የሰላም ድርድሩ በመጪዎቹ ጥቂት ሳምንታት እንዲጀመር እንደሚፈልግ አስታውቋል
የፌዴራል መንግሥቱ የሰላም አማራጭ ኮሚቴ ባቀረባቸው ሦስት የሰላም ዕቅዶች ውስጥ፣ ከሕወሓት ጋር ጠለቅ ያለ የፖለቲካ ውይይት በማድረግ ቀሪ ጉዳዮች በብሔራዊ ምክክሩ በኩል እንዲፈቱ እንደሚፈልግ አስታወቀ፡፡
የጠቅላይ ሚኒስተር ጽሕፈት ቤት ፕሬስ ሴክሬታሪያት ኃላፊ ቢልለኔ ሥዩም ሐሙስ ሰኔ 12 ቀን 2014 ዓ.ም. ለጋዜጠኞች በሰጡት መግለጫ፣ ወደ ተኩስ አቁም ስምምነት ሊያደርስ የሚችል የሰላም ድርድር በሳምንታት ውስጥ እንዲጀመር የፌዴራል መንግሥቱ ፍላጎት እንዳለው አስታውቀዋል፡፡
በዚህ ሒደት ውስጥ መንግሥት በመጪዎቹ ሳምንታት በሁለቱ ተደራዳሪ አካላት ጠለቅ ያለ የፖለቲካ ውይይት ተደርጎ፣ ቀሪ አጀንዳዎች በብሔራዊ ምክክር በኩል እንዲታዩ የሚል አቋም እንዳለው ቢልለኔ አስረድተዋል፡፡
የፌዴራል መንግሥት ከሕወሓት ጋር በሚያደርገው የሰላም ድርድር ሒደት ውስጥ፣ መሠረተ ልማቶችን ወደ ሥራ መመለስና ሰላማዊ ድርድር ማድረግ የተለያዩ ጉዳዮች በመሆናቸው፣ አገልገሎቶቹን ወደ ሥራ ለማስመለስ ምንም ዓይነት ቅደመ ሁኔታ መቅረብ የለበትም ብለዋል፡፡ ይሁን እንጂ በአካባቢው ተንቀሳቅሶ ለመሥራት አስቻይ የፀጥታና የአስተዳደራዊ ሁኔታዎች መስተካከል እንደሚኖርባቸው አክለዋል፡፡
በትግራይ የሚኖሩ ዜጎች የሕወሓት የፖለቲካ ማስፈጸሚያ እስረኞች መሆን የለባቸውም ያሉት ኃላፊዋ፣ መንግሥት ውይይቱ ያለ ምንም ቅድመ ሁኔታ እንዲጀመር ፅኑ ፍላጎት እንዳለው አስረድተዋል፡፡
ሕወሓት የትግራይ ወጣቶችን በኃይል በመመልመል፣ በሰብዓዊ ዕርዳታና በሌሎች መንገዶች የጦር መሣሪያዎችን እንደሚያስገባ ተናግረው፣ በሕገወጥ መንገድ የውጭ ምንዛሪና የኢትዮጵያን ገንዘብ በማዘዋወር ሌሎች ግጭቶችን እንዳያባብስ፣ የሰብዓዊ ዕርዳታ አቅርቦትን ከዓላማው ውጪ ለጦርነት ተዋጊዎች እያቀረበ ቢሆንም፣ የፌዴራል መንግሥት አሁንም ሰላማዊ መንገዶችን እየመረጠ መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡
የመሠረተ ልማት አገልግሎቶችን እንደገና የማስጀመር ጥያቄ በተደጋጋሚ የሚቀርብበት ሁኔታ፣ አገልግሎቱን ከአንድ ማዕከል፣ በአንድ ማብሪያና ማጥፊያ መመለስ እንደሚቻል አድርገው የሚያራምዱት አቋም የተሳሳተና አደገኛ አካሄድ ነው ብለዋል፡፡
በመሆኑም የፌዴራል መንግሥት በትግራይ ክልል የሚገኙ አገልግሎቶችን እንደገና ወደ ሥራ ለማስገባት፣ አስተዳደራዊና የደኅንነት ሥራዎች ሲስተካከሉና ማረጋገጫ ሲኖር እንደሆነ ተናግረዋል፡፡
አክለውም የሕወሓት ኃይሎች ለኢትዮጵያም ሆነ ለትግራይ ሕዝብ የሚጨነቁ ከሆነ፣ ለሰላም ድርድር የሚያቀርቡትን ምክንያት በመተው ለድርድሩ መቀመጥ አለባቸው ብለዋል፡፡
በአፍሪካ ኅብረት የተጀመረውን የሰላም ድርድር የፌዴራል መንግሥት በየትኛውም ቦታ በአጠረ ጊዜ ሊጀመር ፍላጎት እንዳለው በመግለጽ፣ የትግራይ ሕዝብን የሰላም ሁኔታ ለመመለስ፣ ሰላም ከምንም ዓይነት ቅድመ ሁኔታ ጋር መቅረብ የለበትም ብለዋል፡፡
ሕወሓት አሁንም የጦርነት ነጋሪት ጉሰማ ላይ መሆኑንና የድርድሩ ቅድመ ሁኔታ በማስቀመጥ፣ በድርድሩ ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ እያሳደረ እንደሆነ አስረድተዋል፡፡
የሕወሓት ሥራ አስፈጻሚ አባል አቶ ጌታቸው ረዳ ነሐሴ 12 ቀን 2014 ዓ.ም. ለትግራይ ክልል ሚዲያዎች በሰጡት መግለጫ፣ የአገር መከላከያ ሠራዊት በትግራይ ደደቢት አቅጣጫ፣ በትግራይ ታጣቂዎች ላይ ድብደባ ማድረጉንና ይህም የፌዴራል መንግሥቱ ለሰላም ዝግጁ አለመሆኑን ማሳያ ነው ብለዋል፡፡
‹‹የትግራይ ሕዝብና መንግሥት ለሰላም ያላቸው አቋም የማይናወጥ ቢሆንም፣ ሕዝባችንና መሬታችን ተወሮ በተደጋጋሚ እየተቀጠቀጠ የሚቀጥልበት ዕድል የለም፤›› ብለዋል፡፡
በሌላ በኩል የኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትሕ (ኢዜማ) ነሐሴ 13 ቀን 2014 ዓ.ም. ባወጣው መግለጫ፣ የፖለቲካ አለመግባባት በሰላማዊ መንገድ መፈታት አለበት ብሏል፡፡
ፓርቲው በመግለጫው ሕወሓት የሰላም ድርድሩን አማራጭ እየገፋ ራሱን ወደ ጦርነት እያዘጋጀ እንደሆነ ገልጾ፣ ‹‹በተለመደው አውዳሚ መንገድ የጥፋት ነጋሪት እየጎሰመ መሆኑን በአደባባይ እያወጀ ነው፤›› ሲል ወቀሳ ሰንዝሯል፡፡
መንግሥት ለሰላም እያሳየ ያለውን ጥረት አጠንክሮ መቀጠሉ የሚበረታታ መሆኑን፣ በአካባቢው ያለውን ማኅበረሰብ በድጋሚ ለከፋ ሰብዓዊ ጉዳትና መፈናቀል እንዳይዳረግ ወቅታዊ ሁኔታውን ያገናዘበ ጥንቃቄና አስፈላጊ ዝግጅት እንዲያደርግ ማሳሰቢያ ሰጥቷል፡፡