ባንኮች ለብድር ማስያዣ የያዙትን ንብረት ሸጠው ብድራቸውን ለማስመለስ በአዋጅ የተሰጣቸውን ልዩ መብት ይሸረሽራል ያሉት ድንጋጌ በአዲሱ የንግድ ሕግ ውስጥ መካተቱ ከፍተኛ ሥጋት እንዳሳደረባቸው አመለከቱ፡፡ የጉዳዩን አሳሳቢነትና ከዚሁ ጋር ተያይዞ እየገጠማቸው ያለውን ችግር ለብሔራዊ ባንክ እንዳመለከቱም ታውቋል፡፡
በአዲሱ የንግድ ሕግ የተቀመጡ የተወሰኑ ድንጋጌዎች ባንኮች በዋስትና የያዙትን ንብረት የመሸጥ መብታቸውን የሚሸረሽሩ መሆናቸውን የሚገልጹት የባንክ የሥራ ኃላፊዎች፣ በተጨባጭም በአሁኑ ወቅት ችግር እየገጠማቸው እንደሆነም ተናግረዋል። ባንኮቹን ሥጋት ውስጥ የከተተውና በቀጣይም ለፋይናንስ ኢንዱስትሪው ትልቅ ችግር ይሆናል የተባለው በአዲሱ የንግድ ሕግ በአንቀጽ 654 ሥር የተቀመጡ ድንጋጌዎች ናቸው፡፡
በዚህ አንቀጽ ሥር የተቀመጠው መሠረታዊ ድንዳጌ፣ ‹‹…የማይንቀሳቀስ ንብረት መያዣ፣ የንብረት ዋስትና ያላቸውን፣ የቅድሚያ መብት ያላቸውን፣ እንዲሁም ባለሀብትነታቸው እንደተጠበቀ ሆኖ የተደረጉ የሽያጭ ውሎች ያሏቸው ገንዘብ ጠያቂዎችን ጨምሮ፣ በማናቸውም ገንዘብ ጠያቂዎች ክፍያ ለማስፈጸም በተናጠል የሚደረጉ ክርክሮች፣ በሙሉ ባለ ዕዳው ወይም በመልሶ የማደራጀት ኃላፊው በተናጠል ክፍያ ለማስፈጸም የሚደረጉ ክርክሮች እንዲቋረጡላቸው ጥያቄ ማቅረብ ሳያስፈልጋቸው በመጠባበቂያ ጊዜው ወቅት በሕግ ተቋርጠው ይቆያሉ፤›› የሚል ነው፡፡
በተጨማሪም በዚሁ አንቀጽ ሥር፣ ‹‹ለዕዳ ማስዣያነት የዋሉ ንብረቶች በባለዕዳው ይዞታ ውስጥ ካልሆኑ ወይም በተናጠል ክፍያ ለማስፈጸም የሚደረጉ ክርክሮች የንግድ ሥራውን መልሶ የማዋቀር ሥራውን የማስተጓጉል ዕድላቸው አነስተኛ ከሆነ፣ ወይም በተናጠል ክፍያ ለማስፈጸም የሚደረጉ ክርክሮች በአጠቃላይ መቋረጣቸው አንድ ወይም ከዚያ በላይ ገንዘብ ጠያቂዎችን አግባብ ባልሆነ መልኩ የሚጎዳ ከሆነ፣ ሌሎች የክፍያ ጥያቄዎችን በተናጠል ክፍያ ለማስፈጸም የሚቀርቡ ክሶች ላይ ከሚቀመጡ አጠቃላይ ዕገዳዎች የአፈጻጸም ወሰን ውጪ ሊደርግ ይችላል›› የሚለው ድንጋጌ ባንኮቹ አሁን እየገጠማቸው ላለው ችግር መነሻ መሆኑ ጠቁመዋል፡፡
