Tuesday, March 28, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -

‹‹ራሱን የቻለ አገር የራሱን እንጂ የሌሎችን ፍላጎት አያራምድም›› ብርሃኑ ቡልቻ (ዶ/ር)፣ የጌት ፋክት ማኅበር/ድርጅት አባል

እንዲህ ነኝ እያሉ የሠሩበትንም ሆነ የተማሩበትን ከመዘርዘር ይልቅ ኢትዮጵያዊ፣ አሜሪካዊና ኢትዮጵያን የሚወድ ሰው ብባል ይበቃል ሲሉ ነው በትኅትና ስለማንነታቸው የሚናገሩት፡፡ በትምህርታቸው እስከ ዶክትሬት ዲግሪ ገፍተዋል፡፡ በኢትዮጵያ ጉዳዮች ላይ ትክክለኛ መረጃዎችን በመሰብሰብና በመተንተን የሚታወቀው የጌት ፋክት ማኅበር/ድርጅት አባልም ናቸው፡፡ በአሜሪካ በተለይ ዳያስፖራውን ማዕከል ያደረጉ አጀንዳዎችን በቅርበት እንደመከታተላቸው፣ አሜሪካም ሆነች ሌሎች የውጭ መንግሥታት በአሁኑ ወቅት ኢትዮጵያን በተመለከተ የሚያራምዱትን አቋም በሰፊው ያስረዳሉ፡፡ ከወቅታዊ የኢትዮጵያ ጉዳዮች በመነሳት ዮናስ አማረ ከብርሃኑ (ዶ/ር) ጋር ያደረገው ቆይታ እንደሚከተለው ተጠናቅሯል፡፡

ሪፖርተር፡- ጌት ፋክት ሥራው ምንድነው? እዚያ ውስጥ ያለዎት ተሳትፎስ?

ብርሃኑ (ዶ/ር)፡- እኛ ኢትዮጵያዊ አሜሪካዊያን ነን፡፡ ኢትዮጵያን ደጋፊዎች ነን፡፡ ሥራችን እውነተኛውን የኢትዮጵያ ነገር ለአሜሪካ በማቅረብ የሁለቱን አገር ግንኙነት ማስተካከል ነው፡፡ የእኛ ተቋም ጌት ፋክት ዳታዎችን ይሰበስባል፣ የሰበሰበውን ተንትኖ ያቀርባል፡፡ ሥራውም ‹‹ምን እየተባለ ነው?›› የሚለውን አጣርቶ ማቅረብ ነው፡፡ ጌት ፋክት በ‹‹ኖ ሞር!›› ዘመቻ ውስጥ ተሳታፊ ነው፡፡ ሆኖም ሥራችን በዳታ ላይ ያተኮረና ወደ ውስጥ ገብቶ ‹‹ማን ምን እያለ ነው? እንዲሁም ወዴት እየሄድን ነው?›› የሚሉ ጉዳዮችን በመረጃ ትንተና ማቅረብ ነው፡፡ በቅርቡ ያደረግነው የዳታ ትንተና ለምሳሌ የአሜሪካና የአውሮፓውያኖቹ ትኩረት ምን ላይ እንደሆነ አመላካች ነው፡፡ የአውሮፓ ኅብረት፣ የአሜሪካ መንግሥትና የምዕራባውያን ተቋማት ብዙ ዝንባሌ የሰጡት ለትግራይ ጉዳይ ነው፡፡ ለምሳሌ የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ፣ ዩኤስኤይዲ፣ የአሜሪካ ኤምባሲ፣ አንቶኒ ብሊንከን፣ ሳማንታ ፓወርና የመሳሰሉ ስድስት ማሳያዎችን በመውሰድ የ18 ወራት መግለጫዎችን አጠናን፡፡

በመግለጫዎቻቸው ውስጥ ተደጋግሞ በብዛት የተጠቀሰው ቃል 71 በመቶ ትግራይ የሚል ሲሆን፣ 12 እና 16 በመቶ ደግሞ አማራና አፋር ነው፡፡ ጦርነቱ በአማራና በአፋር ክልሎች ውስጥ እየተካሄደ ጭምር ተደጋግሞ ትግራይ ይባል ነበር፡፡ በወሬ ርዕስነት ከሚቀርቡ ጉዳዮች መካከል ተደጋግመው የሚጠቀሱት ደግሞ ‹‹ትግራይ ሲጅ››፣ እንዲሁም ‹‹ትግራይ ሒዩማኒቴሪያን አክሰስ›› የሚሉ ነጥቦች ተደጋግመው ሲጠቀሱ አግኝተናል፡፡ የሕወሓት ዋና አጀንዳዎች ሆነው የሚነሱትም እነዚህ መሆናቸውን ስታይ ደግሞ፣ አንድ ዓይነትና የተናበበ ሐሳብን የማንፀባረቅ ፍላጎት መኖሩን ትረዳለህ፡፡ በአውሮፓ ኅብረት በኩልም ቢሆን በተመሳሳይ የትግራይ ጉዳዮችን ነጥሎ የማጉላት ነገር አግኝተናል፡፡ ትግራይም የኢትዮጵያ አካል እንደ መሆኑ ኢትዮጵያውያን ልክ በአማራና በአፋር የሚሆነውን እንደሚከታተሉት ሁሉ፣ በትግራይ የተፈጠረውንም ሁኔታ ጉዳዬ ብለው መከታተላቸው የሚጠበቅ ነው፡፡ ምዕራባውያኑ ግን የሚፈልጉትን አጀንዳ ነው እየቀረፁ የሚሰጡን፡፡ አንዱን ነጥሎ የማየትና ሌላ አጀንዳ አለባብሶ ማቅረብ አካሄዳቸው መሆኑን በግምገማችን አግኝተናል፡፡

