Thursday, March 23, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ስፖርትሦስት ክልሎች ለእግር ኳስ ፌዴሬሽን ፕሬዚዳንትነት ምርጫ ተፋጠዋል

ሦስት ክልሎች ለእግር ኳስ ፌዴሬሽን ፕሬዚዳንትነት ምርጫ ተፋጠዋል

ቀን:

ምርጫው ተግባራዊ እንዳይሆን በፍርድ ቤት ክስ የመሠረቱ ተቋማት አሉ

የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ነሐሴ 21 ቀን 2014 ዓ.ም. ፌዴሬሽኑን በቀጣይ አራት ዓመታት የሚያስተዳድሩ የፕሬዚዳንትና የሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ምርጫ ያከናውናል፡፡ ሦስት ክልሎች ለፕሬዚዳንትነት ያቀረቧቸው ዕጩዎች ታውቀዋል፡፡

በጎንደር ከተማ ነሐሴ 21 ቀን 2014 ዓ.ም. ይከናወናል ተብሎ በሚጠበቀው የፕሬዚዳንትና የሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ምርጫ፣ ክልሎች ዕጩዎቻቸውን የሚያቀርቡበት የጊዜ ሰሌዳ ትናንት ማክሰኞ ሐምሌ 19 ቀን 2014 ዓ.ም. አብቅቷል፡፡

በአስመራጭነት የተሰየመው አስመራጭ ኮሚቴ ሐምሌ 5 ቀን 2014 ዓ.ም. የምርጫውን ሒደትና አፈጻጸም አስመልክቶ መግለጫ መስጠቱ አይዘነጋም፡፡

ኮሚቴው በጋዜጣዊ መግለጫው እንደስታወቀው፣ የክልልና የከተማ አስተዳደር እግር ኳስ ፌዴሬሽኖች ዕጩዎቻቸውን እስከ ሐምሌ 18 ቀን 2014 ዓ.ም. ድረስ ማሳወቅ እንደሚጠበቅባቸው መግለጹ ይታወሳል፡፡ ይሁንና በተቀመጠው የጊዜ ሰሌዳ መሠረት ዕጩዎቻቸውን እንዲያቀርቡ ጥሪ የተደረገላቸው ክልሎችና ከተማ አስተዳደሮች በቂ ተወዳዳሪ ማቅረብ ባለመቻላቸው፣ አስመራጭ ኮሚቴው አንድ የሥራ ቀን ማለትም እስከ ሐምሌ 19 ቀን 2014 ዓ.ም. ድረስ እንዲራዘምላቸው ማድረጉ የሚታወስ ነው፡፡

ክልሎችና ከተማ አስተዳደሮች ዕጩ ተወዳዳሪዎቻቸውን የሚያሳውቁበት ጊዜ ማብቃቱን ተከትሎ፣ አስመራጭ ኮሚቴው ይህ ዘገባ እስከተጠናቀረበት ድረስ የቀረቡ ዕጩ ተወዳዳሪዎች ዝርዝርና ማንነት አላሳወቀም፡፡

ምንጮች ለሪፖርተር እንዳረጋገጡት ከሆነ፣ እስካሁን ሦስት ክልሎች ፌዴሬሽኑን በፕሬዚዳንትነት እንዲያገለግሉ በዕጩነት አቅርበዋል፡፡ በዚሁ መሠረት ላለፉት አራት ዓመታት ብሔራዊ ፌዴሬሽኑን በፕሬዚዳንትነት ሲመሩ የነበሩት አቶ ኢሳያስ ጅራ የኦሮሚያ ክልል ዕጩ አድርጎ ሲያቀርባቸው፣ የአማራ ክልል ደግሞ የቀድሞ ገቢዎችና ጉምሩክ ዋና ዳይሬክተር፣ የአማራ ልማት ማኅበር ዋና ሥራ አስፈጻሚና በቅርቡ ሥራ የጀመረው አማራ ባንክ አደራጅና የቦርድ ሰብሳቢ አቶ መላኩ ፈንታን ሲያቀርብ፣ የሐረሪ ክልል ደግሞ የኢትዮጵያ ቡና እግር ኳስ ክለብ ዋና ሥራ አስኪያጅ አቶ ገዛኸኝ ወልዴን ማቅረቡ ታውቋል፡፡

