Wednesday, June 19, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

ሳሙና አምራቾች ጥሬ ዕቃ ዋጋ እስከ 480 በመቶ መጨመሩን አስታወቁ

spot_img

ተዛማጅ ፅሁፎች

የሳሙና አምራች ፋብሪካዎች በጥሬ ዕቃ እጥረትና እስከ 480 በመቶ በደረሰ የዋጋ ጭማሪ ምክንያት በቂ ምርት እያመረቱ አለመሆናቸው ተገለጸ።

ለሳሙና ምርት የሚውሉ ጥሬ ዕቃዎች ከፍተኛ የዋጋ ጭማሪ እያሳዩ መሆናቸውንና በቂ አቅርቦትም አለመኖሩን፣ የቲቲኬ ኢንዱስትሪስ ምክትል ዋና ሥራ አስኪያጅ አቶ ግዛው መጨጊያው ገልጸዋል።

ለሳሙና ምርት የሚውሉ በርካታ ግብዓቶች በአብዛኛው ከውጭ የሚመጡ ሲሆን፣ ከአገር ውስጥ የሚገኙ ጥሬ ዕቃዎችም አሉ። በተለይ ‹‹ኑዱልስ›› የተባለው ጥሬ ዕቃ በአንድ ዓመት ውስጥ 480 በመቶ የዋጋ ጭማሪ የታየበት መሆኑን የገለጹት አቶ ግዛው፣ ይህም በኪሎ ግራም 50 ብር ከነበረበት ወደ 240 ብር ከፍ ማለቱን ተናግረዋል፡፡ በየቀኑ ጭማሪ እያሳየ ይገኛልም ብለዋል።

በአገር ውስጥ ከሚገኙት ግብዓቶች ውስጥ ‹‹ዶኖማይት›› የተባለው ጥሬ ዕቃ አሶሳ አካባቢ እንደሚገኝ፣ በተለይም በፀጥታ ችግር ምክንያት በበቂ መጠን ማግኘት አለመቻሉን ገልጸው፣ በዋጋውም ላይ ከነበረበት በኪሎ ግራም ከሦስት ብር ወደ አሥር ብር ከፍ ማለቱን አክለዋል።

በጥሬ ዕቃ እጥረት ምክንያት በአምራቾች ላይ የሚደርሰው ጫና በተጠቃሚዎች ላይም የዋጋ ጭማሪ እንዲኖር እያደረገ መሆኑን ገልጸዋል። በአንድ የሳሙና ምርት ላይም እስከ 70 በመቶ የዋጋ ጭማሪ መታየቱን አስረድተዋል፡፡

የጥሬ ዕቃ እጥረቱ በአቅማቸው ልክ እንዳያመርቱ እያደረጋቸው መሆኑን ገልጸው፣ ‹‹ከዚህ በፊት 24 ሰዓት እንሠራ ነበር፡፡ አሁን ግን በቂ ጥሬ ዕቃ እያገኘን ባለመሆኑና በዋጋው ከፍ ማለት ምክንያት ፈረቃ እያጠፍን ነው፤›› ብለዋል። ለዚህም ከዋጋ ጭማሪው በተጨማሪ፣ ከውጭ ለማምጣት በቂ የውጭ ምንዛሪ አለመገኘቱ እንደሆነ አብራርተዋል።

የሳሙና ግብዓቶች ከሚገኙባቸው ምርቶች መካከል የፓልም ዘይት አንዱ ሲሆን፣ በአገር ውስጥ ያሉ የፓልም ዘይት አምራቾች ግብዓቱን እንዲያቀርቡ ቢሞከርም፣ በበቂ መጠን ማግኘት አለመቻሉን የኬሚካልና ኮንስትራክሽን ግብዓቶች ኢንዱስትሪ ልማት ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር አቶ ሳሙኤል ሐላላ ገልጸዋል።

የግብዓቶቹ እጥረት መኖሩን የገለጹት አቶ ሳሙኤል፣ የውጭ ምንዛሪ እጥረት ከፍተኛ ችግር መሆኑን አስረድተዋል። ለዚህም በአገር ውስጥ ከፍተኛ የሳሙና ግብዓት የማምረት አቅም ስላለ ከውጭ የሚመጡትን ለመተካት ጥናት መጀመሩን ተናግረዋል።

በተለይም ከዕፅዋቶች የሚገኙ እንደ ፈሳሽ ዓይነት የሳሙናና የሽቶ ግብዓቶችን በአገር ውስጥ ማምረት የሚቻል መሆኑን የገለጹት አቶ ሳሙኤል፣ የሳሙና ግብዓቶች በአብዛኛው ከማሌዥያና ከኢንዶኔዥያ የሚመጡ መሆናቸው፣ በአገር ውስጥ ግብዓቶቹን ለማምረት የተቋቋሙት ፋብሪካዎችም በውጭ ምንዛሪ እጥረት ምክንያት በበቂ መጠን አምርተው ማቅረብ አለመቻላቸውን አስረድተዋል።

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች