Sunday, March 26, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ማኅበራዊመመርያ የጣሱ የግል ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት በወንጀልና በፍትሐ ብሔር ተጠያቂ ሊደረጉ ነው

መመርያ የጣሱ የግል ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት በወንጀልና በፍትሐ ብሔር ተጠያቂ ሊደረጉ ነው

ቀን:

በተጠናቀቀው የበጀት ዓመት የመመርያ ጥሰት ፈጽመው እርምት እንዲያደርጉ ውሳኔ ተላልፎባቸው ተግባራዊ ባላደረጉ የግል ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ላይ፣ የትምህርትና ሥልጠና ባለሥልጣን ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በመቀናጀት በወንጀልና በፍትሐ ብሔር ተጠያቂ እንደሚደረጉ አስታወቀ፡፡ 

በ2014 ዓ.ም. በአዲስ አበባና በክልል ከተሞች በተካሄደው ድንገተኛ ፍተሻ የሥነ ሥርዓት መመርያ ጥሰት ፈጽመው የተገኙ የግል የከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ላይ የማስተካከያ ዕርምጃና ማጋለጥ ሲደረግ መቆየቱ የተገለጸ ሲሆን፣ ይህንን ዕርምጃ ከማስቀጠል ባሻገር ውሳኔውን ተግባራዊ ያላደረጉ ተቋማትን በወንጀልና በፍትሐ ብሔር ተጠያቂ ለማድረግ እንቅስቃሴዎች መጀመራቸውን የትምህርና ሥልጠና ባለሥልጣን የኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክተር አቶ ታረቀኝ ገረሱ ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡

ባልተፈቀደ ካምፓስና ቦታ ማስተማር፣ ሲኦሲ ሌላ ጊዜ ታሟላላችሁ በሚል መሥፈርት ያላሟሉ ተመዝጋቢዎችን መቀበል፣ የዕውቅና ፈቃድ ባገኙበት ሕንፃ አለመገኘት፣ የዕውቅና ፈቃድ ለማግኘት ብቻ ሕንፃ በመከራየት ለሕገወጥ ድርጊት መገልገልና የመሳሰሉትን የመመርያ ጥሰቶች በፈጸሙ 373 የግል የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ካምፓሶች ላይ ባለሥልጣኑ በ2014 ዓ.ም. ዕርምጃ መውሰዱን ማስታወቁ ይታወሳል።

ከዚህ ቀደም በተላለፈባቸው ውሳኔ መሠረት ተማሪዎችን እንዲበትኑ፣ ካምፓሶቻቸውን እንዲዘጉ፣ እንዲሁም ሙሉ በሙሉ ተቋማቸውን እንዲዘጉ ትዕዛዝ የተላለፈባቸው የግል ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት፣ ለዕርምጃው ተገዥ መሆናቸውን ባለሥልጣኑ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በመሆን ክትትል ማድረግ መጀመሩ ተጠቅሷል፡፡

ባለሥልጣኑ የመመርያ ጥሰት ፈጽመው ሲንቀሳቀሱ የቆዩ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማትን ከዚህ በላይ የሚታገስበት ደረጃ ባለመኖሩ፣ በወንጀልና በፍትሐ ብሔር ተጠያቂ ለማድረግ አተኩሮ እንደሚሠራ የገለጹት አቶ ታረቀኝ፣ እስካሁን ድረስ ተቋማቱን ተጠያቂ ማድረግ አለመቻሉ ተወቃሽ ሲያደርግ መቆየቱን አስታውቀዋል፡፡

ከዚህ ቀደም ለሪፖርት ግብዓት በሚል በተቋማት ላይ በሚወሰዱ ዕርምጃዎች ላይ የተጠናከረ ክትትል ባለመደረጉ የግል ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ቸልተኛ እንዲሆኑ ከማድረጉም በላይ ችግሮች እንዲከማቹ ማድረጉን፣ በአሁኑ ወቅት የተላለፉ ዕርምጃዎች በትክክል ተፈጸሚ መሆናቸውን ማረጋገጥ የተቋሙ አገልግሎቱን የመምራት አመላካች ጉዳይ ሆኖ መገኘቱን የኮሙዩኒኬሽን ዳይሬክተሩ አስረድተዋል፡፡

የትምህርትና ሥልጠና ባለሥልጣን፣ በተለያዩ አገሪቱ ክፍሎች ከሚገኙ የከተማ ኮሙዩኒኬሽን ቢሮዎች፣ ከፍትሕ ቢሮዎች፣ ከትምህርት፣ ከቴክኒክና ሙያ ቢሮዎች፣ እንዲሁም  ከከተማ ከንቲባዎች ጋር ቅንጅት በመፍጠር ከዚህ ቀደም በትምህርት ተቋማቱ ላይ የተላለፉት የመመርያ ጥሰት ውሳኔዎች ተፈፃሚ መሆናቸውን በደብዳቤ የማሳወቅና የመቆጣጠር ሥራ ይከናወናል ተብሏል።

በአሁኑ ወቅት በአገሪቱ የተለያዩ ከተሞች የሚገኙ ጉዳዩ የሚመለከታቸውን የመንግሥት አካላት መረጃ የማደራጀት ሥራ እየተከናወነ መሆኑን ያስረዱት አቶ ታረቀኝ፣ በቀጣይ ዕርምጃ የተወሰደባቸው ተቋማት ካምፓሶችን በአካል ሄዶ ማረጋገጥና ቁጥጥር ይደረጋል ብለዋል።

ከባለሥልጣኑ ባገኙት መረጃ ተጠቅመው ሕገወጥ ተቋማትን፣ ካምፓሶችንና ቅርንጫፎቻቸውን በማሳሸግ የበኩላቸውን ኃላፊነት እየተወጡ ያሉ የክልል ከተሞች ውሳኔውን ለባለሥልጣኑ በማሳወቅ ላይ እንደሚገኙ የተመላከተ ሲሆን፣ ይህም ተግባር አገርንና ሕዝብን ከሕገወጥ አካላት ለመከላከልና የትምህርትና ሥልጠና ጥራትን ለማስጠበቅ ከፍተኛ አስተዋጽኦ የሚያበረክት መሆኑን ባለሥልጣኑ አስታውቋል፡፡

በተያያዘም ባለሥልጣኑ ድንገተኛ ግምገማ ካደረገ ወዲህ ለመጀመሪያ ጊዜ ከግል ከፍተኛ የትምህርት ተቋም የባለድርሻ አካላት ጋር በተጠናቀቀው ሳምንት የውይይት መድረክ አዘጋጅቶ ነበር፡፡

በውይይቱም በዘርፉ የሚታዩትን ችግሮች ባለበት ለማስቆም የግል የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት በማኅበራቸው መደራጀት እንደሚገባቸው፣ በዚህም ተደማጭነታቸው እንደሚጨምርና ሕገወጥነቱንም ማስቆም እንደሚቻል የትምህርትና ሥልጠና ባለሥልጣን ዋና ዳይሬክተር አንዱዓለም አድማሴ (ዶ/ር) አሳስበዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የመንግሥት ይዞታዎችን ለማልማት የተመረጡ ዲዛይኖች ለዕይታ ቀረቡ

በዳንኤል ንጉሴ የፌዴራል መሬት ባንክና ልማት ኮርፖሬሽን ካለፈው ዓመት አንስቶ...

ተፈናቃዮች በደብረ ብርሃን ወይንሸት መጠለያ

በደብረብርሃን ከሚገኙ ስድስት የተፈናቃይ መጠለያ ካምፖች ወይንሸት መጠለያ አንዱ...