በዚህ አከራከሪ ነው በተባለው ጉዳይ ዙሪያ አስተያየታቸውን የሰጡት የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ፕሬዚዳንት አቶ አቤ ሳኖ፣ ‹‹የንግድ ሕጉ ባንኮች ለብድር ማስያዣነት የተረከቡትን ንብረት ብድሩ ባለመክፈሉ ምክንያት በአዋጅ ቁጥር 97/90 እና በተሻሻለው አዋጅ ቁጥር 216/92 መሠረት ለመሸጥ ሲነሱ፣ ተበዳሪው በአዲሱ የንግድ ሕግ ውስጥ የተካተተውን አንቀጽ በመጥቀስ ጨረታው ወይም ሐራጁ እንዲታገድ በማድረግ በባንኮች ላይ እንቅፋት እየሆነ ነው፤›› ብለዋል፡፡ ይህም አጠቃላይ ሁኔታው እንዲወሳሰብና ግልጽ እንዳይሆን አድርጎታል ብለዋል። አዋጅ ቁጥር 97/90 እና የተሻሻለው አዋጅ ቁጥር 216/92፣ ባንኮች የሰጡትን ብድር ለማስመለስ ሁነኛ ሚና ሲጫወት የቆየና ጤናማ ሁኔታን የፈጠረ ቢሆንም፣ በአዲሱ የንግድ ሕግ ውስጥ ነባሩን አሠራር የሚያዛባ ድንጋጌ መካተቱ በጣም እንዳሳሰባቸው ተናግረዋል፡፡ አዲሱ የንግድ ሕግ ውስጥ የተካተተው አንቀጽ ተበዳሪዎች ይህንን አንቀጽ ጠቅሰው የተያዘባቸው ንብረት በሐራጅ እንዳይሸጥና እንዲዘገይ መብት የሚሰጣቸው በመሆኑ፣ ባንኮች ብድራቸውን ለማስመለስ የሚያስቸግራቸው እንደሚሆንም ይጠቅሳሉ፡፡
ባንኮች በነባሩ አዋጅ በተሰጣቸው መብት መሠረት ዕዳቸውን ለማስመለስ መከተል ያለባቸውን የሕግ ድንጋጌ በማጓደል በንብረት አስያዡ ላይ ጉዳት ከደረሰና ይህንንም ንብረት አስያዡ ማረጋገጥ ከቻለ ለደረሰበት ጉዳት ካሳ የመጠየቅ የሕግ መብት የተሰጠው በመሆኑ የባንኮችንም ሆነ የባለንብረቶችን መብት በእኩል የሚያስከበር እንደሆነ አስረድተዋል። ነባሩ አዋጅ ከላይ የተጠቀሰውን መሰል ድንጋጌዎችንና አስተማማኝ አሠራሮችን የያዘ ቢሆንም፣ አሁን በአዲሱ የንግድ ሕግ ላይ የተጠቀሰው አንቀጽ ግን በተለይ ወደፊት ከፍተኛ ጫና እንደሚያሳድር ሪፖርተር ያነጋገራቸው የባንክ የሥራ ኃላፊዎች ያስረዳሉ፡፡ ከአዲሱ የንግድ ሕግ ጋር በተያያዘ ባንኮች ገጥሞናል ያሉትን ችግር በተመለከተ፣ መረጃ የደረሰው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክም በዕዳ የተያዘ ንብረትን ለመሸጥ የሚያስችለውን (የፎርክሎዠር) አዋጅ የሚፃረር ድንጋጌ በአዲሱ የንግድ ሕግ ውስጥ መኖሩን እንደሚመረምርና ከዚሁ ጋር ተያይዞ በባንኮች የቀረበውን አቤቱታ በጥልቀት ገምግሞ ምላሽ እንደሚሰጥበት ለባንኮቹ ማስታወቁን ለመረዳት ተችሏል፡፡
በጉዳዩ ላይ ሪፖርተር ያነጋገራቸው የሕግ ባለሙያ አቶ ዮሐንስ ወልደ ገብርኤል፣ በአዲሱ የንግድ ሕግ ውስጥ የጠቀሰው አንቀጽ 654 አሁን ሥራ ላይ ካለው የፎርክሎዠር አዋጅ ጋር የሚጋጭ ስለመሆኑ ያምናሉ፡፡ ነገር ግን በሥራ ላይ ያለው የፎርክሎዠር አዋጅ ለባንኮች የተለጠጠ መብት የሚሰጥ እንደሆነም ይጠቅሳሉ፡፡
በአዲሱ የንግድ ሕግ ላይ የተጠቀሰው አንቀጽ ባንኮች ተለጥጦ የተሰጣቸውን መብት የሚገድብ ቢሆንም፣ በአዲሱ የንግድ ሕግ ውስጥ የተካተተው አንቀጽ ግን መኖር ያለበትና አስፈላጊ ስለመሆኑም ተናግረዋል፡፡ ምንም እንኳን ባንኮች የሕዝብ ገንዘብ የሚጠብቁ ቢሆንም፣ የባንኮች ዕዳና ሀብት እንዲህ በቀላሉ የሚታይ ጉዳይ እንዳልሆነ አቶ ዮሐንስ አስረድተዋል። እንደ ባለሙያው ገለጻ፣ ባንኮች በተለይ ብድር ያልመለሱ የንግድ ተቋማትን በሚከሱበት ጊዜ ወይም የብድር ውሉ ላይ ማሻሻያ (ሪኦርጋናይዝ) ለማድረግ መከተል አለባቸው ተብሎ በአዲሱ የንግድ ሕግ የተቀመጠው የአፈጻጸም ሒደት በጣም ምክንያታዊ ነው ብለው ያምናሉ፡፡ ‹‹በአጠቃላይ በኪሳራ ጊዜ የሚፈጠሩ አሠራሮችን ሙሉ ለሙሉ ማስወገድ አለብህ፣ ያለበለዚያ ከሁለት አንዱን መምረጥ አለበት በማለት በንግድ ሕጉ የተቀመጠውን አንቀጽ ተገቢ ነው፤›› የሚሉት አቶ ዮሐንስ፣ እንዲያውም ይህ በንግድ ሕጉ ውስጥ የተካተተው አንቀጽ 654 ላይ ያለው አሠራር የንብረት መብትን ለማስከበር ወሳኝ እንደሆነ ተናግረዋል፡፡
እንደ አቶ አቤ ገለጻ ግን፣ ‹‹አንድ ሐራጅ የወጣበት ንብረትን እንዳይሸጥ የሚታገደው በሌሎች መብት ላይ ጉዳት የሚያስከትልና ጉዳቱ የማይታረም ስለሆነ ነው ቢባል እንኳን፣ ባንኮች ይህንን የማረም አቅም አላቸው፤›› ይላሉ፡፡ ባንኮች ከተበዳሪዎች መብት በሐራጅ ሸጠው ጉዳት ቢደርስ ጉዳቱን የመተካት ግዴታ ባንኮቹ ስላለባቸው፣ አሁን በሥራ ላይ ያለው አዋጅ ተበዳሪዎች በአግባቡ ዕዳቸውን እንዲከፍሉ የሚያስችል እንደሆነ የሚጠቅሱት አቶ አቤ፣ የፎርክሎዠር አዋጁ ሲሻሻልም ለባንኮች ልዩ መብት በመስጠቱ በርካታ ጠቀሜታዎችን እንዳበረከተ ያስታውሳሉ፡፡ ይህ አዋጅ ለባንኮች ብዙ ጠቀሜታ ያለው ሲሆን፣ በተለይ ባንኮች ብድራቸው ሳይከፈል ሲቀር በዋስትና የያዙትን ንብረት በወቅቱ ሸጠው ማስመለስ እንዲችሉ እረድቷቸዋል ብለዋል። በመሆኑም ባንኮች በድፍረት ብድር እንዲሰጡ መተማመኛ እንደሆናቸውም ይገልጻሉ። ይህንን መብት ባጡ ቁጥር ግን ባንኮች ከፍተኛ ጥንቃቄ የማድረግ ኃላፊነት የሚጥል በመሆኑ ብድር ለመስጠት ፈራ ተባ ማለታቸው እንደማይቀር ገልጸዋል። ችግሩ የባንኮች ብቻ ተደርጎ መውሰድ የለበትም የሚሉት