Sunday, March 26, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
እኔ የምለዉበኃላፊነት ከሚያስጠይቁ አስነዋሪ ድርጊቶች እንታቀብ

በኃላፊነት ከሚያስጠይቁ አስነዋሪ ድርጊቶች እንታቀብ

ቀን:

በመርሐ ፅድቅ መኮንን ዓባይነህ

ሸኖ፣ አሌልቱ፣ በኬ፣ ሰንዳፋና ለገጣፎ የመሳሰሉ አነስተኛና መካከለኛ የኦሮሚያ ክልል ከተሞች የግልም ሆነ የሕዝብ ማመላለሻ አሽከርካሪዎችና ተሽከርካሪዎች ከወልድያ፣ ከደሴም ሆነ ከሰቆጣ በሸዋ ሮቢት፣ በደብረ ሲናና በደብረ ብርሃን በኩል አድርገው ወደ አገሪቱ ርዕሰ ከተማ አዲስ አበባ መናኸሪያዎች ለመግባት በየዕለቱ የሚንደረደሩባቸው የኦሮሚያ ክልል ከተሞች ናቸው፡፡ ሆኖም ይህ የየብስ ትራንስፖርት በኦሮሚያ ፀጥታ ኃይሎች ያላግባብ መስተጓጎል፣ አልፎ አልፎም ጭራሹን መቋረጥ ከጀመረ ትንሽ ሰነባብቷል፡፡

ለቁጥር የበዙ የዚያን መስመር መንገደኞች በተለያዩ ጊዜያት ካነጋገሩ የአገር ውስጥና የውጭ መገናኛ ብዙኃን በግርድፉም ቢሆን ለመረዳት እንደተቻለው፣ እየሆነ ያለውና የሚሰማው አስነዋሪ ነገር ሁሉ ፍፁም ለጀሮ ይቀፋል፡፡

ሕዝባዊ አገልግሎት ይሰጣሉ ተብለው ከፍተኛ እምነት የተጣለባቸው የፀጥታ ኃይሎች ከፍ ሲል የተጠቀሱትን ከተሞች መነሻ አድርገው በተቋቋሙት የፍተሻ ኬላዎች ተሽከርካሪዎችን በኃይል እያስቆሙ ያሳፈሯቸውን ሰላማዊ ተጓዦች በፍተሻ ስም ያስወርዳሉ፣ የነዋሪነት መታወቂያዎቻቸውን እየጠየቁ ይሰበስባሉ፣ የአማራ ብሔር ተወላጆችን ለይተው ያለ ኃፍረትና ያለ ይሉኝታ ወደ መጡበት እንዲመለሱ ያስገድዳሉ፡፡ ይልቁንም አሽከርካሪዎችን ለምን ጫናችኋቸው በማለት ያሸማቅቃሉ፣ ያንገላታሉ፡፡

በሒደቱ ተመላላሽ ሕሙማን ሐኪም በያዘላቸው ቀጠሮ መሠረት ወደ ሆስፒታል በወቅቱ እንዳይደርሱ በመከልከላቸው የቁም ሞት ተፈርዶባቸዋል፡፡ የውጭ በረራ የተስተጓጎለባቸው ወገኖችም እንዳሉ ተወስቷል፡፡

ከመካከላቸው ሰብዓዊ ክብርን በሚጋፋ አኳኋን ብሔራዊ ማንነታቸው እየተጠቀሰ ያላግባብ የሚዘለፉና በድብደባ ምክንያት አካላዊ ጥቃት የሚደርስባቸው እናቶችና ሕፃናት እንደሚገኙባቸውም፣ እሮሮዎች በስፋት ተስተጋብተዋል፣ አሁንም ድረስ እየተስተጋቡ ነው፡፡

እዚህ ላይ ታዲያ ይበልጥ የሚገርመው፣ እንደ ኮሶ የሚያንገሸግሸውና ክፉኛ የሚያመው ይህ ሁሉ በደል ከሳምንታት ለበለጠ ጊዜ በገሃድና በማናለብኝነት በወገኖቻችን ላይ ሲፈጸም የአውራ ጎዳናው ባለቤት ነኝ ከሚለው ከፌዴራሉ መንግሥት አንስቶ ጉዳዩ በቀጥታ ከሚመለከታቸው ክልሎች በኩል እየተሰጠ ያለው ምላሽ በጣም ቀዝቃዛና ታዲያ ምን ይጠበስ? የሚል ዓይነት ሆኖ መታዘባችን ነው፡፡

ለምሳሌ የትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ ሚኒስቴር በጉዳዩ የሚያገባው እንደሌለ ሁሉ፣ እንዲህ ያለውን ከረር ያለ ስሞታ ቢያዳምጥም ጀሮ ዳባ ልበስ እንዳለ ነው፡፡

የፌዴራል መንግሥት ኮሙዩኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስትር ደኤታ ነኝ ያሉ አንዲት ሴት ደግሞ ስለጉዳዩ የበኩላቸውን ማብራሪያ እንዲሰጡ ያን ሰሞን በአንድ የውጭ ሚዲያ ተጠይቀው ነበር፡፡ የፈረደባቸው ኦነግ ሸኔና ሕወሓት በድኅረ ወረራ ያሰማሯቸው አሸባሪዎች በተጭበረበረ የመታወቂያ ወረቀት ወደ መዲናዋ ሰርገው ወይም ተሹለክልከው እንዳይገቡ ለመከላከል በታቀደ ዕርምጃ ጥብቅ ፍተሻ እየተካሄደ እንደሆነ እናውቃለን ሲሉ፣ ኃላፊነት የጎደለው የግብር ይውጣ ምላሽ በመስጠት አድራጎቱን ከመኮነን ይልቅ ያልተገባ ኦፊሴላዊ ሽፋን ሲያላብሱት ተደምጠዋል፡፡

የኦሮሚያ ክልላዊ መንግሥት የሲቪልና የፀጥታ ባለሥልጣናትማ ስለጉዳዩ አንዳች ዕውቀት እንደሌላቸው ነበር ደጋግመው የነገሩን፡፡ ለነገሩ ውሉ ጨርሶ ከጠፋባቸው ከእኚያ ሴቲዮ እነሱ ሳይሻሉ አልቀሩም፡፡

ተሳፋሪዎቹ የሚነሱበት የአማራ ክልልም ቢሆን አፍጥጦ ለወጣውና አሁንም ድረስ ሃይ ባይ ሳያገኝ ተጠናክሮ ለቀጠለው ለዚህ ችግር መፍትሔውን በዋነኝነት እየጠበቀ ያለው፣ በበደሉ አድራሽነት ከሚወቀሰው ከኦሮሚያ ክልል የሥራ ኃላፊዎች በመሆኑ ያው እንደተለመደው ነግሮችን አድበስብሶ ከማለፍ ባለፈ ውጤት ይኖረዋል ብሎ ማለፍ እራስን ማሞኘት ነው፡፡

ይህ የዘፈቀደ ዕርምጃ ከገዥው የብልፅግና ፓርቲ የኦሮሚያ ክንፍ አኳያ ሲታይ፣ ወደ አዲስ አበባ ድርሽ እንዳትል  ብንለው አማራ ምን ሊያመጣ ይችላል? እየተባለ ያለ ነው የሚመስለው፡፡

በእርግጥ ለጊዜው ምንም ያመጣው የለም ማለት ይቻል ይሆናል፡፡ ይህ ማለት ግን ለወደፊቱ ምንም የሚያስከትለው መዘዝ አይኖርም ማለት እንዳልሆነ ከወዲሁ መታወቅ ይኖርበታል፡፡

እንደ እኔ ባሉት ጦማርያን አማካይነት ለአካዳሚያዊ ፍጆታ ብቻ የሚያገለግል በሚመስል መልኩ አሸብርቆ በዋቢነት ከመጠቀስ ባለፈ፣ ከወጣበት ጊዜ ጀምሮ ገቢራዊ ለመደረግ ያልታደለው የኢፌዴሪ ሕገ መንግሥት በአንቀጽ 32 ንዑስ አንቀጽ (1) ድንጋጌ ሥር አይደለም የዜጎችን፣ በአገሪቱ የግዛት ወሰን በሕጋዊ መንገድ የሚኖሩ ባዕዳንን የእንቅስቃሴ መብትና የመኖሪያ ሥፍራ ምርጫ ነፃነት ያከብራል፣ ለዚህም በሰነድ የተረጋገጠ ዋስትና ይሰጣል፡፡