ሪፖርተር፡- ምዕራባውያኑ በተለይም አሜሪካ ኢትዮጵያን ጨምሮ በአፍሪካ በሚከተሉት ፖሊሲ፣ በሌሎች የዓለም ኃያላን አገሮች የመቀደም ስሜት ውስጥ የገቡ ይመስላሉ፡፡ እንደ ቻይና፣ ሩሲያ፣ ቱርክና ሌሎችም አገሮች በአፍሪካ ተፅዕኗቸው መስፋቱ እነ አሜሪካን ያሳሰበ አይመስልም ወይ?  

ብርሃኑ (ዶ/ር)፡- አዎን፡፡ በደንብ እያሳሰባቸው ያለ ይመስላል፡፡ አሜሪካኖቹ አፍሪካ ምን ትፈልጋለች ብለው 54 አገሮችን ጠርተው ለማናገር ዕቅድ ይዘዋል፡፡ በቻይናና በሩሲያ የገጠማቸውን መቀደም ለማስመለስ ከፍተኛ ፍላጎት እንዳደረባቸው ያሳያል፡፡ አፍሪካ ትልቅ አኅጉር ነው፡፡ ብዙ ቀጣና ያለውና ብዙ ፍላጎት የሚታይበት አኅጉር ነው፡፡ ምዕራባውያኑ መላው አፍሪካን ሰብስበው ለማናገር መወሰናቸው ጫና እንዳረፈባቸው የሚያሳይ ነው፡፡ ቻይናና ሩሲያ በአፍሪካ በተለይም በምሥራቅ አፍሪካ አካባቢ የራሳቸውን ፍላጎት የሚያስፈጽሙበት ጉባዔና ጉብኝት ጨምሮ ጥረት መጀመራቸው ምዕራቡን ያነቃ ይመስላል፡፡

በአሜሪካም ሆነ በአውሮፓ በኢትዮጵያ ጉዳይ ላይ አንዳንድ ለውጦች እየተመለከትን እንገኛለን፡፡ ኢትዮጵያን በተመለከተ በሰብዓዊ መብት ጥሰት ክሶች የኢትዮጵያ መንግሥትን ማስጨነቅ እንዳላዋጣ የተረዳ ቡድን አለ፡፡ በሌላ በኩል በዚሁ መንገድ መግፋትና ኢትዮጵያ ላይ ጫና ማሳደር የሚፈልግም አለ፡፡ እንደ ጣሊያን፣ ኔዘርላንድስና ዩናይትድ ኪንግደም የመሳሰሉ አገሮች ይህንን ኢትዮጵያን ማስጨነቅ የሚል ጂኦ ፖለቲካዊ አካሄድ አላዋጣም የሚል ድምፅ እየተስተጋባባቸው ነው፡፡ የእኛን የፖሊሲ ክፍተት እነ ቻይናና ሩሲያ እየተጠቀሙበት ነውና እንደ ኢትዮጵያ ካሉ አገሮች ጋር ግንኙነታችንን እናሻሽል የሚል ድምፅ እየጎላ ነው፡፡

በአሜሪካ ፖሊሲ አውጪዎች አካባቢ ከኢትዮጵያ ጋር ግንኙነትን ማስተካከልና የኢትዮጵያን አንድነት ማጠናከር የሚደግፍ ወገን ያለ ቢሆንም፣ የኢትዮጵያን መከፋፈል ለራሳቸውና ለአሜሪካ ጥቅም ለማዋል የሚጥሩ ኃይሎችም ተፈጥረዋል፡፡ እነዚህ ከፋፋይ ኃይሎች ‹‹ኢትዮጵያዊ ነኝ›› ብሎ የቆመውን ወገን ማናገር ከተውና ድምፁን መስማት ካቆሙ ቆይተዋል፡፡ አሁን የትግራይ፣ የኦሮሞ፣ የአማራ ኮሙዩኒቲ እያሉ ኢትዮጵያዊያንን በብሔር ከፋፍለው በተናጠል እያነጋገሩ ነው፡፡ ቀርበው የሚያማክሩት ከአንድነት ኃይሎች ይልቅ፣ ፌዴራላዊ ኃይሎች ነን የሚሉ የብሔር ፖለቲከኞችን ነው፡፡ ኢትዮጵያዊ ነን የሚሉና ለአገራቸው ጥቅም የሚታገሉ ወገኖችን ድምፅ ለመስማት የማይፈልጉ ብዙ አሉ፡፡

ሪፖርትር፡- ይህ አተያይ በኮንግረሱም ሆነ በሴኔቱ አካባቢ የሚንፀባረቅ ነው?