አቶ አቤ፣ በንግድ ሕጉ የተቀመጠው ድንጋጌ የባንኮች ብድር አቅርቦትን የሚያስተጓጉልና በውጤቱም በአገራዊ ኢኮኖሚው ላይ ትልቅ ጉዳት ይዞ ሊመጣ እንደሚችል ሥጋታቸውን አጋርተዋል፡፡ የፎርክሎዠር አዋጁ ከመውጣቱ በፊት የኢትዮጵያ ባንክ ኢንዱስትሪ በጣም የተበላሸ እንደነበር በማስታወስም፣ የፎርክሎዠር አዋጅ ከወጣ በኋላ ግን ብዙ ነገሮች መስተካከላቸውን ገልጸዋል። አዋጅ ቁጥር 97/90 እና የተሻሻለው 216/92 አዋጅ ከወጣ በኋላ፣ ብዙ ንብረቶች ተሸጠው ሳይሆን ንብረቱ ይሸጥብኛል ብለው ተበዳሪዎች ሕጉን አክብረው ግዴታቸውን መፈጸማቸውን የሚገልጹት አቶ አቤ፣ በንግድ ሕጉ የተቀመጠው ድንጋጌ ግን በመልካም እየሄደ የነበረውን አሠራር የሚሸረሽር በመሆኑ ሊታሰብበት እንደሚገባ አሳስበዋል።
በጉዳዩ ላይ ያነጋገርናቸው ሌሎች የባንክ የሥራ ኃላፊዎችም እንደሚገልጹት፣ አንዳንድ ተበዳሪዎች ብድራቸውን ባለመክፈላቸው ባንኮች በሕጉ መሠረት ንብረታቸውን በጨረታ ለመሸጥ ሲሞክሩ የጨረታ ሒደቱን የሚያደናቅፉ ሆነው አግኝተውታል፡፡ የጨረታ ሒደቱን ለማሳገድ ‹‹ባንኩ አታሎኛል››፣ ‹‹ባንኩ አጭበርብሮኛል›› የሚሉና ሌሎች መሰል ማመልከቻዎችን ይዘው ፍርድ ቤት በመቅረብ ጉዳዩ ይታይ የሚል ውሳኔ ሊያስወስኑ እንደሚችሉ ይገልጻሉ። በዚህና መሰል ጥያቄዎች መነሻነት የፍርድ ቤት ሒደቱን በማራዘም በባንኮች ላይ ፈታኝ ሁኔታ እንደሚፈጠሩ ይገልጻሉ።
በአዲሱ የንግድ ሕግ የተጠቀሰው አንቀጽ፣ ባንኮች የሚያወጡትን የዋስትና ንብረት የሽያጭ ጨረታ (ፎርክሎዠር) ተበዳሪዎች ማሳደግ እንዲችሉ መብት የሚሰጣቸው በመሆኑ፣ ባንኮች ብድራቸውን ለማስመለስ እንቅፋት እንደሚሆንባቸው ጠቁመዋል፡፡
በንግድ ሕጉ ለባንኮች እንቅፋት ይሆናል የተባለው ሌላው ድንጋጌ ዕዳን መልሶ ስለማዋቀርና ኪሳራ ይወሰንልኝ (ባንክራፕሲ) ጥያቄን የተመለከተ ነው። ድንጋጌው፣ አንድ ተቋም ኪሳራ ሲገጥመው መውሰድ ስለሚፈልገው ዕርምጃ የሚያብራራ ነው፡፡ አንዳንድ ተበዳሪዎች ግን ይህንን ባልተፈለገ መንገድ ተርጉመው ብድራቸውን ሳይከፍሉ ቀርተው ባስያዙት ንብረት ላይ ሐራጅ ሲወጣ፣ በአዲሱ የንግድ ሕግ ላይ የተቀመጠውን ይህንን ድንጋጌ በመጥቀስ ዕዳቸውን መልሰው ለማዋቅር ለፍርድ ቤት አቤቱታ በማቅረብ ሊከራከሩ ይችላሉ፡፡ በዚህ ምክንያት ባንኮች ለሰጡት ብድር ዋስትና የያዙትን ንብረት ሸጠው ብድራቸውን ለማስመለስ እንቅፋት