በአፋር ክልል የጦርነት ቀጣና በነበረው ዞን አንድ አዳአር ወረዳ የወደቀ ፈንጂ ያነሱ ሁለት ወንድና አንዲት ሴት ሕፃናት ሕይወታቸው ሲያልፍ፣ ሁለት ሕፃናት ቀላልና ከባድ ጉዳት እንደደረባቸው የአፋር ክልል ሰላምና ፀጥታ ቢሮ አስታወቀ፡፡
አደጋው የደረሰው ቅዳሜ ሐምሌ 2 ቀን 2014 ዓ.ም. መሆኑን ለሪፖርተር የተናገሩት የቢሮው ኃላፊ አቶ ኢብራሂም ሁመድ፣ ከዚህ ቀደምም በተመሳሳይ አደጋ የአንድ ሕፃን ልጅ ሕይወት ማለፉን አስረድተዋል፡፡
ኃላፊው እንደሚገልጹት፣ አደጋው የደረሰው ከሕፃናቱ መካከል እረኝነት የዋለ ሕፃን ፈንጂውን ወደ መኖሪያ ቤቱ ይዞ ከመጣ በኋላ ነው፡፡ ‹‹ፈንጂው መኖሩ ሪፖርት ሳይደረግልን ቤት ውስጥ አድሯል፤›› ያሉት አቶ ኢብራሂም፣ ፈንጂውን የተመለከተው አባት ከልጆች አርቆ ማስቀመጡን ገልጸዋል፡፡
ይሁንና በማግሥቱ ጠዋት የቤተሰቡ አባላት ለኢድ አል አድሃ (አረፋ) በዓል ስግደት መውጣታቸውን ተከትሎ፣ ሕፃናቱ ፈንጂውን መልሰው በማግኘታቸው አደጋው እንደተከሰተ ተናግረዋል፡፡ ሦስቱ ሕፃናት ሕይወታቸው ወዲያውኑ ማለፉን፣ አንደኛው ልጅ ደግሞ ከባድ ጉዳት እንደደረሰበት ገልጸዋል፡፡
ሪፖርተር ያነጋገረውና ለቤተሰቡ ቅርብ የሆነ የዕርዳታ ሠራተኛ፣ የሞቱት ሕፃናት ከሰባት እስከ 13 ዕድሜ ያላቸው መሆኑን አስረድቷል፡፡
የሰላምና ፀጥታ ቢሮ ኃላፊው እንደሚያስረዱት፣ አካባቢው ላይ የፈንጂ ማፅዳት ሥራ ባለመከናወኑ እንዲህ ዓይነት አደጋዎች በተደጋጋሚ መከሰቱን ተናግረው፣ ከዚህ ቀደም በእረኝነት በነበሩ ሁለት ሕፃናት ላይ ተመሳሳይ አደጋ ደርሶ አንዱ ልጅ ሕይወቱ ማለፉን አስታውሰዋል፡፡
አቶ ኢብራሂም፣ ‹‹ሬድዋና ካሳጊታ ኃይለኛ ጦርነት የነበረባቸው ቦታዎች ስለነበሩ፣ የወደቁ ፈንጂዎች ናቸው፡፡ ለማፅዳት እያሰብን ነው፡፡ አሁን ሁለተኛ አደጋ ስለተከሰተ ከመከላከያ ሚኒስቴር ጋር እየተነጋገርን ነው፤›› በማለት የቢሯቸውን ቀጣይ ሥራ ገልጸዋል፡፡
የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የሰብዓዊ ዕርዳታ ማስተባበሪያ ጽሕፈት ቤት (ኦቻ) እንደ አፋር ክልል የጦርነት ቀጣና ውስጥ በነበሩ አካባቢዎች ላይ ፈንጂዎችና የጦር መሣሪያ ቅሪቶች አሰሳ አለመካሄዱ ሥጋት መሆኑን በመግለጫዎቹ ላይ ሲጠቅስ ቆይቷል፡፡
እንደ ኦቻ ገለጻ ይህ ዓይነቱ አደጋ እያጋጠመ ያለው በተለይም በጦርነቱ ምክንያት የተፈናቀሉ የክልሉ ነዋሪዎች፣ ወደ መኖሪያ ቤታቸው በሚመለሱበት ጊዜ መሆኑን አስታውቋል፡፡ ነዋሪዎቹ ወደ መኖሪያ ቀዬአቸው ሲመለሱ በአካባቢያቸው ሊያጋጥሟቸው ስለሚችሉ የፈንጂ አደጋዎች በቂ ትምህርት እንደማይሰጣቸው ገልጿል፡፡
ጽሕፈት ቤቱ ከሁለት ሳምንታት በፊት ሰኔ 20 ቀን 2014 ዓ.ም. ባወጣው መግለጫ፣ ‹‹ተፈናቃዮች ፈንጂ የሆኑ የጦር መሣሪያ ቅሪቶችን ጨምሮ ሌሎችም የፀጥታ ዕጦት ሥጋት ቢያድርባቸውም ወደ መኖሪያቸው እንዲመለሱ እየተደረጉ ነው፤›› ብሎ ነበር፡፡
ይሁንና ይኼ ሥጋት በተመሳሳይ በአማራ ክልልም እንዳለ የኦቻ ሪፖርት አሳይቷል፡፡ ግንቦት 9 ቀን 2014 ዓ.ም. በኦሮሞ ልዩ ዞን ባቲ ከተማ ቀበሌ 3 በደረሰ ፍንዳታ አንድ አባትና ሦስት ልጆቹ መሞታቸውና ቢያንስ ሁለት ሴቶችና ሦስት ሕፃናት ላይ ከባድ የአካል ጉዳት መድረሱን ሪፖርቱ አመላክቷል፡፡ ፍንዳታው የተከሰተው በአካባቢው የተተወ የጦር መሣሪያ ቅሪት መሆኑን በሪፖርቱ ላይ ተካቷል፡፡
ትናንት ሐምሌ 5 ቀን 2014 ዓ.ም. በደሴ ከተማ የቦምብ ፍንዳታ ስለመከሰቱ የከተማዋ ኮሙዩኒኬሽን ቢሮ አስታውቋል፡፡ በዚህ ፍንዳታ 11 ሰዎች የመቁሰል አደጋ ሲደርስባቸው፣ እንስሳት መሞታቸውን ቢሮው ገልጿል፡፡ በከተማዋ በሰኞ ገበያ ክፍለ ከተማ ሳላይሽ ቀበሌ ፍንዳታው የደረሰው ቆራሊዮ መጋዘን ከመኪና ላይ ወርዶ ሚዛን ሲመዘን ከነበረ ኬሻ ውስጥ በፈነዳ ቦምብ ምክንያት መሆኑንም ቢሮው አክሏል፡፡