Thursday, September 28, 2023
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

የአገር ውስጥ የፍራፍሬ ገበያን ፍላጎት ይሸፍናል የተባለለት የብላቴው እርሻ ልማት

ተዛማጅ ፅሁፎች

መንግሥት የግብርና ምርታማነትና የፍራፍሬ ምርትን ለማሳደግ በ‹‹አረንጓዴ አሻራ›› በሚል ተነሳሽነት በመላ ኢትዮጵያ የፍራፍሬ ዛፎችን መትከል ጨምሮ፣ አርሶ አደሩ የበጋ መስኖ ልማትን እንዲያለማ ዘመቻዎችን መጀመሩ ይታወቃል። ከእነዚህም ውስጥ በዚህ ዓመት በኢትዮጵያ የተለያዩ አካባቢዎች በበጋ መስኖ በማልማት ከፍተኛ የስንዴ ምርት መገኘቱን የገለጸው መንግሥት፣ የስንዴ ምርቱን ከአገር ውስጥ ፍጆታ ባሻገር ለውጭ ገበያ ለማቅረብ ዝግጅት መጀመሩን ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) በቅርቡ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በነበራቸው ቆይታ ሲናገሩ ተደምጠዋል፡፡ 

ከዚህ ባለፈ መንግሥት ባለሀብቶችን በግብርና ኢንቨስትመንት እንዲሳተፉና ለአገር ውስጥና ለውጭ ገበያ ምርትን የሚያቀርቡበት አማራጭ እንደቀረበ ሲገልጽ ይደመጣል፡፡

ከዚህም ውስጥ የአቮካዶና ሌሎች የፍራፍሬ ልማቶች በአነስተኛ አርሶ አደሮች ብቻ ሳይሆን፣ በኢትዮጵያ በተለያዩ ክልሎች እየለሙ የሚገኙ ሜካናይዝድ እርሻ ልማቶች ተስፋ ተጥሎባቸዋል፡፡ በደቡብ ክልል እየለማ የሚገኘው ግዙፉ ዳኜ ሜካናይዝድ እርሻ ተጠቃሽ ነው፡፡

ቡናና የቅባት እህሎችን ለውጭ ገበያ በመላክ የሚታወቁት ባለሀብት አቶ ዳኜ ዳባ፣ ዛሬ ላይ ከተሰማሩበት የወጪ ንግድ ባሻገር ፊታቸውን ወደ ግብርናው አዙረዋል።

የአገር ውስጥ የፍራፍሬ ገበያን ፍላጎት ይሸፍናል የተባለለት የብላቴው እርሻ ልማት | Ethiopian Reporter | ሪፖርተር
የፍራፍሬ ማሳ በከፊል

የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ለሰጠው ብድር በዋስትና የያዘውን ገናሌ አግሮ ኢንዱስትሪ በግንቦት ወር 2013 ዓ.ም. በግልጽ ጨረታ ተወዳድረው የገዙት አቶ ዳኜ ዳባ የግብርና ይዞታውን ሰኔ 2013 ዓ.ም. ከተረከቡ በኋላ ግዙፍ የግብርና ኢንቨስትመንት ውስጥ ገብተዋል። 

ከሐዋሳ ከተማ በስተደቡብ ምዕራብ 70 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ የሚገኘው የዳኜ የግብርና ተቋም አንድ ዓመት ብቻ ባስቆጠረው የግብርና ኢንቨስትመንት ጅማሮው እንደ ምርጥ ዘር፣ የበጋ መስኖ ስንዴ ልማትና የተለያዩ የፍራፍሬ ዛፎችን የመሳሰሉ የግብርና ምርቶችን በማልማት የሚያጓጓ ውጤት ከወዲሁ ማሳየት ጀምሯል።

በአባያና በብላቴ አካባቢ የተጀመረው ይኼው የእርሻ ልማት ከ2,500 ሔክታር በላይ በሆነ ይዞታ ላይ የተንጣለለ የፓፓያ፣ የሙዝና የተለያዩ የፍራፍሬ ዛፎች ተሸፍኖ ከምርቱ ባሻገር ለአካባቢው ልዩ ውበትን አጓናጽፏል።

