Tuesday, March 28, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ዜናየአማራ ክልል የሃይማኖት ተቋማት ከሚያገኙት የሕንፃ ኪራይ  ገቢ ግብር እንዲሰበሰብ ትዕዛዝ ተላለፈ

የአማራ ክልል የሃይማኖት ተቋማት ከሚያገኙት የሕንፃ ኪራይ  ገቢ ግብር እንዲሰበሰብ ትዕዛዝ ተላለፈ

ቀን:

የአማራ ክልል ገቢዎች ቢሮ ከ2015 ከጀት ዓመት አንስቶ የሃይማኖት ተቋማት ከሆቴል ንግድ ሥራና ሕንፃ ኪራይ ከሚያገኙት ገቢ ላይ ግብር እንዲሰበሰብ ትዕዛዝ አስተላለፈ፡፡

የክልሉ ገቢዎች ቢሮ ኃላፊ አቶ ፀጋ ጥበቡ (ዶ/ር) በክልሉ ለሚገኙ ስምንት የሪጂኦ ፖሊታን ከተማ አስተዳደር የገቢ መምርያዎች በጻፉት ደብዳቤ፣ የሃይማኖት ተቋማት በሆቴል ንግድና ሕንፃ ኪራይ ገቢ የሚያገኙባቸው ሥራዎች፣ ከግሉ ንግድ ዘርፍ ጋር ተወዳዳሪ ሆነው የሚሠሯቸው መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡

እነዚህ የገቢ ምንጭ የሆኑ ሥራዎች የሃይማኖት ተቋማት ‹‹ከተቋቋሙበት ዓለማ ውጪ›› የሆኑ ተግባራት እንደሆኑ በደብዳቤያቸው የገለጹት ፀጋ (ዶ/ር)፣ ተቋማቱ በእነዚህ ሥራዎች ላይ መሰማራታቸው ከተረጋገጠ ታክስ መክፈል እንደሚጠበቅባቸው አሳስበዋል፡፡

ደብዳቤው የተላለፈላቸው የባህርዳር፣ ጎንደር፣ ደሴ፣ ደብረ ማርቆስ፣ ደብረ ብርሃን፣ ኮምቦልቻ፣ ወልድያና ደብረታቦር ከተማ አስተዳደሮች፣ የገቢ መምሪያ ቢሮዎችም ከ2015 በጀት ዓመት ጀምሮ ከሃይማኖት ተቋማቱ ግብርና ታክስ እንዲሰበስቡ ታዘዋል፡፡

በክልሉ ገቢዎች ቢሮ የታክስ አማካሪ አቶ እንግዳወርቅ ገዛኸኝ፣ ትዕዛዙ የተላለፈው በክልሉ የሃይማኖት ተቋማት፣ በእነዚህ ሥራዎች ላይ የሚያገኙትን ገቢ በተመለከተ ወጥ የሆነ አሠራር ባለመኖሩ ነው ብለዋል፡፡ ተቋማቱ ከሕንፃ ኪራይ ከሚያገኙት ገቢ ግብር የሚከፈልባቸው አካባቢዎች እንዳሉ የተናገሩት አቶ እንግዳወርቅ፣ በተለይ በከተማዋ አካባቢ ግን ይሄ ተፈጻሚ እንዳልሆነ ገልጸዋል፡፡ ባህር ዳር ከተማ የሃይማኖት ተቋማቱ ከእነዚህ ገቢዎች ላይ ግብር የማይከፍሉባቸው አካባቢዎች ውስጥ አንዷ ናት ብለዋል፡፡

‹‹ይኼ የፍትሐዊነት ጥያቄም ነው፤›› ያሉት አማካሪው፣ ተመሳሳይ ሥራዎች እየተሠሩ፣ አንድ አካል ግብር የሚከፍል ሌላኛው የማይከፍል መሆን እንደሌለበት አስረድተዋል፡፡

የክልሉ መንግሥት ያወጣቸው የገቢ ግብር፣ የተርን ኦቨር ታክስና የተጨማሪ እሴት ታከስ አዋጆች በሃይማኖት ተቋማት የሚሰጡ ከእምነት ወይም ከአምልኮ ጋር የሚገናኙ አገልግሎቶች ከማንኛውም ታክስ ነፃ እንደሆኑ ይደነግጋሉ፡፡

