ቶኪቻ ዓለማየሁ (ኢንጂነር) በ40ዎች መጀመሪያ ዕድሜ ላይ የሚገኙ ጎልማሳ ናቸው፡፡ እግር ኳስ በሁሉም ኢትዮጵያዊ ዘንድ ተወዳጅ ስፖርት እንደመሆኑ መጠን፣ እሳቸውም አንዱ የእግር ኳሱ ወዳጅ እንደሆነ ይናገራሉ፡፡ ቶኪቻ (ኢንጂነር) እግር ኳስን በቃል እንደሚወዱት ከመግለጻቸውም በዘለለ፣ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ወደ ካሜሮን አፍሪካ ዋንጫ ማለፉን ተከትሎ፣ በሚያስተዳድሩት ድርጅታቸው አማካይነት የ17 ሚሊዮን ብር የስፖንሰርሺፕ ስምምነት በማድረግ የድርሻቸውን መወጣት ችለዋል፡፡
ከነሐሴ 21 እስከ 22 ቀን 2014 ዓ.ም. በሚደረገው የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን፣ የቀጣይ አራት ዓመታት የሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴና ፕሬዚዳንት ምርጫ ለመምራት በድሬዳዋ ተወክለው ዕጩ የሆኑት ቶኪቻ (ኢንጂነር) ወደ አመራርነት ለመምጣት የወሰኑበትን አጋጣሚ ለሪፖርተር አስረድተዋል፡፡
እንደ ዕጩ ፕሬዚዳንቱ አስተያየት ከሆነ፣ ድርጅታቸው ከፌዴሬሽኑ ጋር ስፖንሰርሺፕ ስምምነት ባሠሩበት ወቅት፣ ፌዴሬሽኑ ጉዳይ የማስፈጸም ውስንነት እንዳለበት መታዘባቸው በምርጫው ለመሳተፍ መወሰናቸውን ያስታውሳሉ፡፡
ከ12 በላይ ድርጅቶችን በሥራቸው እያስተዳደሩ የሚገኙት ቶኪቻ (ኢንጂነር)፣ ወደ አመራርነቱ ቢመጡ ፌዴሽኑን መለወጥ የሚያስችላቸው አቅም እንዳለቸው ከተረዱ መሰነባበታቸውን ያነሳሉ፡፡
‹‹ኢትዮጵያ የአፍሪካ ዋንጫ ውድድርን ከመሠረቱ አገሮች መካከል አንደኛዋ ብትሆንም፣ የእግር ኳስ ደረጃዋ ያለበት ሁኔታ ዘመናዊው እግር ኳስ ከደረሰበት ደረጃ አለመድረሱ ያስቆጫል፤›› በማለት አቶ ቶኪቻ ያስታውሳሉ፡፡
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን በውድድር ላይ ከመሳተፍ በዘለለ፣ ለተመልካቹ ማራኪና ተስፋ ሰጪ እንቅስቃሴ ማሳየት የሚችል እግር ኳስን መፍጠር እንደሚያስፈልግ ዕጩ ፕሬዚዳንቱ አስረድተው፣ ለዚህም ተመልካች ስታዲዮም ገብቶ የሚመለከትበት ሁኔታ መፍጠር ያስፈልጋል ይላሉ፡፡
የኢትዮጵያ እግር ኳስ ማግኘት ያለበትን ኢኮኖሚያዊ ጥቅም እንዳላገኘ በፅኑ የሚሞግቱት ዕጩ ፕሬዚዳንቱ፣ ‹‹እግር ኳስ ራሱን የቻለ ኢኮኖሚ ነው፤›› የሚል ዕምነት አላቸው፡፡ በዚህም እግር ኳስ ትራንስፖርትን፣ ንግድና ቱሪዝምን የማንቀሳቅስ አቅም ያለው በመሆኑ ‹‹በእጅ የያዙት ወርቅ ነው›› በማለት ያስረዳሉ፡፡
‹‹እኛ ኢትዮጵያውያን እግር ኳሱ እንደ ብራዚል መሆን አለበት የሚል ሐሳብ የለንም፡፡ በአንፃሩ ግን በኢኮኖሚ መጠቀም አለብን የሚል ሐሳብ አለኝ፤›› ሲሉ አቶ ቶኪቻ ለሪፖርተር ይናገራሉ፡፡
በዚህም መሠረት ይህንን ለማሳካት በእግር ኳሱ መሠረታዊ ለውጥ እንደሚያስፈልግ የሚገልጹት አቶ ቶኪቻ፣ ጎበዝ ተጫዋች ማፍራት ብቻ ሳይሆን፣ ምቹ መሠረተ ልማት፣ ብቁ ዳኛ፣ ብቁ አሠልጣኝ፣ የሕክምና ባለሙያና አቅም ያላቸው ክለቦች መመሥረት ያስፈልጋል በማለት ሐሳባቸውን ይሰነዝራሉ፡፡
በእግር ኳሱ በቂ የገንዘብ አቅም መፍጠር ዋነኛው የስኬት ምሰሶ እንደሆነ የሚያስረዱት ዕጩ ፕሬዚዳንቱ፣ ለዚህም የንግድ ተቋማት ወደ እግር ኳስ ገብተው ምርቶችን እንዲሸጡ የሚያስችል አቅም ያለው ፌዴሬሽን ማደራጀት ያስፈልጋል ይላሉ፡፡
‹‹የኢትዮጵያ እግር ኳስ ውድድሮች ላይ ሞተር ምርትን መሸጥ መለመድ ይኖርበታል፡፡ በርካታ ምርቶችን በውድድሮች ላይ በመሸጥ ገቢን በማሳደግና ክለቦች ያለ ድጎማ የሚተዳደሩበትን መንገድ ማበጀት ያስፈልጋል፤›› ሲሉ አቶ ቶኪቻ ያብራራሉ፡፡
ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ከኢትዮጵያ እግር ኳስ ጋር ተያይዞ የሚነሳው የስታዲዮም ችግር ተጠቃሽ ሲሆን፣ መንግሥት ረብጣ ገንዘቦችን አፍስሶ በክልሎች ያስገነባቸው ስታዲዮሞች ቢኖሩም፣ ብሔራዊ ቡድኑ የሌላ አገር ስታዲየም ለመጠቀም የተገደደበት ወቅት ላይ ይገኛል፡፡
የስታዲየም ጉዳይ ብሔራዊ ፌዴሬሽኑን ለቀጣይ አራት ዓመታት ለሚመሩት አዲሶቹ ዕጩ ተመራጮች ፈታኝ የቤት ሥራ እንደሚሆን ይጠበቃል፡፡ መንግሥት በርካታ ስታዲዮሞችን በክልሎች ማስገንባቱን ያስረዱት ዕጩ ፕሬዚዳንቱ፣ ከዚያም በዘለለ በዩኒርሲቲዎች ላይ ተገንብተው የሚገኙ በርካታ ስታዲዮሞችን ዓለም አቀፍ ደረጃቸውን የጠበቁ ማድረግ የሚቻልበትን ዕድሎች በፊዴሬሽኑ እጅ ላይ እንደነበር ያስታውሳሉ፡፡
‹‹ፌዴሬሽኑ የተገነቡትን ስታዲዮሞች ደረጃቸውን የጠበቁ እንዲሆኑ ማድረግ የሚችልበት አጋጣሚ ነበር፡፡ በክልል የተገነቡ ስታዲዮሞችን ጥቃቅን ጉዳዮችን አገር ውስጥ ባሉ ባለሀብቶች ድጋፍ አማካይነት ማስፈጸም እየተቻለ፣ ብሔራዊ ቡድኑ በባዕድ አገር ስታዲዮም የሚጫወትበት ሁኔታ አግባብ አይደለም፤›› በማለት ዕጩ ፕሬዚዳንቱ ያብራራሉ፡፡
ለዘመናት ከፖለቲካ ነፅቶ የማያውቀውንና ውዝግቦች የማያጡት የኢትዮጵያ እግር ኳስ፣ ከእግር ኳስ ጨዋታው በላይ የውስጥ ሽኩቻው የሰውን ቀልብ ይገዛል፡፡ ከዚህም ባሻገር ፖለቲካዊ ሹመቶች፣ እንዲሁም መቧደን የሚያዘነብልበት የስፖርት ዘርፉ መሆኑን በርካቶች ሲያነሱ ይስተዋላል፡፡
ሆኖም ዕጩ ፕሬዚዳንቱ ከፖለቲካ ጋር ምንም ዓይነት ግንኙነት እንደሌላቸው ገልጸው፣ ማንኛውም ሰው እግር ኳስን ብሎ ከመጣ ከማንኛውም ባለሙያ ጋር በግልጽ መሥራት እንደሚፈልጉ አስረድተው፣ 120 ሚሊዮን ሕዝብን የሚወክል ፌዴሬሽን በአንድ ግለሰብ ውሳኔ እጅ ላይ መውደቅ የለበትም የሚል አቋም እንዳላቸውም ለሪፖርተር አስረድተዋል፡፡
‹‹ፌዴሬሽን የሚመራ አካል በሕገ ደንብ ይመራል እንጂ በስሜት አይመራም፡፡ ተቋም በስሜት የሚመራውን አስተዳዳሪ አይፈልግም፡፡ በዚህም በፌዴሬሽኑ እግር ኳሱ ላይ ልዩነት እንፈጥራለን ለሚሉ ሰዎች በሩን ክፍት ማድረግ ያስፈልጋል፤›› ሲሉ ቶኪቻ (ኢንጂነር) በቀጣይ ፌዴሬሽኑን መምራት የሚፈልጉበትን መንገድ ጠቁመዋል፡፡
በንግዱ ዓለም ስኬታማ ደረጃ ላይ መድረስ የቻሉት ዕጩ ፕሬዚዳንቱ፣ እግር ኳሱ ያለውን ሀብት መረዳት ተገቢ ነው ይላሉ፡፡ ለዚህም የኢትዮጵያ እግር ኳስ ተመልካች የብሔራዊ ቡድኑን መለያ ማግኘት የማይችልበት ቁመና ላይ እንዳለ አስረድተው፣ ይህንን ዕድል ተጠቅሞ ከፍተኛ የገበያ ዕድል መፍጠር እንደሚያስፈልግና በንግድ ዓለም ያሉትን ባለሀብቶች ወደ እግር ኳሱ በማምጣት እንደሚሠራ ጠቁመዋል፡፡
ከ12 በላይ የተለያዩ ድርጅቶችን እየመሩ የሚገኙት ቶኪቻ (ኢንጂነር)፣ ፌዴሬሽኑ በወጣቶች መመራት እንደሚገባ ፅኑ እምነት እንዳላቸው አልሸሸጉም፡፡ በዚህም መሠረት ማንኛውም ተመራጭ ቦታው ላይ የሙጥኝ ማለት ሳይሆን፣ መሥራት የሚገባው በአግባቡ ሠርቶ አቅም ላለው ባለሙያ ማስረከብ ይገባል ይላሉ፡፡
በተለይ ክልሎች ለአመራርነት የሚመርጧቸውን ዕጩ ተወዳዳሪዎች በደንብ ማወቅ እንደሚገባቸውና ውሳኔያቸው ላይ ጥንቃቄ ማድረግ እንደሚገባቸው ያስታውሳሉ፡፡
‹‹ወቅቱ እንደ እኔ ዓይነት ወጣት አመራር ይፈልጋል፡፡ አብዛኛው ኢትዮጵያዊ ወጣት በመሆኑ ወጣት መሪ ይፈልጋል፡፡ ለረዥም ዓመት ያገለገሉ ባለሙያዎች ደግሞ ልምዳቸውን ለወጣቶቹ ማስረከብ አለባቸው፤›› በማለት ዕጩ ፕሬዚዳንቱ አቶ ቶኪቻ ተናግረዋል፡፡
‹‹እኔ ፖለቲካ ውስጥ የለሁም፡፡ እኔ ጋ የሚመጣ ሰው እግር ኳሱን ብቻ ማዕከል አድርጎ መሆን ይኖርበታል፡፡ እኔም ለማንኛውም እግር ኳስን ብሎ ለሚመጣ ባለሙያ በሬ ክፍት ነው፤›› በማለት ቶኪቻ (ኢንጂነር) ሐሳባቸውን ይሰነዝራሉ፡፡
እሑድ ነሐሴ 22 ቀን 2014 ዓ.ም. በሚጠበቀው ምርጫ ላይ ዕጩ ሆነው የቀረቡት ቶኪቻ (ኢንጂነር)፣ ለምርጫው ሲባል ብሔራዊ ቡድኑን ለአፍሪካ ዋንጫ እናሳልፋለን ብሎ የማይጨበጠጥ ቃል መግባት እንደማያስፈልግና ለለውጥ መሠረታዊ ሥራዎች ሠርተው ማሳየት እንደሚያስፈልግ ይገልጻሉ፡፡
በመጪው እሑድ ለሚከናወነው ምርጫ የኢትዮጵያ እግር ኳስ ለፌዴሬሽን ፕሬዚዳንትነት አቶ ኢሳያስ ጅራን ከኦሮሚያና፣ አቶ መላኩ ፈንታን ከአማራ ክልል እንዲሁም ቶኪቻ ዓለማየሁ (ኢንጂነር) ከድሬዳዋ ከተማ አስተዳደር በዕጩ ፕሬዚዳንትነት ቀርበዋል፡፡
በቀጣይ አራት ዓመታትም ፌዴሬሽኑን የሚመራው ፕሬዚዳንት የፊታችን እሑድ በሚደረገው ምርጫ፣ በጠቅላላ ጉባዔው ከክልል በተወከሉ ተወካዮች ምርጫ መሠረት ይታወቃል፡፡