ዳሩ ይህ ፍሬቢስና አማላይ ቃለ ሕገ መንግሥት ብቻውን ምን ይረባናል? የተጻፈ ሕግ በስማችን ስለተጻፈ ብቻ ሕይወት አይኖረውም፡፡ አበው ‹‹አውቆ የተኛን ቢቀሰቅሱት አይሰማም›› የሚሉት ለዚህ ነው፡፡

ውድ ወገኖቼ፣ ቁልፉ የአገራችን ችግር እኮ ለተራዘመ ጊዜ ተንሰራፍቶ የቆየው የተጠያቂነት አለመኖር ባህል ወይም ክፉ ልማ ነው፡፡

እስካሁን ድረስ እንግዲህ ከእነዚህ ሕዝብን ባንገላቱ የፀጥታ ኃይሎች መካከል አንዳቸውስ እንኳ በሕግ ተይዞ ሥልጣንን አለአግባብ በመገልገል ወንጀል የተጠየቀ ስለመሆኑ ያወቅነው ነገር የለም፡፡

ለማናቸውም ፈጣሪ በኪነ ጥበቡ ቶሎ ወደ ቀልባችን እንድንመለስ ካልረዳን በስተቀር፣ የጀመርነው እርስ በርስ የመገፋፋት መጥፎ ልምምድ ፍፁም አደገኛና ዳፋውም ለትውልድ የሚተርፍ በመሆኑ አስተውለን መራመድ ይኖርብናል፡፡ ዕድሉ ስለተመቻቸልን ብቻ ዛሬ በገፍ የምንወስደው ግዙፍ የመከራ ብድር ለነገ የምንከፍለውን ዕዳ እንዳያከብደው መጠንቀቅ አለብን፡፡

አስፍተን ካየነው ተረኝነት የኑሮ ሕግ ነው፡፡ የዛሬ አጥቂ የነገ ተጠቂ የመሆን ዕድል አለው፡፡ ስለሆነም ይህንኑ እውነታ ከወዲሁ ተረድተን በኃላፊነት ከሚያስጠይቁ አስነዋሪ ድርጊቶች ብንታቀብ እላለሁ፡፡

ከአዘጋጁ፡- ጸሐፊው በሕግ ሙያ የመጀመርያ ዲግሪያቸውን በ1981 ዓ.ም. ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የቀድሞው የሕግ ፋኩልቲ ያገኙ ሲሆን፣  በሐምሌ ወር 2001 ዓ.ም. ደግሞ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲና በተመድ የሰላም ዩኒቨርሲቲ ጣምራ ትብብር ይካሄድ ከነበረው የአፍሪካ ፕሮግራም በሰላምና በደኅንነት ጥናት የማስተርስ ዲግሪያቸውን ሠርተዋል፡፡ በአሁኑ ወቅት በአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት በቢሮ ኃላፊ ማዕረግ የርዕሰ መስተዳድሩ ዋና የሕግ አማካሪ ሆነው በማገልገል ላይ ናቸው፡፡ ጽሑፉ የእሳቸውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እየገለጽን፣ በኢሜይል አድራሻቸው clickmerha1@gmail.com ማግኘት ይቻላል፡፡ 

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የ ሳ ም ን ቱ ገ ጠ መ ኝ

ይኼ ጊዜ እንዴት ይነጉዳል እባካችሁ? አምስት ዓመታት አምስት ቀናት...

የኑሮ ውድነት ፖለቲካዊ ገጽታዎች በኢትዮጵያ

እ.ኤ.አ. ሐምሌ 9 ቀን 2022 ዓ.ም. የስሪላንካ መዲና ኮሎምቦ...

‹‹የምድራችን ጀግና›› ሽኝት

«የአፍሪካ አገሮችን አስተባብረው የተሟገቱ ተሟግተውም ያሸነፉ፣ በመጨረሻም አፍሪካ የራስዋን...