ብርሃኑ (ዶ/ር)፡- በሁሉም የመንግሥት እርከኖች የሚታይ ነው፡፡ አሁን የኢትዮጵያን ጂኦ ፖለቲካዊ ጠቀሜታ ተገንዝቦ፣ የአሜሪካ አካሄድ እንዲስተካከል የሚጥር የአሜሪካ ሕግ አውጭ ክፍል አለ፡፡ ምርጫ የሚፈራና የኢትዮጵያን ኮሙዩኒቲ ድምፅ ለመሰብሰብ ያስችለኛል የሚለውን ከፋፋይ መንገድ የሚከተል አለ፡፡ ኢትዮጵያን የበለጠ በመከፋፈል በምርጫ ወቅት ከኢትዮጵያዊያን ለራሱ ብዙ ድምፅ ለመግዛት ብቻ ሳይሆን፣ የአሜሪካንም ጥቅም በዚያ መንገድ አስጠብቃለሁ ብሎ የሚያስብ አለ፡፡ በብሔር ቁርሾ ውስጥ ገብተው ‹‹የኢትዮጵያ ችግር የተናጠል ነውና የኦሮሞ፣ የትግሬ፣ የአማራ ችግር በተናጠል ካልተፈታ›› ማለት የጀመሩ አደገኛ የአሜሪካ ፖለቲከኞች ተፈጥረዋል፡፡

እዚህ አሜሪካ ውስጥ ኢትዮጵያዊም ሁን ሌላ አፍሪካዊ ቢሳካልህም ሆነ ብትወድቅ፣ ጥቁር አሜሪካዊ ተብለህ ነው በጅምላ የምትጠራው፡፡ ኢትዮጵያውያን ይህንን ኖረንበት እያየን፣ ነገር ግን በብሔር እየተቧደንን የአገራችንን አንድነትና ራሳችንን አሳልፈን መስጠታችን የሚጋብዝብን አደገኛ ጣልቃ ገብነትን ነው፡፡ እኛ አሜሪካ ውስጥ ከአፍሪካዊ ጥቁር ቆዳ ቀለማችን ውጪ የሚመለከተን የለም፡፡ እንኳን ወርዶ ብሔራችንን የሚጠራ ማግኘት ቀርቶ፣ አገራችን ኢትዮጵያ መሆኗንም የሚጠቅስ የለም፡፡ እዚህ ስንኖር ከየትኛው አፍሪካ አካባቢ እንደመጣን የሚያውቀን የለም፡፡ ነገር ግን እኛ በራሳችን ወርደንና ለሌሎች ራሳችንን በብሔር ከፋፍለን ማቅረባችን በጣም አሳዛኝ ነው፡፡ ሲጀመር ለአሜሪካ መጤ ነን፡፡ ልጆቻችን ከሌላው አሜሪካዊ እኩል ነፃነትና ፍትሕ እንዲያገኙ እየታገልን፣ በኢትዮጵያ ግን የአንዱ መብት ተከብሮ የሌላው መብት እንዲነፈግ መሯሯጥ ነው ሥራችን፡፡ ይህን ክፍተታችንን ደግሞ በደንብ የሚጠቀምበት ፖለቲከኛ እየመጣ ነው፡፡

ስቴት ዲፓርትመንት የኢትዮጵያን አንድነት የሚደግፉ የኮሙዩኒቲ አባላትን ጠርቶ አያናግርም፡፡ ዕርዳታም ሲሰጥ ራሱ ለኦሮሚያ፣ ለአፋር፣ ለአማራ፣ ለትግራይ፣ ወዘተ እየተባለ ነው፡፡ ኢትዮጵያን እንደ አንዲት ሉዓላዊ አገር ‹‹ኢትዮጵያ›› ብሎ ለመጥራት የማይፈልግ ኃይል እየተፈጠረ ነው፡፡ በብሔር ከፋፍሎ ማየትን የመረጡ አሉ፡፡ ይህ ደግሞ የውጭ ግንኙነት ጉዳይ ሳይሆን ከፋፋይነት ነው፡፡ የኢትዮጵያን አንድነት ወደ ጎን ብሎ በብሔር ገብቶ የሚፈተፍት ፖለቲከኛ ከጀርባው አደገኛ ነገር መያዙን መገመት አለብን፡፡ ኢትዮጵያን የበለጠ በመነቅነቅና በማርገፍገፍ ለማፈራረስ የሚሠራ ፖለቲከኛ እዚህ በአሜሪካ ተፈጥሯል፡፡ ይህ መንገድ ውድቀት እንደሚያመጣ ኢትዮጵያዊያን ነቅተን መከታተል አለብን፡፡

ሪፖርተር፡- ከሁለቱ የየትኛው አመለካከት ነው ጎልቶ እየወጣ ያለው ይላሉ?

ብርሃኑ (ዶ/ር)፡- አሁን የዝምታ ወቅት ላይ ነን፡፡ የውጭ ግንኙነት ፀባይ በአንድ ጊዜ ሳይሆን በረዥም ጊዜ ውጤቱ የሚታይ ነው፡፡ የውጭ ግንኙነት ሚዛን ወይም ፀባይ ለውጦች አዝጋሚ ከመሆናቸው የተነሳ፣ የመጨረሻው ደረጃ ላይ እስኪደርሱ ውጤታቸውን ለመለየት ሊያስቸግር ይችላል፡፡ ይህንን ዓይነት ሁኔታ አጥርተው መለየት የሚችሉት በሳይንሳዊ መንገድ የሚያጠኑት የዘርፉ ባለሙያዎች ይሆናሉ፡፡ አንዳንዴ ወድቀህ ራሱ ውድቀትህ ላይገባህ ይችላል፡፡ ስለዚህ ስለአወዳደቅህ ጥንቃቄ የተሞላበት ግምገማ ማድረግ ያስፈልግሃል፡፡ አሁን የምንሄድበት መንገድ የውድቀት መሆኑን ምልክቶች ይታያሉ፡፡ ከእነዚህ ምልክቶች ተነስተን አደጋውን ማመላከት ካልቻልን ውድቀታችን የከፋ ነው የሚሆነው፡፡