የእርሻ መሬቱን የሸፈኑት አብዛኛዎቹ የፍራፍሬ ዛፎች የተተከሉት ከአንድ ዓመት ባልበለጠ ጊዜ ውስጥ መሆኑን ባለሀብቱ አቶ ዳኜ ዳባ ለሪፖርተር ያስረዳሉ፡፡

የፍራፍሬውን ተክል ለማግኘት የተለያዩ ችግኞችን በከፍተኛ የገንዘብ መጠን የሚገዙ ሲሆን፣ ለአብነትም በእርሻው ውስጥ የሚገኘው ‹‹ግራንድ ናይን›› የተባለውን የሙዝ ዘር ብቻውን ከእስራኤል አስመጥቶ በቢሾፍቱ ከተማ እያመረተ ከሚገኝ ኩባንያ የተገዛ ሲሆን ለአንዱ ችግኝ 75 ብር ይጠይቃል፡፡

በብላቴ ሰፊ የእርሻ መሬት እየለማ የሚገኝ የሙዝ ማሳ አምስት ኪሎ ሜትር ርዝመት ሲኖረው፣ የ1.5 ኪሎ ሜትር የጎን ስፋት አለው፡፡ በሙዝ እርሻው 1.5 ሚሊዮን የሙዝ ችግኞች የተተከሉ ሲሆን፣ የሙዝ ችግኞቹ ከዚህ ቀድም በኢትዮጵያ ከተለመዱት የሙዝ ዝርያ ዓይነት የተለየ ነው፡፡

የሙዝ ተክሉ የሚያፈራው አንድ ዘለላ በጥቅሉ 80 ኪሎ ግራም የሚመዝኑ ብዛት ያላቸው የሙዝ ፍሬዎችን የያዘ ሲሆን፣ የሙዝ ፍሬዎቹ ይዘትም ከተለመደው የሙዝ ዝርያ ተለቅ ያሉ ናቸው።

የሙዝ ምርቱ ለገበያ ሲደርስ በቀን 20 የጭነት መኪና ምርትን ማቅረብ የሚያስችል አቅም እንደሚኖረው ይጠበቃል፡፡ የሙዝ ምርቱ የኢትዮጵያን ከፍተኛ የገበያ ድርሻ የመሸፈን አቅም እንዳለው የተገለጸ ሲሆን፣ ምርቱን ለውጭ ገበያ ለማቅረብ በሒደት ላይ መሆናቸውን አቶ ዳኜ ያስረዳሉ፡፡

ሌላው በብላቴ እርሻ እየለማ የሚገኘው የአቮካዶ ምርት ሲሆን፣ ይህ እርሻ በአሁኑ ወቅት በአንድ ሚሊዮን የአቮካዶ ዛፎች ተሸፍኖ ይታያል።

በመጪው ዓመት የአቮካዶ ዛፎቹ ለአገር ውስጥና ለውጭ ገበያ ከፍተኛ ጥራት ያለው ፍሬ እንደሚያፈሩ ይጠበቃል፡፡

በብላቴ የሚገኘው የአቶ ዳኜ ዳባ የእርሻ ልማት ትኩረት ካደረገባቸው የፍራፍሬ ምርቶች ሌላው የብርቱካን ምርት ሲሆን፣ ለዚሁ የተዘጋጀው የእርሻ መሬትም በአሥር ሺሕ የብርቱካን ዛፎች ተሸፍኖ ይታያል።

ከዚህ በተጨማሪም ወደ 20,000 የሚጠጉ የብርቱካን ግንዶችን ከዑጋንዳ ማስመጣታቸውን ባለሀብቱ የገለጹ ሲሆን፣ በላይኛው አዋሽ የግብርና ልማት የሚለማውን ‹‹ትንሿ ዛፍ›› በሚል ስያሜ የምትታወቀውን ለኢትዮጵያ ተስማሚ የሆነች የቫሌንሲያ የብርቱካን ተክል በመግዛት በብላቴ የእርሻ ልማት እየተተከለ መሆኑን አቶ ዳኜ ጠቅሰዋል፡፡

በአጠቃላይ በብላቴ የእርሻ ልማት ውስጥ በሚቀጥሉት ጥቂት ወራት ወደ 100,000 የብርቱካን ችግኝ እንደሚተከል የገለጹት ባለሀብቱ፣ በሁለት ዓመታት ውስጥም ፍሬ አፍርቶ ለገበያ እንደሚቀርብ ዕምነታቸውን ገለጸዋል።

