የዝንጀሮ ፈንጣጣ እስከ ሰኔ ማብቂያ ድረስ በ42 አገሮች ላይ ተከስቷል፡፡ የተከሰተባቸው አገሮች ደግሞ ከዚህ ቀደም በቫይረሱ የተጠቃ ሰው ኖሯቸው የማያውቁ ናቸው፡፡ ይህ መሆኑ ችግሩ ትኩረት እንዲሰጠው ያስገድዳል የሚለው የዓለም ጤና ድርጅት፣ በተለይ በቤተሰባቸው ወይም በሚኖሩበት አካባቢ መካከል በቫይረሱ የተጠቃ ሰው ያጋጠማቸው ልዩ ትኩረት እንደሚያስፈልጋቸው ይገልጻል፡፡ አንዳንዶቹ የዝንጀሮ ፈንጣጣ ተጠቂዎች የገኙት በግብረሰዶማውያን ማኅበረሰብ ጤና ክሊኒኮች ነው፡፡ ሆኖም በዝንጀሮ ፈንጣጣ መያዝ በእነዚህ ማኅበረሰቦች ብቻ የተወሰነ አይደለም፡፡ ማንኛውም በቫይረሱ ከተጠቃ ሰው ጋር ግንኙነት ያለው ሰው በቫይረሱ ሊያዝ ይችላል፡፡ የዓለም ጤና ድርጅትም የዝንጀሮ ፈንጣጣ ምንድነው፣ እንዴት ይተላለፋል፣ በየትኛው ማኅበረሰብ ውስጥ የሚሉትንና ሌሎች ተዛማጅ መረጃዎችን በጥያቄና መልስ አድርጎ በድረገጹ አስፍራል፡፡ ምሕረት ሞገስ እንደሚከተለው አጠናቅራዋልች፡፡
ጥያቄ፡- የዝንጀሮ ፈንጣጣ ምንድነው?
መልስ፡- የዝንጀሮ ፈንጣጣ ወይም ሞንኪፖክስ የምንለው በሞንኪፖክስ ቫይረስ አማካይነት የሚከሰት ሕመም ነው፡፡ ከእንስሳት ወደ ሰውና ከሰው ወደ ሰው የሚተላለፍ ቫይረስ ነው፡፡
ጥያቄ፡- የዝንጀሮ ፈንጣጣ በመደበኛነት መገኛው የት ነው?
መልስ፡- የዝንጀሮ ፈንጣጣ በመደበኛነት የሚገኘው በመካከለኛውና በምዕራብ አፍሪካ፣ ሞቃታማና ጥቅጥቅ ደኖች ባሉበት እንዲሁም ቫይረሱን የተሸከሙ እንስሳት በሚኖሩበት ሥፍራ ነው፡፡ የዝንጀሮ ፈንጣጣ ያለባቸው ሰዎች አንዳንድ ጊዜ ከመካከለኛውና ምዕራብ አፍሪካ ውጪ ይገኛሉ፡፡ ይህም የሚሆነው ሰዎች የዝንጀሮ ፈንጣጣ በብዛት ከሚገኝባቸው አገሮች ወደሌላ አገር በሚጓጓዙበት ወቅት ነው፡፡
ጥያቄ፡- የዝንጀሮ ፈንጣጣ ምልክቶች ምንድናቸው?
መልስ፡- የዝንጀሮ ፈንጣጣ ምልክቶች በመደበኛነት ትኩሳት፣ ከፍተኛ ራስ ምታት፣ የጡንቻ ሕመሞች፣ የጀርባ ሕመም፣ የጉልበት ማነስ፣ በአብዛኛው በጆሮ ግንድ አካባቢ ማበጥና የቆዳ ላይ ሽፍታ ናቸው፡፡ የሰውነት ሽፍታው በአብዛኛው የሚከሰተው ትኩሳቱ ከጀመረ እስከ ሦስተኛ ቀናት ባለው ጊዜ ውስጥ ነው፡፡ ሽፍታው በተለይ በፊት፣ በእጅና በውስጥ እግር ላይ የሚታይ ነው፡፡ በአፍ፣ በዓይንና በብልት አካባቢ ሽፍታ ሊታይም ይችላል፡፡ የሕመሙ ምልክቶች ከሁለት እስከ አራት ሳምንታት ቆይተው ያለሕክምና በራሳቸው የሚጠፉ ናቸው፡፡ ሰዎች እንደዚህ ዓይነት ምልክቶች ካዩ በአቅራቢያቸው ወደሚገኝ ጤና ጣቢያ መሄድና የምክር አገልግሎት ማግኘት አለባቸው፡፡
ጥያቄ፡- ሰዎች በዝንጀሮ ፈንጣጣ ምክንያት ሊሞቱ ይችላሉ?
መልስ፡- በአብዛኛው የዝንጀሮ ፈንጣጣ ምልክቶች በጥቂት ሳምንታት ውስጥ በራሳቸው ይጠፋሉ፡፡ ነገር ግን በአንዳንድ ግለሰቦች ላይ ውስብስብ የጤና ቀውስና ሞት ሊያስከትል ይችላል፡፡ ጨቅላ ሕፃናትና ሕፃናት እንዲሁም በሽታ የመከላከል አቅማቸው የቀነሱ ሰዎች ከፍተኛ የሕመም ስሜትና ሞት ሊያጋጥማቸው ይችላል፡፡ የዝንጀሮ ፈንጣጣ ውስብስብ የጤና ጉዳት ሲያስከትል የሚታዩት ምልክቶች የቆዳ ኢንፌክሽን፣ የሳንባ ምች፣ መደናገር፣ የዓይን ዕይታን ሊጋርድ በሚችል መልኩ የዓይን ኢንፌክሽን መከሰት ናቸው፡፡ በበሽታው ከተያዙ ሰዎች መካከል በሽታው ወረርሽኝ ከሆነባቸው አካባቢዎች ከሦስት በመቶ እስከ ስድስት በመቶ ያህል ሰዎች ይሞታሉ፡፡ ይህ በአብዛኛው የሚከሰተው በልጆችና ሌላ የጤና እክል ባለባቸው አዋቂዎች ላይ ነው፡፡
ጥያቄ፡- የዝንጀሮ ፈንጣጣ ከእንስሳት ወደ ሰው እንዴት ሊተላለፍ ይችላል?
መልስ፡- የዝንጀሮ ፈንጣጣ ከእንስሳት ወደ ሰው ሊተላለፍ የሚችለው በቫይረሱ ከተጠቃ እንስሳት ጋር በሚኖር ንክኪ ነው፡፡ ቫይረሱን ከሚሸከሙ እንስሳት አይጦችና ዝንጀሮዎች ይገኙበታል፡፡ ከእንስሳት ወደ ሰው የሚተላለፍ የዝንጀሮ ፈንጣጣን ደኅንነቱ ያልተጠበቀ ንክኪን በማስወገድ መግታት ይቻላል፡፡ በተለይ በሽታውን ሊያስተላልፉ ይችላሉ የሚባሉ የታመሙ ወይም የሞቱ እንስሳት ሥጋና ደም መንካት አያስፈልግም፡፡ በሽታው በወረርሽኝ መልክ በተከሰተባቸው አገሮች ማናቸውም የዝንጀሮ ፈንጣጣ ቫይረስ ሊሸከሙ ከሚችሉ እንስሳት ሥጋ ወይም ማንኛውም ክፍል የሚዘጋጅ ምግብ በደንብ መብሰል አለበት፡፡
ጥያቄ፡- የዝንጀሮ ፈንጣጣ ከሰዎች ወደ ሰዎች እንዴት ይተላለፋል?
መልስ፡- በዝንጀሮ ፈንጣጣ የተያዙ ሰዎች ምልክት እያሳዩ ባለበት ሰዓት ወደ ሌላ ሰው በንክኪ ሊያስተላልፉት ይችላሉ፡፡ በተለይ በቫይረሱ የተያዘ ሰው እስኪያገግም ያለው ከሁለት እስከ አራት ሳምንታት ጊዜ ቫይረሱ ይተላለፋል፡፡ ልብሶች፣ አብሮ መተኛትና ፎጣዎች ቫይረሱን ያስተላልፋሉ፡፡ የምግብ ሳህኖችና የምግብ መመገቢያ ቁሳቁሶች በቫይረሱ በተያዘ ሰው ተመርዘው ከሆኑ ቫይረሱን ያስተላልፋሉ፡፡ በምራቅ አማካይነትም ይተላለፋል፡፡ ከታማሚ ጋር የቅርብ ግንኙነት ያላቸው የጤና ባለሙያዎችና የቤተሰብ አባላት ይበልጥ ተጋላጭ ናቸው፡፡ ቫይረሱ በእርግዝና ወቅት እናትየዋን ካጠቃ፣ ወደ ፅንሱ ይተላለፋል፡፡ በወሊድ ወይም ከወሊድ ጊዜ በኋላ በሚኖር ንክኪም ይተላለፋል፡፡ ምልክት ያላሳዩ ሰዎች በሽታውን ያስተላልፉ ወይም አያስተላልፉ የታወቀ ነገር የለም፡፡
ጥያቄ፡- ለቫይረሱ ይበልጥ ተጋላጭ ማን ነው?
መልስ፡- በዝንጀሮ ቫይረስ ከተያዘ ሰው ጋር ንክኪ ያለው ሁሉ ተጋላጭ ነው፡፡ የፈንጣጣ ክትባት የተከተቡ ሰዎች ግን በዝንጀሮ ፈንጣጣ የመጠቃት ዕድላቸው ካልተከተቡት የተሻለ ነው፡፡ ነገር ግን ፈንጣጣ ከዓለም እ.ኤ.አ. በ1980 በመጥፋቱ በዓለም አቀፍ ደረጃ ይሰጥ የነበረው ክትባት ቆሟል፡፡
ጥያቄ፡- ሰዎች ራሳቸውን ከዝንጀሮ ፈንጣጣ እንዴት ሊከላከሉ ይችላሉ?
