Tuesday, March 28, 2023
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

ባህርና ትራንስፖርት ሎጂስቲክስ አገልግሎት ድርጅት ከታክስ በፊት 5.6 ቢሊዮን ብር ማትረፉን አስታወቀ

- ማስታወቂያ -

ተዛማጅ ፅሁፎች

በተጠናቀቀው የበጀት ዓመት በዓለም አቀፍ፣ አገራዊ ግጭቶችና የዓለም የንግድ ኢኮኖሚ መዛባት ችግሮች ምክንያት ዕቅዱን ለመከለስ የተገደደው የኢትዮጵያ ባህር ትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ አገልግሎት ድርጅት፣ ከታክስ በፊት 5.6 ቢሊዮን ብር ማግኘቱን ትናንት ማክሰኞ ነሐሴ 17 ቀን 2014 ዓ.ም. አስታወቀ፡፡

የኮቪድ-19 ወረርሽኝ ተፅዕኖ፣ የሩሲያና ዩክሬን ጦርነት፣ የኮንቴይነር አቅርቦት እጥረት፣ የባህር ማጓጓዣ ዋጋ መናር፣ የወደቦች መጨናነቅ፣ በአገር ውስጥ በጦርነቱ ምክንያት በሦስት ደረቅ ወደቦች (መቀሌ፣ ኮምቦልቻና ወረታ) ሙሉ በሙሉና በከፊል ጉዳት በመድረሱ ምክንያት፣ ለረዥም ጊዜያት አገልግሎቶች በመቋረጣቸው ድርጅቱን በተጠናቀቀው የበጀት ዓመት ፈትነው ከነበሩት ጉዳዮች ውስጥ ተጠቃሽ መሆናቸው ተገልጿል፡፡

ድርጅቱ በተጠናቀቀው የበጀት ዓመት በባህር ትራንስፖርት አገልግሎት ዘርፍ ከሚሰጡት አገልግሎቶች ማለትም የድርጅቱን መርከቦችና የኪራይ መርከቦችን ተጠቅሞ በማጓጓዝ፣ በጭነት አስተላላፊነት አገልግሎት በመልቲ ሞዳልና በዩኒ ሞዳል የትራንስፖርት ሥርዓት ኮንቴይነር በማጓጓዝ፣ በወደብና በተርሚናል አገልግሎት፣ እንዲሁም ከሌሎች የገቢ ምንጮች 51.4 ቢሊዮን ብር ገቢ መሰብሰቡ የታወቀ ሲሆን፣ ይህም ከታቀደው 40.41 ቢሊዮን ብር ገቢ ብልጫ ያሳየ መሆኑ ተገልጿል፡፡

በ2014 የበጀት ዓመት ከታክስ በፊት 5.64 ቢሊዮን ብር ማስመዘገቡን ያስታወቁት የድርጅቱ ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ሮባ መገርሳ፣ ለማትረፍ ከታቀደው 4.74 ቢሊዮን ብር ብልጫ ያለው አኃዝ ከመመዝገቡ ባሻገር፣ የአገልግሎት ድርጅቱ የፋይናንስ አቅም በዚህ ወቅት 64.85 ቢሊዮን ብር መድረሱን ጨምረው ገልጸዋል፡፡

የኮቪድ-19 ወረርሽኝ ባለፉት ሁለት ዓመታት የፈጠረው ተፅዕኖ ውጤቱ በተለይም በተጠናቀቀው የበጀት ዓመት መታየቱ የተመላከተ ሲሆን፣ ይህም ከፍተኛ የሆነ የኮንቴይነርና የወደብ መሣሪያዎች እጥረት፣ የባህር ማጓጓዣ ዋጋ መናር፣ የወደቦች መጨናነቅና መርከቦች በወደብ ረዘም ላለ ጊዜ እንዲቆዩ ማድረጉን ድርጅቱ አስታውቋል።

በተለይ በዓለም አቀፍ ደረጃ በተከሰተ የኮንቴይነር እጥረትና የባህር ማጓጓዣ ዋጋ መናር ምክንያት፣ የኢትዮጵያ የገቢና ወጪ ንግድ እንቅስቃሴ በቀጥታ ተጎጂ እንደሆነ ሪፖርቶች እንደሚያስረዱ ተገልጾ፣ ይህ ሁኔታ በድርጅቱ አፈጻጸም ላይ ተፅዕኖ ያሳደረ ነበር ተብሏል፡፡