እንደሚሆንባቸው እኚሁ ያነጋገርናቸው የባንክ ኃላፊዎች ይገልጻሉ፡፡ ብድር ያበላሹ ወይም ብድሩን ለሌላ ዓላማ ያዋሉ ተበዳሪዎች ይህንን የንግድ ሕጉን አንቀጽ በመጥቀስ ባንኮች ብድራቸውን ለማስመለስ የሚያደርጉትን ጥረት ሊያደናቅፉ እንደሚችሉ ሥጋታቸውን ገልጸዋል። ፍርድ ቤቶችም በዚህ አንቀጽ ላይ ተመሥርተው፣ እንዲሁም የባንክ የሥራ ሒደትን በቅጡ ባለመገንዘብ ፈጣን ውሳኔ የማይሰጡ ቢሆንና ሒደቱ ቢራዘም በባንኮች ላይ ከፍተኛ ጉዳት የሚያስከትል መሆኑን እነዚሁ ያነጋገርናቸው የባንክ የሥራ ኃላፊዎች ይገልጻሉ፡፡ አቶ ዮሐንስ ይህንን ሐሳብ በተወሰነ ደረጃ የሚጋሩት ቢሆንም፣ ባንኮች በፎርክሎዠር አዋጁ የተሰጣቸውን የበዛ መብት ያላግባብ ሲጠቀሙበት ይታያልና ይህንን የተለጠጠ የባንኮች መብት ለመገደብ ድንጋጌው መቀመጡ ተገቢ ነው ይላሉ፡፡
የባንክ የሥራ ኃላፊዎች ደግሞ በተሻሻለውና አሁንም ሥራ ላይ ባለው አዋጅ ማንኛውንም የተበዳሪን ንብረት ሕግ ካስቀመጠው ሥነ ሥርዓት ውጪ ለመሸጥም ሆነ ንብረትነቱን ለመውሰድ የሚደረግ ስምምነት ዋጋ የሌለው ወይም ውጤት አልባ ስምምነት እንደሆነ የሚደነግግ በመሆኑ አዋጁ ሁሉንም ወገን የሚጠቅም እንደሆነ ይከራከራሉ፡፡ አዳሪው ያበደረውን ገንዘብ እንዲያገኝ፣ እንዲሁም ተዳሪም ዕዳውን ከፍሎ ተራፊ ገንዘብ ካለ ከዚሁ ከተራፊ ገንዘብ ተጠቃሚ እንዲሆን የጠቀመ፣ እንዲሁም ንብረቱ በጨረታ በዝቅተኛ ዋጋ እንዳይሸጥ የተለያዩ የሕግ ማዕቀፎች ያሉ በመሆኑ ሒደቱ ጤናማ እንደነበርም ይጠቅሳሉ፡፡
ለባንኮች መብት የሚሰጠው ይህ አዋጅ አበዳሪ ባንኮች የያዙትን ንብረት ለመሸጥ የሽያጭ ሒደቱ በፍርድ ቤት ማለፍ ሳያስፈልገው፣ ባንኮች ለብድር ዋስትናነት የያዟቸውን ንብረቶች ወደ ፍርድ ቤት መሄድ ሳያስፈልጋቸው በቀጥታ መሸጥና ንብረቱን ወደ ገዥ የማዛወር መብት የሚሰጣቸው ነው፡፡
በባንክ በመያዣነት ስለተያዙ የሚንቀሳቀሱና የማይንቀሳቀሱ ንብረቶች በሚል አዋጅ ቁጥር 1997/90 ሲወጣም በአዋጁ መግቢያ ላይ የተገለጸው፣ ባንኮች በዋስትና የተያዙ የማይንቀሳቀሱና የሚንቀሳቀሱ ንብረቶች እንዲሸጡ ለፍርድ ቤት ክስ አቅርቦ ለማስወሰንና ውሳኔውንም ለማስፈጸም የሚወስደው ጊዜ በጣም ረዥም በመሆኑ ታሰቢ ተደርጎ ነው፡፡
በዚህም መሠረት የሚንቀሳቀስ ወይም የማይንቀሳቀስ ንብረት በዋስትና የያዘ ባለገንዘብ ባንክ የሚፈልገውን ዕዳ እንዲከፍል በተወሰነው ጊዜ ሳይከፍል ቢቀር ከሰላሳ ቀናት ያላነሰ ማስጠንቀቂያ ለባለ ዕዳው በመስጠት በመያዣነት የያዘውን የማይንቀሳቀቀስ ንብረት በሐራጅ ለመሸጥና የባለቤትነት መብቱን ለገዥው የማዛወር መብት እንደሚኖረው ይደነግጋል፡፡ ከሁለት ጨረታ በኋላም ባንኮች በጨረታው ዋጋው ንብረቱን ማስቀረት መብት ይሰጣቸዋል፡፡
አዋጅ 1997/90 በተለይ ፍርድ ቤት ክስ መሥርቶ ለማስወሰን የሚወስደው ጊዜ ረዥም መሆኑ፣ እንዲሁም አንድ ባንክ የሚያበድረው ገንዘብ በተለይ ደንበኞች የሚሰበስበው ተቀማጭ ገንዘብ ከመሆኑም በላይ ለዚህ ተቀማጭ ገንዘብ ለአስቀማጮች የሚከፍለው ወለድ በመኖሩ ይህ ገንዘብ አስቀማጩ በባንኩ ካስቀመጠበት ጊዜ ጀምሮ የባንኩ ንብረት የሆነና ባንኩን በፈለገው መንገድ እንዲጠቀምበት መብት የሚሰጥ ነው፡፡
የመያዣ ንብረት ለመሸጥ መከተል የሚገባቸው ሕጉ አሠራሮች ምንም እንኳን ባንኮች የመያዣ ንብረቶችን ከፍርድ ቤት ትዕዛዝ ውጪ በመሸጥ ለዕዳ ማካካሻነት የማዋል ሥልጣን በሕግ ተሰጣቸው ቢሆንም፣ ሽያጩን ለማከናውንም ሆነ ሽያጩ ከተከናወነ በኋላ መከተል ያለባቸው ሥነ ሥርዓቶች ግን እንዳሉ በጉዳዩ ላይ የቀረቡ ጥናታዊ ጽሑፎች ያመለክታሉ፡፡
የአቶ ዮሐንስ ምልከታ ግን የተለየ ነው፡፡ ‹‹ልክ ነው በዚህ የንግድ ሕግ ምክንያት ባንኮቹ ሊቸገሩ ይችላሉ፡፡ እንደቀድሞ በፍጥነት ስንት የተለፋበትን ንብረት አይሸጡም፡፡ ነገር ግን ፎልክሎዠሩን የመጨረሻ አማራጭ ከሚያደርጉት፣ ተበዳሪውን እያስታመሙና እያሠሩ ገንዘቡን የሚመልሱበት ዘዴ ሊኖራቸው ይገባል፤›› በማለት ፎልክሎዠሩን የመጨረሻ አማራጭ እንዲያደርጉ ይህ የንግድ ሕግ ያግዛል ብለው ይከራከራሉ፡፡
ከባንኮች የሚገለጸው ደግሞ የሕዝብ ገንዘብ በአግባቡ መመለስ አለበት የሚል ነው፡፡ አንዳንዶች ሆን ብለው ገንዘቡን እንዳይመለስ ሊያደርጉ እንደሚችሉ፣ ይህ ደግሞ የብድር የማቅረብ ሒደቱ ጥንቃቄ የበዛበት አሠራርን እንዲከተሉ የሚያስገድዳቸው በመሆኑ ብድር ወደ ኢኮኖሚው የሚገባው ገንዘብ እንዲቀንስ ያደርጋል የሚል መከራከሪያ በባንኮት በኩል ይነሳል፡፡ ባንኮቹ እንደሚሉት እንዲህ ዓይነት ሁኔታ ከተከሰተ የባንኮችን አገልግሎትም ሆነ ኢኮኖሚውን እንደሚጎዳ ይከራከራሉ።
ሌሎች ባለሙያዎች ደግሞ የአዲሱ ንግድ ሕግ ድንጋጌ የሁሉንም መብቶች ለማስከበርና የተሟላና የዘመነ የንግድ ሥርዓትን ለመገንባት የተለመ እንደሆነ ይገልጻሉ። ሥጋት የቀረበበት ድንጋጌ ኢኮኖሚውን በተረጋጋ መሠረት ላይ ለማስቀመጥ ያለመ እንጂ የባንኮችን መብት ለመሸርሸርም ሆነ የተበዳሪን ለመጥቀም ተብሎ የቀረበ እንዳልሆነ ገልጸዋል። እየተገነባ የሚገኘው ኢኮኖሚ ወይም አንድ አገር እያደገ ሲሄድ በኢኮኖሚው ውስጥ የሚንቀሳቀስ ሀብት የብዙዎች በመሆኑ አንድ ንብረት በሐራጅ ከመሸጡ በፊት የሌሎች የሀብቱ ተጋሪዎችን መብት ለማስከበር ወይም አለመጣሱን ለማረጋገጥ የተቀመጠ ድንጋጌ እንደሆነ ይገልጻሉ። ለአብነት ያህልም በቀጣዮቹ ቅርብ ዓመታት ውስጥ የአክሲዮን ገበያ በኢኮኖሚው መሠረት ትልቅ ሚና እንደሚኖረው ጠቅሰው፣ በአንድ የዋስትና ንብረት ላይ ሌሎችም መብት የሚኖራቸው ከመሆኑ አንፃር ከተመዘነ በንግድ ሕጉ የተቀመጠው ድንጋጌ ቅሬታ የሚቀርብበት እንዳልሆነ ይከራከራሉ።
በፎርክሎዠር አዋጅ አበዳሪ ባንኩ በንብረት አስያዡ ላይ ለሚያደርሰው ጉዳት ኃላፊነት ያለበት ሲሆን፣ ዋና ዋናዎቹ ሥነ ሥርዓቶችም ለተበዳሪና ለአስያዡ በተበዳሪውንና ንብረቱን ሳያስይዘው የ30 ቀናት የማስጠንቀቂያ መስጠት፣ የንብረቱን ጨረታ ለ30 ቀናት በጋዜጣ ወይም በአየር ላይ እንዲቆይ በማድረግ፣ እንዲሁም ሌሎች ጨረታው የአስያዡን መብት ባስጠበቀ መልኩ ይፈጸማል፡፡ በዚህ ሒደት ሁለት ጊዜ ጨረታ በማውጣት ገንዘቡን ማስመለስ ካልቻለ ባንኩ ንብረቱን በስሙ የማዘዋወር መብት የሚሰጥ ቢሆንም፣ የንግድ ሕጉ ግን ይህንን የሚገዳደር ሆኖ ተገኝቷል፡፡
ባንኮች እያነሱ ባሉት በዚህ ጥያቄ ዙሪያ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ በቅርቡ ከባንኮች ጋር በነበረው ውይይት ላይም፣ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ገዥ የሰጡት ሐሳብ ነበር፡፡ ብድር ማስመለስ ላይ በተለይ ትልልቅ ተበዳሪዎች ባንኮችን ለአደጋ የሚጥሉ እነሱ ስለሆኑ ትኩረት አድርጉ በማለት ባንኮችን ያሳሰቡ መሆኑን የሚገልጹት ይናገር (ዶ/ር)፣ ማድረግ ያለባችሁን ሁሉ እያደረጋችሁ እስከ ፎርክሎዠር ጭምር በመሄድ ብድሩን አስመልሱ የሚል ማሳሰቢያ መስጠታቸውንም አክለዋል፡፡
በዚህ መሠረት አጠናክረው በዚህ ማሳሰቢያ መሠረት የሄዱ ያሉ ባንኮች የመኖራቸውን ያህል አንዳንዶች ያስታመሙ መኖራቸውን ጠቅሰዋል፡፡ ሆኖም ወደ ፎርክሎዠር የገቡ አንዳንድ ባንኮች ላይ ከወትሮ የተለየና ከንግድ ሕጉ ጋር የተያያዘ አዲስ ነገር መምጣቱን የሰሙት በቅርብ ጊዜ መሆኑን ተናግረው፣ ነገር ግን ይህንን ጉዳይ በተመለከተ ከሚመለከታቸው የፍትሕ ተቋማት ጋር የሚነጋገሩበት እንደሆነ ጠቁመዋል፡፡