ኢትዮጵያዊያን እንደ ኢትዮጵያዊ መቆም አለብን፡፡ ከመልካችን ጀምሮ ለረዥም ዘመን አብረን የኖርን፣ የተጋባንና በደም የተጋመድን ሕዝቦች ነን፡፡ ማንም ከውጭ መጥቶ ለችግራችን አካሚ ሊሆን እንደማይችል ማወቅ አለብን፡፡ ሊቢያን፣ ሶሪያን፣ ኮትዲቯርን፣ ማሊንና ሄይቲን እንደ ምሳሌ ማየት እንችላለን፡፡ ማንኛውም ዓይነት የውጭ ጣልቃ ገብነትና መፍትሔ ለኢትዮጵያ አይሠራም፡፡ እንኳን ለእኛ ለራሳቸው ለአሜሪካኖችም የውጭ ጣልቃ ገብነት መፍትሔ አይሆንም፡፡ በግሬት ዲፕሬሽን ወቅት ወይም በሌላ ችግራቸው ጊዜ የራሳቸውን ችግር የፈቱት ራሳቸው ናቸው፡፡ ኢትዮጵያዊያን ከሰው ጥገኝነት ወጥተን በአንድነት መቆም አለብን፡፡ ኢትዮጵያ እንዴት ትዋቀር በሚለውም ሆነ በርዕዮተ ዓለም ላንስማማ እንችላለን፡፡ ‹‹ኢትዮጵያ ትኑር›› በሚለው ጉዳይ ግን መስማማት መቻል አለብን፡፡

ሪፖርተር፡- ኢትዮጵያ ከውጭ ተፅዕኖ እንድትላቀቅ የምግብ ዋስትናዋን ከማረጋገጥ ጎን ለጎን፣ እንደ ህዳሴ ግድብ ያሉ ግዙፍ ፕሮጀክቶችን ሠርታ ለዓለም ማሳየት እንዳለባት ብዙ ይባላል፡፡ እርስዎ ኢትዮጵያ ከሌሎች ነፃና በዓለም መድረክም ተደማጭ ለመሆን ምን ማድረግ አለባት ይላሉ?

ብርሃኑ (ዶ/ር)፡- ራስን መቻል ለአንድ አገር ቁልፍ ጉዳይ ነው፡፡ በምግብ ዋስትናን ማረጋገጥና ራስን መመገብ ለኢትዮጵያ እጅግ ወሳኝ ጉዳይ ነው፡፡ አሁን ያለውን የኢትዮጵያ መንግሥት ላንስማማበት እንችላለን፡፡ ነገር ግን ኢትዮጵያን ከቅኝ ተገዥነት ማላቀቅ የሚቻለው ራስን በራስ በመቻል መሆኑን ተገንዝቦ ስንዴ ለማልማት መነሳቱን መደገፍ አለብን፡፡ ኤክስፖርት ለማድረግ እንችላለን መባሉ የተጋነነ ቢሆን እንኳ፣ የምግብ ፍላጎታችንን በራሳችን ለመሸፈን ስንዴ ላይ መረባረቡ ጠቃሚ ነው፡፡ ኢትዮጵያ ቅኝ አልተገዛችም፡፡ ነገር ግን አሁንም ሆነ ወደፊት የእጅ አዙር ቅኝ ተገዥ እንዳትሆን መጀመሪያ ራሷን መቻል ነው ያለባት፡፡ አንዳንዴ በጂኦ ስትራቴጂካዊ ተፈላጊ አገር ልትሆን ትችላለህ፡፡ ነገር ግን ደግሞ የምዕራባዊያን ጥገኛ እስከሆንክ ነፃነትህ አይረጋገጥም፡፡ ግብፅን ብትመለከት ለምዕራባዊያኑ በጂኦ ፖለቲካው ጠቃሚ ብትሆንም፣ በዓመት ከሁለት ቢሊዮን ዶላር በላይ የእነሱን ድጎማ ትጠብቃለች፡፡ ቦታዋ እንጂ ራሷን ችላ አትቆምም፡፡ አሜሪካ ሌላ አማራጭ ካገኘች ግብፅ አደጋ ውስጥ ናት ማለት ነው፡፡

የዛሬ ስምንት ዓመታት በሕዝብ የተመረጠ መሪን ከሥልጣን አውርዶ በጄኔራል የመተካቱ የፖለቲካ ሴራ ለግብፆች የተሸረበው በአሜሪካኖች ነው፡፡ በጂኦ ፖለቲካው ጠቃሚ ነኝ ብቻ ማለት በቂ እንዳልሆነ ከእነሱ መማር አለብን፡፡ የራስህን ዕድልና ዕጣ ፈንታ በራስህ መወሰን የምትችልበት ቦታ ላይ ካልተገኘህ በስተቀር በጂኦ ፖለቲካው ጠቃሚ ነኝ ማለት ብቻ አይበቃም፡፡ በነገራችን ላይ አሜሪካ ውስጥ ሁሉም ነገር በ30 እና በ40 በመቶ ተወዷል፡፡ ኑሮ በአሜሪካ ከመቼውም ጊዜ በላይ ከብዷል፡፡ የትኛውም የአውሮፓ አገር ብትሄድ ተመሳሳይ ችግር ነው ያለው፡፡ በጀርመን ዘይት በራሽን ካርድ ነው የሚሰጠው፡፡ ምዕራባዊያኑ የዓለም ዋጋ መቃወስ ከተሰማቸው ኢትዮጵያ ፈተናዋ ከባድ መሆኑን ማሰብ ይቻላል፡፡ አሁን ካለው የዓለም የምግብ ሸቀጣ ሸቀጥና የኑሮ ውድነት አንፃር ኢትዮጵያ ችግሯን በራሷ ለማቃለል መፍትሔ መፈለግ መጀመሯ እንደ ቀላል መታየት የለበትም፡፡