አሁን ግብርና ታክስ እንዲከፈል የተጠየቀባቸው የሆቴል ንግድና የሕንፃ ኪራይ ገቢዎች ከሃይማኖት ሥርዓት ጋር እንደማይገናኙ የሚያስረዱት አቶ እንግዳወርቅ፣ ‹‹ከሌሎች የንግድ ተቋማት ጋር የሚወዳደሩባቸው የገቢ ምንጮች ካሉ ግብር መክፈል አለባቸው፤›› ብለዋል፡፡

እንደ የታክስ አማካሪው ገለጻ፣ አሁን በተጀመረው የ2015 በጀት ዓመት ከክልሉ ዓመታዊ ወጪ ውስጥ እስከ 50 በመቶው ከግብር በሚገኝ ገቢ ለመሸፈን መታሰቡ፣ ይህንን ትዕዛዝ የተላለፈበት አንዱ ምክንያት ነው፡፡

የክልሉ መንግሥት በ2014 በጀት ዓመት 26.9 ቢሊዮን ብር ገቢ የሰበሰበ ሲሆን፣ ይህም ይዞት ከነበረው ዕቅድ 89.8 በመቶ ነው፡፡  በቀጣዩ በጀት ዓመት ይህንን ገቢ በ11.39 ቢሊዮን ብር ጨምሮ 38.37 ቢሊዮን ብር ለመሰብሰብ አቅዷል፡፡ ከመደበኛና ከከተማ አገልግሎት ሊሰበሰብ የታቀው አጠቃላይ ገቢ 42.84 ቢሊዮን ብር ነው፡፡

ይህም የክልሉ መንግሥት ለ2015 በጀት ዓመት ያፀደቀውን 95.32 ቢሊዮን ብር 44 በመቶ ይሸፍናል፡፡ የፌደራል መንግሥት በአዲሱ በጀት ዓመት 44.5 ቢሊዮን ብር ድጎማ ለአማራ ክልል አፅድቋል፡፡ የፌደራል መንግሥት ድጎማና ከገቢ ይገኛል ተብሎ የታቀደው ገንዘብ ተደምሮ ዓመታዊው በጀት ላይ የስምንት ቢሊዮን ብር ጉድለት አለ፡፡

የክልሉ መንግሥት በተለይም በተያዘው በጀት ዓመት በሰሜን ኢትዮጵያ ጦርነት ሳቢያ የደረሰበትን ከ288 ቢሊዮን ብር በላይ የሆነ ውድመት፣ ለመልሶ ግንባታ ትኩረት ስለሚያደርግ ወጪውን እንደሚያንረው ይጠበቃል፡፡

የታክስ አማካሪው አቶ አንግዳወርቅ፣ የክልሉ መንግሥት አሁን የሃይማኖት ተቋማት ከሆቴል ንግድ ሥራና ከሕንፃ ኪራይ ከሚያገኙት ገቢ ላይ ሊሰበስብ ካቀደው ግብር ባሻገር፣ አጠቃላይ ገቢውን የሚጨምሩ ሥራዎችን ለማከናወን እንዳቀደና በቀጣይ ይፋ እንደሚያደርግ ተናግረዋል፡፡

‹‹በዚህ ዓመት የክልላችን ወጪ ቢያንስ 50 በመቶ ከገቢ መሰብሰብ አለብን ብለን እየሠራን ነው፡፡ ከዚህ አንፃር ወደፊት ያላየናቸው የገቢ ምንጮች ላይ ሕጉ እስከሚፈቅድልን እንሠራለን፤›› በማለት የክልሉን መንግሥት ዕቅድ አስረድተዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

‹‹ከኦነግ ሸኔ ጋር ያለውን ግጭት በሰላም ለመፍታት ከፍተኛ ፍላጎት አለን›› ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ

መንግሥት ከ‹‹ኦነግ ሸኔ››ጋር ያለውን ግጭት በሰላም ለመፍታት ከፍተኛ ፍላጎት...

ለፋይናንስ ዘርፉ ብቃት ያለው የሰው ኃይል የማፍራት የቤት ሥራን የማቃለል ጅማሮ

የአገሪቱ የፋይናንስ ዘርፍ እያደገ ለመሆኑ ከሚቀርቡ ማስረጃዎች ውስጥ  የግል...

የምድር ባቡርን የሚያነቃቃው የመንግሥት ውሳኔ

በኢትዮጵያ ወደብ አልባነት ላይ የተደመረውን የሎጀስቲክስ ችግር ለመፍታት ግዙፍ...