የዕጩ ማቅረቢያ ቀን ገደብ መጠናቀቁን ተከትሎ፣ አስመራጭ ኮሚቴው የቀረቡ ዕጩ ተወዳዳሪዎችን ዝርዝርና ማንነት በዚህ ሳምንት እንደሚያሳውቅ ይጠበቃል፡፡

በሌላ በኩል የባህልና የስፖርት ሚኒስቴር በቅርቡ አገር አቀፍ የስፖርት ማኅበራት የሚቋቋሙበትን ሁኔታ አስመልክቶ ባዘጋጀው መመርያ፣ ‹‹በትውልድ ኢትዮጵያዊ ሆነው የሌላ አገር ዜግነት ያላቸው ወገኖች፣ አገር አቀፍ ብሔራዊ ፌዴሬሽኖችን በፕሬዚዳንትና በምክትል ፕሬዚዳንትነት አሊያም በዋና ጸሐፊነት ተመርጠው ማገልገል አይችሉም›› በሚል ይፋ ያደረገው መመርያ ክስ ቀርቦበታል፡፡

ክሱን የመሠረተው የኢትዮጵያ ፕሮፌሽናል የተጫዋቾች ማኅበር ሲሆን፣ የክሱ ጭብጥ ደግሞ፣ በኢትዮጵያ የሕጎች ሁሉ የበላይ ሕግ በሆነው ሕገ መንግሥት፣ ‹‹በትውልድ ኢትዮጵያዊ በዜግነት ደግሞ የሌላ አገር ዜግነት ያላቸው ትውልደ ኢትዮጵያውያን፣ አገር አቀፍ ብሔራዊ ምርጫ እንዲሁም በወታደራዊና የደኅንነት  ተቋማት መሥሪያ ቤቶች በስተቀር በሌሎች የኢትዮጵያ ተቋማት በምርጫም ሆነ በበጎ ፈቃድ አገልግሎት አገራቸውን ማገልገል እንደሚችሉ ይደነግጋል›› የሚለውንና በመመርያው የስፖርት ማኅበሩ አባላት በቀጥታ ዕጩ ተመራጭ ማቅረብ ይችላሉ የሚለውን መተላለፋቸውን በመጥቀስ ነው፡፡

በመሆኑም ክሱ በቅርቡ ይደረጋል ተብሎ በሚጠበቀው የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን የፕሬዚዳንት ምርጫ፣ የባህልና የስፖርት ሚኒስቴር መመርያን መነሻ በማድረግ የቀረበ የምርጫ ሒደት በመሆኑ፣ ጉዳዩ በፍርድ ቤት ውሳኔ እስኪሰጠው ድረስ ምርጫው እንዲታገድለት የፕሮፌሽናል ተጫዋቾች ማኅበር ጠይቋል፡፡

ክሱን ተቀብሎ እያየው ያለው የፌዴራል የመጀመርያ ደረጃ ፍረድ ቤት ቂርቆስ ምድብ ችሎት ትናንትና ሐምሌ 19 ቀን 2014 ዓ.ም. በሰጠው ትዕዛዝ ፌዴሬሽኑ ለቀረበበት ክስ እስከ ሐምሌ 29 ቀን 2014 ዓ.ም. ድረስ ምላሽ ሰጥቶ እንዲቀርብ አስታውቋል፡፡  

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

[ክቡር ሚኒስትሩ ከሚያከብሯቸው አንድ የቀድሞ ጉምቱ ፖለቲከኛ ስልክ ተደውሎላቸው እያወሩ ነው]

አንዳንድ ነገሮች ቢያሳስቡኝ ነው ቀጠሮ ሳልይዝ ላወራህ የፈለኩት ክቡር...

የትግራይ ክልል የሽግግር አስተዳደር ምሥረታና የሰላም ስምምነቱ ሒደት

በትግራይ ክልል ጊዜያዊ የሽግግር መንግሥት ለመመሥረት ደፋ ቀና እየተባለ...

ጥራዝ ነጠቅነት!

ከሜክሲኮ ወደ ጀሞ እየሄድን ነው፡፡ የተሳፈርንበት አሮጌ ሚኒባስ ታክሲ...