Saturday, March 25, 2023
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

የትራንዚት ኮሪደሮችን ለማስፋት አገሮች የሚያደርጉት ስምምነት እየተጠበቀ ነው

- ማስታወቂያ -

ተዛማጅ ፅሁፎች

የአሰብ ወደብን ለመጠቀም ዝግጅት መደረጉ ተጠቆመ

ኢትዮጵያ ከጂቡቲ ወደብ በተጨማሪ የትራንስፖርት ኮሪደሮችን ለማስፋት ከጎረቤት አገሮች ጋር የሚደረጉ የሁለትዮሽ ስምምነቶችን እየጠበቀች መሆኑ ተገለጸ፡፡

ይህ የተገለጸው የኢትዮጵያ ባህርና ትራንስፖርት ሎጂስቲክስ አገልግሎት ድርጅት፣ የተጠናቀቀውን የበጀት ዓመት የሥራ አፈጻጸም አስመልክቶ በተሰጠ ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ ነው፡፡

በጋዜጣዊ መግለጫው ሰሞኑን የኬንያ የወደብ ሹሞች ኢትዮጵያ መጥተው የላሙን ኮሪደር ኢትዮጵያ እንድትጠቀም ስለማግባባታቸው፣ እንዲሁም በኢትዮጵያ መንግሥት በኩል የአሰብ ወደብን የመጠቀም ፍላጎት አስመልክቶ ከጋዜጠኞች ለድርጅቱ ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ሮባ መገርሳ ጥያቄዎች ቀርበዋል፡፡

ከዚህ ቀደም ከአሰብ ወደብ አጠቃቀም ጋር የተያያዙ የዝግጅት ሥራዎች ሲደረጉ መቆየታቸውን በመረጃ ደረጃ እንደሚያውቁ የተናገሩት የድርጅቱ ዋና ሥራ አስፈጻሚ፣ ዝግጅቶቹ ተጠናቀውና የሁለትዮሽ ስምምነቱ ተቋጭቶ የአሰብ ወደብ አግልግሎት ለመስጠት ዝግጁ በሚሆንበት ጊዜ ድርጅታቸው ለመጠቀም መዘጋጀቱን አስታውቀዋል፡፡

‹‹ከአሰብ ጋር ተያይዞ ለተነሳው ጥያቄ በማንኛውም ጊዜ የሁለትዮሽ ስምምነት ተጠናቆ ኮሪደሩ ለአገልግሎት ክፍት ሲሆን፣ ድርጅቱ አገልግሎት የሚሰጥበት ሁኔታ ይኖራል፡፡ በጉጉት እንጠብቀዋለን፣ ተወዳዳሪ ነው፤›› በማለት አስረድተዋል፡፡

ኢትዮጵያ ለገቢና ወጪ የትራንዚት ትራንስፖርት ኮሪደር በዋነኛነት እየተጠቀመች ያላችው የጂቡቲ ወደብን መሆኑን ያስረዱት አቶ ሮባ፣ ይህም የታወቀ አሠራር ተዘርግቶለት በሁለትዮሽ ወይም በአገሮች ውስጥ የሚገኙ የሚመለከታቸው ባለሥልጣን መሥሪያ ቤቶች የሚያደርጉትን ስምምነት መሠረት አድርጎ የሚከናወን መሆኑን አብራርተዋል፡፡ 

ከጂቡቲ ውጪ በሌሎች አገሮች ወደቦች የትራንዚት ትራንስፖርት ዝርዝር አጠቃቀም ላይ የአገሮች የሁለትዮሽ ስምምነቶችና ፕሮቶኮል አለመዘጋጀቱ ይታወቃል፡፡ የባህር ትራንስፖርትና ሎጀስቲክስ አገልግሎት ድርጅት የሚመለከታቸው የመንግሥት አካላት የሚያደርጉትን የሁለትዮሽ ስምምነት መሠረት አድርጎ ወደ አገልግሎት  የሚገባ  መሆኑን ያስረዱት አቶ ሮባ፣ የመንግሥት የልማት ድርጅት በመሆኑ  የሚመራው አገሮች ወይም የሚመለከታቸው የባለሥልጣን መሥሪያ ቤቶች  በሚያደርጉት የስምምነት መርህ መሠረት መሆኑን ገልጸዋል፡፡

ከኬንያ ወደብ ባለሥልጣን በኩል የተደረገ ግንኙነትን አስመልክቶ በተለይም ላሙና ሞንባሳ ለኢትዮጵያ ካላቸው ቅርበት አንፃር አገልግሎት መስጠት የሚችሉበት ሁኔታ ይኖራል የተባለ ሲሆን፣ ነገር ግን ይህንን ዕውን ለማድረግ የሚስፈልገው የሁለትዮሽ ስምምነት፣ የጉምሩክና የትራንዚት ፕሮቶኮሎች መጠናቀቅ አስፈላጊነቱ ተመላክቷል፡፡

የወደብ አጠቃቀምን አዋጭ የሚያደርገው ቅርበት፣ ዋጋና ኮሪደሩ ውጣ ውረድ የሌለበት ቀልጣፋ አገልግሎት የሚሰጥበት መሆኑ የሚገለጽ ሲሆን፣ ከዚህ አኳያ የላሙ ኮሪደር በተለይም ለብትን ጭነትና ለኮንቴይነር ጭነት አዋጭ ስለመሆኑ ይነገርለታል፡፡

በተለይም የኤክስፖርት ካርጎ በተለይም ቡና በላሙ ወደብ በኩል ቢስተናገድ ውጤታማ ወይም አዋጭ ይሆናል የሚል ዕምነት እንዳለ የተናገሩት አቶ ሮባ፣ በኬንያ የወደብ ባለሥልጣን በኩል በአፍሪካ ብቸኛው አገርን የሚወክል ኩባንያ (ፍላግ ኬርየር) ከሆነው የባህር ትራንስፖርትና ሎጀስቲክስ አገልግሎት ድርጅት ጋር ለመሥራት ከፍተኛ ፍላጎት አላቸው ብለዋል፡፡

በተወሰነ ደረጃ የሶማሌላንድ የትራንዚት ትራንስፖርት ኮሪደርና በበርበራ ወደብ በኩል የሚስተናገዱት ጭነቶች ለምሥራቁ የአገሪቱ ክፍል ፍጆታ ተደራሽ የሚሆኑ ቁሳቁሶች የሚመጡበት መሆኑን አቶ ሮባ ገልጸው፣ የሱዳን ኮሪደርም ለኢትዮጵያ ገቢ ፈሳሽ ጭነት አገልግሎት የሚሰጥ የትራንዚት ትራንስፖርት ኮሪደር እንደሆነም አስረድተዋል፡፡

ሚያዚያ 28 ቀን 2013 ዓ.ም. በሐያት ሬጀንሲ ሆቴል የተባበሩት ዓረብ ኤምሬትስ ዲፒ ወርልድ ኩባንያ የኢትዮጵያን ድርሻ የበርበራ ወደብ ኮሪደር ለማልማት የሚያስችል ስምምነት ከትራንስፖርት ሚኒስቴር ጋር በተፈራረመበት ወቅት ንግግር ያደረጉት ሚኒስትሯ ወ/ሮ ዳግማዊት ሞገስ፣ መንግሥት ከኬንያ ጋር የሚያገናኘውን የላሙና ከሱዳን ጋር የሚያስተሳስሩትን የሱዳን ወደብ ኮሪደሮች ከውጭ ኩባንያዎች ጋር በጋራ የማልማት ዕቅድ እንዳለው አስታወቀው ነበር፡፡

‹‹የጂቡቲ ወደብ ኮሪደር ዋነኛ የምንጠቀመው ኮሪደር ሆኖ ይቀጥላል፤›› ያሉት ሚኒስትሯ፣ ነገር ግን ኢትዮጵያ ሰፊ አገር ከመሆኗ አንፃር ሁሉንም ነገር ከአንድ ቦታ በሚመጡ ገቢ ምርቶች ማዳረሷ በሎጂስቲከስ ዘርፍ ውጤታማ እንዳትሆን እያደረጋት ነው ማለታቸው ይታወሳል፡፡ ‹‹በመሆኑም አማራጩን በማስፋት በአጭር ጊዜ፣ በዝቅተኛ ወጪና ውስብስብነቱ በቀነሰ መንገድ ገቢና ወጪ ምርቶችን ከአገር ውስጥና ወደ አገር ውስጥ ማስገባት አለብን ብለን ስለምናምን፣ እንደ መጀመርያ እንቅስቃሴ ከዲፒ ወርልድ ጋር ስምምነቱን ለመፈራረም በቅተናል፤›› ሲሉ ማስረዳታቸው ይታወሳል፡፡

 

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች