Saturday, March 25, 2023

መቶ በመቶ የከፈሉ የ40/60 ቤቶች ተመዝጋቢዎች ለሕገ መንግሥት ጉዳዮች አጣሪ ጉባዔ ምላሽ እንዲያቀርቡ ታዘዙ

- Advertisement -spot_img

በብዛት የተነበቡ

  • ክሩክሩ ሰበር ደርሶ ለተመዝጋቢዎቹ ተፈርዶ ነበር

የ40/60 የጋራ መኖሪያ ቤቶች በቅድሚያ እንዲሰጣቸው በሰበር ሰሚ ችሎት ተወስኖላቸው የነበሩና ሙሉ ለሙሉ የቆጠቡ ተመዝጋቢዎች፣ ስለቀረበባቸው አቤቱታ ለሕገ መንግሥት ጉዳዮች አጣሪ ጉባዔ ምላሽ እንዲያቀርቡ ታዘዙ፡፡

ተመዝጋቢዎቹ አቤቱታ የቀረበባቸው በአዲስ አበባ ከተማ ቤቶች ልማት ኮርፖሬሽን (የቁጠባ ቤቶች ልማት ኢንተርፕራይዝ) አመልካችነት ነው፡፡ የኮርፖሬሽኑን አቤቱታ የተመለከተው ጉባዔው፣ ጉዳዩ ‹‹የሕገ መንግሥት ጉዳይ እንዳለበት እምነት በማሳደሩ›› ተጠሪዎች ምላሽ እንዲሰጡ በማለት ትዕዛዝ ሰጥቷል፡፡

ተጠሪዎቹ ምላሻቸውን እንዲያቀርቡ የታዘዙት በጽሑፍ እንደሆነ ለሪፖርተር የተናገሩት የጉባዔው ጽሕፈት ቤት የኮሙዩኒኬሽ ጉዳዮች ዳይሬክተር ወ/ሮ ይርጋለም ጥላሁን፣ ጉባዔው ምላሹን ተመልክቶ ሊከተላቸው የሚችላቸው ሦስት አማራጮች እንዳሉ አስረድተዋል፡፡

‹‹ጉባዔው ከምላሹ በኋላ ትርጉም አያስፈልገውም ብሎ ካሰበ ውሳኔ ያሳልፋል፣ ካልሆነ ደግሞ የሕዝብ ይፋ ውይይት ተደርጎ ሐሳብ እንዲሰጥበት ይደረጋል፤›› በማለት ሁለቱን አማራጮች ገልጸዋል፡፡ ጉባዔው የተለያዩ አካላት የሚሳተፉበት ውይይት አድርጎ በሚያገኘው ሐሳብ አቤቱታው ትርጉም ያስፈልገዋል ብሎ ካመነ፣ ለፌዴሬሽን ምክር ቤት የውሳኔ ሐሳብ እንደሚያቀርብ ገልጸዋል፡፡

ከ900 በላይ የሚሆኑ የ40/60 የጋራ መኖሪያ ቤቶች ተመዝጋቢዎች ጉዳይ ወደ ሕገ መንግሥት ጉዳዮች አጣሪ ጉባዔ የሄደው፣ ተመዝጋቢዎቹ ባለፈው ዓመት ሰኔ 16 ቀን 2013 ዓ.ም. የታገዱባቸው ቤቶች እንዲሰጧቸው የሰበር ሰሚ ችሎት ከወሰነ በኋላ ነው፡፡ ውሳኔውን ተከትሎ ከሳሾቹ የአፈጻጸም መዝገብ ከፍተው ሰኔ 2 ቀን 2014 ዓ.ም. ፍርድ ቤት የአስተዳደሩ ኃላፊዎች ቀርበው እንዲያስረዱ ቀጠሮ ተሰጥቶ እንደነበር፣ የተመዝጋቢዎቹ ጠበቃ አቶ አንዱዓለም በዕውቀቱ ለሪፖርተር ተናግረዋል፡፡

ይሁንና የአሁኑ የአዲስ አበባ የቤቶች ልማት ከኮርፖሬሽን ውሳኔውን በመቃወም የሕገ መንግሥት ትርጓሜ እንዲሰጠው ለጉባዔው አቤት በማለቱ፣ ሚያዝያ 4 ቀን 2014 ዓ.ም. ቀጠሮ ተይዞበት የነበረው የአፈጻጸም ሥርዓት መቋረጡን አቶ አንዱዓለም አስረድተዋል፡፡

ባለፈው ሳምንት 29 አቤቱታዎችን የመረመረው የሕገ መንግሥት ጉዳዮች አጣሪ ጉባዔ 27 አቤቱታዎችን ‹‹የሕገ መንግሥት ጥሰት የሌለባቸው›› በማለት ሲዘጋ፣ ቀሪዎቹ ሁለቱ የሕገ መንግሥት ጉዳይ እንዳለባቸው ተመልክቷል፡፡ የሕግ መንግሥት ጉዳይ አለባቸው ከተባሉት አቤቱታዎች ውስጥ አንዱ የሆነው ሙሉ ለሙሉ የከፈሉ የ40/60 ተመዝጋቢዎች ጉዳይ፣ ለተጨማሪ ማጣራት ተጠሪዎች ምላሽ እንዲሰጡ ትዕዛዝ ተላልፎበታል፡፡

የሁለቱ ወገኖች ክርክር መነሻ የሆነው የቀድሞው የከተማ ልማትና ኮንስትራክሽን ሚኒስቴር አውጥቶት በነበረው የዕጣ አወጣጥ መመርያ ቁጥር 21/2005 ነው፡፡ የመመርያው አንቀጽ 16 እና አንቀጽ ሁለት ንዑስ አንቀጽ ስድስት የቤቱን ዋጋ መቶ በመቶ የከፈሉ የ40/60 ተመዝጋቢዎች በቅድሚያ ቤት እንደሚያገኙ የዕጣ ውድድሩ የሚደረገው ሙሉ ክፍያ በፈጸሙ ተመዝጋቢዎች መካከል እንደሆነ በመደንገጉ ነው፡፡

ነገር ግን በቀድሞው የአዲስ አበባ ከተማ ምክትል ከንቲባ ታከለ ኡማ (ኢንጂነር) የሚመራው የከተማ አስተዳደሩ የካቲት 27 ቀን 2011 ዓ.ም. ዕጣ ሲያወጣ፣ 20 እና 40 በመቶ የቆጠቡ ተመዝጋቢዎች በዕጣው ውስጥ እንዲካተቱ አድርጓል፡፡ በዚህም ምክንያት ሙሉ ለሙሉ ከቆጠቡት ተመዝጋቢዎች ውስጥ አብዛኞቹ የቤት ባለቤት ለመሆን አልቻሉም፡፡

በወቅቱ የዕጣ አወጣጡ መመርያውን የጣሰና ክፍያ ሲፈጽሙ ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ጋር የገቡትን ውል የሚጥስ መሆኑን በመጥቀስ፣ ጉዳዩን ወደ ፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ፍትሐ ብሔር ችሎት ወስደውት ነበር፡፡ የሁለቱ አካላት ከሥር ፍርድ ቤት እስከ ሰበር ድረስ ባደረጉት ክርክር ተመዝጋቢዎቹ ቤቱ እንዲሰጣቸው ተፈርዶላቸዋል፡፡

ፍርድ ቤት ይኼንን ቢወስንም ውሳኔው እንዳልተፈጸመ የሚያስረዱት ጠበቃው አቶ አንዱዓለም፣ ‹‹በተደጋጋሚ ፈጽሙ ሲባሉ መቁጠሪያ ጊዜ አጣን እያሉ አልፈጸሙም፡፡ ይኼንን ስናይ ቀጠሮ እያዘገዩ ነው ብለን አቤት አልን፤›› በማለት የአፈጻጸም መዝገብ የተከፈትበን ሒደት አስረድተዋል፡፡ የአዲስ አበባ ከተማ ቤቶች ልማት ኮርፖሬሽን ጉዳዩን ወደ ሕገ መንግሥት ጉዳዮች አጣሪ ጉባዔ ሲወስደው የአፈጻጸሙ ሒደት ተቋርጧል፡፡

ኮርፖሬሽኑ መቶ በመቶ የቆጠቡ የ40/60 ተመዝጋቢዎች የጋራ መኖሪያ ቤት ቅድሚያ እንዲሰጣቸው የተሰጠውን ውሳኔ በመቃወም ትርጉም እንዲሰጥ አቤቱታውን ያቀረበው፣ ስለፍትሐዊነትና እኩል ተጠቃሚነት የሚደነግጉ ሁለት የሕገ መንግሥት አንቀጾችን በመጥቀስ ነው፡፡

በቀዳሚነት የተጠቀሰው የሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 41 ንዑስ አንቀፅ ሦስት፣ ‹‹የኢትዮጵያ ዜጎች ሁሉ በመንግሥት ገንዘብ በሚካሄዱ ማኅበራዊ አገልግሎቶች በእኩልነት የመጠቀም መብት አላቸው፤›› የሚል ነው፡፡

ሌላኛው አንቀጽ 89 ንዑስ አንቀጽ ሁለት ደግሞ መንግሥት የኢትዮጵያውያን የኢኮኖሚ ሁኔታዎች ለማሻሻል፣ እኩል ዕድል እንዲኖራቸው ለማድረግና ሀብት ፍትሐዊ በሆነ መንገድ የሚከፋፈሉበትን ሁኔታ የማመቻቸት ግዴታ እንዳለበት የሚደነግግ ነው፡፡

ጉባዔው በዚህ አቤቱታ ላይ ሰፊ ጊዜ ወስዶ እንደ ተወያየና እንደ ተከራከረ የተገለጸ ሲሆን፣ በመጨረሻም ‹‹የሕገ መንግሥት ጉዳይ እንዳለበት እምነት በማሳደሩ›› ውሳኔ ወይም የውሳኔ ሐሳብ ከመሰጠቱ በፊት፣ በጉባዔው ለተጨማሪ ማጣራት ተጠሪዎች ምላሽ እንዲሰጡ በማለት ትዕዛዝ ሰጥቷል።

የተመዝጋቢዎቹ ጠበቃ የሆኑት አቶ አንዱዓለም የጉባዔውን ትዕዛዝ እንደሰሙ ገልጸው፣ እስካሁን ግን በጽሑፍ የደረሳቸው ነገር እንደሌለ ተናግረዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ትኩስ ጽሑፎች

ተዛማጅ ጽሑፎች

- Advertisement -
- Advertisement -