ሌላው እንደ ህዳሴ ያሉ ግድቦችን መጨረስና በኢነርጂ ራስን መቻልም ትልቁ ከውጭ ጣልቃ ገብነት ራስን ነፃ ማውጫ መንገድ ነው፡፡ በኢነርጂ ራስን መቻል ሥራ ይፈጥራል፣ ቢዝነስ ያስፋፋል፣ ፋብሪካና ፈጠራ ያበረታታል፣ ትምህርት ይሻሻላል፣ በአጠቃላይ ዓይንህ ይበራል፡፡ ይህ ደግሞ ራሱን በራሱ የቻለ አገር ለመፍጠር ወሳኝ ይሆናል፡፡ ቅኝ ግዛት በአፍሪካ ባበቃ ማግሥት ወደ ሥልጣን የመጡ መሪዎች ይህን ነበር ሲሰብኩ የኖሩት፡፡ እንደ ቶማስ ሳንካራ ያሉ አመራሮች ራስን ስለመቻልና ከተረጂነት ስለመውጣት ነው የታገሉት፡፡ በዚህ የተነሳ ተገድለዋል፡፡ ራሱን የቻለ አገር የራሱን እንጂ የሌሎችን ፍላጎት አያራምድም፡፡ በዚህ የተነሳ ነው ብዙ የአፍሪካ መሪዎች ጠላት ተብለው የተፈረጁት፡፡ ምዕራባዊያኑ ፍላጎቴን ፈጽምልኝ ይሉሃል፡፡ ነገር ግን ለእኔ የሚጠቅመኝንና አንተን የሚያኖርህን ምረጥ ነው የሚሉህ እንጂ፣ በሰጥቶ መቀበል ላይ የተመሠረተ ግንኙነትን እንደ ኢትዮጵያ ካሉ ደሃ የአፍሪካ አገሮች ጋር መመሥረት አይፈልጉም፡፡

ሪፖርተር፡- በዲፕሎማሲው አማራጭ እንዳለ ማሳየት አይቻልም ወይ? ምዕራባዊያኑ ፊታቸውን ሲያዞሩ እንደ ሩሲያ፣ ቱርክ፣ ኢራን፣ ቻይና፣ ወዘተ የመሳሰሉ የግንኙነት አማራጮች እንዳሉ ማሳየትና የዲፕሎማሲ አማራጮችን ማስፋት አይገባም ወይ?

ብርሃኑ (ዶ/ር)፡- በሚገርም ሁኔታ ኢትዮጵያ በዲፕሎማሲ ታሪኳ ሁሉንም አቻችሎ መሄድን ስትተገብር ኖራለች፡፡ ይህ በጣም ጠቃሚ ነው፡፡ በውጭ ግንኙነት በኩል መንግሥት ቢለዋወጥም ኢትዮጵያ ወጥ የሆነ ሚዛናዊ አካሄድን ስትከተል ቆይታለች፡፡ በደርግ ዘመን ከተሠራው ስህተት አንዱ ወደ አንድ ወገን ያጋደለ ዲፕሎማሲ መከተል ነበር፡፡ በምሥራቁና በምዕራቡ ዓለም ያለው ፍጥጫ አንዳንዴ ግትርነት የበዛው ነው፡፡ ከሁለቱም ጋር መቀራረብ ለኢትዮጵያ በጣም ጠቃሚና አዋጭ ነው፡፡ ሲጫኑንም ቢሆን በማኩረፍና ፊትን በማዞር ሳይሆን፣ ምርጫ በማጣታችን ግንኙነታችን መላላቱን ማሳየት መቻላችን ዛሬ በጣም ጠቅሞናል፡፡ አንዳንዶቹ እንደ ጣሊያንና ኔዘርላንድስ ያሉ አገሮች ፊታቸውን የመለሱት የእኛን ግንኙነት የማሻሻል ፍላጎት በማየት ነው፡፡ በስድስት ወራት ውስጥ ነገሮች ወደ በጎ መንገድ ይዞራሉ ብዬ አላስብም ነበር፡፡ ከእኛ ጋር አንድ ደቂቃ ተቀምጦ ማውራት የማይፈልጉ ፖለቲከኞች ዛሬ በደንብ ለማዳመጥ ዝግጁ ሲሆኑ እያየን ነው፡፡ አሁን እየተከተልነው ያለነው መንገድም ምዕራቡን ያለዘበና የበሰለ ነው እላለሁ፡፡

ሪፖርተር፡- ዳያስፖራው በአገራዊ ምክክሩ እንዲሳተፍ የሚጠይቁና እንደ አንድ ባለድርሻ አካል ቢታይ የሚሉ ድምፆች ይሰማሉ፡፡ በእርግጥም በውጭ አገሮች ቢኖርም ዳያስፖራው ለአገሩ ሩቅ አይደለምና በአገራዊ ምክክሩ ምን ሚና ሊኖረው ይገባል ይላሉ?

ብርሃኑ (ዶ/ር)፡- ብዙው ዳያስፖራ ውጭ የሚኖረው የሌላ አገር ዜግነት ይዞ ነው፡፡ በኢትዮጵያ ሕግ ደግሞ ሁለት ዓይነት ዜግነት አንድ ሰው ሊኖረው አይችልምና ይህን መሰሉ ሕግ ካልተጣሰ በስተቀር፣ በአንዳንድ ጉዳዮች ላይ ዳያስፖራው ከዜጎች እኩል ተሳትፎ ይኑረው ማለት ያስቸግራል፡፡ በግሌ ዳያስፖራው ለኢትዮጵያ ይጠቅማል የሚለውን በጎ ሐሳብ ለምክክር ኮሚሽኑ በጽሑፍ ቢያቀርብና ልምዱን ቢያጋራ መጥፎ ነው ብዬ አላስብም፡፡ ዳያስፖራው ካለው የውጭ ልምድና ዕውቀት አንፃር ምን ዓይነት ሐሳብ አለው? ተብሎ የሚጠየቅበትና ሐሳቡን የሚያጋራበት ዕድል ቢመቻች ችግር የለውም ነው የምለው፡፡

ነገር ግን ዳያስፖራው በአብዛኛው በአገር ቤት ነዋሪ ባለመሆኑና ያለውን ነባራዊ ሁኔታ በተጨባጭ መረጃ ለመገንዘብ ስለሚቸግረው፣ በአገሩ ነዋሪ ከሆነው ዜጋ እኩል ይሳተፍ ማለት ትንሽ ከባድ ነው የሚሆነው፡፡ በአገር ቤት እኮ አዋቂ፣ የተማሩና ለአገራቸው ተቆርቋሪ የሆኑ ብዙ ሰዎች አሉ፡፡ ለእነሱ ሐሳባቸውን የሚያቀርቡበት ዕድል በሰፊው ቢኖር እላለሁ፡፡ ዳያስፖራውም ቢሆን በሁሉም ነገር ካልገባሁ ከማለት ይልቅ፣ በአገር ቤት ላሉ ዜጎች ዋናውን ድርሻ በመስጠት የተወሰኑ መንገዶች ድረስ ሐሳቡን ቢያካፍል ነው የምለው፡፡ በዚህ መሰል አገራዊ ምክክር ልምድ ያላቸው ሰዎች ይኖራሉና እነሱም የሚሳተፉበት ዕድል ይኖራል ብዬ እገምታለሁ፡፡

ሪፖርተር፡- ዳያስፖራው ከረዥም ጊዜ ጀምሮ በኢትዮጵያ ፖለቲካ ውስጥ ጠንካራ ተፅዕኖ ያለው በመሆኑ፣ ያለ ልዩነት እንዲሳተፍ መደረጉ የሚያዋጣ አይሆንምን?

ብርሃኑ (ዶ/ር)፡- መፈለግና ማድረግ የተለያዩ መሆናቸው አንዳንዴ መታወቅ አለበት፡፡ የዳያስፖራው የፖለቲካ ተሳትፎ እስከ የት መሆን አለበት የሚለው ላይ ብዙ አተያይ ነው ያለው፡፡ ዳያስፖራው ፖለቲካዊ ፍላጎትም ሆነ ተሳትፎ አለው ቢባልም፣ በሕጉ ግን በምርጫ እንኳ መሳተፍ አይችልም፡፡ መፈለግና ማድረግ ውስንነት እንዳላቸው መቀበል አለብን፡፡ የብሔራዊ ምክክር ኮሚሽኑ በሚያዘጋጃቸው ዕድሎች ዳያስፖራው ሐሳብ ቢሰጥ ምንም ችግር አይሆንም፡፡ ነገር ግን ውጭ አገር እየኖሩ በአገር ቤት እንዲህ ካልሆነ ማለት ትንሽ ያነጋግራል፡፡ አንዳንዱ ሰው እዚህ 40 እና 30 ዓመታት የኖረ ሊሆን ይችላል፡፡ ከአገር የራቁና ተጨባጩን የኢትዮጵያ የየዕለት ሁኔታ የማያውቁ ዳያስፖራዎችን ኢትዮጵያ ውስጥ ምን ቢደረግ ይሻላል ብሎ መጠየቁ አንዳንዴ ፍትሐዊ ላይሆንም ይችላል፡፡ እዚያው በኢትዮጵያ ምን መደረግ አለበት ለሚለው ጉዳይ ዕውቀቱና ልምዱ ያላቸው በርካታ አገር ወዳድ ዜጎች መኖራቸውን ማመን አለብን፡፡ እነዚህን ወገኖች አልፈን ውጭ አገር፣ ከአገር ርቆ የሚኖር ዳያስፖራን መፍትሔ አምጣ ማለቱ ላያዋጣ ይችላል፡፡

በእርግጥ በዳያስፖራ ያለው ኢትዮጵያዊ ስለትውልድ አገሩ ያስባል፡፡ ደግሞም በአገሩ ጉዳይ ያገባዋል፡፡ ሐሳቡ ቢሰማ ጥሩ ነው፡፡ ለትውልድ አገሩ ይጠቅማል የሚለውን ያጋራል፡፡ ተሳትፎው በአገር ቤት ካለው ተጨባጭ ሁኔታ ጋር አስታርቆና ሚዛን በጠበቀ መንገድ መሆን አለበት፡፡

ሪፖርተር፡- ድርድር ሊካሄድ እየተጠበቀ ነውና የሚሰምር ይመስልዎታል? የዳያስፖራውስ ሚና ምን መሆን አለበት?