ከተጀመረ ስድስት ወራት ያለፉት የሩሲያና የዩክሬን ጦርነት በአውሮፓ የንግድ ኮሪደርና በጥቁር ባህር ወደቦች አካባቢ ከሚያጋጥሙ የንግድ መስተጓጎሎች በተጨማሪ፣ በምዕራቡ ዓለም በሩሲያ ላይ እየተጣሉ ያሉ የኢኮኖሚ ማዕቀቦች፣ በዓለም የንግድ እንቅስቃሴ ላይ ተፅዕኖ ማሳደራቸው ይታወቃል፡፡

ኮቪድ-19 ዓምናም ሆነ ከዚያ በፊት በነበረው ጊዜ የዓለም የንግድ እንቅስቃሴን በእጅጉ ከማወኩም በላይ፣ በተለይ የኢትዮጵያ 60 በመቶ የሚደርሰው ገቢ የኮንቴይነር ጭነት የሚነሳበት በቻይና ወደብ አካባቢ ተፅዕኖው አሁንም ድረስ የሚታይ ነው ያሉት አቶ ሮባ በወደቦች መጨናነቅ፣ የኮንቴነር እጥረትና የመርከብ ማጓጓዣ ዋጋ መናር በዓመቱ ካጋጠሙ ተፅዕኖዎች ተጠቃሾቹ መሆናቸውን አብራርተዋል፡፡

አቶ ሮባ  የድርጅታቸውን የ2014 የበጀት ዓመት ዕቅድ አፈጻጸምን አስመልክቶ በተቋሙ ዋና መሥሪያ ቤት በሰጡት መግለጫ እንደተናገሩት፣ ዓለም አቀፋዊ የሎጂስቲክስ ዘርፉን ያጋጠሙት ክስተቶች ከመጉላታቸው በፊት ተቋሙ ባቀደው ዕቅድ ውስጥ ለአብነትም ማዳበሪያ 2.2 ሚሊዮን ቶን ይገዛል የሚል ዕቅድ ቢኖርም ከዋጋ መናርና የምርት እጥረት ጋር ተያይዞ የተገዛው 1.28 ሚሊዮን ቶን ነበር፡፡ ከዚህ በተጨማሪም  በተጠናቀቀው የበጀት ዓመት ወደ አገር ውስጥ የገባው ብረት መቀነሱ ተገልጾ፣ ለሲሚንቶ ምርት በግብዓትነት የሚያገለግለው የድንጋይ ከሰል በአገር ውስጥ ምርት ይተካል በሚል ግዥው በመቀነሱ፣ በዚያው ልክ የድርጅቱ የገቢ ጭነት የማስተናገድ ድርሻው ቀንሶ ያለፈበት ዓመት እንደነበር አቶ ሮባ አስረድተዋል፡፡

የባህርና ትራንስፖርት ሎጂስቲክስ አገልግሎት ድርጅት ከላይ የተዘረዘሩ ጉዳዮችን ከግምት ውስጥ በመክተት የነበረውን ነባራዊ ሁኔታ ያገናዘበ የዕቅድ ክለሳ በማድረግ ወደ ሥራ ገብቶ 7.2 ሚሊዮን ቶን የወጪና ገቢ ጭነት ማስተናገዱ የተገለጸ ሲሆን፣ ከዚህም ውስጥ 116 ሺሕ ኮንቴይነር ገቢ ጭነትና ከአንድ ሚሊዮን ቶን በላይ የኤክስፖርት ጭነት በጂቡቲ ወደብ በኩል ማስተናገዱን አስታውቋል፡፡

‹‹የድርጅቱ መርከቦች ሙሉ በሙሉ ዕዳቸውን ከፍለው ጨርሰው ወደ ትርፍ ገብተዋል፤›› ያሉት አቶ ሮባ፣ 1.5 ሚሊዮን ቶን የሌሎች አገሮችን ጭነት ከማጓጓዛቸው ባሻገር፣ 19 ሺሕ ኮንቴይነሮች የኢትዮጵያ ጭነቶች እንደተጓጓዙባቸው ገልጸዋል፡፡ ከዚህ በተጨማሪ ድርጅቱ በተጠናቀቀው የበጀት ዓመት 76 ሚሊዮን ዶላር የውጭ ምንዛሪ ገቢ ማግኘቱን፣ በመርከቦች ምክንያት የተገባው ብድር ተከፍሎ ተጠናቆ ለመጀመርያ ጊዜ ከ1.8 ቢሊዮን ብር በላይ በመርከቦቹ አማካይነት ትርፍ ማስመዝገቡን አስታውቋል፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች