በቀደመው ሥርዓተ ትምህርት ላይ ችግሮች አሉ፣ የትምህርት ጥራት አልተጠበቀም፣ በተማሪዎችም ሆነ በአገር ዕድገት ላይ የሚፈለገውን ለውጥና ዕድገት አላመጣም ተብሎ አዲስ የትምህርት ፍኖተ ካርታ መዘጋጀት የጀመረው በ2007 ዓ.ም. ነው፡፡
ከማርቀቅ አንስቶ ወደ አጠቃላይ ትግበራ ለመግባት እስከ ስምንት ዓመታት የወሰደው ፍኖታ ካርታ አሁን ላይ ሥርዓተ ትምህርትም ተቀርፆ ወደ ሙሉ ትግበራ ለመግባት ወደ መጨረሻው ምዕራፍ ተደርሷል፡፡
በ2014 ዓ.ም. አዲሱን የትምህርት ፍኖተ ካርታ ተንተርሶ የተዘጋጀው ሥርዓተ ትምህርትም በአዲስ አበባ ከተማ ትምህርት ቢሮ ሥር በሚገኙ 44 ትምህርት ቤቶች ውስጥ የሙከራ ትግበራ ተደርጓል፡፡ በ2015 ዓ.ም. ሙሉ ለሙሉ ትግበራ ውስጥ የሚገባ ሲሆን፣ በ2016 ዓ.ም. ደግሞ የማጠቃለያ ግምገማ የሚደረግ ይሆናል፡፡
በ2015 ዓ.ም. ወደ ሙሉ ትግበራ ይገባል በተባለውና በ2014 ዓ.ም. በሙከራ ደረጃ በተተገበረው ሥርዓተ ትምህርት ዙሪያ የአዲስ አበባ ትምህርት ቢሮ በአዲስ አበባ በግል ትምህርት ቤቶች ዘርፍ ከተሰማሩ ባለቤቶች፣ የትምህርት አመራሮችና መንግሥታዊ ካልሆኑ ትምህርት ቤቶች ከተወጣጡ የሚመለከታቸው አካላት ጋር ማክሰኞ ነሐሴ 10 ቀን 2014 ዓ.ም. ውይይት አድርጓል፡፡ በውይይቱም የሥርዓተ ትምህርቱ መልካም ጎኖችና በመተግበር ሒደት ሊያጋጥሙ ስለሚችሉና የሚያደናግሩ ወይም በሥርዓተ ትምህርቱ በግልጽ ባልተጻፉ የትምህርት ይዘቶች ላይ ጥያቄዎች ቀርበዋል፡፡ ሥጋቶችም ተነስተዋል፡፡ በመሠረታዊነት የተነሱ አስተያየቶች ደግሞ ተማሪዎች በሚወስዷቸው ትምህርቶች ዙሪያ የሰው ኃይልና የሀብት ችግር የሚገጥም መሆኑ ይገኝበታል፡፡
ከዚህ በተጨማሪም በተለይ ቋንቋን በተመለከተ አዲስ አበባ የብዙ ብሔሮች መኖሪያ፣ የተለያዩ ቋንቋዎች የሚነገርባት ከመሆኗ አንፃር ተማሪዎችን በአፍ መፍቻ ቋንቋ ማስተማር የሚለው ግልጽነት የጎደለው በመሆኑ የሚማሩትን ቋንቋ በግልጽ እንዲያስቀምጥ የሚለውም ሌላ የተነሳ ሐሳብ ነበር፡፡
የቀደመው ሥርዓተ ትምህርት የትምህርት እርከን ከአዲሱ ጋር ሲነፃፀር ምን ይመስላል?
በቀደመው ሥርዓተ ትምህርት ቅድመ አንደኛ ደረጃ (ኬጂ)፣ አንደኛ ደረጃ (ከአንድ እስከ ስምንት) አጠቃላይ ሁለተኛ ደረጃ ከዘጠኝ እስከ 12ኛ ክፍል ሆኖ አሥረኛ ክፍል የሚሰጠው ብሔራዊ ፈተና መሰናዶ ትምህርት ለመከታተል ወይም ቴክኒክና ሙያ ለመግባት የሚወሰንበት፣ 12ኛ ክፍል የሚሰጠው ብሔራዊ ፈተና ደግሞ ወደ ዩኒቨርሲቲ ለመግባት የሚያስችል ሆኖ ከሃያ ዓመታት ላላነሰ ጊዜ ሲተገበር ቆይቷል፡፡
በአዲሱ ሥርዓተ ትምህርት የተቀመጠው የትምህርት እርከን አጠቃላይ ትምህርት ቅድመ አንደኛ ደረጃ (ከአምስት እስከ ስድስት ዓመት ሕፃናት) (ይህ ከአዲስ አበባ ነባራዊ ሁኔታ አንፃር ከአራት እስከ ስድስት ዓመት በሚለው ለማስተካከል እየተሠራበት ነው)፣ አንደኛ ደረጃ ከአንደኛ እስከ ስድስተኛ ክፍል ሆኖ ተማሪዎች ስድስተኛ ክፍል ላይ ክልላዊ ፈተና የሚወስዱም ይሆናል፡፡ ከሰባተኛ እስከ ስምንተኛ መካከለኛ ደረጃ ትምህርት ሆኖ ስምንተኛ ክፍል ላይ ብሔራዊ ፈተና ይሰጣል፡፡
ከዘጠኝ እስከ 12ኛ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት የሚሰጥበት ሲሆን፣ ለአራት ዓመታት የሚሰጠው ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት አደረጃጀቱ በዘጠነኛ እና አሥረኛ ክፍሎች በአጠቃላይ ትምህርት የሚማሩበት፣ 11ኛ እና 12ኛ ክፍሎች በተለዩ የትምህርት መስኮች ተደራጅቶ ትምህርት የሚሰጥበት ነው፡፡
በቅድመ አንደኛ ደረጃ (መዋዕለ ሕፃናት) የአፍ መፍቻ ቋንቋን፣ አካባቢ ሳይንስ፣ የግልና ማኅበራዊ ስሜታዊ ዕድገት፣ ሥነ ጥበብ፣ ሒሳብ፣ ጤናና የሰውነት ማጎልመሻ ትምህርቶች የሚሰጡ ሲሆን፣ በዚህ የትምህርት እርከን በቀደመው ሲሰጥ የነበረው እንግሊዝኛ ቋንቋ አልተካተተም፡፡
በአንደኛ ደረጃ (ከ1 እስከ 6ኛ ክፍል) ትምህርት የአፍ መፍቻ ቋንቋ፣ የአገር ውስጥ ቋንቋ፣ እንግሊዝኛ፣ ሒሳብ፣ አካባቢ ሳይንስ፣ ግብረ ገብ፣ ክወናና ዕይታ ጥበብ እንዲሁም ጤናና ሰውነት ማጎልመሻ ትምህርት የተካተተበት ሲሆን፣ ከዚህ ቀደም ከነበረው የትምህርት ዓይነት በተጨማሪ የአገር ውስጥ ቋንቋና ክወናና እይታ ጥበብ በተጨማሪ ገብተዋል፡፡
በመካከለኛ ደረጃ (7 እና 8ኛ ክፍል) የአፍ መፍቻ ቋንቋ፣ የአገር ውስጥ ቋንቋ፣ እንግሊዝኛ፣ ሒሳብ፣ አጠቃላይ ሳይንስ (ፊዚክስ፣ ኬሚስትሪ፣ ባዩሎጂ ባንድ ላይ) ማኅበራዊ ሳይንስ፣ ዜግነት፣ ሥነ ጥበብ፣ ኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ፣ ጤናና ሰውነት ማጎልመሻ እንዲሁም የሥራና የቴክኒክ ትምህርቶች የሚሰጡበት ይሆናል፡፡ በዚህ እርከን የአገር ውስጥ ቋንቋ፣ የሥራና የቴክኒክ ትምህርት፣ ሥነ ጥበብ ተጨምረው የተካተቱ ናቸው፡፡
ከዘጠኝ እስከ አሥረኛ ክፍል እንግሊዝኛ፣ ሒሳብ፣ ኢንፎርሜሸን ቴክኖሎጂ፣ ፊዚክስ፣ ኬሚስትሪ፣ ባዩሎጂ፣ ጂኦግራፊ፣ ታሪክ፣ የዜግነት ትምህርት፣ ኢኮኖሚክስ፣ የመጀመርያ ቋንቋና የጤናና ሰውነት ማጎልመሻ በጋራ የሚሰጡ የትምህርት ዓይነቶች ሲሆኑ፣ በአማራጭ የትምህርት ዓይነቶች ደግሞ አንድ ተጨማሪ የአገር ውስጥ ቋንቋ፣ አንድ ተጨማሪ የውጭ ቋንቋና ሥነ ጥበብ ተካተዋል፡፡
11ኛ እና 12 ክፍል በተፈጥሮ ሳይንስ የጋራ የትምህርት ዓይነቶች እንግሊዝኛ፣ ሒሳብ፣ ፊዚክስ፣ ኬሚስትሪ፣ ባዩሎጂ፣ ኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂና ግብርና ሲሆኑ፣ በሥራና ቴክኒክ ትምህርት ደግሞ ማኑፋክቸሪንግ፣ ኮንስትራክሽን፣ ኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ፣ ጤና ሳይንስና ግብርና የሚሰጡ ይሆናል፡፡
በማኅበራዊ ሳይንስ ዘርፍ እንግሊዝኛ፣ ሒሳብ፣ ጂኦግራፊ፣ ታሪክ፣ ኢኮኖሚክስ፣ ኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ የሚሰጡ ሲሆን፣ በማኅበራዊ ሳይንስ ዘርፍ ሆኖ በሥራና ቴክኒክ ትምህርት ዓይነቶች ሥር ቋንቋና ማኅበራዊ ሳይንስ፣ ቢዝነስ እንዲሁም ሥነ ጥበባት የሚማሩ ይሆናል፡፡
አዲሱን ሥርዓተ ትምህርት ለመተግበር የአዲስ አበባ ትምህርት ቢሮ ዝግጅት
ቢሮው እንደሚለው በአዲሱ ሥርዓተ ትምህርት ማዕቀፍና መርሐ ትምህርት ተዘጋጅቷል፡፡ የመምህሩን መምሪያ ጨምሮ 200 መጻሕፍት በአማርኛ፣ በአፋን ኦሮሞና በእንግሊዝኛ ተተርጉመዋል፡፡
መጽሐፍቱ የተዘጋጁበት የመማሪያ ቋንቋ ከቅድመ መደበኛ እስከ ስድስተኛ ክፍል በአማርኛ፣ ከሰባተኛ ክፍል በኋላ ያሉት በእንግሊዝኛ ሲሆን፣ በአፋን ኦሮሞ ደግሞ የተተረጎሙት ከቅድመ መደበኛ እስከ ስምንተኛ ክፍል ነው፡፡
የአዲስ አበባ ትምህርት ቢሮ ምክትል ቢሮ ኃላፊ አቶ አድማሱ ደቻሳ፣ የአዲስ አበባ የትምህርትና ሥልጠና ጥራት ቁጥጥር ባለሥልጣን ምክትል ዋና ሥራ አስኪያጅ ወ/ሮ ፍቅርተ አበራና የትምህርት ቢሮው ኃላፊዎች በተገኙበት፣ በ2015 ዓ.ም. ወደ ሙሉ ትግበራ በሚገባው አዲሱ ሥርዓተ ትምህርት አተገባበር ላይ ከግልና መንግሥታዊ ካልሆኑ ትምህርት ተቋማት ባለቤቶችና አመራሮች ጋር በነበረው ውይይት ባደረጉበት ወቅት ከተሳታፊዎች የተለያዩ ጥያቄዎችና ለትግበራው ተግዳሮት ይሆናሉ የተባሉ ሐሳቦች ተነስተዋል፡፡
በአዲስ አበባ በ2015 ሙሉ ለሙሉ ይተገበራል በተባለው ሥርዓተ ትምህርት ላይ የተነሱ ጥያቄዎች
ከግልና መንግሥታዊ ካልሆኑ ተቋማት ከመጡ ተሳታፊዎች ከተነሱ ጥያቄዎች ውስጥ በአማርኛና በአፋን ኦሮሞ መጽሐፍ ዝግጅት ሲደረግ፣ ሲለበስ ሲዘጋጅና አጠቃላይ ሥርዓተ ትምህርቱን በትምህርት ቤቶች ለማስተማር የሚያስችሉ ቅድመ ሥራዎች ሲከናወኑ ለምን የግል ትምህርት ቤቶች እንዲሳተፉና እንዲገመገሙ አልተደረገም? የግል ትምህርት ቤቶች በበቂና በስፋት ሐሳብ እንዲሰጡበት አልተደረገም? ትምህርት የሚሰጠው ለዜጎቻችን እስከሆነ ድረስ አንድ ዓይነት የጋራ ሥራ ለመሥራት በግሉ ዘርፍ ለተሰማሩት ‹‹ይህንን ተግብሩ›› ብሎ ከማውረድ ይልቅ፣ በስፋት እንዲሳተፉበት ለምን አልተደረገም? የሚሉት ይገኙበታል፡፡
አዲሱ ሥርዓተ ትምህርት በ2015 ዓ.ም. ሙሉ ለሙሉ ይተገበራል ቢባልም፣ ትምህርት ሊጀመር ከወር ያነሰ ጊዜ ቀርቶ መጽሐፍና ሌሎች መረጃዎች ያልደረሳቸው መሆኑም ተጠቁሟል፡፡
የትምህርት ሥራ ጊዜ የሚፈልግ፣ አዲስ ሥርዓተ ትምህርት ሲመጣ ደግሞ እያንዳንዱ ትምህርት ቤትና መምህር ከሥርዓተ ትምህርቱ ጋር የተመሳሰለ ዝግጅት ማድረግ የሚጠበቅበት ቢሆንም፣ ለዚህ በቂ ጊዜ ሳይሰጥ ወደ ሙሉ ትግበራ ግቡ ማለቱ የታለመውን የትምህርት ጥራት አያመጣውም የሚል አስተያየትም ተሰጥቷል፡፡
ስብሰባው በተካሄደበት ዕለት ከሁሉም አቅጣጫ የተነሳው ጥያቄ ሥርዓተ ትምህርቱን ሆነ መጻሕፍትን አስመልክቶ ያሉ መረጃዎች በአግባቡ ለግል ትምህርት ቤቶች እንዳልደረሱ፣ ማኅበራዊ ገጽ ላይ የሚለጠፈውን ብቻ እያነበቡ እንደሆነና ይህ ክፍተት የተፈጠረው በአዲስ አበባ ትምህርት ቢሮና በግል ትምህርት ቤቶች መካከል መረጃ ልውውጥ የሚደረግበት ሥርዓት በአግባቡ ባለመኖሩ መሆኑም ተነስቷል፡፡
ከግል ትምህርት ቤት የተሳተፉ አካላት፣ የትምህርት ቢሮ አመራሮች ስለ አዲሱ ሥርዓተ ትምህርት በፓወር ፖይንት ገለጻ ሲያደርጉ በርካቶች በሞባይላቸው ከስክሪን ላይ ፎቶ ሲያነሱ የነበረ ሲሆን፣ ይህንን ያመጣው ትምህርት ቢሮው ለትምህርት ቤቶች ሥርዓተ ትምህርቱን ቀድሞ ባለመስጠቱ፣ ቴክኖሎጂን ተጠቅሞ ማሠራጨት እየቻለ ባለመሠራጨቱ ነው ተብሏል፡፡
አዲሱ ሥርዓተ ትምህርት ጥሩ አይደለም የሚል አስተያየት ከየትኛውም ወገን አልተነሳም፡፡ አብዛኛው ጥያቄ ያተኮረው አተገባበሩ ላይ ሊገጥሙ የሚችሉ ችግሮች ናቸው፡፡