ከላይ ከተጠቀሱት የፍራፍሬ እርሻዎች በተጨማሪ በ500,000 የፓፓያ ዛፎች የተሸፈነው ማሳና የፓፓያ ፍሬዎቹ የእርሻ ልማቱ ልዩ ውበት ሆኖ ይታያሉ።

ፍሬ እያፈራ የሚገኘው ፓፓያ ለመጪዎቹ አራት ዓመታት የሚሰበሰብ ሲሆን፣ ከአንድ ግንድ በዓመት አራት ኩንታል የፓፓያ ምርት እየተሰበሰበ መሆኑን ባለሀብቱ አቶ ዳኜ ገልጸዋል። በአሁኑ ወቅት የፓፓያ ምርቱ ለአገር ውስጥ ገበያ እየቀረበ መሆኑንና ከዚህ የፓፓያ ምርት ሽያጭ የሚገኝ ገቢም የእርሻ ልማቱን ሠራተኞች ሙሉ ደመወዝ እየሸፈነ መሆኑን አስረድተዋል።

‹‹በአጠቃላይ የዛፍ ተከላው በመጪው ወቅት ከፍተኛ ምርት እንደሚሰጥ ተስፋ እናደርጋለን፤›› በማለት አቶ ዳኜ ይናገራሉ፡፡

እንደ አቶ ዳኜ አስተያየት ከሆነ የሙዝና የብርቱካን የገበያ ፍላጎት ሟሟላት የሚያስችል አቅም ያለው ምርት እያለሙ እንደሚገኙና አንድ ኪሎ ግራምን ከ28 እስከ 30 ብር ድረስ የማቅረብ ፍላጎት እንዳላቸው ገልጸው፣ በሸማቹና በአቅራቢው መካከል የሚገቡ ደላሎች ጉዳይ ግን አሳሳቢ መሆኑን ይጠቁሟሉ፡፡

‹‹መንግሥት ደላለው ጣልቃ ገብቶ ሸማቹ ላይ ዋጋ እንዳይጨምርበትና አርሶ አደሩ ቀጥታ ከሸማቹ ጋር እንዲገናኝ ትኩረት አድርጎ መሥራት አለበት፤›› ብለዋል፡፡

ሌላው በብላቴው እርሻ እየለማ የሚገኘው አቮካዶ ሲሆን፣ ለእያንዳንዱ የአቮካዶ ዝርያ ችግኝ 200 ብር የወጣበት መሆኑን፣ ከችግኙ የተወሰነው ክፍል እስከ 350 ብር ወጪ ተደርጎበታል፡፡

ባለሀብቱ የእርሻ መሬቱን ሲረከቡ በደን የተሞላ መሆኑን ተከትሎ፣ ደኑን ለመመንጠር የተለያዩ ማሽነሪዎችን መጠቀማቸውን፣ በአካባቢው የውኃ እጥረት በመኖሩ 12 የከርሰ ምድር ጉርጓድ ለመቆፈር ከ200 ሚሊዮን ብር በላይ ወጪ መደረጉን አቶ ዳኜ ለሪፖርተር አስረድተዋል፡፡

እርሻው ከፍራፍሬ ምርት በተጨማሪ በተያዘው የመኸር ወቅት ለውጭ ገበያ የሚቀርቡ የእህል አዝዕርቶችን እያለሙ ሲሆን፣ የተሻሻሉ የስንዴ ዘሮችን በማልማት ለዘር አከፋፋዮች ማቅረብ ሌላው የእርሻ ልማቱ የተሰማራበት የግብርና ልማት እንደሆነም ጠቅሰዋል።

በአሁኑ ወቅትም የተሻሻሉ የበቆሎና የበሎቄ ዘሮችን በማምረት ላይ መሆናቸውን ገልጸው፣ እየተመረቱ የሚገኙት የተሻሻሉ አዝዕርቶች ዘር በመጪው መኸር ለአርሶ አደሩ እንደሚቀርብ ገልጸዋል።

እንደ ባለሀብቱ ገለጻ በአሁኑ ወቅት እየተመረተ የሚገኘው የተሻሻለ የበቆሎ ዘር ቢያንስ አሥር በመቶ የሚሆነውን የአርሶ አደሩን የመኸር ወቅት ማሳ ሊሸፍን የሚችል ነው።

