Tuesday, March 28, 2023
- Advertisment -
- Advertisment -

የሕዝባችን አብሮነት በአልፎ ሂያጅ አጀንዳዎች አይጠለፍ!

ሰሞኑን ደግሞ አዲሱ አጀንዳ የአዲስ አበባና የኦሮሚያ ክልል የፊንፊኔ ልዩ ዞን አስተዳደራዊ ወሰን ማካለል ጉዳይ ነው፡፡ አከላለሉ ፍትሐዊና አብሮነትን ያከበረ ከሆነ መልካም ነው፡፡ ነገር ግን አለመተማመን በሰፈነበት የፖለቲካ ምኅዳር ውስጥ የተቃርኖ ድምፆች ሲሰሙ ማዳመጥ ተገቢ ነው፡፡ የኢትዮጵያ ሕዝብ በአገሩ ሰላም እንዲሰፍን፣ በእኩልነት ላይ የተመሠረተ ሥርዓት ኖሮ ፍትሕ ለሁሉም ተደራሽ እንዲሆን፣ በአገሩ ጉዳይ በነፃነት ተሳታፊ ሆኖ ዴሞክራሲያዊት አገር እንድትኖረው ይፈልጋል፡፡ መጠራጠርና መፈራራት የሌለበት፣ ከአሉባልታና ከሐሜት የፀዳ፣ በመከባበርና በመተሳሰብ ላይ የተመሠረተ ግንኙነት እንዲዳብር፣ የመወያየትና የመደራደር ባህል እንዲሰፍን፣ ኅብረ ብሔራዊ አንድነትን የሚያጠናክሩ የጋራ እሴቶች እንዲከበሩና ለግጭት የሚዳርጉ አላስፈላጊ ድርጊቶች እንዲገቱ የዘወትር ፍላጎቱ ነው፡፡ ዘመን ተሻጋሪ የሆኑት የማኅበራዊ መስተጋብሮቹ ውጤት የሆነው አብሮነቱና አንድነቱ ቀጣይነት ሊኖረው የሚችለው፣ በኢትዮጵያ ምድር ፍትሕና እኩልነት ሲሰፍኑ ነው፡፡ የኢትዮጵያና የአጠቃላይ ሕዝቧ አብሮነት መከበር አለበት፡፡ ፖለቲከኞችም ሆኑ በፖለቲካው ዙሪያ ያሉ ደጋግመው ማሰብ ያለባቸው፣ በትውልድ ቅብብሎሽ እዚህ የደረሰውን የሕዝብ አብሮነት እንዳያበላሹ ነው፡፡ ከወሰን ማካለሉ በላይ የሕዝብ አብሮነት ይታሰብበት፡፡

ብዙ ጊዜ ኃላፊነት በጎደላቸው ውሳኔዎችና ድምዳሜዎች ሳቢያ ሕዝብ በሚደርስበት መከራ ሕይወቱ ለሕልፈት ይዳረጋል፣ ለአካል ጉዳት ይጋለጣል፣ ከቀዬው ይፈናቀላል፣ የአገር ሀብት ይወድማል፡፡ ከግጭት ለመላቀቅና በእኩልነት ለመኖር የሚቻለው በአገር ጉዳይ የጋራ ስምምነት ሲኖር ብቻ ነው፡፡ ለዘመናት በክፉና በደግ ጊዜያት አብሮ የኖረ ሕዝብ መሀል ችግር እንዳይፈጠር መጠንቀቅ ይገባል፡፡ ነባሩን የሕዝብ አብሮነትና ወንድማማችነት የሚቃረን እንዳይሆን ጥንቃቄ ያስፈልጋል፡፡ በፖለቲከኞች መካከል የሚስተዋለው በእልህ የታጀበ የቃላት ምልልስ ለማንም አይጠቅምም፡፡ ፖለቲከኞች ከአጉል እልህ ውስጥ ወጥተው ሕጋዊውን መንገድ በመከተል፣ የሕዝብ ለሕዝብ ግንኙነቱ እንዳይበላሽ ጥረት ያድርጉ፡፡ የኢትዮጵያውያን ነባሩና ቱባው አብሮ የመኖር እሴት በአጉል ፖለቲካ አይባላሽ፡፡ ለሕዝብ ፈቃድ መገዛት የሚቻለው በዚህ መንገድ ብቻ ነው፡፡ የሕዝባችን ፍላጎት በሰላም በእኩልነት መኖር እንደሆነ ይታወቅ፡፡ ለግጭት ከሚያነሳሱ ፕሮፓጋንዳዎች በመታቀብ አብሮ ለመኖር የሚያስችሉ ጉዳዮች ላይ ይተኮር፡፡ ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዝብ እርስ በርሱ ተከባብሮና ተስማምቶ መኖር የቻለውና እስካሁንም የዘለቀው፣ ከሚለያዩት ይልቅ አንድነቱን የሚያጠናክሩ የጋራ እሴቶቹ ስለሚበልጡበት ነው፡፡

ይህ እንደ ዘበት የሚነገር ተራ ማስመሰል አይደለም፡፡ ወይም አንዳንድ ማስተዋል የጎደላቸው ወገኖች እንደሚሉት፣ በሕዝብ መካከል መቼም ቢሆን ቂም በቀል ኖሮ እርስ በርሱ ሲጋጭ አይታወቅም፡፡ ይልቁንም በተለያዩ ጊዜያት የተነሱ ወራሪዎችን በጋራ የመከተውና ደሙን ለአገሩ ያፈሰሰው ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዝብ ነው፡፡ የአውሮፓን ኮሎኒያሊስት ኃይል አይቀጡ ቅጣት ቀጥቶ የዓለም ጥቁር ሕዝቦችን አንገት ቀና ያደረገው ይህ ታላቅና ጀግና ሕዝብ ነው፡፡ ለፓን አፍሪካኒዝም መመሥረት ምክንያቱ እሱ ብቻ ነው፡፡ አፍሪካውያን ከቅኝ አገዛዝ ቀንበር ነፃ ለመውጣት ሲታገሉ፣ ዘመን አይሽሬ አስተዋጽኦ ያበረከተው ይህ ምሥጉንና ኩሩ ሕዝብ ነው፡፡ ይህ ጀግና ሕዝብ ከሰሜን እስከ ደቡብ፣ ከምዕራብ እስከ ምሥራቅ በተዘረጋው መልክዓ ምድር ውስጥ በፍቅር የሚኖር ነው፡፡ ይህ ሕዝብ በአፍሪካ ምድር እንደ አንበሳ እያገሳ በነፃነት የኖረ የነፃነት ቀንዲል ነው፡፡ በዘህ ዘመን እርስ በርሱ ተጋጨ ሲባል አያሳዝንም? አያሳፍርም? ይህ ኩሩ ሕዝብ ይከበር፡፡ በተለያዩ ጎራዎች ቢሠለፉም የአገር ጉዳይ ያገባናል የሚሉ ወገኖች ከፍተኛ ጥንቃቄ ማድረግ አለባቸው፡፡ አገር የምትኖረው ሕዝብ በሰላም ወጥቶ በሰላም ሲኖር ብቻ ነው፡፡

የኢትዮጵያ ሕዝብ በነፃነት፣ በማኅበራዊ ፍትሕና በእኩልነት መኖር ይፈልጋል፡፡ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ተገንብቶ አገሩ እንድታድግለትና ሰላም እንድትሆንለት ይፈልጋል፡፡ ሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶቹ ተከብረውለት የሥልጣኑ ትክክለኛ ባለቤት መሆን አለበት፡፡ የፈለገውን የመሾም ያልፈለገውን የመሻር መብት የእሱ ብቻ ሊሆን ይገባል፡፡ ይህ ምኞት ዕውን መሆን የሚችለው ደግሞ በሁሉም አቅጣጫ መደማመጥ ሲኖር ብቻ ነው፡፡ የአገሪቱ ፖለቲካ የቧልተኞችና የራስ ወዳዶች መጠቃቀሚያ ከመሆን ወጥቶ፣ ለእውነተኛ ውይይትና ለድርድር ጥርጊያ ጎዳናው ሊመቻች ይገባል፡፡ የራስ ወዳዶችና የግብዞች ‹‹የትም ፍጪው ዱቄቱን አምጪው›› ዲስኩር ይበቃል፡፡ ለሥልጣን ብቻ በሚደረግ የእልህ ሽኩቻ ዴሞክራሲ አይገነባም፡፡ እንዲህ ዓይነቱ ጤነኝነት የጎደለው አካሄድ ትርፉ የአገር ውድመት ነው፡፡ ሕዝብን ለዕልቂት መዳረግ ነው፡፡ ሕዝብን ማዕከል ያላደረገ በቅዥት የሚመራ ፖለቲካ አገርን ከማጥፋት የዘለለ ፋይዳ የለውም፡፡ በተለይ ለሥልጣንና ከበስተጀርባው ያለውን ጥቅም ብቻ በማሰብ አገርን በማተራመስ ሕዝብን ለማሰቃየት የሚደረገው ግብግብ፣ በሰከኑና አርቆ አሳቢ ዜጎች ይብቃ መባል አለበት፡፡ ሌላውም እንዲሁ ኃላፊነቱን ሊወጣ ይገባል፡፡ ከሕዝብ በላይ ማንም የለምና፡፡