ብርሃኑ (ዶ/ር)፡- ኢትዮጵያ ለረዥም ጊዜ በጦርነት መቀጠሏ አደጋ አለው፡፡ በመላው ዓለም የኮሮና ወረርሽኝ ያስከተለው ተፅዕኖ ገና አልተወገደም፡፡ በዚህ ላይ ደግሞ የዩክሬንና የሩሲያ ጦርነት ባስከተለው ተፅዕኖ የዓለም ምግብ አቅርቦትን ጨምሮ የዓለም ገበያ በእጅጉ ተናግቷል፡፡ ይህ ሁሉ ዓለም አቀፍ ቀውስ እያለ፣ ጦርነት መቀጠሉ ለኢትዮጵያ አደጋ ነበረው፡፡ መንግሥትም ይህንን በመረዳት ግጭቱ እንዲቆም የወሰደው ውሳኔ ተገቢ ነበር እላለሁ፡፡ በተቃራኒው ያሉም ይህንን ዕድል መጠቀም አለባቸው ነው የምለው፡፡

በግሌ ጦርነቱ ቆሞ ኢትዮጵያ ወደ ሰላም ብትገባ ሁሉም ይጠቀማል እላለሁ፡፡ በፊትም ቢሆን በጦርነት ችግርን መፍታት ያዋጣል ተብሎ ነው የተጀመረው፡፡ አሁን ደግሞ ከውድመት ውጪ በተግባር የተገኘ ነገር ባለመኖሩ ወደ ድርድር መገባቱ ተገቢ ነው እላለሁ፡፡ በሰላም ችግሩን መፍታት እንደሚቻልም ማሳየት መቻል አለብን፡፡ ዳያስፖራው ከጦርነቱ ጋር ተያይዞና አሁንም በድርድሩ ወቅት በተለይ በዲፕሎማሲ ውትወታ ትልቅ ተሳትፎ አለው፡፡ በተለይ ኢትዮጵያ ከባድ ጫና ባረፈባትና በተጨነቀችበት ወቅት የውጭ መንግሥታትን ትክክል አይደላችሁም ብሎ ለማሳመን ብዙ ጥሯል፡፡ በተሳሳተ መረጃና አረዳድ ነው የወሰናችሁት ብሎ ስለኢትዮጵያ ተጨባጭ ሁኔታ ለማስረዳት ዳያስፖራው ብዙ በሮችን አንኳኩቷል፡፡ ኢትዮጵያ ላይ ያረፈውን ጫና ለመቀነስ ከ20 ሺሕ በላይ ሰዎችን በመሰብሰብ ሠልፍ ከማካሄድ በተጨማሪ፣ ብዙ ፖሊሲ አውጪዎችን በመገናኘት ለማሳመን ብዙ የውትወታ ሥራ ዳያስፖራው ሲሠራ እንደነበር ይታወቃል፡፡ አሁንም ቢሆን ዳያስፖራው ለሰላሙ አጀንዳ ተመሳሳይ አቅም መጠቀም አለበት እላለሁ፡፡ የሻከሩ ነገሮች እንዲለሰልሱ በማድረግና በተቃራኒው ከተሠለፉ ወገኖች ጋር ጭምር ነገሮችን ለማለዘብ መሥራት አለበት፡፡ በተለይ አንድነታችንና አሰባሳቢ የሆነውን ኢትዮጵያዊነታችንን የሚሸረሽረውን ብሔር ተኮር አስተሳሰብ መቅረፍ ይኖርብናል፡፡ እዚህ በብሔር መቧደን ባህል እየሆነ መጥቷል፡፡ አንዱ ሌላውን በማግለል የራሱን ቡድን ፈጥሮ ነው የሚንቀሳቀሰው፡፡

ኢትዮጵያ ውስጥ መሆን የለበትም የምንለውን ዘረኝነት እኛ እዚህ እየሆንነው ነው፡፡ የተለያየ ዘር ቢኖረንም በኢትዮጵያዊነታችን ግን አንድ ነን፡፡ ኦሮሞ፣ አማራ፣ ትግሬ፣ ወዘተ አንድ ጠረጴዛ ላይ መቀመጥ ካልቻልን እንዴት ወደ ሰላም መምጣት እንችላለን? የዳያስፖራው መሰባሰብና አንድነት ለኢትዮጵያም ምሳሌ ነው የሚሆነው፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ ከ100 ሚሊዮን በላይ ሕዝብ አለ፡፡ እዚህ አሜሪካ 500 ሺሕ ኢትዮጵያዊ ነው ያለው፡፡ 500 ሺሕ ሰዎችን አንድ ማድረግ ሳትችል ከ100 ሚሊዮን በላይ ኢትዮጵያዊያንን አንድ ለማድረግ እንዴት መከራከር ትችላለህ? እኛ አለመቀራረባችን ከምንፈልገው አንድነት ጋር ይቃረናል፡፡ የእኛ ቁጭ ብሎ ማውራቱ ለሰላም፣ ለመተማመን፣ ብሎም ለድርድሩና ለዕርቁ ግብዓት ነው የሚሆነው፡፡

ሪፖርተር፡- የታላቁ ህዳሴ ግድብ ሁለተኛው ተርባይን ኃይል አመንጭቶ ሦስተኛ ዙር የውኃ ሙሌት ተካሂዷል፡፡ ግድቡ እዚህ እንዲደርስ በገንዘብም ሆነ በዲፕሎማሲ ዘመቻው ዳያስፖራው የተጫወተው ሚና ቀላል አይደለምና ለዚህ ስኬት በመብቃቱ እርስዎ በግል ምን ተሰማዎት? በዳያስፖራው ያለው ስሜትስ ምን ይመስላል?

ብርሃኑ (ዶ/ር)፡- ህዳሴ ግድብ በአንድነት መቆማችንን ያሳየንበት ፕሮጀክት ነው፡፡ በችግር ጊዜ በጋራ ቆመን ምን መሥራት እንደምንችል ያሳየንበት ግድብ ነው፡፡ ፋይናንስ ከመከልከል በተጨማሪ፣ እናንተ ይህንን ዓይነት ግዙፍ ፕሮጀክት መሥራት አትችሉምና በትንንሽ ሥራዎች ላይ ብትተጉ ብለው ሲንቁንና ድጋፍ ሲነፍጉን በጋራ ተነሳን፡፡ እንዴት እንዲህ እንባላለን ብለን በቦንድም ሆነ በብዙ መንገዶች ዳያስፖራው ሲደግፍ ነው የቆየው፡፡ ‹‹ማይ ገርድ››፣ ‹‹አይዞን››፣ ሌላም የገቢ ማሰባሰቢያ ሥራዎች ላይ ዳያስፖራው ተሳትፎ ነበረው፡፡ አሁንም ቢሆን ዳያስፖራው በግድቡ ላይ ያለው አቋም የማይነቀነቅ ነው፡፡ እዚህ ደረጃ መድረሱ ብዙ ሰዎችን ማስደሰቱን ታዝቤያለሁ፡፡ ኃይል ማመንጨት ጀመረ ሲባልና ውኃው ሞልቶ መፍሰሱ ሲታይ ዳያስፖራው ያደረገው ድጋፍ ፍሬ ማፍራት መጀመሩ በደንብ እየተሰማው ነው፡፡ ግድቡ ውኃ መሞላቱና ኃይል ማመንጨቱ ብቻ ሳይሆን፣ ከአሁን በኋላ ወደኋላ መመለስ የማይቻልበት ደረጃ ላይ መድረሱ ቀላል ትርጉም የለውም፡፡ ግድቡ ለኢትዮጵያ በቀጣናው ያላትን ተፅዕኖ ስለሚጨምር፣ ሰላምና መረጋጋትን ለማስፈን የምትችልበት ደረጃ ላይ መድረሷን ተስፋ የሚሰጥም ነው፡፡ ይህ ስኬት ለዳያስፖራው ዕፎይታ ነው፡፡ ከአሁን ቀደም ግድቡን እናስቆመዋለን የሚሉ ኃይሎች በተናገሩ ቁጥር ዳያስፖራው በስሜት ተቆጥቶ ሲቃወም ነበር፡፡ የአሜሪካ መሪን ጨምሮ፣ ግብፆቹና ሱዳኖቹ የሚሸርቡትን ጫና በየጊዜው ለመመከት ዳያስፖራው የተቆጣ ነብር ሆኖ ሲታገል ቆይቷል፡፡ አሁን ግድቡ ወደኋላ የማይመለስበት ደረጃ ደረሰ መባሉ ለዳያስፖራው ትልቅ ደስታ ነው የሆነው፡፡ 

ተዛማጅ ፅሁፎች

- Advertisment -

ትኩስ ፅሁፎች ለማግኘት

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

የኦሮሞን ሕዝብ ታሪክ አልባ በማድረግ ታሪክ አይሠራም

በኢተፋ ቀጀላ​​  ከዛሬ ሃምሳ ዓመት ወዲህ ከተፈጠሩት የኦሮሞ ድርጅቶች መካከል ከኢጭአት በስተቀር፣...

የፓርላማ አባላት ስለሰላም ስምምነቱ አፈጻጸም ግልጽ መረጃ የለንም አሉ

‹‹ሕወሓትን ለፍረጃ አብቅተውት የነበሩ ጉዳዮች በአብዛኛው መልክ ይዘዋል›› ሬድዋን...

ጉራጌን በክላስተር ለመጨፍለቅ የሚደረገውን ጥረት እንደሚቃወም ጎጎት ፓርቲ አስታወቀ

ለጉራጌ ሕዝብ ሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶች መከበር እንደሚታገል የሚናገረው አዲሱ...

‹‹ኢኮኖሚው ላይ የሚታዩ ውጫዊ ጫናዎችን ለመቀልበስ የፖሊሲ ሪፎርሞች ያስፈልጋሉ›› ዓለም ባንክ

በዓለም ደረጃ ከተፈጠረው የኢኮኖሚ አለመረጋጋት ጋር በተገናኘ፣ በኢትዮጵያ ውጫዊ...