መልስ፡- ሰዎች በዝንጀሮ ፈንጣጣ ከተጠረጠረ ወይም ከታመመ ሰው ጋር ያላቸውን ግንኙነት በማቋረጥ ራሳቸውን ከቫይረሱ ሊከላከሉ ይችላሉ፡፡ የጤና ባለሙያ ከሆነ ወይም ከታማሚው ጋር አብሮ የሚኖር ሰው ካለ፣ ታማሚው ራሱን ለይቶ እንዲያቆይና ሰውነቱን እንዲሸፍን ማበረታታት ያስፈልጋል፡፡ በተለይ የሚያስሉና የሚያስነጥሱ ከሆነ አፍና አፍንጫቸውን በሕክምና ማስክ መሸፈን አለባቸው፡፡ ከታማሚው ጋር ግንኙነት ያለው ሰውም ማስክ ማድረግ አለበት፡፡ ንክኪን ማስወገድ፣ ተጠቅሞ የሚጣል ጓንት ማድረግም ይገባል፡፡ በቫይረሱ ከተጠቃ ሰው ጋር ግንኙነት ካለ እጅን በሳሙናና ውኃ መታጠብ ወይም አልኮል ባለው የእጅ ማፅጃ መጠቀም ያስፈልጋል፡፡ የሕሙማኑን ልብስ፣ አንሶላ፣ ፎጣና ሌሎች ልብሶች በሞቀ ውኃና በሳሙና ማጠብ፣ የተመገበባቸውን ዕቃዎች በፀረ ባክቴሪያ ማፅዳት፣ የተነካኩ ቦታዎችን ማፅዳትም ከቫይረሱ ራስን ለመከላከል ያግዛል፡፡
ጥያቄ፡- ለዝንጀሮ ፈንጣጣ ክትባት አለ?
መልስ፡- ለፈንጣጣ የተለያዩ ክትባቶች አሉ፡፡ እነዚህ የዝንጀሮ ፈንጣጣን በተወሰነ መልኩ ለመከላከል ያስችላሉ፡፡ ለፈንጣጣ ተብሎ የተመረተውና ለዝንጀሮ ፈንጣጣም ያገለግላል ተብሎ እ.ኤ.አ. በ2019 ተቀባይነት ያገኘ ክትባት ቢኖርም፣ በዓለም አቀፍ ደረጃ በስፋት አልተሠራጨም፡፡ በመሆኑም የዓለም ጤና ድርጅት ተደራሽነቱን ለማስፋት እየሠራ ነው፡፡
ጥያቄ፡- ለዝንጀሮ ፈንጣጣ ሕክምና አለ?
መልስ፡- የዝንጀሮ ፈንጣጣ በአብዛኛው በራሱ ጊዜ የሚጠፋ/የሚድን ነው፡፡ ነገር ግን ሽፍታው እንዲድን ማድረግ ይገባል፡፡ የአፍ መጉመጥመጫና የዓይን ጠብታ በሐኪም ትዕዛዝ መጠቀም ይቻላል፡፡ ፈንጣጣን ለማከም የተሠራው ኢንቲቫይራል መድኃኒት ለዝንጀሮ ፈንጣጣም ጥቅም ላይ እንዲውል በጥር 2022 ላይ ተፈቅዷል፡፡
ጥያቄ፡- የዝንጀሮ ፈንጣጣ በግብረ ሥጋ ግንኙነት ይተላለፋል?
መልስ፡- የግብረ ሥጋ ግንኙነትን ጨምሮ በንክኪ ቫይረሱ ይተላለፋል፡፡
ጥያቄ፡- የዝንጀሮ ፈንጣጣ ደም በመለገስ/በመውሰድ ጊዜ ይተላለፋል?
መልስ፡- የዝንጀሮ ፈንጣጣ ቫይረስ በደም ውስጥ የሚቆይበት ጊዜ አጭር ነው፡፡ የበሽታው ምልክት በጀመረባቸው ጊዜያት ከሆነ በደም ውስጥ ይኖራል፡፡ ሕመም በተሰማ ጊዜ ማንም ቢሆን ደም መለገስ የለበትም፡፡ ደም የመስጠት ዕቅድ ቢኖርም፣ የራስን ጤና መፈተሽና የዝንጀሮ ፈንጣጣ ምልክት አለመኖሩን ማረጋገጥ ያስፈልጋል፡፡ ሰዎች ደም ሲለግሱ ማሟላት ያለባቸው ፕሮቶኮሎች ሁሌም መከበር አለባቸው፡፡ ይህ ተግባራዊ የሚደረገው ሰዎች በለገሱት ደም ምክንያት ሌሎችን እንዳይበክሉ ነው፡፡