በአሁኗ ኢትዮጵያ ለአገራቸው ዕውቀታቸውን፣ ገንዘባቸውን፣ ልምዳቸውንና አለን የሚሉትን ነገር በሙሉ ፈቃዳቸው ለመስጠት ዝግጁ የሆኑ አኩሪ ዜጎች ብዙ ናቸው፡፡ ትውልድን ከመኮትኮት ጀምሮ ለአገር ልማትና ዕድገት ማንኛውንም መስዋዕትነት ለመክፈል የተዘጋጁ እነዚህ አኩሪ ወገኖች ከመቼውም ጊዜ በላይ ያስፈልጋሉ፡፡ ከአድርባይነትና ከአጉል ይሉኝታ ርቀው የሰላ ሒስ በማቅረብ ስህተትን የሚያርሙና ቀናውን ጎዳና የሚያሲዙ በሻማ ብርሃን ጭምር መፈለግ አለባቸው፡፡ ከራሳቸውና ከመሰሎቻቸው ጥቅም ባሻገር የአገር ጉዳይ ደንታ የማይሰጣቸው እንዲታረሙ፣ ሕዝብን ከሕዝብ ጋር እያጋጩ ሰላም የሚያደፈርሱና የአገር ሀብት እየዘረፉ የሚፎልሉ በሕግ እንዲጠየቁ፣ ሥርዓተ መንግሥቱ በሕግ የበላይነት ሥር እንዲሆንና ሕዝብ እንዲከበር ይፈለጋል፡፡ ይህ ፍላጎት ዕውን መሆን የሚችለው ደግሞ በመፈክር ጋጋታና በአስመሳይነት አይደለም፡፡ መጪው አዲስ ዓመትም በርካታ የተንከባለሉ ጥያቄዎችን አዝሎ የሚመጣ በመሆኑ፣ በኃላፊነት ስሜት መመራት ተገቢ ነው፡፡ በፖለቲካ አመለካከታቸው ምክንያት የተገፉ ዜጎች ሳይቀሩ በነፃነት የሚንቀሳቀሱበት ምኅዳር መፈጠር አለበት፡፡ ይህ ደግሞ በሕግ ዋስትና ያገኘ መብት ነው፡፡ ሕዝብ ይህ መብት እንዲከበር ይፈልጋል፡፡

ኢትዮጵያ ታላቅ አገር ናት፡፡ የአፍሪካውያን መሰባሰቢያቸውም ናት፡፡ ለአፍሪካውያን ጭምር የጋራ ቤት የሆነችው ይህች ኩሩና የኩሩዎች አገር፣ ከደረጃዋ ወርዳ መገኘት የለባትም፡፡ ሕዝቧ አርዓያነቱ ከአድማስ እስከ አድማስ በዓለም የታሪክ መዝገብ ህያው ሆኖ ሰፍሮ እያለ፣ በከተማ ወሰንና መሰል ጉዳዮች ተጋጨ ሲባል ተቃርኖ ይፈጥራል፡፡ የሁሉም ኢትዮጵያውያን ብቻ ሳይሆን የአፍሪካውያንም ጭምር የጋራ መኖሪያ በሆነችው አዲስ አበባ ከተማ መጠራጠርና መፈራራት እንዳይፈጠር፣ በዚህ ክፍተት ደግሞ የአገሪቱ ታሪካዊ ጠላቶች ሰተት ብለው ገብተው ትርምስ እንዳይፈጥሩና የሕዝባችንን የአብሮነት ደማቅ ታሪክ እንዳያበላሹ መጠንቀቅ ተገቢ ነው፡፡ ለጊዜያዊ ጥቅምና ሥልጣን ሲባል ብቻ የሕዝባችንን ታሪክ ማበላሸትና አገሪቱን የማትወጣው ችግር ውስጥ መክተት ይቅር የማይባል ትልቅ ጥፋት ነው፡፡ ይልቁንም የኢትዮጵያ ሕዝብ በጨዋነት፣ በአርቆ አሳቢነት፣ በአስተዋይነት፣ በይቅር ባይነትና በጀግንነት የጋራ እሴቶቹ እስካሁን ያቆያትን አገር በመከባበርና በመተሳሰብ ማስቀጠል ይገባል፡፡ የሕዝባችን አብሮነት በአልፎ ሂያጅ አጀንዳዎች አይጠለፍ!

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

የኦሮሞን ሕዝብ ታሪክ አልባ በማድረግ ታሪክ አይሠራም

በኢተፋ ቀጀላ​​  ከዛሬ ሃምሳ ዓመት ወዲህ ከተፈጠሩት የኦሮሞ ድርጅቶች መካከል ከኢጭአት በስተቀር፣...

የፓርላማ አባላት ስለሰላም ስምምነቱ አፈጻጸም ግልጽ መረጃ የለንም አሉ

‹‹ሕወሓትን ለፍረጃ አብቅተውት የነበሩ ጉዳዮች በአብዛኛው መልክ ይዘዋል›› ሬድዋን...

ጉራጌን በክላስተር ለመጨፍለቅ የሚደረገውን ጥረት እንደሚቃወም ጎጎት ፓርቲ አስታወቀ

ለጉራጌ ሕዝብ ሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶች መከበር እንደሚታገል የሚናገረው አዲሱ...

‹‹ኢኮኖሚው ላይ የሚታዩ ውጫዊ ጫናዎችን ለመቀልበስ የፖሊሲ ሪፎርሞች ያስፈልጋሉ›› ዓለም ባንክ

በዓለም ደረጃ ከተፈጠረው የኢኮኖሚ አለመረጋጋት ጋር በተገናኘ፣ በኢትዮጵያ ውጫዊ...
- Advertisment -

ትኩስ ፅሁፎች

ለፋይናንስ ዘርፉ ብቃት ያለው የሰው ኃይል የማፍራት የቤት ሥራን የማቃለል ጅማሮ

የአገሪቱ የፋይናንስ ዘርፍ እያደገ ለመሆኑ ከሚቀርቡ ማስረጃዎች ውስጥ  የግል...

የምድር ባቡርን የሚያነቃቃው የመንግሥት ውሳኔ

በኢትዮጵያ ወደብ አልባነት ላይ የተደመረውን የሎጀስቲክስ ችግር ለመፍታት ግዙፍ...

የፓርላማ አባላት ስለሰላም ስምምነቱ አፈጻጸም ግልጽ መረጃ የለንም አሉ

‹‹ሕወሓትን ለፍረጃ አብቅተውት የነበሩ ጉዳዮች በአብዛኛው መልክ ይዘዋል›› ሬድዋን...

ብሔራዊ ባንክ የፖሊሲ ማሻሻያዎችን ይፋ ሊያደርግ ነው

የፋይናንስ ዘርፉን ለማረጋጋት የሚረዳ ሪፎርም ማጠናቀቁን የገለጸው የኢትዮጵያ ብሔራዊ...
spot_img

ተዛማጅ ፅሁፎች

ግልጽነትና ተጠያቂነት የጎደለው አሠራር ለአገር አይበጅም!

ሰሞኑን የአሜሪካና የኢትዮጵያ መንግሥታት በሰሜን ኢትዮጵያ ጦርነት ተፈጽመዋል በተባሉ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶችና የጦር ወንጀሎች መግለጫ ላይ አልተግባቡም፡፡ አለመግባባታቸው የሚጠበቅ በመሆኑ ሊደንቅ አይገባም፡፡ ነገር ግን...

የምግብ ችግር ድህነቱን ይበልጥ እያባባሰው ነው!

በአገር ውስጥና በውጭ የተለያዩ ተቋማት የሚወጡ መረጃዎች እንደሚያሳዩት፣ በአሁኑ ጊዜ በኢትዮጵያ ከ22 ሚሊዮን በላይ ዜጎች አስቸኳይ የምግብ ዕርዳታ ያስፈልጋቸዋል፡፡ እነዚህ ወገኖች በሰሜን ኢትዮጵያ ጦርነት፣...

መብትና ነፃነትን የሚጋፉ ድርጊቶች ይወገዱ!

ኢትዮጵያውያን በየትኛውም የአገሪቱ ክፍል የመዘዋወር፣ የመኖር፣ የመሥራትና ሀብት የማፍራት ሕጋዊ መብት አላቸው፡፡ ይህ መብት በግልጽ የተደነገገው በሥራ ላይ ባለው ሕገ መንግሥት ሲሆን፣ አሁንም ሕገ...