የትግራይ ክልል መልሶ ግንባታና ነዋሪዎችን ማቋቋም ፕሮጀክት፣ በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት (ተመድ) የፕሮጀክት አገልግሎቶች ጽሕፈት ቤት በኩል ሊከናወን ነው፡፡ ፕሮጀክቱ የሚከናወነው የዓለም ባንክ ድጋፍ በሚያደርግለት የ19 ቢሊዮን ብር፣ የብሔራዊ መልሶ ግንባታና ነዋሪዎችን ማቋቋሚያ ፕሮጀክት አካል ነው፡፡
የገንዘብ ሚኒስቴርና የተመድ የፕሮጀክት አገልግሎቶች ጽሕፈት ቤት ማክሰኞ ሐምሌ 5 ቀን 2014 ዓ.ም. የሦስተኛ ወገን ትግበራ ስምምነት የፈጸሙ ሲሆን፣ ፕሮጀክቱ በትግራይ የሚተገበረው በክልሉ ያለው ሁኔታ እስከሚሻሻል ድረስ መሆኑን የገንዘብ ሚኒስቴር አስታውቋል፡፡
ጽሕፈት ቤቱ የፕሮጀክቱን ግማሽ ክፍል እንደሚተገብር የገለጸው ሚኒስቴሩ፣ ሌላውን የፕሮጀክቱን ክፍል የሚተገብር ሦስተኛ ወገን ለመምረጥ በድርድር ላይ መሆኑን ባወጣው መግለጫ አስረድቷል፡፡
የዓለም ባንክ 15.6 ቢሊዮን ብር ድጋፍ ያደረገለት ይህ የአምስት ዓመት ፕሮጀክት በጦርነትና በግጭቶች የተጎዱትን የትግራይ፣ የአማራ፣ የአፋር፣ የኦሮሚያና የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልሎችን የሚያካትት ነው፡፡ እንደ ገንዘብ ሚኒስቴር መረጃ ፕሮጀክቱ ሁለት ዋነኛ ግቦች ሲኖሩት ቀዳሚው በእነዚህ አካባቢዎች የመልሶ ግንባታ፣ የመሠረታዊ አገልግሎቶችን ተደራሽነት ማሻሻል፣ የአየር ንብረት ተፅዕኖን መቋቋም የሚያስችል የማኅበረሰብ መሠረተ ልማትን የመዘርጋት ሥራዎች ላይ ያተኮረ ነው፡፡ የትምህርት፣ የጤናና የውኃ አቅርቦቶች ተደራሽነትም በዚህ ግብ ውስጥ ተካቷል፡፡
ሁለተኛው ግብ ደግሞ በእነዚህ አካባቢዎች የፆታዊ ጥቃት ምላሽ አገልግሎቶች ተደራሽነት የማሻሻልና የፆታዊ ጥቃት ሰለባዎችን መደገፍ ላይ ትኩረት ያደርጋል፡፡
ፕሮጀክቱን ለማስፈጸምና ለመከታተል የተለያዩ ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቶችን ያካተተ ኮሚቴ ሲቋቋም በዋናነትም የገንዘብ ሚኒስቴር፣ የፍትሕ ሚኒስቴር፣ የትምህርት ሚኒስቴር፣ የሴቶችና ማኅበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር፣ የከተማና መሠረተ ልማት ሚኒስቴር፣ የጤና ሚኒስቴርና የሰላም ሚኒስቴር ተካተውበታል። ፕሮጀክቱን የማስፈጸም ዋነኛ ኃላፊነት ግን የገንዘብ ሚኒስቴር ነው፡፡
ይሁንና አሁንም የግጭት ቀጣና በሆኑ አካባቢዎች ፕሮጀክቱ የሚተገበረው ከመንግሥት ጋር ስምምነት በሚፈጽሙ ሦስተኛ ወገን ተቋማት በኩል መሆኑ፣ በዓለም ባንክና የገንዘብ ሚኒስቴር ስምምነት ላይ ተጠቅሷል፡፡
በዚህም መሠረት የዚህ ፕሮጀክት አካል በሆነው የትግራይ ክልል ይህንን ፕሮጀክት ለመፈጸም፣ የኢትዮጵያ መንግሥት ለተመድ የፕሮጀክት አገልግሎቶች ጽሕፈት ቤት ውክልና ሰጥቷል፡፡ ስምምነቱን የፈረሙትም ከመንግሥት በኩል የገንዘብ ሚኒስትሩ አቶ አህመድ ሺዴና የጽሕፈት ቤቱ የኢትዮጵያ ዳይሬክተር ወ/ሮ ወርቅነሽ መኮንን ናቸው፡፡
ጽሕፈት ቤቱ አሁን ስምምነት የፈጸመው የፕሮጀክቱን የመጀመሪያ ግብ ብቻ ሲሆን፣ የፆታዊ ጥቃት ሰለባዎችን ከመደገፍ ጋር የተያያዘው ሥራ በሌላ ሦስተኛ አካል የሚተገበር መሆኑን የገንዘብ ሚኒስቴር በመግለጫው አስታውቋል፡፡ ሦስተኛ አካልን ለመምረጥም መንግሥት ድርድር እያደረገ እንደሆነ ተጠቅሷል፡፡
በስምምነቱ መሠረት የተመድ የፕሮጀክት አገልግሎቶች ጽሕፈት ቤት በትግራይ ክልል ለማኅበረሰቡ ፈጣን የምላሽ አገልግሎት መስጠትና ከኅብረተሰቡ ጋር በመመካከር፣ በግጭቱ የተጎዱ መሠረተ ልማት አውታሮችን መልሶ መገንባት ሥራዎችን ያከናውናል፡፡ በተጨማሪም በማኅበረሰብ ደረጃ ያሉ ማኅበራዊ ተቋማትን ይደግፋል ተብሏል፡፡
ጽሕፈት ቤቱ መንግሥት በትግራይ ክልል ይህንን ፕሮጀክት በራሱ መዋቅር መተግበር የሚችልበት ሁኔታ እስከሚፈጠር ድረስ የተሰጡትን ኃላፊነቶች ሲያከናውን፣ በክልሉ ያለው ሁኔታ ሲሻሻል ጽሕፈት ቤቱ ሥራውን ለመንግሥት እንደሚያስረክብ በመግለጫው ተጠቅሷል፡፡
የሰሜኑ የአገሪቱ ክፍል ያለው ጦርነት በሰላማዊ መንገድ ይፈታል በሚል ዕቅድ የ2015 ዓ.ም. በጀት የያዘው መንግሥት፣ የበጀት ዓመቱ የትኩረት አቅጣጫዎች ካላቸው ውስጥ መልሶ ማቋቋምና ሰብዓዊ ዕርዳታ ተጠቃሽ ነው፡፡
በዚህ በጀት ዓመት ለመልሶ ግንባታ 20 ቢሊዮን ብር የተያዘ ሲሆን፣ ይህ የገንዘብ መጠን ክልሎች እንደደረሰባቸው የጉዳት መጠን ድልድል እንደሚደረግበት ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) ባለፈው ሳምንት ሰኔ 30 ቀን 2014 ዓ.ም. ለፓርላማ አባላት መናገራቸው ይታወሳል፡፡