‹‹ሾኔ›› የተሰኘ ዝርያን ጨምሮ የተለያዩ የተሻሻሉ የበቆሎ ዘሮችን በአባያ በሚገኘው ከ1,000 ሔክታር በላይ የእርሻ ይዞታ ላይ የማልማት ሥራ የተጀመረ ሲሆን፣ በብላቴ በሚገኝ ይዞታ ላይ ደግሞ 400 ሔክታር መሬት በዘር እንደሚሸፈን ገልጸዋል። የተሻሻሉትን የበቆሎ ዘሮች ለኢትዮጵያ ዘር ኢንተርፕራይዝና ለሌሎች አጋር ድርጅቶች እንደሚያቀርቡም አቶ ዳኜ አስረድተዋል። በቀጣይ ዓመት ከእነዚህ ማሳዎች እስከ 50,000 ኩንታል የተሻሻለ በቆሎ ይመርታል ተብሎ እንደሚጠበቅም ገልጸዋል፡፡

ባለፈው ክረምት የዳኜ የእርሻ ተቋም ለደቡብ ክልል ኢንተርፕራይዝ የተሻሻሉ የስንዴ ዘሮችን በማልማት ለአርሶ አደሮች መከፋፈሉንም ጠቅሰዋል፡፡ የብላቴው የእርሻ ልማት ለግብርና ሥራዎቹ ለሚያስፈልገው የአፈር ማዳበሪያ በዓመት ከ20 ሚሊዮን ብር በላይ ወጪ እንደሚደረግም አቶ ዳኜ ይጠቅሳሉ፡፡ 

እርሻው ለድንገተኛ አደጋ መጠባበቂያ የሚሆን በተለያዩ እርሻው ቦታዎች የሚገኙ ሦስት ግዙፍ የውኃ ገንዳዎችን በማዘጋጀት ላይ ሲሆን፣ የኤሌክትሪክ ኃይል መቆራረጥ ወይም የጄኔሬተሮች ብልሽት ከተከሰተ በመጠባበቂያ ገንዳዎቹ የተያዘው ውኃ በአማራጭነት ጥቅም ላይ እንደሚውል ገልጸዋል።

በእርሻው የተለያዩ ማዕዘናት ውስጥ ስድስት ዋና ዋና የቡድን መሪዎች ያሉ ሲሆን፣ በመሪዎቹ ሥር ወደ 3,000 የሚጠጉ የጉልበት ሠራተኞች በዕለት ተዕለት የግብርና ሥራ ላይ ይሳተፋሉ። በተጨማሪም 20 ከፍተኛ የግብርና ባለሙያዎች ሙሉ በሙሉ በእርሻ ሥራው ላይ ክትትል እንዲያደርጉ ተመድበዋል፡፡

አቶ ዳኜ ያከናወኗቸው ተግባራት ሌሎች ትልልቅ ባለሀብቶችን በተመሳሳይ መንገድ እንዲከተሉ ማድረጉ የተሰማቸውን ደስታ ገልጸው፣ ይህም አገሪቱን ከመመገብ ባለፈ ለውጭ ገበያ በማቅረብና ተፈላጊውን የውጭ ምንዛሪ በማምረት ረገድ ትልቅ ፋይዳ እንዳለው ያላቸውን እምነት ገልጸዋል። 

ለጉብኝት ወደ ውጭ አገር በሚሄዱበት ወቅት፣ የጉብኝታቸው አንድ አካል የሆነው ለም የብርቱካን ማሳ ወደ ግብርናው ለመግባት እንዳነሳሳቸው የሚገልጹት ባለሀብቱ፣ በቡናና በቅባት እህሎች ለውጭ ገበያ ንግድ ላይ ነበር የከርሙት፡፡ ሆኖም ወደ ግብርናው ፊታቸውን ያዞሩት ባለሀብቱ፣ ወደ ሥራው ሲገቡ ከፍተኛ ገንዘብ ኢንቨስት ማድረጋቸውን ይናገራሉ፡፡ 

በዚህም መሠረት ግብርናውን የበለጠ ለማሳደግ ተጨማሪ ከፍተኛ ገንዘብ እንደሚያስፈልጋቸው ገልጸው፣ ከልማት ባንክ ብድር ጠይቀው በመጠባበቅ ላይ እንደሚገኙ አክለዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች