በትግራይ ክልል የተካሄደውን ጦርነት በሰላም ለመፍታት መሠረት ይጥላል ተብሎ የታመነበት የድርድር አጀንዳ ይሰምራል የሚለው ጉዳይ ቀቢፀ ተስፋ እየሆነ ይመስላል፡፡ የጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት ፕሬስ ሴክሬታሪያት ኃላፊ ቢልለኔ ሥዩም፣ ‹‹አሸባሪው ሕወሓት አሁንም ወደ ጦርነት ለመግባት ተደጋጋሚ ትንኮሳዎችን እያደረገ ነው፤›› በሚል የሰላም ጥረቱ ሊሰናከል የሚችልበትን ምክንያት ሐሙስ ነሐሴ 12 ቀን 2014 ዓ.ም. በሰጡት መግለጫ መናገራቸው ይታወሳል፡፡
በዚያው ዕለት ከመቀሌ ‹‹የቆመ ጦርነት የለም›› የሚል መግለጫ ለጋዜጠኞች የሰጡት የሕወሓት ቃል አቀባይ አቶ ጌታቸው ረዳ በበኩላቸው፣ ‹‹የተኩስ አቁም ስምምነቱ ቴክኒካሊ ፈርሷል፤›› ብለው መናገራቸው ሲዘገብ ነበር፡፡
መንግሥትና የሕወሓት ኃይሎች ሊደራደሩ ነው የሚለው ተስፋ ካለፈው አንድ ወር ወዲህ በጉልህ ቢሰማም፣ በአጭር ጊዜ ውስጥ ግን ይህ ተስፋ ሊከስም የተቃረበ መስሏል፡፡ የድርድሩን መጀመር የሚያበስረው ፊሽካ እየተጠበቀ ባለበት ጊዜ፣ ሁለቱ ወገኖች መካሰስና መወነጃጀላቸውን ጀምረዋል፡፡ የት፣ በምን ጉዳይና በምን ሁኔታ ድርድሩ እንደሚካሄድ ሲጠበቅ የቃላት ጦርነት በሁለቱ መካከል መልሶ መከፈቱ፣ ድርድሩን ሊያደናቅፈው ይችላል የሚል ሥጋት አሳድሯል፡፡ ወትሮም የድርድሩ ጥረት ያልጣማቸውና ቢጀመርም አይሰምርም የሚሉ ኃይሎች ግምታቸው የሰመረ ይመስላል፡፡
‹‹በአደራዳሪዎች የሰላም ፍላጎት አለው እየተባለ የሚዘመርለት መንግሥት ጊዜያዊ የተኩስ አቁሙን አፍርሶ ትንኮሳ ፈጽሞብናል፡፡ ለሰላም ያሉ ዕድሎችን አሟጦ ለመጠቀም ካለን ፍላጎት አንፃር እንጂ ወደ ጦርነት ለመግባት እስኪበቃን ተተንኩሰናል፤›› በማለት የተናገሩት የሕወሓቱ ቃል አቀባይ፣ የድርድሩ አጀንዳ ገና ከወዲሁ ተስፋ አስቆራጭ መሆኑን ነው የተናገሩት፡፡ አቶ ጌታቸው አክለውም የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ የአፍሪካ ጉዳዮች ምክትል ጸሐፊ ድርድሩ የሚጀመርበትን ቀን እየጠበቅን ነው ማለታቸውን አጣጥለውታል፡፡ ‹‹ምክትል ጸሐፊው ጊዜና ቦታ ጠቅሰው የሚቀረን ማደራደር ነው ብለው መናገራቸው ከየት እንዳመጡት አናውቅም፤›› ሲሉ የገለጹት አቶ ጌታቸው፣ በመንግሥት በኩል የሰላም ሐሳብ አለመኖሩን ነበር የተናገሩት፡፡
መንግሥት በሰጠው መግለጫም ቢሆን የሰላም ጥረቱ እንቅፋት እየገጠመው መሆኑን ያመለክታል፡፡ ዋና እንቅፋት የሆነው ደግሞ የሕወሓት ኃይል ነው ያሉት ቢልለኔ፣ ሕወሓት ለአደራዳሪዎች ቅድመ ሁኔታ በመደርደር ወደ ድርድር ላለመግባት እያሴረ ነው የሚል ውንጀላ አቅርበዋል፡፡
ከሰሞኑ በሁለቱ ወገኖች መካከል ከሚታየው ሁኔታ በመነሳት፣ አንዳቸው በሌላኛቸው ላይ ነጥብ ለማስቆጠር ፈልገዋል የሚለው ግምት ብዙዎች እያጋሩ ናቸው፡፡
‹‹እኔ ለሰላም ጥረቱ ዝግጁ ብሆንም ተቀናቃኜ ግን ወደ ድርድሩ ለመግባት ፈቃደኝነት አይታይበትም፤›› የሚል ክስ አንዳቸው በሌላቸው ላይ ማቅረብ የፈለጉ ይመስላልም ይላሉ፡፡ ሁለቱ ወገኖች ወደ ድርድሩ ሳይገባና ገና ምኑም ሳይያዝ ወደ መወቃቀሱ ለምን ገቡ? የሚለው ብዙ ማብራሪያ የሚፈልግ ነው፡፡
ወትሮም ቢሆን በዚህ የድርድር ሐሳብ አንዳችም አመኔታ እንደሌላቸውና ጥረቱም እንደማይሰምር ሲናገሩ የቆዩት አንጋፋው የፖለቲካ ሰው አቶ አንዳርጋቸው ጽጌ፣ ይህንን ቀድመው መናገራቸውን ያስታውሳሉ፡፡ ‹‹ሕወሓት በታሪኩ በውይይት ችግር ፈትቶ አያውቅም፤›› ሲሉ የገለጹት አቶ አንዳርጋቸው፣ ከወያኔ ባህሪ በመነሳት ድርድሩ ጨርሶ አይሳካም ብለው ለመደምደም መብቃታቸውን ያስረዳሉ፡፡
የፖለቲካ ተንታኙ አቶ ኡመር ረዲ በበኩሉ ‹‹ድርድሩን ይሳካል/አይሳካም የሚያስብለው የሁለቱ ወገኖች ድርድሩን በቅንነት መፈለግ ወይም አለመፈለጋቸው ብቻ አይደለም፡፡ ለዚህ ድርድር መሰካት ሚና ያላቸው እጅግ ብዙ ምክንያቶች አሉ፤›› ሲል ነው የሚናገረው፡፡
‹‹የፌዴራል መንግሥት ሰዎች ቅዱስ ናቸው ባይባልም እንኳን፣ የፌዴራል መንግሥቱ ድርድሩ መካሄድ በመጀመሩ የሚያጣው ነገር አይኖርም ብሎ መቀበል አይከብድም፤›› ሲል የሚያክለው አቶ ኡመር፣ መንግሥት ለድርድር ከሕወሓት በተሻለ ፍላጎት አለው ወደሚለው ድምዳሜ እንደሚያዘነብል በተቃራኒው ከሕወሓት ታሪክ በመነሳት፣ ‹‹ቡድኑ በቀውስ ውስጥ ካልሆነ በሰላም መኖርን አይችልበትም፤›› ሲል የሚናገረው አቶ ኡመር የድርድሩ እንቅፋትም ይኸው የሕወሓት መሠረታዊ ባህሪ መሆኑን ያስረዳል፡፡
ሕወሓት በአሁኑ ጊዜ ድርድር የሚለው ተገዶ መሆኑን የሚጠቅሰው አቶ ኡመር፣ አቅም ቢኖረው ኖሮ መዋጋት ምርጫው ይሆን እንደነበር ይገልጻል፡፡
ከአንድ ወር በፊት የሕወሓት ቃል አቀባይ አቶ ጌታቸው በሰጡት መግለጫ ግን፣ ‹‹ዕድል ከገጠመው ትግራይን በጦር ለማንበርከክ የሚፈልገው ወይም ለመዋጋት የሚያስበው ማን እንደሆነ አሳምረን እናውቃለን፤›› በማለት ነበር ለውጊያ የተዘጋጀው መንግሥት መሆኑን የወነጀሉት፡፡
አቶ ጌታቸው በዚያ መግለጫቸው ሕወሓት ወደ ድርድሩ ለመግባት እንደ ቅድመ ሁኔታ ያስቀመጣቸውን ነጥቦች ዘርዝረው ነበር፡፡ ‹‹በምንም ሁኔታ ለድርድር የማይቀርቡ አምስት ቅድመ ሁኔታዎች›› ሲሉ የጠቀሱት አቶ ጌታቸው፣ ሰብዓዊ ዕርዳታ ያለ ገደብ መቅረብ፣ የመሠረተ ልማት አገልግሎቶች መመለስ፣ ‹‹የምዕራብ ትግራይ›› (ወልቃይት) መመለስ፣ የኤርትራ ጣልቃ ገብነት መቆምና በትግራይ ለተፈጸሙ ሰብዓዊ ወንጀሎች ተጠያቂዎችን ለሕግ ማቅረብ የሚሉ አጀንዳዎችን በቅድመ ሁኔታነት ዘርዝረዋል፡፡
ከሰሞኑ መግለጫ ያወጣው የሰላም አማራጭ ዓብይ ኮሚቴ በበኩሉ፣ መንግሥት ያለ ቅድመ ሁኔታ እንደሚደራደር ነበር ይፋ ያደረገው፡፡ ይሁን እንጂ ወደ ድርድሩ ለመግባት የተኩስ አቁም ስምምነት ማድረግ እንደሚያስፈልግ የኮሚቴው መግለጫ ይጠቅሳል፡፡ የተኩስ አቁም ስምምነት ከተደረገም መሠረታዊ አገልግሎቶችን ዳግም ሥራ ለማስጀመር መንግሥት እንደሚያመቸው የሚያስታውቀው የኮሚቴው መግለጫ፣ የተኩስ አቁም ላይ ለመድረስ ንግግር የሚደረግበትን ቦታና ጊዜ አደራዳሪው የአፍሪካ ኅብረት እንዲያስታውቅ ይጠይቃል፡፡
ይሁን እንጂ የሰላም አማራጭ ዓብይ ኮሚቴው የሰጠውን መግለጫ በተመለከተ የተጠየቁት የሕወሓት ቃል አቀባይ አቶ ጌታቸው፣ ለዚህ መልስ መስጠቱ አላስፈላጊ መሆኑን በመጥቀስ ነበር ጉዳዩን ያለፉት፡፡
ከዚህ በመነሳት ቅድመ ሁኔታዎችን በማብዛት ወደ ድርድሩ ለመግባት ከመንግሥት ይልቅ፣ ሕወሓት ዳተኛ እየሆነ ነው የሚል እምነት በብዙዎች ላይ አድሯል፡፡ ሕወሓት ይህን የሚያደርገው ቢቻል በድርድር ስም ጊዜ በመግዛት አቅም አደርጅቶ መንግሥትን ለመውጋት ነው የሚል መላ ምት እየተሰጠ ይገኛል፡፡ ከዚህ በተጨማሪም ሕወሓት ወደ ቀደመ ማንነቱ ለመመለስና የነበረውን ሁኔታ በነበረበት ለማስቀጠል የሚያደርገውን መፍጨርጨር ታክቲክ ነው በማለት ሁኔታውን ይገልጹታል፡፡
ይሁን እንጂ የፈለገው ቢሆን ሕወሓት ወደ ነበረው ማንነቱ መመለስ እንደማይችል ነው ብዙዎች የሚገምቱት፡፡ የፖለቲካ ተንታኙ አቶ ኡመር ሕወሓት የነበረውን መልሶ እንደማያገኝ ይናገራል፡፡
‹‹ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ (ዶ/ር) የኢትዮጵያ ጦር ከትግራይ ሲወጣ፣ መቀሌ ከዚህ በኋላ የፖለቲካም ሆነ የኢኮኖሚ ስበት ማዕከል አይሆንም ብለው ተናግረው ነበር፡፡ ይህ በተወሰነ መንገድ እውነት ሆኗል፡፡ ሕወሓትና የሕወሓት ተቀፅላ የሆኑ የፖለቲካና የኢኮኖሚ ተቋማት አቅማቸው በሚታይ ሁኔታ ደክሟል፡፡ ሕወሓት የሚገዛው የጂኦግራፊ ወሰን ቀንሷል፡፡ የነበረው ወታደራዊ ጡንቻም በሚታይ መልኩ አንሷል፡፡ ይህን ሁሉ ያጡት ደግሞ ራሳቸው በጀመሩት ውጊያ ነው፡፡ ወደ ድርድሩ ለመግባት ወደ ነበርንበት ካልተመለስን የሚል ጥያቄ ቢያቀርቡም ፈጽሞ አይሳካም፤›› በማለት አቶ ኡመር የሕወሓት ፍላጎት እንደማይሳካ ያስቀምጠዋል፡፡
ሕወሓት ወደ ድርድሩ ለመግባት ባስቀመጣቸው ቅድመ ሁኔታዎች ብቻም ሳይሆን በአደራዳሪዎች ሚናና በድርድሩ ሁኔታ ላይ የሚያንፀባርቃቸው ነጥቦችም ከመንግሥት ጋር ለመግባባት የሚፈትነው ይመስላል፡፡ ሕወሓት በእነዚህ ሁለት ነጥቦች ላይ እንኳን ከሌሎች ጋር ከራሱም ጋርም ለመግባባት ይቸገራል የሚሉ በርካቶች ናቸው፡፡ ይህን ደግሞ ቡድኑ ከሚሰጣቸው መግለጫዎች መታዘብ እንደሚቻል ተንታኞች ይናገራሉ፡፡
ሕወሓትን በውጭ አገር የወከሉት ተደራዳሪ ፍሰሐ አስግዶም (አምባሳደር)፣ እ.ኤ.አ. ሰኔ 10 እና 17 ቀን 2022 ርዕዮት ለተባለው የዩቲዩብ ሚዲያ የሰጧቸው ሁለት ቃለ መጠይቆች፣ የቡድኑ ቃል አቀባይ አቶ ጌታቸውና ሌሎች የቡድኑ አመራሮች ከሚናገሩት ሐሳብ ጋር ፍፁም መቃረን እንደሚታይባቸው በርካቶች ይናገራሉ፡፡
ፍሰሐ (አምባሳደር) ከመንግሥት ጋር በቀጥታ ሳይሆን በሦስተኛ ወገን ድርድር ሲካሄድ መቆየቱን በመጥቀስ፣ በመጋቢት ወር አካባቢ መንግሥት በተናጠል አደረግኩት ያለውን የሰብዓዊ ረድኤት ተኩስ አቁም ዕርምጃ በዋናነት በአሜሪካኖች ጥረት የተደረሰ የሰላም ስምምነት መሆኑን ተናግረው ነበር፡፡
ሆኖም የአፍሪካ ኅብረት ዋና አደራዳሪ የኦሊሴጉን ኦባሳንጆ ሚናን ያጣጣሉት ፍሰሐ (አምባሳደር)፣ ‹‹ኦባሳንጆ እንኳን ብቻቸውን ይቅርና እሳቸውን የሾማቸው የአፍሪካ ኅብረትም ምንም ጥርስ የሌለው አንበሳ መሆኑ ይታወቃል፡፡ ኦፊሴላዊ አደራዳሪ ናቸው ቢባልም ነገር ግን በድርድሩ ዋናውን ሥራ የሚሠሩት አሜሪካኖቹ ናቸው፤›› በማለት ሲናገሩ መደመጣቸው ደግሞ በእጅጉ አስገራሚ ሆኖ ነበር የከረመው፡፡
የሕወሓት ቃል አቀባይ የሆኑት አቶ ጌታቸው ግን የዛሬ ወር በሰጡት መግለጫ የኦሊሴንጎን ኦባሳንጆን ሰብዕና በማጣጣል ከፍሰሐ (አምባሳደር) ጋር የሚመሳሰል አቋም ቢያሳዩም እንኳ የአፍሪካ ኅብረትን ሚና ግን በተቃራኒው ከፍ አድርገው ለማመላከት መጣራቸው የሕወሓት አቋምን የማይጨበጥ አድርጎት ቆይቷል፡፡
አቶ ጌታቸው፣ ‹‹ኦባሳንጆን በተደጋጋሚ ጊዜ ብናገኛቸውም በወጉ ሮድማፕ የሌላቸውና ሪፖርት ጸሐፊም የሌላቸው ናቸው፤›› ብለው፣ ከመንግሥት ጋር የተለየ ግንኙነት በመፍጠራቸው በእሳቸው በኩል የሚካሄድ ድርድር ፍትሐዊ አይሆንም የሚል እምነት እንዳላቸው ተናግረው ነበር፡፡ ‹‹የአፍሪካ ችግሮች በአፍሪካዊ መፍትሔ መፍታት በሚለው መሠረታዊ ጽንሰ ሐሳብ እናምናለን፤›› ያሉት አቶ ጌታቸው፣ የትግል ጓዳቸው ፍሰሐ (አምባሳደር) ከተናገሩት በተቃራኒ የአፍሪካ ኅብረት የዋና አደራዳሪነቱን ሚና መወጣት እንደሚችል ለማስረዳት ሞክረው ነበር፡፡ አቶ ጌታቸው ከዚህ በተጨማሪም በአፍሪካ ኅብረት ሥር ሆኖ የኬንያው ተሰናባች ፕሬዚዳንት ኡሁሩ ኬንያታ ወይም የሞዛምቢኩ የቀድሞ መሪ ዮሀኪም ኪሳኖ፣ ካልሆነም የደቡብ አፍሪካው የቀድሞ ፕሬዚዳንት ታቦ ምቤኪ ድርድሩን እንዲመሩ እንደሚፈልጉ ነው የተናገሩት፡፡
ሕወሓቶች የአፍሪካ ኅብረት ሚና እዚህ ግባ የማይባል ነው ቢሉም፣ መልሰው ደግሞ ‹‹የአፍሪካ ችግር በአፍሪካ መፍትሔ ይፈታል›› ሲሉ ነው የሚታዩት፡፡ ኦሊሴጉን ኦባሳንጆ ለአደራዳሪነት አይመጥኑም ብለው ሌሎች አደራዳሪዎች እንዲመደቡ ሲፈልጉ ይሰማል፡፡ በሌላ በኩል ድርድሩን የሚመሩት አሜሪካና የአውሮፓ ኅብረት እንጂ የአፍሪካ ኅብረት ሚና ከምልክትነት ያላለፈ መሆኑን ይናገራሉ፡፡ ይህ በሕወሓት ውስጥ ያለውን የአቋም መምታታት አመላካች ብቻ ሳይሆን፣ ከመንግሥት ጋር ለድርድር ለመቀመጥ ፈተና እንደሚሆን የሚገምቱ በርካቶች ናቸው፡፡
መንግሥት ከአፍሪካ ኅብረት የአደራዳሪነት ሚና ውጪ የማንንም ጣልቃ ገብነት እንደማይቀበል መግለጹ ደግሞ፣ ከሕወሓት ጋር በአደራዳሪዎች ሚና ለመግባባት ጉዳዩ ፈታኝ እንደሚሆን ይጠበቃል፡፡ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ አቶ መለስ ዓለም (አምባሳደር)፣ ከአፍሪካ ኅብረት ውጪ የሚደረግ ሌላ የአደራዳሪነት ሚና በመንግሥት ተቀባይነት እንደማይኖረው በይፋ መናገራቸው ሕወሓት በዚህ ጉዳይ ከመንግሥት ጋር እንዴት አድርጎ ወደ አንድ ገጽ መምጣት ይችላል የሚለውን ጉዳይ የተንጠለጠለ አድርጎታል፡፡
‹‹የሕወሓት አመራሮች ደብረ ጽዮን (ዶ/ር) እና ጌታቸው ረዳ መንግሥት በአፍሪካ ኅብረት ጥላ ሥር በሕገ መንግሥቱ መሠረት ድርድሩ ይካሄድ ማለቱን እንደተቀበሉት ተናግረዋል፡፡ ነገር ግን ድርድሩ ሲቃረብ የአፍሪካ ኅብረትን ሚና እያጣጣሉት ነው፡፡ ከዚህ በተጨማሪም እነሱ በሚመፃደቁበት ሕገ መንግሥት ይፈታ መባሉን በሚፃረር ሁኔታ የጦር መሣሪያ አንፈታም፣ ታጣቂዎቻችንንም አንበትንም እያሉ ነው፤›› በማለት የጠቀሰው የፖለቲካ ተንታኙ አቶ ኡመር፣ ይህ ደግሞ ለድርድሩ እንቅፋት መሆኑን ያስረዳል፡፡
‹‹ምዕራብ ትግራይ›› (ወልቃይት) የሚባለው የወሰን ይገባኛል አጀንዳ ለሕወሓት ቀላል እንደማይሆን ያመለከተው አቶ ኡመር፣ ምዕራባውያኑ የሚያሾሩት ከተቻለም የሰላም አስከባሪ ኃይል በትግራይ በማስፈር የሚካሄድ የድርድር ሒደትን ሕወሓቶች በግልጽ መፈለጋቸው እንደሚታይ ያብራራል፡፡
መንግሥት ገና ለገና የምዕራባውያኑ ጫና ይበረታል በሚል ሥጋት የድርድሩን ሒደትም ሆነ የአደራዳሪዎችን ሚና ለመቀየር መገደድ እንደማይኖርበት ያመለከቱት አንጋፋው ፖለቲከኛ አቶ አንዳርጋቸው በበኩላቸው፣ የኤርትራ በድርድሩ መግባት አለመግባት ጉዳይ ጋር በተገናኘ ሰፊ ማብራሪያ ሰጥተዋል፡፡
‹‹በኢትዮጵያ ውስጥ ማንም ይግባ/ይውጣ ብሎ የመወሰን ጉዳይ የማንም ሳይሆን የኢትዮጵያ መንግሥት ነው፤›› ሲሉ የሚናገሩት አቶ አንዳርጋቸው፣ የኤርትራ ኃይል ይውጣ ወይም ኤርትራ በድርድሩ አትሳተፍም የማለት ሥልጣኑ የሕወሓትም ሆነ የምዕራባውያኑ አለመሆኑን አስምረውበታል፡፡
‹‹ኢትዮጵያ ሉዓላዊ ግዛቴን ኤርትራ ወራለች አላለችም፡፡ የኢትዮጵያ መንግሥት ኤርትራ እንድትገባም ሆነ እንድትወጣ የማድረግ ሥልጣን አለው፡፡ ራሳቸው ሕወሓቶች ኤርትራ እንዳትገባ በመፈለግ ነበር አስመራን በሚሳይል የደበደቡት፡፡ ራሱ የአሜሪካ መንግሥት ጦርነቱን ቀጣናዊ አታድርጉት ብሎ መግለጫ እስኪሰጥ ድረስ እነሱ ነበሩ የኤርትራን ጣልቃ ገብነት የጋበዙት፡፡ የኤርትራ መንግሥት እዚህ ውስጥ የገባው ሉዓላዊ ደኅንነቱን ለማስጠበቅ መሆኑ ይታወቃል፡፡ እነሱ ግን አሁንም ቢሆን የኤርትራ መንግሥትን ስለማፍረስ ሲያቅራሩ ይታያሉ፡፡ ሕወሓት ከኢትዮጵያ አልፎ ለኤርትራም ቀጣናዊ ሥጋት ነው፡፡ ስለዚህ ኤርትራ ያገባታል፤›› በማለት አቶ አንዳርጋቸው ተናግረዋል፡፡
የኢትዮጵያ መንግሥት ከሕወሓት ጋር ሳይሆን በቀጥታ ከኤርትራ መንግሥት ጋር መገናኘትና መደራደር ይችላል ሲሉ የሚጠቅሱት አቶ አንዳርጋቸው፣ ከዚህ ውጪ ግን ሕወሓቶች ራሳቸውን እንደ ሉዓላዊ አገር ቆጥረው ኤርትራን በተመለከተ እንወስን ማለታቸው ፈጽሞ ተቀባይነት የሌለው ነው ይላሉ፡፡
በሌላ በኩል፣ ‹‹የዲፕሎማሲ ዝርክርክነት ይታየኛል›› ሲሉ የሚናገሩት አቶ አንዳርጋቸው፣ ኢትዮጵያ እንኳን ድርድሩ ውስጥ ገብተው እንዲፈተፍቱ ቀርቶ፣ ‹‹ምዕራባውያኑ በታዛቢነትም ቢሆን ዝር እንዲሉ መፍቀድም የለባትም፤›› በማለት ሐሳባቸውን አጠቃለዋል፡፡