኖ መገኘቱን ኃላፊዋ አስረድተዋል፡፡
አሻ እና የጥሎሽ የክፍያ መጠን
የአሻ (ካሳ) ክፍያ ከ28 እስከ 30 የቀንድ ከብቶችን የሚጠየቅ ነው፡፡ በዚህም ምክንያት የዞኑን ፀጥታ ጥያቄ ውስጥ አስገብቷል ብለዋል፡፡ ለጋብቻ ሥርዓት የሚጠየቀው የጥሎሽ ክፍያ ከ14 ከብቶች በላይ መሆኑን፣ ከአሥር ሺሕ ብር በላይ በተጨማሪ እንደሚጠየቅ አስረድቷል፡፡ በዚህም ወጣቶች ለጋብቻ ሲደርሱ ለጥሎሽ የሚጠየቁት ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ በመምጣቱ፣ ለዝርፊያና ላልተገባ ወንጀሎች እየተዳረጉ ነው፡፡ ባህሉ ለብሔረሰቡ ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ትስስስር የሚፈጥር መሆኑን ያስረዱት ወ/ሮ ኅብረት፣ ነገር ግን ከጊዜ ወደ ጊዜ የሚጠየቀው የገንዘብና የከብቶች መጠን በመጨመሩ ለፀጥታ መደፍረስ ምክንያት ሆኗል፡፡
የሕግ ባለሙያዎች በመሆኑም የማኅበረሰብ ክፍሎችን በማናገርና በማወያየት የከብቶችንና የገንዘብ መጠኑን ለመወሰን በሕግ መደንገግ እንዳለበት ከስምምነት ደርሰዋል፡፡
ማኅበረሰቡን በማወያየትም ግብዓት እየተሰበሰበ መሆኑን፣ የተገኘ ምክረ ሐሳብ ተካቶ በክልል ምክር ቤት አማካይነት እንደሚያፀድቅ አክለዋል፡፡