የኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማኅበር ከዓለም አቀፍ ቀይ መስቀል ኮሚቴ ከኔዘርላንድና ከኦስትሪያ ቀይ መስቀል ማኅበራት ግምታቸው 70 ሚሊዮን ብር የሚያወጡ አምቡላንሶች፣ ጄኔሬተሮችና 19 ቀላል ተሽከርካሪዎች ድጋፍ ማግኘቱን አስታወቀ፡፡
ድጋፉም የዓለም አቀፍ ቀይ መስቀል ኮሚቴ የኢትዮጵያ ልዑክ ኃላፊ ኒኮላስ ቮን አርክስ፣ የኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማኅበር ጸሐፊ አቶ ጌታቸው ታአ እና ሌሎች አካላት በተገኙበት ሰኞ ነሐሴ 16 ቀን 2014 ዓ.ም. ሳሪስ አካባቢ በሚገኘው የማኅበሩ ማሠልጠኛ ማዕከል ላይ የድጋፍ ርክክብ አድርገዋል፡፡
የኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማኅበር ጸሐፊ አቶ ጌታቸው ታአ እንደገለጹት፣ ከአይሲአርሲና ከሌሎች ተቋሞች የተደረገው ድጋፍ ለማኅበረሰቡ የሚሰጡትን አገልግሎቶች ወደ ተሻለ ደረጃ ለማሳደግና አንድ ዕርምጃ ከፍ ለማድረግ አስተዋጽኦ ይኖረዋል፡፡
ማኅበሩ የ20 አምቡላንሶች፣ የ19 ቀላል ተሽከርካሪዎችና የ25 ጄኔሬተሮች ድጋፍ የተደረገለት መሆኑን የገለጹት አቶ ጌታቸው፣ እነዚህም ግብዓቶች ለሁሉም ክልሎች ተደራሽ እንደሚሆኑ፣ የቅድሚያ ቅድሚያ የሚያገኙት ግን በጦርነት ምክንያት የተጎዱ ክልሎች መሆናቸውን አስረድተዋል፡፡
የተደረገው ድጋፍ የማኅበሩን አቅም ከማሳደጉም በላይ የማኅበረሰቡን ጥያቄ የሚፈታ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
የዓለም አቀፍ ቀይ መስቀል ኮሚቴ የኢትዮጵያ ልዑክ ኃላፊ ኒኮላስ ቮን አርክስ በበኩላቸው፣ ‹‹ድጋፉ በግጭትና በተፈጥሮ አደጋ ምክንያት የሕክምና ቁሳቁስ እጥረት ያጋጠማቸውን የአገሪቱ ክፍሎች ታሳቢ ያደረገ ነው፤›› ብለዋል፡፡
ድጋፉ በተለያዩ የኢትዮጵያ ክፍሎች ለሚገኙ የቀይ መስቀል ማኅበራት ተደራሽ እንደሚሆንና በተወሰነ መልኩም የግብዓት እጥረት ችግሮችን ለመፍታት እንደሚረዳ ኃላፊው አክለዋል፡፡
በአፋር ክልል በተከሰተው ግጭት ምክንያት በተለያዩ ቦታዎች ላይ ተዘዋውረው የሚያገለግሉ አምቡላንሶች መውደማቸውና አካባቢው ላይ አሁንም ቢሆን የግብዓት ችግር መኖሩን የኢትዮጵያ ቀይ መስቀል የአፋር ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት ኃላፊ አቶ አሊ ሳህሊ ተናግረዋል፡፡
ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤቱ ከዚህ በፊት በስድስት አምቡላንሶች ለማኅበረሰቡ አገልግሎት ይሰጥ እንደነበር ያስታወቁት ኃላፊው፣ ከእዚህም አምቡላንሶች መካከል አንዱ በጦርነቱ የተነሳ መውደሙን አብራርተዋል፡፡
የኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማኅበር የደቡብ ወሎ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት ኃላፊ አቶ መላኩ ቸኮል እንደገለጹት፣ በጦርነቱ ምክንያት የወደሙ ንብረቶችን ለመተካትና ያሉትን ችግሮች ለመፍታት ድጋፉ ትልቅ አስተዋጽኦ አለው፡፡
የሰብዓዊ አገልግሎትን ተደራሽ ለማድረግ ማኅበሩ ጉልህ ሚና እየተጫወተ መሆኑን፣ በተለይም በጦርነቱ ምክንያት ከቦታ ቦታ ተዘዋውረው ይሠሩ የነበሩ አምቡላንሶችም መሠረቃቸውን ጠቁመዋል፡፡
የኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማኅበር በአሁኑ ወቅት በ400 አምቡላንሶች አገልግሎት እየሰጠ ሲሆን፣ በ256 ጣቢያዎች አምቡላንሶችን በማሠራጨት ከ400 ሺሕ በላይ ዜጎችን ተደራሸ እያደረገ መሆኑ በወቅቱ ተገልጿል፡፡