የፌደራል የሥነ ምግባርና ፀረ ሙስና ኮሚሽን የፌዴራል መንግሥት የአስፈጻሚ አካላት የጥቅም ግጭት መከላከያ ረቂቅ ደንብ አዘጋጀ፡፡
በኮሚሽኑ የተዘጋጀውን ረቂቅ ለፍትሕ ሚኒስቴር በማቅረብ አስተያየት ተሰጥቶበታል፡፡ በፍትሕ ሚኒስቴር አስተያየት የሀብት ማሳወቂያና ምዝገባ አዋጅ ቁጥር 668/2002 አንቀጽ 14 ላይ የተጠቀሰው በቂ መሆኑ እንደተገለጸላቸው፣ በኮሚሽኑ የሕግ አገልግሎት ሥራ አስፈጻሚ አቶ ገዛኸኝ ጋሻው ለሪፖርተር ተናግረዋል፡፡
ፍትሕ ሚኒስቴር ለኮሚሽኑ በአዋጁ የተጠቀሰው በቂ መሆኑንና ደንብ መዘጋጀት ለምን አስፈለገ የሚል ምላሽ ከሰጠ በኋላ፣ ኮሚሽኑ ተጨማሪ ሐሳቦችን በማካተት ወደ ሚኒስትሮች ምክር ቤት ለመላክ ተጨማሪ ውይይቶች ለማድረግ በሒደት ላይ መሆኑን አቶ ገዛኸኝ አስረድተዋል፡፡
ኮሚሽኑ የሀብት ምዝገባ አዋጅ ላይ የተጠቀሰውን የጥቅም ግጭት ለመከላከልና ተግባራዊ ለማድረግ፣ በመመርያ ወይም ደንብ በማውጣት መወሰን እንደሚችል ይገልጻል፡፡
የጥቅም ግጭት ደንብ ከፀደቀ በኋላ በአገሪቱ ለሚገኙ 183 የሕዝብ አገልግሎትና ፈቃድ ሰጪ አስፈጻሚ ተቋማት አስገዳጅ ደንብ ይሆናል ተብሏል፡፡
የግል፣ የቤተሰብ፣ የፖለቲካ፣ የገንዘብ ነክና ሌላ ዓይነት ፍላጎቶች በተቋማት ኃላፊነት ውስጥ ጣልቃ እየገቡ፣ ተቋሙን የሚጠቅም የውሳኔ አቅም መግታት ሲጀምሩ የጥቅም ግጭት እንደሚፈጠር ተገልጿል።
ይህንን መሠረት በማድረግ የጥቅም ግጭትን በተመለከተ ተቋማት በየራሳቸው መተዳደሪያ ደንብ ላይ እንደ አንድ አንቀጽ ሆኖ ቢሠፍርላቸውም፣ ተፈጻሚነታቸው ግን ደካማና ቅጣት የሌለው በመሆኑ፣ የጥቅም ግጭት ደንብ ራሱን ችሎ እንዲወጣ በማስፈለጉ ምክንያት የተዘጋጀ ነው ሲሉ አቶ ገዛኸኝ ገልጸዋል፡፡
የጥቅም ግጭት መከላከያ ደንብ ራሱን ችሎ ሲዘጋጅ አስገዳጅ ሁኔታዎችንና ዕርምጃ የሚወሰድበትን የሕግ ድንጋጌ እንደሚያሳይ፣ የጥቅም ግጭት ማለት በተለይ የተቋማት ኃላፊዎች የሚወስኑት ውሳኔ ከግል ጥቅም ጋር የሚያያዝ መሆን እንደሌለበት ተመልክቷል፡፡
‹‹በዚህ ደንብ መሠረት የመንግሥትንና የግል ንብረትን አንድ ላይ መጠቀም አይቻልም፡፡ ይህም ማለት አንድ የመንግሥት ኃላፊ የራሱ ድርጅት ቢኖረው ለተቋሙ ከራሱ ድርጅት ዕቃ እንዲገዛ መፍቀድ የለበትም፡፡ ግዥ ሲፈጸም በጨረታ ሒደት የራሱን ድርጅት ማካተት አንደማይችል ደንቡ ይጠቅሳል፤›› ሲሉ አቶ ገዛኸኝ ገልጸዋል፡፡
በዚህ ደንብ አመራር ላይ ያሉ ግለሰቦች በዓይነትም ሆነ በገንዘብ ምንም ዓይነት ጥቅማ ጥቅሞችን መቀበል የማይቻል በመሆኑ፣ ሙስናን ለመከላከል የሚረዳና ዓለም አቀፍ ድርጅቶች የሚፈልጉት ነው ብለዋል፡፡
የጥቅም ግጭትን በተመለከተ አንዳንድ ተቋማት በየግላቸው መተዳደሪያ ደንብ ላይ እንደ አንድ አንቀጽ ሆኖ ይጠቀሳሉ፡፡ ነገር ግን ተፈጻሚነታቸው ደካማና ቅጣት የሌለው በመሆኑ የጥቅም ግጭት ደንብ ራሱን ችሎ መውጣት እንዳለበት አስረድተዋል፡፡
በተጨማሪም ስለጥቅም ግጭት መከላከል በኮሚሽኑ የተዘጋጀው የሀብት ምዝገባ አዋጅ ላይ የተጠቀሰ ቢሆንም፣ ደንቡ ራሱን ችሎ ሲዘጋጅ አስገዳጅ ሁኔታዎችንና ዕርምጃ የሚወሰድበትን የሕግ ድንጋጌ ያስቀምጣል፡፡
የሥነ ምግባርና ፀረ ሙስና ኮሚሽን አዋጅ ቁጥር 881/2007 መሠረት ቀላል፣ መካከለኛና ከባድ በሚል የቅጣት እርከኖች እንደተፈጠረው የጥቅም ግጭት ዓይነት የገንዘብና የእስራት ቅጣት ይኖራቸዋል፡፡ በአዋጁ የተጠቀሱት ቅጣቶች በጥቅም ግጭት መከላከያ ደንብ ውስጥ እንዲካተቱ በማድረግ በትክክል እንዲፈጸም ያስችላል ተብሏል፡፡
በተመሳሳይ በኮሚሽኑ አዋጅ ቁጥር 668/2002 መሠረት ማናቸውም ተሿሚዎች፣ ተመራጮችና የመንግሥት ሠራተኞች ሀብት እንዲያሳውቁና እንዲያስመዘግቡ የሕግ ግዴታ ተጥሎባቸዋል፡፡ ኮሚሽኑም የመዘገበውን መረጃ ሕጉ በሚፈቅደው መሠረት ለሕዝብ ይፋ የማድረግ ሥልጣንና ኃላፊነት እንደተሰጠው በግልጽ ተደንግጓል፡፡