ከአዲሱ ሥርዓተ ትምህርት ይዘት አኳያ የግልም ሆነ የመንግሥት ትምህርት ቤቶች ራሳቸውን በሰው ኃይልና በሀብት ማደራጀት የሚጠበቅባቸው ቢሆንም፣ በተለይ አዳዲስ በተጨመሩና በተጨፈለቁ ትምህርቶች ላይ ትምህርት የሚሰጥ ባለሙያ አለመኖሩ፣ አዲሱ ሥርዓተ ትምህርት በጥራት እንዳይተገበር ያደርጋል የሚል ሥጋት ተሰንዝሯል፡፡
በርካታ ቋንቋ በሚነገርባት አዲስ አበባ ከቅድመ መደበኛ እስከ መካከለኛ ደረጃ ከሚሰጡ የትምህርት ዓይነቶች ‹‹የአፍ መፍቻ ቋንቋ››፣ ‹‹የአገር ውስጥ ቋንቋ›› የሚለውም ግልጽነት ይጎድለዋል የሚል ጥያቄ ተነስቶበታል፡፡ ለአዲስ አበባ የአፍ መፍቻ ቋንቋ የቱ ነው? የሚመርጠው ወላጅ ነው? ትምህርት ቤቱ ነው ወይስ መንግሥት? የሚለውም ተነስቷል፡፡
ከዘጠኝ እስከ አሥረኛ ክፍል ከአማራጭ የትምህርት ዓይነቶች አንድ የአገር ውስጥ ቋንቋ ተብሎ የተቀመጠውም ጥያቄ ተነስቶበታል፡፡ የግል ትምህርት ቤቶች የትኛውን ቋንቋ መርጠው ሊያስተምሩ ነው? የሚል ጥያቄም ተነስቷል፡፡
አፋን ኦሮሞ ከአፀደ ሕፃናት ጀምሮ በሁሉም ትምህርት ቤቶች እንደ ቋንቋ ይሰጣል ወይስ በአፋን ኦሮሞ ብቻ በሚያስተምሩ ትምህርት ቤቶች ነው? በዘርፉ ቋንቋውን በማስተማር የሠለጠነ የሰው ኃይልስ አለ ወይ? የሚለውም ተጠይቋል፡፡
መንግሥት በ2015 ዓ.ም. በፔዳጎጂ ያልሠለጠኑ መምህራን አያስተምሩም ብሎ በማስታወቁ ብቻ የግል ትምህርት ቤቶች ሥጋት ላይ መውደቃቸውን፣ ከዚህ ቀደም በተደጋጋሚ የሠለጠኑ ብቁ መምህራን እጥረት አለ ብለው ያነሱ እንደነበር፣ በአዲሱ ሥርዓተ ትምህርት አዳዲስ የትምህርት ዘርፎች መካተታቸው በዘርፉ የሠለጠነ የሰው ኃይል ሳይኖር ውጤታማነቱን ይጎዳዋል የሚሉ አስተያየቶችም ሰንዝረዋል፡፡
መስማትና ማየት የተሳናቸው ተማሪዎች በተለይ ቋንቋ ላይ እንደሚቸገሩ፣ መግባባት የሚችሉትም በተለይ መስማት የተሳናቸው በእንግሊዝኛ (የምልክት) መሆኑንና አሁን በአዲስ የተዘጋጁ መጻሕፍት እነሱን የማያሳትፍ መሆኑም በመድረኩ ከተነሱ ጥያቄዎች ይገኙበታል፡፡
ቋንቋ ከታች ከሕፃንነት ዕድሜ ጀምሮ የሚለመድ፣ መነሻውም የመጀመርያዎቹ የዕድሜ ጊዜዎች ቢሆኑም፣ በዓለም አቀፍ ደረጃ የቴክኖሎጂው፣ የዲፕሎማሲው የምርምሩና የብዙ ዘርፎች መግባቢያ የሆነው እንግሊዝኛ ቋንቋ በቅድመ መደበኛ ትምህርት እንደ አንድ የትምህርት ዓይነት ሆኖ እንዲሰጥ አለመካተቱ ጥያቄ ተነስቶበታል፡፡ ከዚሁ ጎን ለጎንም በቅድመ አንደኛ ደረጃ ግብረ ገብ ትምህርት እንዲካተት ተጠይቋል፡፡
በአዲሱ ሥርዓተ ትምህርት ከዚህ ቀደም ከነበረው የትምህርት ዓይነት በተጨማሪ ሌሎች መካተታቸው መልካም ቢሆንም፣ የመምህራን እጥረት ስለሚኖር መምህራን በብቃት እስኪገኙ ድረስ ‹‹ይህንን ትምህርት በዚህ ዘርፍ የሠለጠነ ሊያስተምር ይችላል፤›› የሚል መመርያ አውርዱ የሚል አስተያየትም ተሰጥቷል፡፡
የመምህራንና የግብዓት ችግር እንደሚኖር በተለይ አዲስ በተጨመሩ የማኑፋክቸሪንግ፣ ኮንስትራክሽን፣ ግብርና፣ ሥነ ጥበብ እንዲሁም ፊዚክስ፣ ኬሚስትሪና ባዩሎጂ በተጣመሩበት ከሰባት እስከ ስምንትኛ ክፍል በሚማሩት አጠቃላይ ሳይንስ ትምህርት ዘርፎች መንግሥት እንደሚለው በፔዳጎጂ ጭምር የሠለጠኑ መምህራንን ማግኘት እንደማይቻል ተነስቷል፡፡
የግል ትምህርት ቤቶች በአብዛኛው ቤት ተከራይተው የሚሠሩ፣ መሬት ጠይቀው የማይሰጣቸው ሆነው ለዓመታት መክረማቸው በመድረኩ የተነሳ ሲሆን፣ ይህ ችግር ባለበት፣ በመካከለኛ ደረጃ ከሰባት እስከ ስምንተኛ ክፍል እንዲሰጡ የተባሉት የሥራና ቴክኒክ ትምህርት፣ የኢንፎርሜሸን ቴክኖሎጂ እንዲሁም ሥነ ጥበብ ትምህርቶች ከንድፈ ሐሳብ ባለፈ በተግባር ጭምር ለመስጠት የሚያስችል ሀብት በአጭር ጊዜ ማጎልበት ስለማይቻል አተገባበሩ በሒደት ቢሆን የሚል ሐሳብም ተሰንዝሯል፡፡
11ኛ እና 12ኛ ክፍል በተፈጥሮ ሳይንስ በሥራና ቴክኒክ ትምህርት የተካተቱት ማኑፋክቸሪንግ፣ ኮንስትራክሽን እንዲሁም ግብርና የተግባር ትምህርት የሚፈልጉ በመሆናቸው ይህንን የግል ትምህርት ቤቶች እንዴት ያሟሉታል? ከመንግሥት ምን ድጋፍ ይደረጋል? የሚል ሐሳብም ተነስቷል፡፡
እንደ አጠቃላይ ሥርዓተ ትምህርቱ ላይ አሉታዊ ሐሳብ ያልተሰነዘረ ሲሆን፣ ሲተገበር የሚገጥሙ የመምህራንና የሀብት እጥረት እንዲሁም የቋንቋ ትምህርት ላይ ያሉ ብዥታዎች እንዲጠሩ ተጠይቋል፡፡
መንግሥት ትምህርትን ከፖለቲካ እንዲለይ፣ በትብብር ብቁና ለአገሩ የሚጠቅም ዜጋ ለማፍራት በጋራ እንዲሠሩ፣ ሥርዓተ ትምህርቱ በመምህራንና በሌሎች ግብዓቶች ካልታገዘ ባዶ እንዳይቀር እንዲታሰብበት፣ መንግሥት የግል ትምህርት ቤቶችን እንደ መንግሥት ትምህርት ቤቶች ዓይቶ የተበላሸ እንዲስተካከል፣ የተሳሳተ ካለ እንዲታረም የጎደለ ካለ በሒደት እንዲሟላ እንዲያደርግ ለመንግሥት ትምህርት ቤቶች እንዳያዳላም ተጠይቋል፡፡
የ6ኛ ክልላዊ ፈተናና የ8ኛ ብሔራዊ ፈተናን በ2015 ዓ.ም. የሚወስዱ ተማሪዎች በ2015 በተማሩት የአንድ ዓመት ትምህርት ብቻ ይመዘናሉ ወይስ እንዴት ይሆናል? የሚለውም ተጠይቋል፡፡
በተደጋጋሚ ጥያቄ በተነሳበት ‹‹የአገር ውስጥ ቋንቋ›› ‹‹አፍ መፍቻ ቋንቋ›› ዙሪያ ያነጋገርናቸው ተሳታፊዎች ተማሪዎች የትኛውንም ቋንቋ ቢማሩ ተጠቃሚ እንደሚሆኑ፣ በቋንቋዎች በመግባባት ብቻ ብዙ ችግሮችን እንደሚፈቱ፣ ነገር ግን በሥርዓተ ትምህርቱ በድፍን መቀመጡ ለአተገባበር እንደሚያስቸግር፣ በመሆኑም አማራጭ ቋንቋዎች ተብለው ቋንቋዎች ተቀምጠው ከእነዚህ ውስጥ ተማሪዎች የመረጡትን እንዲማሩ፣ ትምህርት ቤቶችም ከወዲሁ መምህራን ፈልገው እንዲያዘጋጁ ቢሠራ መልካም ነው ብለዋል፡፡
የአዲስ አበባ ትምህርት ቢሮ አመራሮች መልስ
በአዲሱ ሥርዓተ ትምህርት ዙሪያ ለተነሱ ጥያቄዎች መልስ የሰጡ አመራሮች ከመድረኩ ግብዓት ማግኘታቸውን፣ ወደፊት አብሮ ለመሥራት እንደሚያስችል ተናግረዋል፡፡
ሁሉም የተነሱ ጥያቄዎች በመድረኩ ላይ መልስ እንደማያገኙ፣ በአሠራር መልስ የሚያገኙ፣ በመመሪያ የሚወርዱ እንደሚኖሩ፣ በርካቶቹ ጥያቄዎችና የተነሱ ሐሳቦች ቀጣይ ሥራ የሚፈልጉ መሆናቸውን፣ የሠለጠኑ መምህራን ገበያው ላይ በብዛትና በብቃት የማይገኙ በመሆኑም፣ ማን ምን ያስተምር? የሚለው በአጭር ጊዜ ተጣርቶ ወደ ታች እንደሚወርድም አስታውቀዋል፡፡
ሥርዓት ትምህርቱ ሲቀረፅ አገር ችግሯን እንድትፈታ፣ ዜጎቿ በዕድሜያቸው ደረጃ እንዲማሩ ለማስቻል መሆኑን፣ አንድ ልጅ በሕፃንነቱ በእናት ቋንቋው የማሰብ መብት እንዳለውም ተነግሯል፡፡
ትምህርት የመንግሥት ሥራ ብቻ ሳይሆን የግል ዘርፉም መሆኑን፣ በመሆኑም አድልኦ እንደሌለና የግል ዘርፉ እንዲሳተፍ እንደሚበረታታ፣ በዝግጅት ወቅትም ከተወሰኑ የግል ትምህርት ቤቶች ተወካዮች ጋር ውይይት እንደተደረገ ገልጸዋል፡፡
ሥርዓተ ትምህርቱ የግልና የመንግሥት ትምህርት ቤት ተብሎ እንዳልተዘጋጀ፣ ሁሉም ዜጋ በጋራ የሚማርበት መሆኑን፣ እንደከዚህ ቀደሙ በተዥጎረጎረ ማለትም ሒሳብ በአማርኛ፣ ሒሳብ በእንግሊዝኛ፣ ሳይንስ በአማርኛ ሳይንስ በእንግሊዝኛ እየተባለ እያንዳንዱ ትምህርት በእንግሊዝኛ ተተርጉሞ የሚማሩበት ሥርዓት እንዳበቃና ይህንን ማድረግ እንደማይቻል፣ ሁሉም ተማሪ መንግሥት ባዘጋጀው መጽሐፍ እንደሚማሩ ተነግሯል፡፡
መጻሕፍት ይዘት ላይ የሚነሱ ቅሬታዎች ከመምህሩ ጀምሮ አስተያየት እየተሰጠበት በሒደት ሊስተካከል የሚችልበት አሠራር መዘርጋቱም ተገልጿል፡፡
አጋዥ መጻሕፍት ለመጠቀም የሚከለክል ነገር ባይኖርም የግል ትምህርት ቤቶች በራሳቸው አጋዥ መጻሕፍት ማዘጋጀት እንደማይችሉ፣ የተዘጋጁ መጻሕፍትን በትምህርት ቢሮ አስገምግመው መጠቀም እንደሚችሉም ተጠቁሟል፡፡