Tuesday, March 28, 2023

በኢሠፓ ስም ፓርቲ ለማቋቋም የቀረበው ጥያቄ በምርጫ ቦርድ ውድቅ ተደረገ

- Advertisement -spot_img

በብዛት የተነበቡ

የደርግ መንግሥት ዋነኛ ፓርቲ በነበረው በኢትዮጵያ ሠራተኞች ፓርቲ (ኢሠፓ) ስያሜ ፓርቲ ፓርቲ ለማቋቋም ለኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ቀርቦ የነበረውን ጥያቄ፣  ቦርዱ ውድቅ አደረገው፡፡

ቦርዱ ጥያቄውን ውድቅ ያደረገበትን ዋነኛ ምክንያት አድርጎ የገለጸው፣ በ1983 ዓ.ም. ፓርቲው ከሥልጣን መውረዱን ተከትሎ የወጣውን ሰላማዊ ሠልፍና ሕዝባዊ የፖለቲካ አዋጅ ነው፡፡ አዋጁ በአንድ አንቀጽ ኢሠፓን ‹‹ፀረ ዴሞክራሲና ወንጀለኛ ድርጅት›› በማለት ያፈረሰው ሲሆን፣ እስካሁንም ይህ አዋጅ በሥራ ላይ ነው፡፡

ፓርቲው ጥያቄውን ያቀረበው ይህ አዋጅ ሳይሻርና በአንድ ወቅት በአገሪቱ የፖለቲካ ታሪክ ውስጥ ህልውና ከነበረው ፓርቲ ጋር ተመሳስሎ በመቅረቡ ነው፡፡ በዚሀም ሁኔታ ውስጥ ምርጫ ቦርድ ጥያቄውን ለመቀበል ያልተሻረ ሕግ በመኖሩና የፈረሰ ድርጅትም እንደገና እንደተቋቋመ የሚያስመልስ የሕዝብ ዕይታ ይፈጥራል ሲል፣ ለፓርቲው አስተባባሪዎች ለእነ አቶ ዮሐንስ ታደሰ ማክሰኞ ነሐሴ 17 ቀን 2014 ዓ.ም. በቦርዱ ሰብሳቢ ወ/ሪት ብርቱካን ሚደቅሳ ተፈርሞ የተሰጠው ደብዳቤ ያስረዳል፡፡

በቀድሞው የኢትዮጵያ ፕሬዚዳንት ሌተና ኮሎኔል መንግሥቱ ኃይለ ማርያም ዋና ጸሐፊነት ሲመራ የነበረው ኢሠፓ፣ ከ1977 ዓ.ም. ጀምሮ እስከ ደርግ መንግሥት ውድቀት 1983 ዓ.ም. ድረስ ለስድስት ዓመታት አገሪቱን አስተዳድሯል፡፡ ሌተና ኮሎኔል መንግሥቱን ጨምሮ የተወሰኑ አመራሮች በስደት፣ ሌሎች በርካቶች ደግሞ በእስር ለዓመታት አሳልፈዋል፡፡ የቀይ ሽብርን ክስ ጨምሮ በበርካታ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች አመራሮቹ ተከሰው እስራት ከተፈረደባቸው በኋላ፣ በይቅርታ መለቀቃቸው አይዘነጋም፡፡   

ምርጫ ቦርድ በምርጫ ወቅት እንዲህ ዓይነት አቀራረቦች የሕዝብ ዕይታን እንደሚያምታቱ በመግለጽ፣ ኢሠፓ በሚባል ስያሜ ፓርቲ ለመመሥረት የቀረበለትን ጥያቄ ሰኞ ነሐሴ 16 ቀን 2014 ዓ.ም. ባደረገው ስብሰባ ውድቅ ማድረጉን አስታውቋል፡፡

የፓርቲው አስተባባሪዎች ሌላ ስያሜ በመምረጥ የፖለቲካ እንቅስቃሴ ማድረግና  ዓላማቸውን ማራመድ እንዲችሉ፣ እንዲሁም ለመመዝገብ የሚያስችላቸውን ጥያቄ እንዲያቀርቡ ምርጫ ቦርድ ውሳኔ ማስተላለፉን አስረድቷል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ትኩስ ጽሑፎች

ተዛማጅ ጽሑፎች

- Advertisement -
- Advertisement -