የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በአቃቂ ቃሊቲ ክፍለ ከተማ የሚያስገነባው የአነስተኛና መካከለኛ ማምረቻ የኢንዱስትሪ መንደር በጀቱ 7.7 ቢሊዮን ብር ነው፡፡ ኤም ሲጂ እና ቲ ኤን ቲ ኮንስትራክሽን በተባሉ ተቋራጮች ግንባታው የሚከናወነው የኢንዱስትሪ መንደር፣ የግብርና ምርቶች ማቀነባበርያ፣ የእንጨትና ብረታ ብረት ሥራዎች፣ የጨርቃ ጨርቅና አልባሳት፣ የኮንስትራክሽን ግብዓቶች፣ የቆዳና ቆዳ ውጤቶች፣ የኬሚካልና ፕላስቲክ ውጤቶች ኤሌክትሮኒክስና የመድኃኒት ፋብሪካም ጭምር የሚይዝ ይሆናል፡፡ የከተማው አስተዳደር በራሱ በጀት የሚያከናውነው ግንባታ በ93 ሄክታር መሬት ላይ የሚያርፍ ነው፡፡ 21 ወለል ያላቸው (B+G+4+4M) ሼዶች፣ ስምንት ባለአንድ ወለል የማኑፋክቸሪንግ ሼድ፣ 400 የግብዓት አቅራቢዎችና ምርት መሸጫ ሱቆች፣ የአረንጓዴና የመዝናኛ ቦታዎች ይኖሩታል፡፡ 200 ባሶችን የሚያቆም በሦስት ዞን የተከፈለ መኪና ማቆሚያ፣ የጉድጓድ ውኃ ማመንጫ፣ ክሊኒክ፣ ዴይ ኬርና የእንግዳ መቀበያ ከግንባታው ከሚካተቱት ውስጥ ይገኙበታል፡፡ የግንባታ ውሉም ነሐሴ 17 ቀን 2014 ዓ.ም. በከተማ አስተዳደሩና በተቋራጩ መካከል ተፈርሟል፡፡
(ምንጭ፡- አዲስ አበባ ከንቲባ ጽሕፈት ቤት)