የባንኮችን መብት የሚሸረሽር ነገር እንዳይኖር፣ እንዲህ ዓይነት ሁኔታም ከተፈጠረ ለባንኮች ከፍተኛ አደጋ ስለሚሆን የሚመለከታቸው ተቋማት ለዚህ ዕልባትና መፍትሔ ለመስጠት ዕገዛ ያደርጋሉ የሚል እምነት እንዳላቸውም አቶ ይናገር ገልጸዋል፡፡
በንግድ ሕጉ ውስጥ የተካተተው አንቀጽ 654 አስፈላጊነትና ተገቢነት ላይ አጠንክረው ሐሳባቸውን የገለጹት አቶ ዮሐንስ በበኩላቸው፣ የንግድ ሕጉ አንቀጽ 654 ያወጣው ድንጋጌ ከፎርክሎዠር ሕጉ ጋር መጋጨቱ የማይቀር ቢሆንም ሚዛናዊ ነው ይላሉ፡፡ የንግድ ሕጉ በጣም ምክንያታዊ እንደሆነ ግጭቱ ያለው የዕግድ ጉዳይ ላይ ነው ብለዋል፡፡ በ654 አንድን የቢዝነስ ተቋም ሪኦርጋናይዝ ለማድረግና ይህንን ለማስፈጸም እንጂ ባንኮችን መብታቸውን ለማሳጣት እንዳልሆነም ያምናሉ፡፡ ስለዚህ በንግድ ሕጉ የተጠቀሰው አንቀጽ አሠራር መሠረት መሄድም ትክክል ነው የሚል አቋም አላቸው፡፡
‹‹በመሠረቱ የፎርክሎዠር ሕግ የመጀመርያ ሳይሆን የመጨረሻ አማራጭ ነው፡፡ አሁን ያለው የፎርክሎዠር አሠራር ባንኮች ተበዳሪያቸውን ብድሩን መክፈል ካልቻለ ወዲያውኑ ገንዘባቸውን የማስመለስ አካሄድ እንጂ የተበዳሪው ተቋም እንደገና አንሰራርቶ ገንዘብ አግኝቶ የበለጠ ደንበኛ ሊሆን የሚችልበትን መንገድ የሚረዳ አፈጻጸም አይደለም ብለዋል፡፡
‹‹ስለዚህ ሚዛናዊ ድንጋጌ አስፈላጊ ነው፡፡ ለዚህ ደግሞ የአዲሱ የንግድ ሕግ ጠቃሚ የሆነ አንቀጽ አስፍሯል፤›› በማለት ከባንኮች ሥጋት በተለየ ያላቸውን ሐሳብ ሰንዝረዋል፡፡ አያይዘውም የፎርክሎዠር ድንጋጌ የመጨረሻ አማራጭ ተደርጎ የሚገባው ስለመሆኑ የሚገልጹት አቶ ዮሐንስ ግን፣ አሁን በከፍተኛ ሁኔታ አቢውዝ እየተደረገ የግለሰቦችን ንብረትና ሀብት ጊዜ ሳይጠብቅ እየተሸጠ በመሆኑ፣ ይህንን ለማስቀረት የንግድ ሕጉ ተገቢ የሆነ አንቀጽ ማስቀመጡን ያምናሉ፡፡
ያገጋገርናቸው የባንክ ኃላፊዎች ደግሞ ወደ ፎርክሎዠር የሚወጣው እንደተባለው ለተበዳሪው እስከመጨረሻው ለማገዝ ጥረቶች ከተደረጉ በኋላ ነው፡፡ ብዙ ባንኮች ከፎርክሎዘር በፊት ተበዳሪዎችን ያስታምማሉ፡፡ ተጨማሪ ብድር ሁሉ አቅርበው እንዲያንሠራሩ ያደርጋሉ፡፡ እነዚህ ሁሉ ዕገዛዎች ከተደረጉ በኋላ መስተካከል ካልቻለ ማስያዣውን ለመሸጥ ይገደዳሉ ብለዋል፡፡