Tuesday, March 28, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ማኅበራዊበበጀት ዓመቱ ከግንባታ ሥራ ላይ የወደቁ 23 ሰዎች ከፍተኛ የአካል ጉዳትና ሞት...

በበጀት ዓመቱ ከግንባታ ሥራ ላይ የወደቁ 23 ሰዎች ከፍተኛ የአካል ጉዳትና ሞት እንዳጋጠማቸው ተገለጸ

ቀን:

በ2014 በጀት ዓመት በአዲስ አበባ በግንባታ ሥራ ላይ ተገቢው የደኅንነት መጠበቂያ ግብዓቶችን ለሠራተኞቻቸው ባላሟሉ የኮንስትራክሽን ድርጅቶች ችግር፣ 23 ሰዎች በሥራ ላይ እያሉ ከሕንፃ ወድቀው ከፍተኛ የአካል ጉዳትና ሞት እንዳጋጠማቸው ተገለጸ፡፡

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የግንባታ ፈቃድና ቁጥጥር ባለሥልጣን በግንባታ ሥራ ላይ ተገቢውን የደኅንነት መጠበቂያ ግብዓቶችን ለሠራተኞቻቸው በማያሟሉ የኮንስትራክሽን ድርጅቶች ላይ ክትትልና ቁጥጥር እያደረገ እንደሚገኝ አስታውቆ፣ ግዴታቸውን በማይወጡ ድርጅቶች ላይ ዕርምጃ ለመውሰድ ከደንብ ማስከበር ባለሥልጣን ጋር መግባባት ላይ ተደርሷል ብሏል፡፡

የባለሥልጣኑ የኮሙዩኒኬሽን ዳይሬክተር አቶ አረጋዊ ማሩ ለሪፖርተር እንዳስረዱት፣ በግንባታ ወቅት የሚያጋጥሙ ቀላል አደጋዎች በቁጥር በርካታ ናቸው፡፡ በብዛት ለባለሥልጣኑ በሪፖርት የሚቀርቡለት ከፍተኛ የአካል ጉዳትና የሞት አደጋ ክስተቶች ናቸው ብለዋል፡፡

በተጠናቀቀው የበጀት ዓመት ደረሰ ከተባለው የ23 ሰዎች የአካል ጉዳትና ሞት ሪፖርት ውስጥ፣ 21 ያህሉ የሞት አደጋ እንደነበር የኮሙዩኒኬሽን ዳይሬክተሩ አስረድተዋል፡፡

ግንባታ የሚያከናውን ማንኛውም አካል ተገቢውን የደኅንነት ጥንቃቄ ሊያደርግ እንደሚገባ ፈቃድ በሚወስድበት ወቅት የሚመሳከር እንደሆነ የተገለጸ ሲሆን፣ ፈቃድ ከተወሰደም በኋላ ግንባታውን ደኅንነቱን በሚያስጠብቅ መንገድ እየተከናወነ ነው? ወይስ አይደለም? የሚለው በክትትልና በቁጥጥር የሚረጋገጥ መሆኑን ተጠቅሷል፡፡ ነገር ግን በዚህ ሒደት ውስጥ ለአደጋ መንስዔ የሆነው ችግር የሚስተዋል መሆኑን አቶ አረጋዊ ገልጸዋል፡፡ በተለይም ግንባታ በሚያከናውኑ ድርጅቶች ለምልከታ በሚኬድበት ሰዓትና በሌላ ወቅት በድንገት ፍተሻ ሲደረግ ክፍተቱ የሚታይ ስለሆነ፣ ባለሥልጣኑ እስከ ወረዳ ድረስ ባለው መዋቅር በስፋት ሊሠራበት ዕቅድ መያዙ ተገልጿል፡፡

በሌላ በኩል በተያዘው የበጀት ዓመት ከተፈቀደላቸው የግንባታ ቦታ ውጪ የሚጠቀሙና በእግረኛ መንገድ ላይ የተለያዩ የግንባታ ዕቃዎች በማስቀመጥ የእግረኛ መንገድን በማጨናነቅ አካል ጉዳተኞችን ለከፍተኛ ችግር እያጋለጡ የሚገኙ ድርጅቶችና ግለሰቦች ላይ ዕርምጃ ለመውሰድ፣ ከደንብ ማስከበር ባለሥልጣን ጋር ለመሥራት የመግባቢያ ሰነድ መዘጋጀቱን ያስታወቀው የግንባታና ቁጥጥር ባለሥልጣን፣ በ2014 ዓ.ም. ከላይ ከተጠቀሱት ችግሮች ጋር በተገናኘ በ136 ድርጅቶች ላይ ሕጋዊ ዕርምጃ መወሰዱን አስታውቋል፡፡

በ136 ድርጅቶቹ ላይ የግንባታ ግብዓቶችን እንዲያነሱ ከማድረግ አንስቶ ንብረታቸውን የመውረስ፣ እንዲሁም የመጨረሻ ጽሑፍ ማስጠንቀቂያና የዕገዳ ውሳኔ የማስተላለፍ ዕርምጃዎች መወሰዳቸውን የኮሙዩኒኬሽን ዳይሬክተሩ ገልጸዋል፡፡

በተጠናቀቀው የበጀት ዓመት በ10,674 ግንባታዎች ላይ ክትትልና ቁጥጥር መደረጉን ያስታወቀው ባለሥልጣኑ፣ በ2015 የበጀት ዓመት 3,400 የማስጀመሪያ ፈቃድ፣ 3,400 አዲስና 6,000 ነባር ግንባታዎች ክትትልና ቁጥጥር ለማድረግ መታቀዱን ገልጾ፣ ከዚህ በተጨማሪም 280 የግንባታ ማራዘሚያ፣ 5,000  ግንባታዎች ያሉበትን ደረጃ የሚገልጽ የመስክ ሪፖርት፣ እንዲሁም 7,000 ዕድሳት   አገልግሎቶችን አከናውናለሁ ብሏል፡፡

ከሐምሌ 1 ቀን 2014 ዓ.ም. ጀምሮ በማዕከልና በክፍለ ከተማ የሚሰጡ አዲስ የግንባታ ፈቃድ፣ የፕላን ስምምነት፣ ማሻሻያ፣ የስም ለውጥና አገልግሎት ለውጥ ለሚፈልጉ ተገልጋዮች ሙሉ በሙሉ በኦንላይን መስጠት መጀመሩን ባለሥልጣኑ አስታውቋል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ለፋይናንስ ዘርፉ ብቃት ያለው የሰው ኃይል የማፍራት የቤት ሥራን የማቃለል ጅማሮ

የአገሪቱ የፋይናንስ ዘርፍ እያደገ ለመሆኑ ከሚቀርቡ ማስረጃዎች ውስጥ  የግል...

የምድር ባቡርን የሚያነቃቃው የመንግሥት ውሳኔ

በኢትዮጵያ ወደብ አልባነት ላይ የተደመረውን የሎጀስቲክስ ችግር ለመፍታት ግዙፍ...

የፓርላማ አባላት ስለሰላም ስምምነቱ አፈጻጸም ግልጽ መረጃ የለንም አሉ

‹‹ሕወሓትን ለፍረጃ አብቅተውት የነበሩ ጉዳዮች በአብዛኛው መልክ ይዘዋል›› ሬድዋን...